የቀድሞው የቦሌ ታወርስ ስራ አስኪያጅ አብነት ገብረመስቀል ላይ የቀረበው ክስ ባቀረቡት ጥያቄ ተቋረጠ

0
757

ማክሰኞ ግንቦት 20 ቀን 2016 (አዲስ ማአዳ) የፍትህ ሚኒስቴር ባለኃብቱ እና ቦሌ ታወርስ የግል ድርጅትን በስራ አስኪያጅነት የመሩት አብነት ገብረመስቀል የተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ክስ ግንቦት 15 እንዲቋረጥ ውሳኔ ተላልፏል።

የፌደራል ዐቃቤ ሕግ አብነት ገብረመስቀልን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ላይ ባቀረበው የሙስና እና ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀሎች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ተሰምቶ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ነበር።

በዚህም መሰረት መዝገቡ የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለመስማት በቀጠሮ ላይ ባለበት ወቅት አብነት ገበረመስቀል ባደረባቸው ከባድ ህመም ምክንያት ክርክሩን ለመቀጠል አስጊ ሁኔታ ላይ በመሆናቸ ክሱ እንዲቋረጥላቸው መጠየቃቸውን ተከትሎ ግንቦት 15 ቀን 2016 ፍትህ ሚኒስቴር ጥያቄያቸውን መቀበሉ ተገልጿል።

በዚህም የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ያቀረበውን ክስ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 መሰረት እንዲቋረጥ መወሰኑን አዲስ ማለዳ ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ባለኃብቱ ስፋታቸው 3 ሺሕ 383 እና 1 ሺሕ 971 ካሬ ሜትር የሆኑ እና ስያሜያቸው ‘ሲ’ እና ‘ዲ’ የተባሉ የካርታ ይዞታዎች ለቦሌ ታወርስ ማስፋፊያነት የተሰጡ ሆነው ሳለ፤ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አብነት ገብረመስቀል የቦሌ ታወርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥምን ከካርታዎቹ ላይ እንዲወጣ በማስደረግና “የግል ንብረቴ ነው” በማለታቸው፤ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሃ ብሔር ችሎት ክስ ተመስርቶ ክርክር ላይ መቆየቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

በዚህም በሕገ ወጥ መንገድ ካርታ ያወጡባቸው ኹለት ይዞታዎች ለቦሌ ታወርስ ኃ/የተ/የግ/ማ እንዲመለሱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥቅምት 5 ቀን 2016 ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here