ሰኞ መስከረም 27 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ፕሬዝዳንት የሆኑትን አቶ ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ማንሳቱን አስታውቋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት የካቢኔ አባላትን ጨምሮ 13 ኃላፊዎችን በተመሳሳይ መልኩ ከኃላፊነት ማውረዱን የገለጸው ቡድኑ፤ በምትኩ ተተኪ አመራሮችን መሾሙን ይፋ አድርጓል።
የእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 በይፋዊ የህወሓት የፌስቡክ ገጽ ባሰራጨው መግለጫ ነው።
ህወሓትን ወክለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በክልሉ ዞኖች በአመራርነት የተመደቡ ኃላፊዎች እንዲነሱ ውሳኔ የተላለፈው፤ በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው አርብ ባካሄደው ስብሰባ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል።



