ዓርብ ጳጉሜ 01 ቀን2016(አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ የባለሶስት እና አራት እግር ተሸከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ስራ እንድናቆም የተደረገበት መንገድ ፖለቲካዊ ነው የሚሉት አሽከርካሪዎቹ በከተማ አስተዳደሩ እየቀረቡ ያሉ ምክንያቶችም አሳማኝ አይደሉም ይላሉ፡፡
አክለውም ከስራቸው መስተጓጎላቸውን እና እንግልት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለየ መልኩ ትኩረት ይደረግብናል የሚሉት አሽከርካሪዎቹ በከተማ ላይ እንደልብ መንቀሳቀስ ተከልክለን ባለንበት አሁን ደግሞ ውስጥ ለውስጥም መስራት አለመቻላችን የዕለት ጉርስ ማግኘት እንዳንችል እያደረገን ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ተጠቃሚዎች ምንም አይነት ምትክ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪ ሳይዘጋጅ አገልግሎታቸውን ማቋረጥ ለኛም ከባድ ችግር ሆኗል ሲሉ በምሬት ገልጸዋል፡፡
እገዳው በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በተጠቃሚውም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው የሚሉት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በተለይም ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት በማይቻልባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪዎች ትልቅ መፍትሄ እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡
የትራንስፖርት ችግር ባለበት መንደር ውስጥ እንኳ የምንገለገልባቸውን ተሸከርካሪዎች አገልግሎት ማቋረጥ አግባብ የሌለው እና በሂደት እንዲያሟሉ መደረግ የሚቻለውን ሰነድ በአንዴ አሟሉ መባሉ ትክክል አይደለም ብለዋል፡፡
ቤተሰብ የምናስተዳደርበት ስራችንን በሰበብ ባስባቡ ማስተጓጎል ለባሰ የኑሮ ችግር እያጋለጠን በመሆኑ ተመዛዛኝ ውሳኔ እንዲሰጥ እና አገልግሎት ሳይቋረጥ ሰነዶቹን እንድናሟላ የሚያስችለንን መንገድ እንዲፈጠርልን እንጠይቃለን ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ይህን ጉዳይ ተከትሎ ገደቡ እስከመቼ እንደሚቀጥል እንዲሁም ስለአማራጭ የትራንስፖርት አቅርቦት ስለመዘጋጀቱ አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮን ለመጠየቅ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡



