ሐሙስ ነሐሴ 02 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ቀደም ሲል የውጭ አገር ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ቢሮ ከፍተው እየሰሩ ነው በሚል በመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በመስጠት እንዲሰራጭ ያደረገው መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
አዲስ ማለዳ ከፖሊስ ኮሚሽኑ ባገኘችው የቃል እና የሰነድ ማስረጃ ቀደም ሲል አባይ አሰሪዎች ማህበር ባለቤትነታቸው እና የሚተዳደሩት በውጪ ሃገር ዜጎች ነው ያላቸው ፒ.አር.ኤስ (PRS)፣ ሲ.ኦ.ኤስ.ጂ (COSG) በቀድሞው አዋጅ ቁጥር 632/2001 እና ይህንኑ አዋጅ ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ ወይም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 እና ይህን መመሪያ ያልተላለፉና የሚተዳደሩትም ሆነ ባለቤትነታቸው በኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እና በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚገኙ መሆናቸውን ተመልክታለች፡፡
‹
ከዚህ ባለፈም በአባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ስም ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ በማውጣት መረጃ የሰጠው አካል ከአባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንቱ ፀሃፊውና ሌሎች በማህበሩ ስር የሚመለከታቸው አካላት እውቅና ውጪ የተሰጠ መሆኑን ፖሊስ ኮሚሽኑ ባደረኩት ማጣራት ደርሼበታለሁ ብሏል፡፡
አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር ቀደም ሲል የውጭ አገር ዜጎች የሚያስተዳድሯቸው ድርጅቶች ሕግና ደንብ የማይፈቅደውን ስራ በመስራት በማህበሩ አባላት ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሱ ነው ካላቸው ውስጥ አንዱ የሆነው ሲ.ኦ.ኤስ. ጂ (COSG) ድርጅትን የሚመሩት ኮማንደር አስራት አረጋ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ድርጅታቸው በእርሳቸው እንደሚመራና በውጪ ሃገር ዜጋ የማይመራ፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ሆነ ከሌሎች ከሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ህጋዊ እውቅና እና ፈቃድ ያለው ድርጅት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ኮማንደር አስራት አረጋ አክለውም በድርጅታችን ላይ ለደረሰው የስም ማጥፋት ተግባር ክስ ለመመስረት መረጃዎችን በማደራጀት ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡
ሌላኛው አባይ የጥበቃ አሰሪዎች ማህበር የውጭ አገር ዜጎች ከሚያስተዳድሯቸው ድርጅቶች ካላቸው ውስጥ ፊዚካል ሪስክ ሶሉሽን ኃላ/የተ/የግ/ማህበር (PRS) በንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 መሰረት ፈቃድ የተሰጠው እና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም ጭምር ህጋዊ እውቅና ያገኘ ድርጅት መሆኑን እና ባለቤቱም ኢትዮጵያዊ ስለመሆናቸው አዲስ ማለዳ ከፖሊስ ኮሚሽኑ ያገኘችው የሰነድ ማስረጃ ያመላክታል፡፡


