ፖሊሶች ለኮሪደር ልማት ስራ የተነሱ ብረቶችን ሊሸጡ ሲሉ በመከልከሌ ተደበደብኩ- ተበዳይ

0
342
Ethiopian police officers stand while holding Ethiopian national flags in Addis Ababa, Ethiopia, on September 6, 2021, during a ceremony held to support the Ethiopian military that is battling against the Tigray People's Liberation Front (TPLF) in the Amhara and Afar regions. (Photo by Amanuel Sileshi / AFP) (Photo by AMANUEL SILESHI/AFP via Getty Images)

ለግለሰቡ ደህንነት ሲባል ስሙ ያልተጠቀሰው ተበዳይ “የመንግስትን ንብረት እንዲጠብቁ የተመደቡ ፖሊሶች እየፈፀሙ ያሉትን የዘረፋ ተግባር አይቼ በማስቆሜ ከፍተኛ የሆነ ድብደባና እንግልት ደርሶብኛል” ሲል ቅሬታው ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ወጣቱ በሚሰራበት የኮንስትራክሽን ስራ ዘርፍ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ላይ እየሰራ ይገኛል። ባለፈው ወር መጋቢት መጨረሻ ላይ ከአድዋ ፕሮጀክት በእሪ በከንቱ በኩል አድርጎ ወደ አራት ኪሎ በሚወስደው መንገድ ላይ በስራ ላይ በነበሩበት ወቅት፤ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ የኤለክትሪክ ኃይል የሆነ የብረት ምሰሶ ከቦታው እንዲነሳ ተደርጎ ስለነበር የኤሌክትሪክ ኃይል መጥቶ እንዲወስደው አሳውቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ብረቱን እስከሚያነሳው ከሌሎች ስራዎች ጎን ለጎን  የብረት ምሰሶውን በመጠበቅ ላይ እንደነበሩ የገለጸው ቅሬታ አቅራቢ፤ በወቅቱ ሁለት ፖሊሶች ወደ ስፍራው ብረታ ብረቶችን ከሚገዛ ሰው ጋር በመምጣት ዋጋ ተደራድረው መኪና ላይ ለመጫን ማስተካከል ሲጀምሩ መመልከቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ይህ ሲሆን ብረቱን ለመግዛት የመጣው ሰውን በማባረር እንዲሄድ ካደረገ በኋላ እንዳይሸጡ መከላከሉን ለአዲስ ማለዳ የተናገረው የኮንስትራክሽን ባለሞያው ፖሊሶቹ በአካባቢው የነበረ ሌላ አንድ ፖሊስ በመጥራት ለሶስት ድብደባ እንዳደረሱበት፤ እንዲሁም በድንጋይ እንደፈነከቱት ተናግሯል። ባደረሱበት ጉዳት አሁንም ድረስ ህክምና እየተከታተለ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ ሶስቱ ፖሊሶች ላይ ባደረሱበት የድብደባ ወንጀል ክስ መመስረቱን እንዲሁም የህክምና ማስረጃ ለፖሊስ ጣቢያ በማቅረቡ መታሰራቸውን የገለጸው ግለሰብ ነገር ግን ፖሊሶቹ ለሰባት ቀናት ብቻ ታስረው በዋስ መለቀቃቸውን እንዲሁም የብረት ምሰሶውን ለመሸጥ ባደረጉት ሙከራ ላይ ምንም ዓይነት የተጠያቂነት እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው ቅሬታ አቅራቢው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።

ይኼው ክስተተ ከተፈጠረ አንድ ወር የሞላው ሲሆን በአሁን ሰዓት የክሱ ሂደት ያለበትን ሁኔታ ለመርማሪው ሲጠይቅ “ከዚ በኋላ ጉዳዩን የሚመለከተው ፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤት ሲቀርቡ እንደውልልሃለን” የሚል ምላሽ ማግኘቱን በመግለጽ “የሕግ አካላት ሕግ ተላልፈው እያለ ጉዳዩ ችላ ተብሏል” ሲል ለአዲስ ማለዳ ቅሬታውን አሰምቷል።

ፖሊሶቹ የፈጸሙበት ድርጊት “በዚህ ብቻ አላበቃም” የሚለው ግለሰቡ በድብደባው ላይ ተሳትፈው የነበሩት የፖሊስ አባላት “ተጎድተናል እና ካሳ ልትከፍለን ይገባል” በሚል በተደጋጋሚ ወደ ስልኩ የሚደውሉ በመሆኑ አሁን ለደህንነቱ ስጋት እንደሚሰማው ነግሮናል። 

“ሌባ ቢሰርቅ ለፖሊስ አቤት እንላለን፤ ፖሊስ ግን ሌባ ከሆነ የሕዝቡ የከተማዋ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል?” የሚለው ቅሬታ አቅራቢው “አለቃቸው በግልፅ የነገረኝ ደመወቸው ትንሽ ስለሆነ ነው እንዲህ የሚያደርጉት” የሚል ምላሽ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ነገር ግን ድርጊቱን ያጋላጠው ግለሰብ ደመወዝ ማነስ ሕገ ወጥ ለመሆን ምክንያት ይሆናልን” ሲል ጥያቄውን ያቀርባል።

አዲስ ማለዳ በዚሁ ጉዳይ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ምላሽ ለማካተት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል። በአንጻሩ ክሱን የያዘው የራስ ደስታ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የምርመራ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኢኒስፔክተር እሸቱ ይመር አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በመግለጽ ያነጋገረች ሲሆን ክሱን ስለማወቃቸውም ሆነ ስላለበት ሁኔታ “የፖሊስ ጣቢያው አሰራር የማይፈቅድ በመሆኑ” በማለት ምላሽ ሳይሰጡን ቀርተዋል። 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here