ለ4 ዓመታት ሲቆራረጥ የነበረው ደሞዛችን ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ እየተንገላታን ነው ሲሉ መምህራን ገለጹ

0
473

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን ዛባጋዞ በተባለው ወረዳ የመንግስት ሠራተኞች በተለይ መምህራን ደመወዝ እየተሰጠን አይደለም፤ በደል እየደረሰብን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ተናግረዋል። 

ከ2012 ጀምሮ የደመወዝ መቆራረጥ እንደነበረ የገለጹት መምህራኑ በአሁን ሰዓት ግን “ከነጭራሹም ምንም አይነት ደመወዝ እየተከፈለን አይደለም” በማለት አስረድተዋል። 

በተለያዩ ጊዜያት ለልማት እና መሰል ምክንያቶችን በመፍጠር ደመወዝ በተደጋጋሚ እንደሚቆረጥባቸው ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት መምህራን “እሱም አልበቃ ብሎ በየመሀሉ እየተዉት ከዛ ደግሞ እየሰጡን ሲያንገላቱን ቆይተዋል” በማለት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻው መምህራን ያሉበትን የችግር ሁኔታ ገልጸዋል። 

እንደመምህራኖቹ ገለጻ በወረዳው ላለፉት 2 ወራት “አግባብ በሌለው” መልኩ ‘ዳውሮ ዞንን እናልማ’ በሚል ደመወዛቸው ሲቆረጥ ከቆየ በኋላ ሙሉ ለሙሉ መሰጠት አቁሟል። በዚሁ አካባቢ ሌሎችም የመንግስት ሠራተኞችም ተመሳሳይ ችግር እንዳጋጠመቸው አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ተረድታለች። 

መምህራኑ አንድ ላይ በመሰብሰብ እና ፊርማ በማሰባሰብ ለወረዳ እንዲሁም ለክልሉ አስተዳደር ቅሬታ እንዳቀረቡ የገለጹልን ሲሆን ነገር ግን ይህን መረጃ እስከሚሰጡን ጊዜ ድረስ ምንም አይነት ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ጠቁመዋል። 

በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በተመሳሳይ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ጉዳዩን ተመልክቶ የክልሉ አስተዳደር የመምህራኑ ደመወዝ የተቆረጠበትን ሕጋዊ ምክንያት እንዲያስረዱ እና እንዲያሳውቋቸው የጠየቁበትን ደብዳቤ ያስገቡ ቢሆንም የክልሉ አስተዳደር ምላሽ አለመስጠቱን ጠቁመዋል። 

ከ290 በላይ መምህራን ደመወዛቸው ያልተከፈላቸው ሲሆን በአሁኑ ሰአትም አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ግን ስራ የማቆም አድማ አልያም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሊገደዱ እንደሚችሉ አዲስ ማለዳ መረዳት ችላለች።

አዲስ ማለዳ በዳውሮ ዞን በኃላፊነት ያሉ አንድ ግለሰብ ጋር ባደረገችው ማጣራት ጉዳዩን አስተባብለዋል። ሌሎች ሁለት ኃላፊዎች ደግሞ ከአዲስ ማለዳ ሚዲያ እንደሆነ ከተገለጻለቸው በኋላ በድጋሚ ስልክ ሳይመልሱ ቀርተዋል። 

በተመሳሳይ በደቡብ ኢትዮጵያን በዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የደመወዝ መዘግየት እና ያለመከፈል የተመለከቱ  አቤቱታዎችን በማጣራት ሰራተኞቹ ችግር ላይ መሆናቸውን እና በዚሁ ምክንያት ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ መሆኑን የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

በዎላይታ ዞን ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከ2012 ጀምሮ የሚስተዋሉ መሆኑን፣ ከችግሮቹ መካከልም በየወሩ መጨረሻ ሊከፈል የሚገባው ደመወዝ ከ10 እስከ 20 ቀን እንደሚዘገይ ንቅናቄው ገልጿል። 

እንዲሁም ከመስከረመ ወር 2016 ጀምሮ እስከ የካቲት 2016 በየወሩ መጨረሻ መከፈል የሚገባው ደመወዝ   አንድ ሶስተኛ በመቆራረጥ በሶስት ዙር  ሲሰጥ መቆየቱን በዚህም ደምወዝ አለመከፈል ምክንያት ትምህርት ቤቶች እየተዘጉ ነው ማለቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው መምህራን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው እና ከክልሉም አልፎ በፌደራል ደረጃ ችግራቸው እልባት እንዲያገኘ እንዲደረግላቸው አሳስበዋል።

አዲስ ማለዳ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም ከዳውሮ ዞን አስተዳደሮች ስለጉዳዩ ለመጠየቅ ያደረገችው ጥረት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here