ረቡዕ ነሐሴ 15 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ)የአለም ጤና ድርጅት የአለማችን ስጋት ነው ያለው
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ክትባት በጥቂት ቀናት ውስጥ በአፍሪካ መሠጠት እንደሚጀመር የአፍሪካ ሲዲሲ አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ሲዲሲ ባወጣው መረጃ እንደገለጸው በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የክትባት እጥረት ቢኖርም ስርጭቱ ያየለባት አሀጉረ አፍሪካ ክትባቱን በቀዳሚነት ታገኛለች ሲል አስታውቋል፡፡
ከዚህ ባለፈም የክትባቱ የዋጋ አልቀመሴነት በርካታ ሀገራት ገዝቶ የማቅረብ አቅም የሌላቸው በመሆኑ በቂ አቅርቦት እንዳይኖር እክል መፍጠሩ ተገልጿል።
ይህም አሁኑ ባለው ሁኔታ የአንድ ዶዝ ክትባት ዋጋ 100 ዶላር ወይም በብር 12 ሺህ ብር ገደማ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ጄን ካስያ እስከ መጪው ሳምንት ድረስ በሽታውን በአሁጉሪቱ ለመቆጣጠር እቅድ መውጣቱን የተናገሩ ሲሆን ስርጭቱ በሚገኝበት ሁኔታ ዙሪያ ከአለም ጤና ድርጅት ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አክለውም በመጪዎቹ ቀናት 200ሺ ዶዝ ክትባት ለድርጅቱ እንደሚቀርብ እና ተጨማሪ 10 ሚሊየን ዶዝ ክትባት እንደሚስፈልግ ነው የገጠቆሙት፡፡
የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ በንክኪ ፣ በጾታዊ ግንኙነት ፣ ልብስ በመጋራት እና በሌሎች መንገዶች የሚተላለፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡



