ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 13፤ 2012)

0
773

ዳሰሳ ዘ ማለዳ (ጥር 13፤ 2012)

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የካቢኔ ሹም ሽር አካሄዱ። ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስትር፣ መላኩ አለበል የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እና አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል። ሚኒስትሮቹ ከጥር 6 ቀን 2012 ጀምሮ መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የሚኒስትሮቹ ሹመትም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርቦ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል። (ኢቲቪ)

……………………………………………………………………………………………………………………

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአራት ፓርቲዎች የእውቅና ሰርተፍኬትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጠ። በእስክንድር ነጋ የሚመራውን የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲን ጨምሮ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን ቦርዱ ዛሬ ይፋ አድርጓል። ተሻሽሎ በፀደቀው የምርጫ ሕግ መሰረት ጊዜያዊ እውቅናው የሚያገለግለው ለሦስት ወራት ብቻ ሲሆን፣ አመልካቾች በቂ ምክንያት አቅርበው የጠየቁ እንደሆነ ለተጨማሪ ሦስት ወር ሊራዘም ይችላል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………

ኩዌት ከኢትዮጵያ የቤት ሠራተኞችን ልትመለምል ነው። የኩዌት እና የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባላሥልጣናት ባሳለፍነው ሐሙስ በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሰረት፣ ሠራተኞቹ ልምድ ያላቸው፣ የሥራ ውጤታማነታቸው የላቀ እንዲሁም እንግሊዝኛ ቋንቋን የሚናገሩ እንዲሆኑ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን ገልፍ ኒውስ ዘግቧል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………

ሐሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀም ግብር የሰወሩት ግለሰብ በእስራት ተቀጡ። ከንግድ የሚገኝ ትርፍ ላይ የሚጣለውን የንግድ ትርፍ ለመሰወር በማሰብ ከ 2004 እስከ 2007 ባለው የበጀት ዓመት ያከናወኗቸውን የውጪ አገር ግብይቶች ዋጋ ለማሳነስ ሐሰተኛ ደረሰኝ የተጠቀሙት ሥራ አስኪያጅ፣ የስድስት ዓመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት ተፈርዶባቸዋል። የስምኦን ኤሌክትሮ መካኒካል ኢንጅነሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ግለሰብ፣ የግብይት ዋጋን በማሳነስ፣ ያልተፈቀዱ እና በማስረጃ ያልተደገፉ ወጪዎችን በማቅረብ እንዲሁም ያልተፈቀዱ የፋክቱር ደረሰኞችን በመጠቀም ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን፣ ከሥራ አስኪያጁ በሻገር ጥፋተኛ የተባለው ድርጅቱ 80 ሺሕ ብር ቅጣት ተጥሎበታል። ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጉምሩክ ችሎች ውሳኔ ሰጥቷል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ በቅርቡ ፓርቲውን የተቀላቀሉት ጃዋር መሐመድ ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንዳላቸው የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርብ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ደብዳቤ ጻፈለት። የቀድሞው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) ሥራ አስኪያጅ ጃዋር መሐመድ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፣ የውጪ ዜግነታቸውን መልሰው የኢትዮጵያ ዜግነት ለመውስድ እየሞከሩ እንደነበር መግለፃቸው ይታወሳል። ይሁንና የዜግነቱ ጉዳይ እልባት ሳያገኝ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲን በመቀላቀላቸው ቦርዱ ማስረጃ መጠየቁን  የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ተናግረዋል። (ዋዜማ ራዲዮ)

………………………………………………………………………………………………………………………

በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጉጂ ዞን በተቀሰቀሰ አዲስ ግጭት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ። ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል በተካሄደ ፍልሚያ በዞኑ ባሉ የተለያዩ ቀበሌዎች ነዋሪዎቹ መፈናቀላቸውን እና ከዞኑ መቀመጫ ነገሌ ከተማ በ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ላይ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙም የተመድ ኦቻ ሪፖርት አመላክቷል። (አዲስ ስታንዳርድ)

……………………………………………………………………………………………………………………

 

 

 

 

 

 

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here