ረቡዕ መስከረም 14 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የመንግስት ሰራተኛውንና ከ10 በላይ ሰራተኛ ቀጥረው የሚያሰሩ የግል ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ለማስጀመር ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታውቋል፡፡
የማህበረሰብ ጤና መድህንን ለማስጀመር ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የመዋቅር ለውጦች ማድረጉንም አገልግሎቱ አስረድቷል፡፡
የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎትን በፐርሰንት ከሰራተኛው በሚቆረጥ መዋጮ የሚሰጥ የጤና መድህን ፕሮግራም መሆኑን የገለጸው አገልግሎቱ በዝቅተኛ ደረጃ ያለውን የህብረተሰብ ከፍል ተጠቃሚ በማድረግ ረገድም እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዜጎች ካልተገባ የጤና ወጪ ተጠብቀው ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ አሁን ላይም የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎትን ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል፡፡



