
ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ ከሚገኙ የጋሪ መኖሪያ ቤት ባለቤቶች በተለየ መልኩ በካሬ የምንከፍለው የግብር መጠን ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎብናል ሲሉ የኮዬ ፈጬና ቱሉዲምቱ የጋራ መኖሪያ ቤት ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አሰምተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ለጣራና ግድግዳ ተብሎ የወጣው የግብር ተመን በካሬ 80 ብር ሆኖ እያለ እኛ በካሬ 133 ብር እንድንከፍል እየተገደድን ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚመለከተውን አካል ለምን ብለን ብንጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ብለዋል፡፡
ይህ በግብር ስም የሚፈጸም የተጋነነ ክፍያ አልበቃ ብሎ ለሚሊሻ፣ ቡሳ ጎንፋኖ ተብሎ ለሚጠራው አደረጃጀትና ለመሰል ጉዳዮች እስከ 3200 ብር እንድንከፍል እየተገደድን ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
ማህበራዊ ሃላፊነትን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ እንደ ዜጋ ግዴታችን መሆኑን ብናውቅም ከእቅም በላይ የሆነ ክፍያ እንድንፈጽም መገደዳችን ግን አግባብ አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡
አሁን ላይ ይህን ክፍያ መክፈል ያልቻሉ ነዋሪዎችና የቤት ባለቤቶች ለጭንቀት ተዳርገዋል ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች የሚመለከተው አካል ይህን ቅሬታችንን ሊሰማንና መልስ ሊሰጠን ይገባል ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ምላሽ እንዲሰጧት የሸገር ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የከተማ አስተዳደር ስራ ሃላፊዎችን በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም፡፡
በቀጣይም ከከተማ አስተዳደሩ የሚሰጥ ምላሽ ሲኖር አዲስ ማለዳ ይዛ የምትቀርብ ይሆናል፡፡



