ሰኞ ጳጉሜ 04 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ “የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል” ተብለው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ መፍቀዱ ተጠቁሟል፡፡
ፍርድቤቱ የክስ መመስረቻ የ5 ቀን ጊዜ ለዐቃቤ ህግ የፈቀደ ሲሆን በተጠረጠሩት 6 ግለሰቦች ላይ ከ14 በላይ ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ማጣሪያ ስራ ማጠናቀቁንና የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን አስታውቋል።
የፌደራል መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን ፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ከ”ጸረ ሰላም ሃይሎች ተልዕኮ በመቀበል ተንቀሳቅሰዋል” የሚል ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።
ዛሬ በዋለው ችሎት የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ተሰይሞ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ጳጉሜን 1 ቀን 2016ዓ.ም መረከቡን ጠቅሶ ማስረጃ ተመልክቶ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ክስ ለማቅረብ እንዲያስችለው ክስ ለመመስረቻ ጊዜ 5 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።
በነሀሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ መቀሌ ለጉዞ በተዘጋጀ አውሮፕላን ውስጥ የአቪዬሸን አሰራርን በጣሰ መንገድ ግርግርና ወከባ ፈጥረዋል በተባሉ 6 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፌደራል ፖሊስ የ”ሽብር ወንጀል” ምርመራ መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።



