ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) ለውጭ ገቢ ከሚውሉ የሀገር ውስጥ ምርቶች ቡና ዋነኛው ቢሆንም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የዋጋ ጭማሬ ካሳዩ ምርቶች መካከልም አንዱ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የሰላም እጦትና የደላሎች መበራከት ምርቱን ወደ መሃል አገር ለማጓጓዝ እክል መፍጠሩን በውጭ ንግድ ያል የተሰማሩ ነጋዴዎች ደጋግመው የሚያነሱት ችግር ነው፡፡
ቡናን ለውጪ ምርት የሚያቀርቡ ነጋዴዎች እንደሚሉት የታሰበውን ያህል ምርት ለውጪ ገበያ ማቅረብ ያልተቻለው በበቂ ሁኔታ ወደ ከተማ መግባት ባለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ ነጋዴዎች ከገበሬው ተረክበው ምርቱን ለእኛ የሚያስረክቡ በመሀል ያሉ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያን ተከትሎ በመጣው የገበያ አለመረጋጋት በመጠቀም ምርቱን በመደበቅ ዋጋ እያሶደዱብን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አክለውም ከዚህ ቀደም ከሀገር ውጪ ይላክ በነበረው ምርት የተሻለ ገቢ ማግኘት ይቻል ነበር ይሁንና አሁን ላይ የታሰበውን ያህል ገቢ ማምጣት ግን አልተቻለም ይባስ ብሎ በሀገር ውስጥ የምንረከብበት ቀድሞ ከነበረው 60 በመቶ የሚሆን የዋጋ ጭማሬ አሳይቷል ብለዋል፡፡
በፊት በፈረሱላ 3ሺህ900 አካባቢ የምንገዛው ቡና አሁን እስከ 6ሺክ ብር እየተሸጠ መሆኑ ጠቁመውም የገበያው ሁኔታ እስኪረጋጋ በዚሁ መንገድ ሊቀጥል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ካለው የሰላም ችግር አንጻር የጭነት ተሸከርካሪዎች በየኬላው ላይ እየተያዙብን እና ማለፊያ ገንዘብ በታጠቁ ሀይሎች እየተጠየቁ መሆኑ ሌላኛው ችግር ነው ብለዋል፡፡
በአንጻሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የእሴት ሰንሰለትንና የገበያ ዕድሎችን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የግብርና ሚኒስቴር ገልጾ የእሴት ሰንሰለትንና የገበያ ዕድሎችን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ከቡና ወጪ ንግድ 1 ነጥብ 43 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቆ እንደነበርም አይዘነጋም።



