ሰኞ ጥቅምት 4 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ለአመታት በእረስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኛው አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና የዕርስ በዕርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀሎች ጥፋተኛ መባላቸው ታውቋል፡፡
አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱበት ክሶች በዛሬ ቀጠሮ የጥፋተኝነት ፍርድ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ የመከራከሪያ ነጥቦችን አቅርቦ ክርክር መደረጉ ይታወቃል።
የግራ ቀኙን ክርክር መርምሮ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ በሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ መሰረት ችሎቱ ተሰይሞ የአቶ ታዲዮስ ታንቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን በሙሉ ድምፅ ውድቅ አድርጎታል።
አቶ ታዲዮስ ዝርዝር የሠነድ መከላከያ ማስረጃዎች ካሏቸው ማቅረብ እንዲችሉ ለታኅሣስ 21 ቀን የተቀጠረ ሲሆን÷ የሚቀርቡ የመከላከያ ማስረጃዎችን አሰማምን በሚመለከት በዕለቱ ሌላ የቀጠሮ ቀን የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል።
ተከሳሹ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት እና የእርስ በርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በፍትሕ ሚኒስቴር በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በኩል ተደራራቢ አራት ክሶች ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።



