የአማራ ክልል የዚህ ዓመት የአስር ወራት የቱሪዝም ገቢ ካለፈው ዓመት ዘጠኝ ወራት ያነሰ ሆኗል

0
195

👉🏿 በ2016 አስር ወራት 5 ሚልየን 908 ሺህ 591 ጎብኚዎች

👉🏿  በ2015 ዘጠኝ ወራት ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጎብኚዎች   

ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ በ2016 ዓመት አስር ወራት ውስጥ ከ2 ነጥብ 6 ቢልየን ብር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን በ2015 ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከተገኘው ያነሰ ነው።

ባለፉት አስር ወራት 2 ቢሊዮን 66 ሚሊዮን 515 ሺህ 933 ብር ገቢ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ያገኘ ሲሆን በ2015 ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ተገኝቶ ነበር።

“ባለፉት ወራት በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የቱሪዝም ምጣኔ ሃብቱን ማዳከሙን” የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነትን በቅርቡ የተቀበሉት መልካሙ ጸጋዬ መግለጻቸውን አዲስ ማለዳ ከክልሉ ኮምኒኬሽን ቢሮ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። በተለይም ኑሯቸውን በዘርፉ ላይ መሠረት ያደረጉ ሠራተኞች፣ አስጎብኚ ማኅበራት እና በዘርፉ የተደራጁ ማኅበራት ችግር ላይ መውደቃቸው ታውቋል።

አዲስ ማለዳ የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍ የአስር ወራት ክንውን ካለፈው ዓመት ተቀራራቢ ጊዜ ጋር ስታነጻጸር ዝቅተኛ ሆኖ አግኝታዋለች።

በበጀት ዓመቱ የክልሉን መዳረሻዎች ይጎበኛሉ ተብሎ ከታቀደው 7 ሚሊዮን 118 ሺህ 784 የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ውስጥ በ10 ወሩ 83 በመቶ መሳካቱን ክልሉ ያስታወቀ ሲሆን ይህም 5 ሚልየን 908 ሺህ 591 ጎብኚዎች ማለት ነው። በ2015 ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ ገብተው እንደነበር አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

በዚህ ዓመት 292 የሆቴል እና የቱሪዝም አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታቸውን አጠናቅቀው አገልግሎት እንዲጀምሩ፤ እንዲሁም ለ190 የቱሪስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ መሰጠቱ ተገልጿል። በተጨማሪም ለ23 ሺህ 369 ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here