ዕረቡ ህዳር 04 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በቅርቡ በአዋሽ ፈንታሌ አካባቢ በተደጋጋሚ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በተለያዩ አካባቢዎች ንዝረት መሰማቱ ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ንዝረት በመሰማቱ በከተማዋ ላይ ያሉ ህንጻዎችን ስጋት ላይ ጥሏቸዋል ተብሏል፡፡
ህንጻዎቹ የመድን ሽፋን ያላቸው ቢሆንም አብዛኞቹ የመድን ሽፋኑን እንደማይጠቀሙ ተጠቁሟል፡፡
የህብረት ኢንሹራንስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽም “በመዲናችን የሚገኙትን ግዙፍ ህንጻዎች ዓላማ ያደረጉ የተለያዩ ምርቶች ቢኖሩንም በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ህንጻዎች የኢንሹራንስ ሽፋን የላቸውም” ሲሉ አስታውቀዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ይህን የተናገሩት ህብረት ኢንሹራንስ የ30ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ ባዘጋጀው የጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነው።
በተጨማሪም “ከዚህ ቀደም በከተማው ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች በርካታ ሕንፃዎች እንዲወድሙ ምክንያት ሆኗል፣ በወቅቱም መንግሥት ለባለሀብቶች ወጪውን ለመሸፈን ዕርምጃ የወሰደ ቢሆንም መንግሥት በቀጣይ ጊዜ ኃላፊነቱን እንደማይሸከም በግልጽ ተናግሯል” ሲሉ የህብረት ኢንሹራንስ ምክትል ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ደስታ ገልጸዋል፡፡
አክለውም “የመሬት መንቀጥቀጥ ኢንሹራንስ፣ የእሳት አደጋ ኢንሹራንስ እና ሌሎች ወሳኝ ሽፋኖችን የሚያካትት የመድኋን ሽፋኖች ያሉ ቢሆንም አደጋው እየጨመረ ቢመጣም ብዙዎቹ እነዚህ አገልግሎቶች እንደተጠበቀው እየተጠቀሙ አይደለም” ሲሉ ጠቁመዋል።



