አእምሮ፣ የሐሰት ትርክትና ማኅበራዊ ተግዳሮቱ – ከኢትዮጵያ አንጻር!

0
672

አካባቢያዊ እንቅስቃሴዎች የግለሰብ አእምሮ ይወስኑታል፤ ይህ የሆነው ሁላችንም ከተፈጥሯችን በተጨማሪ የአካባቢያችን ውጤቶች ስለሆንን ነው። ይህም አእምሮ የተዘራበትን እንደሚያበቅል ያሳያል የሚሉት መላኩ አዳል፤ ውስብስቡን የአንጎል፣ የአእምሮና የሕዋሳትን አሠራር ከውጫዊና አካባቢያዊ ተጽእኖ አንጻር ቃኝተውታል። እናም የሐሰት ትርክት እየነገሩ ይህን ተፈጥሮ ላልሆነ ተግባር የሚያውሉ በሕግ የሚጠየቁበት ማዕቀፍ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ። ሐይማኖትም ሥነ ምግባር ከማነጽ ጀምሮ የተለያዩ በጎ ጎኖች ያሉት ቢሆንም፤ ሰው ጠያቂና ምክንያታዊ እንዲሆን ለማስቻል ሊያካትቷቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ሲሉ ያጨምራሉ።

እያንዳንዱ ግለሰብ ለሕይወቱ ትርጉም የመስጠት እንዲሁም ይህን ሕይወቱን በሃቀኝነትና በሙሉ ስሜት የመምራት ኃላፊነት አለበት። ይህም የህልውነት ፍልስፍና ይመስለኛል በአመዛኙ በቀን ተቀን ኑሯችን እየተመራንበት ያለው። ነገር ግን ግለሰብ ማኅበረሰብን መፍጠሩ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰብም ግለሰብን ይሠራል። አእምሯችን ሳይቀር ማኅበራዊ አእምሮ (social mind) ነው። ከህልውነት ፍልስፍና አንጻር ግለሰባዊነት የሚደገፍበት ምክንያት የማኅበረሰቡን ጉድፎች ለማሳየት፣ ጠንካራ ጎኑን ለማጠንከርና አስፈላጊ የባህል ለውጦችን እውን በማድረግ የማኅበረሰብን እድገት ለማምጣት ነው። በዚህ ሂደት የሥነ ምግባርና ሞራል ብያኔዎች ችግር እንዳይፈጥሩ መሥራት፣ ካልሆነም ጥሶ የመውጣት አስገዳጅ ሁኔታዎች ይፈጠሩ ይሆናል።

ከዚህ አንጻር፣ በአንድ ግለሰብ እራሱን ችሎ መቆም አስፈላጊነት ባምንም፣ እጅግ መስዋትነትን የሚፈልግ ትልቅም ተግባር መሆኑ እሙን ነው። ምክንያቱም ግለሰብ ስትሆን የምትጋፋቸው የማኅበረሰብ ህፀጾች አሉና። እናም በማኅበረሰብና በግለሰብ መካከል ያለው የሞራል ሚዛን፣ የማኅበረሰቡ እውቀት የሚወሰን ስለሆነ፣ ለግለሰብ አሳቢነት፣ ፈጣሪነት እንቅፋት ሲሆን ይታያልና የሚዛኑ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል።

እዚህ ላይ የህልውነት ፍልስፍና በግለሰብነት መቆም ላይ ሊያስከትለው በሚችለው ተጽእኖ ብስማማም፣ የመምረጥ ነጻነቱን ሙሉ የነጻ-ፈቃድ አድርጎ ማየቱ ላይ አልስማማም። ምርጫ መኖር ብቻ የነጻ-ፈቃድ ማሳያ ሊሆን አይችልምና። በእርግጥ በመጀመሪያ ስለ ነጻ-ፈቃድ ትርጉም መስማማት ይኖርብናል። ለብዙ ሰው ነፃ-ፈቃድ ማለት አንድ ሰው የተለያዩ አማራጮች በሚያጋጥሙት ጊዜ ከአማራጮቹ መካከል ማንኛውንም አማራጭ የመምረጥ ነፃነት አለው ማለት ነው። ይህም ማለት ከአማራጮቹ መካከል አንዱን ወይም የተወሰኑትን እንዲመርጥ ተጽዕኖ የለበትም ማለት ነው።

ነገር ግን የምንመርጥበት አእምሮ ሳይቀር የኛ ብቻ ያልሆነ፣ የአንጎልና የአካባቢ ውጤት ነው። የእያንዳንዱ ሰው የአንጎል ሁኔታ ደግሞ ግለሰቡ በተፀነሰበት አንዲት ቅጽበት በጀነቲክስና በአስተዳደጉ ሂደት በአካባቢው ተወስኗል። ይህም ማለት፣ ያለን ማኅበራዊ አእምሮ ነው ማለት ነው። ስለዚህም የህልውነት ፍልስፍናን ዋናውን መነሻ፣ የነጻ-ፈቃድ መኖርን ስህተት ያደርገዋል። ምክንያቱም ሰው የተለያዩ አማራጮች በሚያጋጥሙት ጊዜ በምርጫው ውሳኔ ላይ የግለሰቡ ፍላጎት ከፍተኛ ድርሻ ስላለው።

ግለሰቡ ለጉዳዩ በቀረቡት አማራጮች ላይ እኩል ፍላጎት የማይኖረው ከሆነ በጉዳዩ ላይ የመምረጥ ነጻነት የለውም ማለት ነው። ምክንያቱም ግለሰቡ ለጉዳዩ ከቀረቡት አማራጮች መካከል የበለጠ የሚፈልገውን አማራጭ እንዲመርጥ ስለሚገደድ ነው። ይህም ሰው በፍላጎቱም ላይ ቢሆን ነፃነት የሌለው መሆኑን ያሳየናል።

ሰው ከሌሎች እንስሳት የተለየው ለአዋቂዎች በአማካኝ 1300 ግራም የሚመዝን አዕምሮ ባለቤት መሆን በመቻሉ ነው። የአስተሳሰባችን ሁኔታ በነርቭ ህዋሳት ብዛት፣ በመካከላቸው ባለው አደረጃጀትና ግንኙነት፣ በጀነቲክስ እና በውጫዊው የዓለም ሁኔታ የሚወሰን ነው። የነርቭ ህዋሳት በመካከላቸው ያለው ከፍተኛ አደረጃጀትና ግንኙነት፣ ሰውን ትልቁ አሳቢ ፍጡር እንዲሆን አድርጎታል። ይህም አዕምሮአችን መነጋገር የሚችሉ የነርቭ ህወሳት መካከል ብቻ የሚደረግ የኔትወርክ (የሞጁሎች) ስብስብ ነው ማለት ነው።

እነዚህ ሞጁሎች የራሳቸውን ሥራ ያለ ማእከላዊ እዝ በራሳቸው መሥራት የሚችሉ፣ ቋሚ ያልሆኑ፣ እርስ በርስ፣ ከሌላ የሰውነት አካል፣ ከአካባቢ፣ ከሌላ አዕምሮ ጋር በሚያደርጉት መስተጋብር የሚለዋወጡ ናቸው። ይህም ከተለያዩ ሞጁሎች የተገኘውን የተሻለ ውሳኔ መምረጥና ትክክል የመወሰን እድሉ እንዲሰፋ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በአንድ አይነት ሃይል (ንቃተ-ህሊና) የምንመራ እንድንሆንም አስችሎናል።

በአምስቱ የስሜቶቻችን ህዋሳት ከውጭ የምናገኝው መረጃ ለእያንዳንዱ ሞጁል መፈጠር ወሳኝ ነው። አዕምሯችን ጀነቲክሳችን የፈቀደለትን ሁሉ መማር ይቻላል። ይህም ማለት ጀነቲክሳችን ያልፈቀደለትን ግን ምንም ሥልጠና ቢያገኝ መማር አይችልም ማለት ነው። እንደተባለው ለአዕምሮ እድገት አንዱ ግብዓት፣ ከአካባቢያችን የምናገኘው ትምህርትና ሥልጠና ነው። ብዙዎች የአዕምሮ ውሳኔዎች ባልነቃው የአዕምሮ ክፍል የሚከወኑ ናቸው። ምክንያቱም ንቁ የአዕምሮ ክፍል ውሳኔዎች ብዙ ጊዜና ሜሞሪ ስለሚፈልጉ ውድ ናቸውና።

ይህም በጠቅላላው የሚያመለክተን ሰው በተወሰነ ደረጃ ንቃተ-ህሊናውን የሚጠቀም ቢሆንም፣ ባብዛኛው ጊዜ ግን የውስኔዎቹ መነሻ የአልነቃው የአዕምሮ ክፍል መሆኑን ነው። በተጨማሪም፣ ጀነቲክስና አካባቢ አዕምሮን በተፅእኖ እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ አዕምሮም በጀነቲክስና በአካባቢ ላይ ተፅዕኖው የጎላ ነው። አንዲሁም ሁላችንም ዩኒቨርሱን በሚመራው የተፈጥሮ ፊዚካል ሕግ ውጭ አይደለንም። ይህም ሁሉንም የፊዚሎጂና ኢኮሎጂ መስተጋብሮችን እንደሚወስን ነው። ስለዚህም የነፃ-ፈቃድ መኖር እጅግ አጠራጣሪ ነው።

ሰው ለእድገቱ ብዙ ወጪ የሚያወጣ ቢሆንም እግረ መንገዱን የአዕምሮ እድገቱን እንዲያፋጥን፣ የባህል ትምህርትና ክህሎት እንዲያዳብር ረድቶታል። ይህ ከሌላው የመማር አቅም በሰው ልጅ እጅግ ያደገም ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የቋንቋ እና የማስመሰል (immitation) አቅምን የጨመሩ የአዕምሮ ክፍሎች ከሌሎች ቅርቦቹ እንሰሳት የበለጠ ማደጉ ነው። ይህም የሚያመለክተው፣ ለነዚህ ወሳኝ ሁነቶች መኖር ከመማር አቅም መጎልበት በተጨማሪ ለዋናው የሞጁሉ መኖር የጀነቲክስ መኖር ወሳኝ መሆኑንም ነው።

አስመስሎ የማድረግ አቅም በመስተዋት የነርቭ ሕዋሳት (mirror neurons) የሚከወን ነው። ይህ የአዕምሮ ሥራ እውቀትን በምሳሌ እንድናስተላልፍ ጠቅሞናል። ይህም ዘገምተኛ ከሆነው የዳርዊን ዝግመተ ለውጥ በተነፃፃሪ ፈጣን ወደ ሆነው የባህል ለውጥ እንድንገባ አግዟል። ይህም ከዘገምተኛ ለውጥ ወደ አብዮታዊ ለውጥ እንድንገባ አግዞናል። ይህ ለውጥ ጥንት በእሳት፣ መሣሪያዎች፣ አልባሳት፣ ቤት ግንባታ፣ ሥነ-ጥበብ፣ በዋነኝነትም በቋንቋ መፈጠር፣ ቀጥሎም በተለያዩ አብዮቶች፣ አሁን ደግሞ በኢንፎርሜሽን አብዮቱ ታግዞ እየፈጠነ ነው።

እኛ አሁን በአመለካከት ውጥንቅጥ ውስጥ ገብተናል። ለዚህም ምክንያቱ የሞራል እና የጥልቅ እሳቤ መዳከም፣ የሃይማኖትና ብሔር አክራሪነት፣ የአናሳነት፣ የበታችነትና የበላይነት ሥነ ልቦና በመብዛቱና የእነዚህ ውጤቶች ችግር ስላለብን ነው። ሞራል ስንል ሁሉም ቦታ ያለ፣ ፍጹማዊ የሆነና የነገሮች መጥፎነት ወይም በጎነት ነው። የሞራል ሚዛን ሲዛባ የሞራል ችግርን ያስከትላል። ጥልቅ እሳቤ ዓላማው አእምሮን ኮትኩቶ ማልማት ነው። ነገር ግን በምክንያታዊነት ነገሮችን መቀበል ወይም መጣል ካልቻልን፣ እራሳችንን የማረም ችሎታና ማመዛዘንን ካላዳበርን፣ ችግር ውስጥ ያስገባል።

ጥልቅ እሳቤን ለማሻሻል፣ ትምህርት ስርአታችን የሥነ-ሰብ ትምህርቶችንና አገራዊ እውቀትን እንዲጨምር ማድረግ፣ የማንበብ ባህላችንን ከሕፃንነት ጀምሮ ማሳደግ፣ ቤተ መጽሐፍትን ማስፋፋት፣ ደራስያንን እና ተመራማሪዎችን እንዲጽፉ ማበረታታት፣ የህትመትና የመጸሐፍት ዋጋ እንዲቀንስ መሥራትም ያስፈልጋል። ስለዚህም ድርጊታችን የሞራል ሚዛንን ያለፈና ጥልቅ እሳቤንም ያገናዘበ እንዲሆን ያስፈልጋል።

አንዳንዶች ሥነ-ምግባርንና ሞራልን በሰውነታችን ያገኘነው እንጂ ከሃይማኖት ያገኘነው አይደለም ይላሉ። ሌሎች ደግሞ፣ የሰው ልጅ እውቀት ሞራልን ወለደ፤ ሞራልም ሃይማኖት ሆነችና ደካማው ሰው ጠንካራውን የሚያስርባት ገመድ ሆና አረፈችው ይሉናል። እኔ ግን ሃይማኖቶች ያበረከቷቸው የሞራል እሴቶችም አሉ እላለሁ። በሰው ልጅ የፍላጎት ጎልቶ መውጣት የሰውን የሥነ-ምግባርና ግብረ-ገብነት በእጅጉ እየጎዳው ነው። ሃይማኖት ለምንም ዓላማ ይፈጠር፣ ለሥነ-ምግባርና ሞራል፣ ለሥነ-ጥበብ፣ ለባህል፣ ለሥነ-ጽሑፍ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ አበርከቷል፣ እያበረከትም ነው።

በዚህ በኩል ሃይማኖት ሥነ-ምግባርና ሞራል በማስተማር የራሱ በጎ ጎን አለው ብዬ አምናለሁ። ሃይማኖት አመክንዮንና ነጻ ሐሳብን በመግታት የኅብረተሰብን እድገት የሚጎዳበት ሁኔታም ይኖራል። ‹ለማወቅ ከፈለግህ/ሽ ተቀበል› ይላል ሃይማኖት። ሳይንስ ደግሞ ‹ለማወቅ ከፈለግህ/ሽ መርምር› ይላል። ሳይንስ የሌለውን ሞራልን ሲፈልግ፣ ሃይማኖት ደግሞ የሌለውን ምክንያታዊነትን ይፈልጋል። ከዚህ ጋር ተገናኝቶ፣ በአገራችን ውስጥ ያለብን ችግር፣ ሃይማኖት ባህልና የኑሮ ፍልስፍና በመሆኑ ምክንያት፣ አመክንዮ ከማኅበረሰባችን መጥፋቱ ነው። በአመክንዮ የተመሰረተ አስተሳሰብና መጠይቅ እንደ አፈንጋጭ የሚያስቆጥር መሆኑም ጭምር ነው።

ብዙዎቹ የሃይማኖት ትምህርቶች የሰውን የማወቅ ውስንነት በማጋነን ስለሚሰብኩ የሰውን በራስ መተማመን በማጥፋትና የሚመጣው ዓለም ናፋቂ፣ ሙሉ በሙሉ ቁስ ናቂ በማድረግ፣ ለሐሳብ መሃንነትና ለኋላ ቀርነት የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል። አንዳንዶች ሃይማኖትን የሰላም መንገድ አድርገው ቢያዩትም፤ ሃይማኖቶች የጦርነት አነሳሾች እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል። ለምሳሌም የአረቢያ ኢምፓየርና የእስልምና መስፋፋት፣ የመስቀል ጦርነቶችንና የቫቲካን ኢትዮጵያ በጣልያን እንድትወጋ ባፓፓው ቡራኬ ለሙሲሎኒ ማድረግ ትንሾቹ ማሳያዎቹ ናቸው። ነገሥታት ሥልጣናቸውን ለማራዘም፣ ግብጽ በምትልካቸው ጳጳሶች በኩል ኢትዮጵያ እንዳታድግ ተጠቅመውበታል።

አሁንም ለአዲሶቹ ቀኝ ገዥዎችና ለአረብ የነዳጅ ዘይት ቱጃሮች ባሮች እንድንሆን እያደረገን ነው። ለዚህም ይሆናል አንዳንዶች፣ ሃይማኖት አብዛኛውን ሕዝብ አደንዝዞ ለአገዛዝ ለማመቻቸት ሆን ተብሎ ከጊዜ በኋላ የተፈጠረ መሣሪያ ነው የሚሉት። የተባሉት የሃይማኖት ችግሮች እንዳሉ ሆነው፣ ከመሰረቱ አሁኑኑ ይናድ ማለት ግን አግባብነት የለውም፣ ከባህላችንና ማንነታችን ጋር ተሰላስሏልና። እናም መደረግ ያለበት፣ ከሃይማኖቶች ቀኖና ጋር የማይጋጩ ሳይንሳዊ ሐሳቦችን ቀስ በቀስ ወደ ሃይማኖቶች በማስገባት ስህተትነት ያላቸውን ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በሂደት መቀነስ ነው። በተጨማሪም መንግሥትና ሃይማኖት መለያየት ያለበትና ልንከተለውም የሚገባ ነው። ነገር ግን አሁንም ቢሆን የመለየቱ ድንበር በመሪዎች እየተጣሰ ነውና ሊታሰብበት ይገባል።

በተጨማሪም የአናሳነት፣ የዝቅተኝነቱንና የበላይነትን ሥነ ልቦና ከተለያዩ የማኅበረሰባችን ክፍሎች እየተመለከትን ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው አንጎላችን ከአካባቢ ጋር ባለው መስተጋብር ምክንያት ማኅበራዊ አእምሮን ይፈጥራል። አእምሮ ማኅበራዊ የተባለው፣ በብዙ አካባቢያዊ ነገሮች ስለሚወሰን ነው፣ ሁላችንም ከተፈጥሯችን በተጨማሪ የአካባቢያችን ውጤቶችም ነንና። ይህም የሚያሳየን አእምሮ ጥሩ ስንዘራበት ጥሩ፣ መጥፎ ስንዘራበት መጥፎ የሚያፈራ መሆኑን ነው።

ለዚህም በኦሮሞ/አምሃራ/ትግሬ መካከል የሚደረጉ የጥላቻ ትርክቶች በወጣቱ ዘንድ ያመጡት ጽንፈኛ ብሔርተኛነት ተፅዕኖ መመልከት በቂ ነው። ጽንፈኛ ብሔርተኛነት በኅብረተሰብ ዘንድ ከተሰበከ፣ የኅብረተሰብ መገለጫ ሊሆንበት የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ እያየን ነው። ይህ የሚያሳየው፣ የሐሰት ትርክት በአንጎል አወቃቀር ላይ ተፅዕኖ እንደሚያስከትልና አንጎልም እንዴት እንደሚሠራም ጭምር ነው። ለዚህ ሁሉ የአገራችን ችግሮችም የ1960ዎቹ ግራ-ዘመም ወጣቶች በተለይም ሻዕብያ፣ ሕወሓትና ኦነግ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ።

ስለዚህም ጥሩ ከፈለግን፣ አንጎላችንን ጥሩ እንመግበው፣ ያልዘሩትን መሰብሰብ አይቻልምና። እናም ይህን ስህተት ትርክት የሚቀይር፣ ብሎም የሚተካ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚመጥን የባህል አብዮት የሚያስፈልገን ይመስለኛል።

የመታለልና ውሸትን ማመንም ከአምስቱ የስሜቶቻችን ህዋሳት መረጃ የመውሰድ ድክመት፣ አንጎል ያገኘውንና የነበረውን መረጃ የመተንተንና ድምዳሜ የሚደርስበት መዋቅራዊ ጉድለት ውጤት ነው። ፖለቲከኞች ለ50 ዓመታት እውነትን በመደበቅና ውሸትን እንደእውነት በማቅረብ በማኅበረሰባችን አስተሳሰብ ላይ እየፈጠሩት ያለውን ተጽእኖ እየተመለከትን ነው። ይህንን የሰውን ተፈጥሮ በማወቅ ሰዎችን በአጭርና ረጅም ጊዜ ለማኅበረሰብ በማይጠቅምና ለራሱ ጥቅም ለማዋል የሚጥር ቡድን ወይም ተቋም ከድርጊቱ ሊገታ ይገባል።

ይህም እንደ ማኅበረሰብ እውነትንና ውሸትን የምንለይበት፣ ያወቀው ላላወቀው የሚያስተምርበት መንገድ መፈለግ አለበት። እያወቁ የሚያታሉና የማኅበረሰብ አስተሳሰብን የሚያበላሹ ሰዎች፣ የሰውን ተፈጥሮ ላልሆነ ተግባር የመጠቀም ሂደት ነውና እንደ ወንጀል የሚቆጠርበት የሕግ ማእቀፍ ሊሠራለት ይገባልም።

አእምሯችን ማኅበራዊ አእምሮ መሆኑ ሰውን በጥሩ ጎኑ ማኅበራዊ እንስሳ፣ በመጥፎ ጎኑ ደግሞ በመንጋነት እንዲኖር አድርጎታል። ለዚህም ነው መንግሥት ያስፈለገው፤ ተቋማትን እንዲገነባ፣ መንጋው ደካሞችን እንዳይበላ የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ። ጠባብ ብሔርተኝነት ብሎም የመንጋነት ሥነ-ልቦና፣ ሁነቶችን አጋኖ መመልከትና የመጠቃት ስሜት፣ ለተግባር ችኩል መሆንና በስሜት መነዳት፣ ቁጡነት፣ የመንጋውን ሐሳብ በቀላሉ መቀበልና መስማማት፣ ከሌሎች ጋር አለመቻቻል፣ ስለጎጤ እንጂ ስለአገር ምን አገባኝ ባይነት፣ አምባገነናዊነትና ወግ አጥባቂነት በማሳየት ይገለጻል።

ሰዎች በቡድን ሲሆኑ የግል ማንነታቸውንና ራስን የመግዛት አቅም በመዘንጋት ከመንጋው አስተሳሰብ ጋር በመቀላቀል ለብቻቸው ሲሆኑ የማያደርጉትን ድርጊት ያደርጋሉ። ይህ የሚሆንበት ምክንያት በመንጋው ውስጥ ተጠያቂነትን የሚያመልጡበት መንገድ ስለሚፈጥርላቸው ነው። እነዚህ ወገኖቼ እጅግ ያሳዝናሉ፣ ምክንያቱም ይህን ጠባብነትና ችግር አምጪውን የሐሰት ትርክት፣ ስህተትነት አያውቁምና። ይህ ችግር የሚያመለክተው የማሰብና የማሰላሰል የአንጎል ክፍልን በአነሰና ስሜትን የበለጠ የመጠቀም ውጤት መሆኑን ነው።

ስለዚህም ከመንጋነት መውጣትና ሰውን ሰው ያሰኘውን አስቦ ለራስም፣ ለሌላውም የሚጠቅም ማድረግ ያስፈልጋል። ብቻችን መኖር የማንችልባትና መስተጋብር አስፈላጊ የሆነበት ህልውና (ዩኒቨርስ) አካል ነንና። ፖለቲከኞችም ከዚህ የሐሰት ትርክት መውጣትና ለማኅበራዊ አንድነት የሚጠቅሙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለባቸው።

የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት አስተሳሰቡን የለየውን አእምሮ እንዴት እንደሚሠራ፣ ሜሞሪ (ትዝታ) እንዴት እንደሚያስቀምጥና ለምን ስህተት እንደሚገጥመው መጠየቅ የጀምረው ቀድሞ ቢሆንም፤ የታወቀው ግን በጣም ጥቂቱ ነው። ለመሆኑ ሜሞሪ ከአእምሮና ከማኅበረሰብ አንጻር ምንድን ነው?

ሜሞሪ የአእምሮ መረጃን ላልተወሰነ ጊዜ የማስቀመጥና የማስታውስ አቅም፣ እሱንም ነጋችንን ለመወሰን መጠቀም መቻል ነው። ሜሞሪ የአጭር ጊዜ እና የረጅም ጊዜ ተብሎ ሊከፈል ይችላል። የአጭር ጊዜ ሜሞሪ ቅጽበታዊ፣ ትንሽ መንስኤ የከወነው፣ በሌሎች ነገሮች በቀላሉ የሚስተጓጎል እና በትንሽ ጊዜ የሚረሳ ነው። ረጅም ሜሞሪ በተቃራኒው፣ በብዙ ጊዜ ድግግሞሽ መንስኤ የመጣ፣ በሌሎች ጣልቃ ገብነት በቀላሉ የማይስተጓጎልና ረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው። ረጅም ሜሞሪ በአንጎል ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። የረጅም ጊዜ ሜሞሪ በተለያዩ ሞጁሎች ተደጋግሞ መያዙ በአደጋ ወይም ሌላ ምክንያት መረጃ እንዳይጠፋ ያግዛል። እናም ይህ የአጭርና ረጅም የሜሞሪ ስርአት ክፍፍል አእምሯችን ለማይረባው መረጃ ሁሉ እንዳይደክም፣ መረጃን መርጦ መጠቀም እንዲችል ያደርገዋል።

ሜሞሪ በነርቭ ሴሎች ሲናፕስ ግንኙነት እና ከነሱ በሚመነጩ ኬሚካሎች (neurotransmitters) እንዲሁም በተለያዩ ፕሮቲኖች በሚወሰን ግንኙነት የሚፈጠር ነው። የነርቭ ሴሎች ከእነሱ በሚመነጩ ኬሚካሎች አመካኝነት እርስ በርሳቸው ያወጋሉ፤ ይህም ሜሞሪን ይፈጥራል። ሜሞሪ የሚቀመጠው አንድ የአእምሮ ክፍል ብቻ ሳይሆን የተለያየ የአእምሮ ክፈሎች ነው። ይህም ማለት ሜሞሪ በአንድ ቦታ በሚገኝ ኔትወርክ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፣ ከተለያየ ቦታ ላይ በሚፈጠሩ የነርቭ ሴሎች የሚደረግ የህብረት ግንኙነት ውጤት ነው።

ለምሳሌ፣ መኪና መንዳት በተለያየ የአእምሮ ክፍሎች መኪና አነዳዱ፣ የት እንደሚኬድ መወሰን፣ የትራፊክ ሕግ ማስታወሱና በቂ ነዳጅ መኖሩ የሚወሰነው በተለያዩ ኔትዎርኮች ነው። እነዚህም ሜሞሪዎች በአንድ የአእምሮ ክፍል ስለሚቀመጡ፣ የአንዱ መታወስ ሁሉንም እንድናስታውስ ያደርገናል። ይህም ማለት ሜሞሪ ማለት የተያያዙ አካላት ኔትወርክ ነው ማለት ነው። ለዚህም ነው አንድን ነገር ስናስታውስ ተያያዥ ነገሮችን የምናስታውሰው።

የሜሞሪው መፈጠርና የማስታወስ አቅም በነርቭ ሕዋሳት ‹ሲናፕስ› ግንኙነት ጥንካሬ እና ከነሱ በሚመነጩ ኬሚካሎች መጠን ይወሰናል። አንጎል እንደ አካባቢያዊ ሁኔታውና መንስኤ እራሱን የሚያስተካክልም ነው። መርሳት የሚመጣው ከአእምሮ ችግር ካለ፣ በስህተት መንገድ መልእክቱ በመቀመጡ፣ መንስኤው በቂ ካልሆነ፣ መንስኤውን ለመቀበል የሚያስፈልጉት ነገሮች ካልሠሩ፣ ሞጁሉ በመቀየሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

በጠቅላላው የነርቭ ሕዋሳት በከፍተኛ ጫና የሙድ መቀየር፣ በሆርሞኖች፣ በጀነቲክስ፣ በአልኮልና ሲጋራ፣ በእድሜ፣ በትኩረት ማነስ፣ በእንቅልፍ ማነስና በበሽታ ምክንያት አወቃቀርን ሊቀይሩ ወይም ሊሞቱና ሙሉ ሜሞሪን ሊታወክ ወይም ሊቀይረው ይችላል። በዚህም መንገድ ሕዋሳቱ በተለየ መንገድ ኔትዎርካቸውን ሊፈጥሩ ይችላሉ። የነርቭ ስርአትን የሚቆጣጠሩ ኬሚካሎች የሜሞሪን ስርአት ይቀይራሉ።

ሜሞሪ በሕዋሳት ብቻ አይደለም የሚገኘው፣ የሕዝብም አለ። የሕዝብ ሜሞሪ ተፈጥሯዊም ማኅበራዊ ስሪትም የሆነ፣ የጋራ ባህሉን የሚያጠቃልለው (እሴቶቹ፣ ምልክቶቹ፣ ቋንቋው፣ ወግና ልምዱ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እውቀቱ) እና ከማኅበረሰብ-ማኅበረሰብ፣ ከአገር-አገር ወይም ከትውልድ-ትውልድ መተላለፍ የሚችለውና ከጊዜ ጋር የሚካሄደውን ለውጥ ያካተተ ትልቅ ሐሳብ ነው።
የዛሬ የሕዝብ ሜሞሪ፣ ከትናንት የተለየ ነው። ሕትመቱ፣ ትራንስፖርቱ፣ ኢንተርኔቱ፣ ፊልሙ፣ ሙዚቃው፣ በእጅጉ ቀይሮታል። በዚህም ምክንያት የዓለም ሕዝቦች ከምንጊዜውም በላይ ተቀራርበዋል፤ የጋራ ሜሞሪውም በዝቷል። ብዙ ጊዜ የሚደጋገሙ ሐሳቦች በሜሞሪያችን ለረዥም ጊዜ የመቀረጻቸውን ያህል በመደጋገማቸው ምክንያት ስለነዚያ ጉዳዮች ያለን ሐሳብም እንዲቀየር ያደርጋል። ለዚህም ይመስለኛል ውሸት ሲደጋገም እውነት የሚመስለን። የሜሞሪ መታድስ፣ አሮጌውን በአዲሱ በመተካት ባለፈ ጊዜ እንዳንኖር ረድቶን ይሆናል። ግን ፖለቲከኞቻችን በዚህም ሐሳብ እየተጠቀሙብን ይሆን?

ታሪክ ያልተንሻፈፈ ሙሉ ትናንትን ሲያሳየን፣ የሕዝብ ሜሞሪ ግን አንዷን ብቻ ነጥሎ ሊያሳየን የሚሞክር በመሆኑ ከማኅበረሰብ-ማኅበረሰብ ሊለያይ ይችላል። የሕዝብ ሜሞሪ አገር ሊያደርገው እንደፈለገው የሚሆን ነውና እውነት ላይሆን ይችላል። በተለይም የጎጠኝነት አስተሳሰብ ለሕዝብ ሜሞሪ መለያየት ዋናው ምክንያት ነው። የሕዝብ ሜሞሪ በአፈ-ታሪክና በፖለቲከኞችም የሚተረክ በመሆኑ ምክንያት ወይም ፖለቲከኞች ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ ትርክቱን ሊያንሻፉትና ጎጂ ሊያደርጉት ይችላሉ።

በአምስቱ ህዋሶቻችን የሚሰበሰበው መረጃ፣ በአዕምሮአችን መልዕክት የመቀበልና የማደራጀት ልዩነት ምክንያት ለተለያየ አራጓጎም ተጋላጭ ስለሆነ፣ በግል አመለካከት (perception) እና እውነት (reality) መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ለዚህም ነው የሕዝብ ሜሞሪ የተሠራበት መንገድ ጎጂም ጠቃሚም የሚያደርገው። እናም የእኛው እውነት፣ እውነት ላይሆን ይችላልና የሌሎችን እውነትና የተረዱበትን መንገድ መመርመር ይጠበቅብናል። ሰዎች ምን እያሰቡ እንደሆነ ለመረዳት፣ ባለፈ ልምድ መሰረት ካደረገ ፍረጃ መውጣት ይጠይቃል።

አንድን ኅብረተሰብ ለመለወጥ፣ በመጀመሪያ ራስን መለወጥንና ሌሎች ሰዎች/ቡድኖች ነገሮችን የሚመለከቱበትን ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ነባራዊ ሁኔታን ማጤንና አሳታፊነትን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ መግባባትንና መተማመንን፣ ብሎም ለችግሮቻችን መፍትሔ በማምጣት ለጋራ ተጠቃሚነት ያበቃናል። እናም እውቀትን መሰረት ላደረገ ውይይት፣ ለጋራ ርዕዮትና እሴቶች ግንባታ እንትጋ፤ የለውጥ መሰረቶች ናቸውና! እስኪ ይህ የባህል አብዮት ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዴት እውን ሊሆን እንደሚችል፣ መሪነቱንና ኃላፊነቱን ማን መውሰድ እንዳለበት እንወያይበት።

ታሪክ ያልተንሻፈፈ ሙሉ ትናንትን ሲያሳየን፣ የሕዝብ ሜሞሪ ግን አንዷን ብቻ ነጥሎ ሊያሳየን የሚሞክር በመሆኑ ከማኅበረሰብ-ማኅበረሰብ ሊለያይ ይችላል። የሕዝብ ሜሞሪ አገር ሊያደርገው እንደፈለገው የሚሆን ነውና እውነት ላይሆን ይችላል። በተለይም የጎጠኝነት አስተሳሰብ ለሕዝብ ሜሞሪ መለያየት ዋናው ምክንያት ነው። የሕዝብ ሜሞሪ በአፈ-ታሪክና በፖለቲከኞችም የሚተረክ በመሆኑ ምክንያት ወይም ፖለቲከኞች ለራሳቸው ዓላማ ሲሉ ትርክቱን ሊያንሻፉትና ጎጂ ሊያደርጉት ይችላሉ።

በአምስቱ ህዋሶቻችን የሚሰበሰበው መረጃ፣ በአዕምሮአችን መልዕክት የመቀበልና የማደራጀት ልዩነት ምክንያት ለተለያየ አራጓጎም ተጋላጭ ስለሆነ፣ በግል አመለካከት (perception) እና እውነት (reality) መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። ለዚህም ነው የሕዝብ ሜሞሪ የተሠራበት መንገድ ጎጂም ጠቃሚም የሚያደርገው። እናም የእኛው እውነት፣ እውነት ላይሆን ይችላልና የሌሎችን እውነትና የተረዱበትን መንገድ መመርመር ይጠበቅብናል። ሰዎች ምን እያሰቡ እንደሆነ ለመረዳት፣ ባለፈ ልምድ መሰረት ካደረገ ፍረጃ መውጣት ይጠይቃል።

አንድን ኅብረተሰብ ለመለወጥ፣ በመጀመሪያ ራስን መለወጥንና ሌሎች ሰዎች/ቡድኖች ነገሮችን የሚመለከቱበትን ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊና ነባራዊ ሁኔታን ማጤንና አሳታፊነትን ይጠይቃል። ይህ ደግሞ መግባባትንና መተማመንን፣ ብሎም ለችግሮቻችን መፍትሔ በማምጣት ለጋራ ተጠቃሚነት ያበቃናል። እናም እውቀትን መሰረት ላደረገ ውይይት፣ ለጋራ ርዕዮትና እሴቶች ግንባታ እንትጋ፤ የለውጥ መሰረቶች ናቸውና! እስኪ ይህ የባህል አብዮት ምን መምሰል እንዳለበት፣ እንዴት እውን ሊሆን እንደሚችል፣ መሪነቱንና ኃላፊነቱን ማን መውሰድ እንዳለበት እንወያይበት።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 61 ታኅሣሥ 25 2012መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here