ትውልዳቸው ምዕራብ ኢትዮጵያ ወለጋ ላይ በ1950 ነው። የሦስት ልጆች አባት የሆኑት ታደሰ ጥላሁን፣ የኖክ ማደያ ዋና ሥራ አስፈጻሚም ናቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኮሜርስ በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደያዙ ነበር ወደ ሼል ግሩፕ ያቀኑት። በዛም ሠልጥነው የተለያዩ አገራት ለመንቀሳቀስ እድል አግኝተዋል። የተለያዩ የአፍሪካ አገራትም በአመራርነት ቆይተዋል። ወደ ኖክ ከመሠራታቸው አስቀድሞ፣ የምሥራቅ አፍሪካን የነዳጅ ገበያ ጥርት አድርገው የተረዱ ሆነው ነበር።
ኖክ ገበያውን በ2004 ተቀላቀለ። በሰዓቱ የውጪ ግዙፍ የሆኑ የነዳጅ ገበያዎች ኢትዮጵያን ጥለው በመውጣታቸው፣ ኖክ የገበያውን ፍላጎት የማሟላት ከባድ ሥራ ጠብቆት ነበር። የኖክ ባለድርሻ የሆኑት ሼሕ መሐመድ ሑሴን አሊ አላሙዲ፣ ታደሰ ጥላሁን እና አብነት ገብረመስቀል ሲሆኑ፣ ከእነርሱም ታደሰ ነበሩ ኖክ በፍጥነትና በአጭር ጊዜ በገበያው ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆን ያስቻሉት።
ታደሰ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የአፍሪካ ነዳጅ ማጣሪያ ኩባንያዎች ኅብረት የቦርድ አባል ናቸው። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ነዳጅ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። በበጎ አድራጎት ተሳትፎም ትልቅ ድርሻ እየተወጡ ሲሆን፣ ለባለቤታቸው ገነት ሐደጎ መታሰቢያ፣ በ2015 ለተቸገሩ ቤተሰቦች ትምህርት እና በግብርና ድጋፍ የሚያደርግ ፋውንዴሽን አቋቁመዋል።
በኢትዮጵያ እያደገ ላለው የነዳጅ ፍላጎት፣ የአገር ውስጥ ነዳጅ ኩባንያዎች እየጎረፉ ቢሆንም፣ የባለሙያ ድጋፍ እና ካፒታል ያንሳል ሲሉ ይሟገታሉ። የምሥራቅ አፍሪካ አገራትም ነዳጅ ማጣሪያ ላይ ትኩረት በማድረግ በጋራ ሊሠሩ ይገባል ባይ ናቸው። ከ40 ዓመት በላይ ከተቀዳ ልምዳቸው ለማካፈልም የሚሰስቱ አይደሉም። የዒትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው ባልደረባ አሸናፊ እንዳለም የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።
ስለራስዎ ይንገሩን፤ እንዴት ነው የኖክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሊሆኑ የቻሉት?
ኖክ ከመግባቴ በፊት ሼል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነበርኩኝ። ናይጄሪያና ኬንያን ጨምሮ ብዙ የአፍሪካ አገራትም ሠርቻለሁ። የሼል ዋና መቀመጫ ከሱዳን እና ሞካምቢክ ቀጥሎ መገኛው በሱዳን ነበር። በመጨረሻም ባለቤቴ ኢትዮጵያ መኖር ስለፈለገች ኢትዮጵያ መጣሁ። በሙያዬም የሂሳብ ባለሙያ ነኝ።
የአፍሪካ ነዳጅ አጣሪ ኩባንያዎች ማኅበር ሊቀመንበር ነበሩና፤ የአፍሪካን የነዳጅ ገበያ እንዴት ያዩታል?
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከነዳጅ ፍለጋና ማውጣት ጋር በተያያዘ ከአፍሪካ ኅብረት የኃይል መምሪያ ጋር ስብሰባ ነበረን። በአፍሪካ የነዳጅ ፍለጋ እየተስፋፋ፣ ከሞሮኮ፣ ሊብያ እና ግብጽ ከመሳሰሉ ሰሜን አፍሪካ አገራት ወደ ምዕራብ አፍሪካ (ናይጄሪያ) እንዲሁም ቀጥሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አንጎላ፣ ዩጋንዳ እና ሱዳን እየተሰራጨ ነው። ኬንያም በቅርቡ የነዳጅ ድፍድፍ አግኝታለች። ይህም ከኢትዮጵያ ቅርብ በሆነው የኦሞ ወንዝ ዳር ላይ ነው። ታንዛንያ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳንም ነዳጅ አግኝተዋል፣ ይህ በኢትዮጵያም ሊሆን የሚችል ነው።
ይሁንና በእነዚህ አገራት የነዳጅ አጠቃቀም አሁንም አስቸጋሪ ነው። በቀደመው ጊዜ ናይጄሪያ ነዳጅን ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ ትልክ ነበር። ሆኖም ይህን ያልተጣራ ነዳጅ አሜሪካ ማስገባት ስታቆም ናይጄሪያ ትልቅ ገበያ አጥታለች። ለአፍሪካ አገራት ድፍድፍ ነዳጅን ወደ ውጪ አገራት መላክ አዋጭ አይደለም። ናይጄሪያም ያንን ነዳጅ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመላክ ተገዳለች። ያም ሆኖ የመካከለኛው ምሥራቅ ገበያም ምቹ አልነበረም፣ ገበያው ቀድሞ ያደገ ስለሆነ። ስለዚህ እንደ ናይጄሪያ ያሉ ነዳጅ ላይ ጥገኛ የሆኑ የአፍሪካ አገራት፣ በዚህ ምክንያት እየወደቁ ነው።
ያም ሆኖ፣ የአፍሪካ የነዳጅ ፍላጎት ከእለት እለት እየጨመረ ይገኛል፤ የኢትዮጵያም እንደዛው። ነገር ግን የአገራቱ የኢኮኖሚ ደረጃ ነዳጅ ማጣራትን ፈታኝ አድርጎታል። ለምሳሌ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ነዳጅ ማጣሪያዎች፣ በቀን ከ400 ሺሕ በላይ በርሜል ነዳጅ ያጣራሉ። እንዲህ ያሉ ማጣሪያዎችን ለመግጠም ከ10 ሚሊዮን በላይ ዶላር ያስፈልጋል። ይህም በአፍሪካ ነዳጅ ማጣሪያን ማቋቋምን ከባድ የሚያደርገው ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ይህን ሊያሟሉ የሚሉ በማጣራት ልምድ ያላቸው ናቸው።
ለምሳሌ ዳንጎቴ ያልተጣራ ነዳጅ መላክ አዋጭ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ በናይጄሪያ ትልቅ ማጣሪያን እያስገነባ ይገኛል። ይህም በቀን 600 ሺሕ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ማጣራት የሚችል ነው። ግንባታው በ2022 ሲጠናቀቅ፣ ናይጄሪያን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ምዕራብ አፍሪካን በነዳጅ ተደራሽ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም አቅም ያላቸው የአፍሪካ አገራት የጋራ ማጣሪያዎችን ማቋቋም ላይ ማተኮር አለባቸው። በተናጠል እነዚህን መሥራት ከፍተኛ ወጪ ስላለው ነው። በአፍሪካ ኅብረት ላይ የተነሳው የውይይት ጉዳይም ይህ ነበር።
ለምሳሌ የምሥራቅ አፍሪካን ጉዳይ እናንሳና፣ የት ነው ነዳጅ ማጣሪያን ለማቋቋም ትክክለኛ ቦታ የሚሆነው?
በሐሳብ ደረጃ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዩጋንዳ እና ኬንያ፣ በኬንያ ነዳጅ ማጣሪያ እንዲቋቋም ነበር ሐሳብ ያቀረቡት። ተመራጩ መንገድም ነዳጅ ባለበት ማጣሪያውን መገንባት ነው። ድፍድፍ ነዳጅን ከሩቅ ቦታ አምጥቶ እዚህ ማጣራት ተመራጭ መንገድ አይደለም። እንደሰማሁት የኢትዮጵያ መንግሥት ሞጆ ላይ ነዳጅ ማጣሪያ ለመመሥረት አቅዷል። ይህም ጥሩ አካሄድ አይመስለኝም። ምክንያቱም ድፍድፍ ነዳጅን ወደ አገር ውስጥ አስገብተህ አጣርተህ፣ ተጣርቶ ከሚመጣው ባነሰ ዋጋ ልትሸጠው አትችልም።
ለምን ይሆን ኢትዮጵያ ከሌሎች አፍሪካ አገራት ጋር ይህን ነዳጅ ማጣሪያ ማቋቋም ያልተሳካላት?
በፊት ፖለቲካ እና ብሔራዊ ነጻነት እንዲህ ያሉ ትልልቅ ሥራዎችን ለመሥራት ወሳኝ ነጥብ ነበሩ። አሁን ግን ሁሉም የአፍሪካ አገራት ተስማምተዋል። እንደበፊቱ ሆኖ የሚቀጥል አይሆንም።
ባለፉት 15 ዓመታት ከውጪ የምናስገባው የነዳጅ ምርት እያደገ ነው። የትኛው ዘርፍ ነው ፍላጎቱን እየመራ ያለው?
እሱ በጣም የሚስበኝ ጉዳይ ነው። የዛሬ 15 ዓመት እኛ ስንቋቋም፣ በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ፍላጎት 1.5 ሚሊዮን ቶን ነበር። አሁን 4 ሚሊዮን ቶን ወይም 4 ቢሊዮን ሊትር ደርሷል። ይህ ማለት ምንም ማለት አይደለም። ይህን ስል ማሳያ አለኝ። በአፍሪካ የኃይል ምንጭን ቀላቅሎ መጠቀም (ኢነርጂ ሚክስ) የሚባል ነገር አለ። አፍሪካ ከሚያስፈልጋት የኃይል ምንጭ ውስጥ የነዳጅ ፍላጎት ወይም ለመኪና የምንጠቀመው ነዳጅ 22 በመቶ ነው። ቀጥሎ ባዮ ማስ ማለትም እንጨት ከሰል የሚለው 45 በመቶ ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ደግሞ 90 በመቶ ነው።
ስለዚህ የእኛ ዘመዶች በሙሉ የሚጠቀሙት ከሰል ወይም ከእንጨት ጋር የተያያዘውን ነው ማለት ነው። የኃይል ፍጆታችን ያለው እዛ ነው። እና የእኛ ፍላጎት 4 ቢሊዮን ደረሰ ብልህ አትደነቅ። ለአፍሪካ እርሱ 45 ነው። ከእኛ ተሽለዋል። እኛ አሁንም በእንጨት ላይ ጥገኛ ነን። ለዛ ነው በየዓመቱ ዛፎቻችንን የምንቆርጠው።
የተፈጥሮ ጋዝ ለምሳሌ ትልቅ ኢኮኖሚ ያላቸው፣ እንደ ደቡብ አፍሪካና ግብጽ የሚጠቀሙበት ነው። ከዛ ቀጥሎ ያለው ከሰል ነው። ከሰልን ከደቡብ አፍሪካ አምጥተን ለሲሚንቶ ፋብሪካ ነው የምንጠቀመው። ይህም 30 በመቶ ነው። ስለዚህ የነዳጅ ፍላጎታችን ገና ነው።
ላለፊት 10 እና 15 ዓመታት፣ 1.5 ሚሊዮን ወደ 4 ሚሊዮን ሊትር ያደረሰው ፍላጎት ምንድን ለሚለው፣ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በራሳችን ጥፋት ወደብ አልብ አገር ሆነናል። ስለዚህ ትራንስፖርት ወሳኙ የምርታችን ተጠቃሚ ነው። ማለትም ትራንስፖርት ቀዳሚ ሆኖ ይመራል። ቀጥሎ የአየር መንገዱ ነው የሚከተለው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፍጆታ ቀላል አይደደም።
እንዳሉት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ትሠራላችሁ። ከዚህ ጋር አያይዘው በኢትዮጵያ ያለውን የነዳጅ አጠቃቀም ከሌሎች አገራት አንጻር እንዴት ያዩታል?
አሁን የቦርድ አባል ነኝ [በኢትዮጵያ አየር መንገድ]። እና ከናፍጣ ቀጥሎ ያለው የጄት ነዳጅ ነው ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው። ይህም ዋናው አየር መንገድ ነው፣ ነዳጅ ደግሞ ለመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫዎች ነው። ኢትዮጵያ እንደ አገር አንድ ሚሊዮን መኪና ብቻ ነው ያላት። ኬንያ ትንሽ አገርና ትንሽ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር ብትሆንም የመኪናዋ ብዛት ሦስት ሚሊዮን ነው ያለው። ልዩነቱን ማየት ይቻላል።
እሱን ካልከኝ የቤት ውስጥ ያለውን የጋዝ ተጠቃሚነትና ፍጆታ ልናነሳ እንችላለን። እንደ ኬንያ እና ዩጋንዳ ያሉ ትንንሽ አገራት፣ ከ400 ሺሕ ቶን በላይ ነው በዓመት የሚጠቀሙት። ከኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ጋር ስናነጻጽረው፣ ኢትዮጵያ በዓመት 15 ሺሕ ቶን ብቻ ነው በዓመት የምትጠቀመው።
ከኬንያ ሲነጻጸርና ለምን ቀነሰ ስንል፣ ምክንያቱም ኬንያውን የሠለጠኑና መሣሪያዎች ያሟሉ ናቸው። ከከሰል ወደ ነዳጅ በየቤቱ አሳድገዋል። ከእኛ የተሻለ የኃይል አቅርቦት ኖሯቸው አይደለም።
ከውሃ በሚመነጭ ኃይልስ ምን ያህል ድርሻ አለው?
እሱ 2 በመቶ ብቻ ነው። መረጃውን ለማግኘት ትንሽ ያስቸግራል። ኢትዮጵያ በሃይድሮ ፓወር ኹለተኛ አቅም ያላት አገር ናት፤ ከኮንጎ ቀጥሎ። ግን ኮንጎ የኢትዮጵያን ያህል እያሳደገች አይደለም። እኛ ፕሮጀክቶቹን የምንይዝበት መንገድ ነው እንጂ፣ አሁን ላይ መለወጥ እንችል ነበር። ያ በሚሆን ጊዜ ነገሮች ሊሻሻሉ ይችላሉ። ቅድም እንዳልኩት ግን ከእንጨት ጋር የተያያዘ ነው የኃይል ፍጆታችን።
የእኛ የነዳጅ ፍጆታ ሰባት በመቶ ነው የሚያሳየው። አሁን ላይ ባለው ሁኔታ ቢበዛ አስር በመቶ ነው ብለን ልንይዝ እንችላለን። ይህ ማለት ተጠቃሚነታችን በጣም ገና ነው፤ ኢኮኖሚው ገና አልተነሳም ነው። የእኛ ሰዎች በእግር ነው እየሄዱ ያሉት። ስለዚህ የነዳጅ ፍላጎታችን ገና ወደፊት የሚያድግ ነው። ወደፊት የኤሌክትሪክ መኪናዎች ወደ አፍሪካ በብዛት ይገባሉ፤ አሁን ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ እንደጀመሩት።
እና የኢትዮጵያ ኢነርጂ ሚክስ ገና ነው። ለምሳሌ ከሕዝብ ብዛት አንጻር፣ በአፍሪካ ከፍተኛው ነዳጅ የሚጠቀሙት አንደኛ ግብጽ ናት። አራቱ የሰሜን አፍሪካ አገራት፣ የአፍሪካን ሃምሳ በመቶ ፍላጎት ነው የሚጠቀሙት። የቀረውን ደግሞ የሰብ ሰሃራ አፍሪካ አገራት ይካፈላሉ። ይሄ በዚህ ላይ እያለ፣ እንደ ኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎታችን ገና ብዙ የሚቀረው ነው።
ይህ ከሆነ የነዳጅ ማጣሪያ እዚህ [ኢትዮጵያ] መሆን ቢችል፣ የነዳጅ ዋጋ አሁን ካለበት ሊቀንስ ይችል ነበር?
ጥሩ ጥያቄ ነው። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅርቦት በመንገድ ትራንስፓርት የሚከናወን ነው። ይህም ለነዳጅ ማጓጓዣ በጭራሽ የሚመከር አይደለም። የነዳጅ ማጓጓዣ በተቻለ አቅም፣ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሰፊ አገራት፣ በረጅም ቧንቧ መሆን አለበት። እናም የእኛ ምርት ውድነት በትንስፖርቱ ምክንያት ነው። ከጅቡቲ እስከ አዲስ አበባ የምናመጣው በተዘረጋ መስመር ወይም ቧንቧ ቢሆን ኖሮ፣ ግማሽ ያህሉ ይመጣ ነበር።
ኢትዮጵያ ባቡር ሐዲድ ላይ እየሠራች ነው፣ ይህም ኤሌክትሪክ የሚጠቀም ነው። የኤሌክትሪክ መኪኖችም መምጣታቸው አይቀርም። እና ይህ ከተሳካ የነዳጅ ፍላጎቷ ሊቀንስ ይችላል ማለት እንችላለን?
ደረጃ በደረጃ እንነጋገር፣ የሚቀድመው ምንድን ነው? እኛ ጎበዝ ከሆንን ተፈጥሮ ያደለን ሃይድሮ ፓወር ነው። የትም አገር ብትሄድ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት እንደ እኛ ዓይነት መልክአ ምድር የላቸውም። ኢትዮጵያ አሁን የህዳሴ ግድቡን እንዲሁም ኦሞ ላይ የሚሠራውን ግድብ ቶሎ ጨርሳ ወደ ሥራ ብታውል፣ ኬንያዎች አራት እጥፍ ነው ሊያመርቱበት የሚችለው። ስለዚህ ለኢኮኖሚ በጣም የሚጠቅም የኃይል ምንጭ ይሆናል፤ ለጎረቤቶቻችን። ኤሌክትሪክ ለኢኮኖሚ ገበያ ላይ የምናቀርበው ምርት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ብዙ የምንጠቀምበት ነው፣ ለድህነት ቅነሳ ብቻም አይደለም።
ዋናው ነገር እስከ አሁን የተበላሸው ስርዓት ያለው የፕሮጀክት አያያዝ አለመኖር ነው።
ባቡር አልከኝ፤ ባቡር ላይ ብዙ መዋዕለ ነዋይ አፍስሰን ነበር። ግን አንደ ሊትር ነዳጅ በባቡር አላጓጓዝንም። መስመሩ ግን የተዘረጋው ከጅቡቲ አዋሽ ነው፣ አልቆ ተመርቋል ተብሏል። ሥራ ላይ ካልዋለ መመረቅ ምን ማለት ነው። ስለዚህ እሱ ቢገጥም ኖሮ፣ አንድ የትራንስፖርት ወጪ ይቀንስልናል። ኹለተኛ የተበደርነውን እዳ ምንም ሳንጠቀምበት መክፈል አንጀምርም።
ባቡሮቹ መሥራት ያልቻሉት ለምንድን ይመስልዎታል?
ኹለት ኪሎሜትር ቢሆን ነው፣ ከጅቡቲ ጠረፍ እስከ ባቡር ተርሚናሉ ያለው ርቀት ። እሱ አልተገናኘም። በዚህ በኩል አዋሽ ዴፖ እና ባቡር መንገዱ አልተገናኘም። ቀላል የፕሮጀክት አመራር ነው፣ እንጂ ሌላ ችግር የለም፣ መስመሩ ተዘርግቷል። ለባቡሩ የሚሆን ኤሌክትሪክ ኃይል አለን ወይ ከሆነ ጥያቄው፣ እሱ ይቅርና ገና መስመሩ አልተገናኘም። እና ኹለቱም ነው ችግሩ።
የኤኬክተሪሪክ ምርታችንን ብንጨምር አንደኛ ገበሬዎች በየቤታቸው መብራት ያበራሉ። ኹለተኛ ኃይል ሸጠህ የውጪ ምንዛሬ ታገኛለህ። ያ ቀላል አይደለም። ኹለት ቢሊዮን ይጠጋል፣ ከውሃ የሚገኘው ኃይል።
ነዳጅ አቅርቦትና ስርጭቱ ላይ እንምጣ። ብዙዎችን መሳብ ችሏል። የነዳጅ ፍላጎቱ እድገት ነው ይህን በማድረጉ በጥቅሉ ጥሩ ቢዝነስ ነው ማለት እንችላለን?
ቀደም ብዬ እድገቱን አንስቻለሁ። እንደውም ገና አልጀመርንም። ወደፊት የነዳጅ ፍላጎት እንዴት እንደሚያድግ እናያለን፤ ማስቆም የሚቻል አይደለም፣ ኢትዮጵያ እያደገች ነው። ምንአልባት ከ5 ዓመት በኋላ በእጥፍ ያድጋል ብዬ አስባለሁ፤ 5 ዓመት ላይወስድም ይችላል።
በኢትዮጵያ የነዳጅ ስርጭት ጋር በተያያዘ የጀርባ ታሪኩን እናንሳ። የዛሬ 65 ዓመት አካባቢ የነዳጅ ማጣሪያ አሰብ ላይ ሲቋቋም ነው፣ አሁን የሚሠራት የነዳጅ ማሰራጫ መዋቅር የተቋቋመው። ያኔ ያደረጉት ምን ነበር፣ መንግሥት ያመጣል፤ ኩባንያዎች ያንን ይከፋፈሉና ያሰራጫሉ። ኹለት ነገሮች ነበሩት፣ የስርጭት አሠራሩ የሚሄድበት።
አንደኛው የመኪና ቅባት ምርቶች ናቸው። ከጠቅላላው ፍላጎት ዝቅተኛ የሆነው፣ ከአንድ በመቶ በታች ያለው ነው። የዚህን ማሪጅን ከፍ አድርገው የዋናውን ምርት ዝቅ አድርገው ኹለቱ ተቻችለው እንዲሄዱ ነው ያቋቋሙት፣ የመጀመሪያዎቹ። ነዳጅ የሚጠቀመው ተራው መንገደኛ ነው። ዘይቱን የሚገዛው ደግሞ ባለመኪናው ነው። እና የተሸለ መክፈል አለበት ብለው፤ የሱን ማሪጅን ኩባንያዎች እንዲያገኙ፣ ነዳጅ በርካሽ ዋጋ እንዲሸጡ ነው ያደረጉት።
በዛ መልክ እስከ አሁን ሲሠራት ነበር። ደርግ አልለወጠውም፣ ኢሕአዴግም አልሞከረውም፣ አሁኑ መንግሥም በዛው መልኩ ነው ያለው። ነገር ግን በዛን ጊዜ ያሉት ነዳጅ ማደያዎች በጣም አነስተኛና ትንሽ ናቸው። አሁንም ቢሆን በጣም አነስተኛ ነው።
ይህን ስል በቁጥር ላስቀምጥ እችላለሁ። ለምሳሌ ኬንያ በሕዝብም በስፋትም ትንሽ ናት፤ ግን ከ2500 ማደያዎች በላይ አሉ። እኛ አንድ ሺሕ አልደረስንም። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ኢኮኖሚው እያደገና መንገዶች እየተስፋፉ ነው፣ አዲስ ከተሞች ተመስርተዋል። እነዚህ የሚፈጥሩት ነዳጅ ፍላጎት አለ። ገበሬውም ነዳጅ ይፈልጋል። ስለዚህ ብዙ ማደያ በከተማ ብቻ ሳይሆን በገጠር ያስፈልጋል። አዲስ አበባም ጥቂት ነው ያለው፣ ያንሰናል።
መንግሥት ያሰበው ወደ ዘርፉ የመግቢያ መንገዱን ቀላል ብናደርገው፣ ብዙ ባለሀብት በስርጭት ይኖራል፣ ብዙ ማደያ ይኖራል የሚል ነው። በዚህም ማንኛውም አካባቢ ለመድረስ እንችላለን ብለው ነበር ያሰቡት። ግን ተሳስተዋል። አንደኛ ተመኑ ዝቅተኛ ስለሆነ ተጨባጭ አልነበረም። የተፈጠሩት ኩባንያዎችም ሦስት ነገር የላቸውም። አንደኛ የገንዘብ አቅም የላቸውም፣ ኹለት እውቀት የላቸውም፣ ሦስተኛ ተቋማዊ ጥንካሬ የላቸውም፤ በሰው ኃይልም ያንን የሚሠራ አወቃቀር የላቸውም።
እነርሱ የገቡበት ጥሩ እያደገ ያለ ዘርፍ መስሏቸው አይደለም። ያኔ አብዛኞቹ ሲገቡ የጋዝና የናፍጣ ዋጋ ቢያንስ የ2 ብር ልዩነት ነበረው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲጨነቅ የነበረው፣ የጋዝ ዋጋ ይደጎም ነበር። ከመጀመሪያ ጀምሮም ጋዝን የሚጠቀሙ ደሀ እናቶቻችን ስለሆኑ ብዙ መክፈል የለባቸውም ተብሎ ይደጎም ነበር።
ያንን እያደባለቁ ሲሸጡ ነበር፤ ያኔ። በዚህ መንገድም ሲጠቀሙበት ነበር። እና ይህንን ነገር ብዙ ስንጮኽ ነበር። ታንዛንያም ተመሳሳይ ችግር ነበር። የእነርሱን አዋጅ አምጥቼ እንደውም ለንግድ ሚኒስቴር ነው የሰጠሁት። ይህ ካልተሰስተካለ መኪናዎቻችን እና ማሽኖቻችን ያበላሻሉ። ምክነያቱም ለእነርሱ የተባለውን ምርት ሳይሆን ጋዝ የሚጠቀሙት በነዳጅ ቦታ ነው። ይህን ካላቆማችሁ ብዬ አሳወቅሁ።
በዛ ምክንያት የኹለቱ ዋጋ እኩል ሲሆን፣ የገቡት ሰዎች በአንድ ጊዜ ዝም ነው ያሉት። ከዛ በኋለ የገቡበት ብድር ስለሚገኘ ነው። የአንድ ወር ብድር ነበረው፤ እሱ እየወሰዱ ለሌላ ጉዳይ ያውሉታል። ክፍያ በሚጠየቁ ጊዜ መክፈል አልቻሉም።
እና ትክክለኛ በሆነ ውሳኔ አይደለም የገቡበት። ምክንያም ይህ የሚገኘው ከብዛት ነው። ለመቆየት ብዙ ማደያ ሊኖርህ ይገባል። እንጂ ኹለት ሦስት ማደያ ሠርቶ፣ አዋጭ አይደለም። ይህንንም መንግሥት ያውቃል።
እዚህ ላይ ትልልቆቹ ከገበያ የወጡት በትርፍ ኅዳጉ ምክንያት ነው? ኖክስ ይህን እንዴት ሊቋቋመው ቻለ?
ሼል ትልቅ ተቋም ነው። እኔም እንደ ትምህርት ቤት ነው የማየው፣ ከእነርሱ ጋር የሠራሁበትን። እነርሱ ለቅቀው የሄዱበት ምክንያት በትርፍ ኅዳጉ አነስተኛ ስለሆነ የተቋሙን ደረጃ ለመጠበቅ ሲሉ እውነተኛ ውሳኔ ወሰኑ። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከተወሰኑ የአፍሪካ አገራትም ወጥተዋል። እኛ በዓለም ዐቀፍ ተቋም አስጠንተንና አቅርበን ትንሽ አሻሽለዋል። ግን እኛ የጠየቅነው ጋር ይለያያል፤ አይገናኝም። ግን የተወሰነ ልዩነት አለው።
ኖክ ገና ከመጀመሩ በፊት በ11 ማደያ ነው የጀመረው። በአንድ ቀን 11 ማደያ ከፍተን ነው የጀመርነው። በዛ ላይ እዚህ ውስጥ የሚሠሩ ሰዎች ከእኔ ጋር ከሼል የመጡ ናቸው። ዘርፉን ለመምራት በእውቀት ደረጃ አቅም ነበራቸው። የአገር ውስጥ ኩባንያዎች አፍሪካ ውስጥ ስኬታማ አይሆኑም ብለው ሲያሾፉ ነበር። ግን በኹለት ዓመት ገበያውን ተቆጣጠርን።
የእኛን ማደያዎች አይተህ ከሆነ፣ አንደኛ በአንድ ጊዜ 12 መኪናዎችን ያስተናግዳሉ። አቅማቸው ትላልቅ ነው፤ የምርት ችግር ከሌለ በቀር። ሌላው ነዳጅ ብቻ አይደለም፣ ብዙ አገልግሎት ነው የምንሸጠው። መኪና መጣቢያ አለ፣ ሱፐር ማርኬት አለ፣ የመኪና ቅባት መሸጫ አለ፣ ሱፐር ማርኬት አለ፣ ብዙ ነገሮች ስላሉ እነዛ ተሳስረው ብዙም ባናተርፍ ያዋጣናል።
በተጨማሪ ዓመታዊ ድርሻችንን መልሰን ለልማት እናውላለን። ለዛ ነው ትልቁን ሕንጻ መሥራት የቻልነው፣ ቦሌ መንገድ ላይ። ለዛም ኖክ መኖርና መዝለቅ ችሏል።
አንድ የነዳጅ ኩባንያ ትርፋማ ለመሆን ምን ያህል ማደያ ሊኖረው ይገባል?
አንደኛ ማደያዎቹ ምን ያህል ይሁኑ የሚለው፣ የተቋም አቅምና መዋቅር ይወስናል። አመራር ላይ የተወሳሰበ ከሆነ ብዙ ወጪ ያስወጣል። ግን ለዚህ ብዙ ውስብስብ አይደለም። የራሳቸውን ጸሐፊ አስቀምጠው መምራት ይችላሉ። ግን ኢኮኖሚካሊ መምራት ይችላሉ። አንድ አምስትና ዐስር ማደያዎች ቢኖሩ መቀጠል ይችላሉ።
ለኖክ ግን ከባድ ነው። በጣም ከባድ ነው። በተለይ አቭዬሽን ውስጥ ከገባህ ከባድ ነው። ለቦሌ አሁን 1.5 ቢሊዮን ዶላር ነው ኢንሹራንስ የሚሸፍነው። ፕሪምየሙ አነስተኛ ሊሆን ይችላል፣ ግን ያን ያህል ኃላፊነት አለበት። ስለዚህ ያልካቸው ኩባንያዎች እንደኛ የተወሳሰበ ነገር ላያስፈልጋቸው ይችላል። ግን በሙያና በእውቀት ሊመሩት ይገባል። ለዚህም ማሳያ እነ ጎመጁ እና ታፍ አሉ።
ብድርን በሚመለከት ከመንግሥት ጋር ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ለእኛም ችግር እየፈጠሩብን ነው። ምክንያቱም ለኖክ ብድር ነው የምትሰጡት፣ ለእኛ ግን በካሽ ክፈሉ ትሉናላችሁ። ፍትሐዊ ያልሆነ ውድድር ነው እተካሄደ ያለው። ስለዚህ ለኖክም በካሽ ሽጡና እኛም በካሽ ገዝተን ገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንሁን ብለው ጠይቀዋል። እና መንግሥት እየገባ ነው። እኔንም ጠይቀውኛል።
እኛን በገንዘብ በካሽ ግዙ ቢሉን፣ ከባንክ ገንዘብ እናገኛለን። በየወሩ ሠላሳ ቢሊዮን ነው ለመንግሥት የምንከፍለው። በየሳምንቱ 700 ሚሊዮን ነው የምንከፍለው። ስለዚህ ያንን ለማግኘት ከኪስህ ማውጣት አትችልም፣ የገንዘብ ተቋማትን ነው መጠቀም የምንችለው።
እናም ‹በተመሳሳይ ደረጃ እናስተናግዳችኋለን ካላችሁ፣ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ለሁላችንም የትርፍ ኅዳጉን አስተካክሉ፣ መዝለቅ የቻለ ይዘልቃል› ነው የምንለው።
ብድሩ ከባንክ የሚገኝ ቢሆን ትርፍ ኅዳጉ እና ወለዱ ምን ያህል ይጣጣማል?
አሁን በዓለም አቀፍ ዋጋ ነው የሚሸጡት። ግን የእኛ ተመን በአፍሪካ ዝቅተኛ ነው። አሁን ሲቸገሩ ነው እውነቱን መቀበል የጀመረው፣ መንግሥት። እኛ ስንስፋፋና ኢኮኖሚው ሲያድግ፣ የገበያ ፍላጎት ሲጨምር ማደያዎች መጨመር አለባቸው። አሁን ማደያ ክፈቱ እያሉ እየለመኑን ነው። አሉም አላሉም ግን እኛ አሁንም መዋዕለ ንዋይ እያፈሰስን ነው።
በነገራችን ላይ ኬንያም፣ የመንግሥት ተቋማት በገቢ ንግዱ አይሳተፉም። ኩባንያዎች ናቸው የሚያስገቡት። እኔም ይህን እየለመንኳቸው ነው። እኛ እናስገባ፣ እናንተ ዋጋውን መቆጣጠር ትችላላችሁ።
ይህ አለመሆኑ በእናንተ ላይ ምን ዓይነት ጫና ይኖረዋል?
አያዳክመንም። እነርሱ በትርፍ ኅዳጉን ያስተካክሉ እንጂ፣ ችግር አይኖርም። እንደውም የእኛ አቅም የግል ባንኮችን ያነቃቃቸዋል፤ ብድር ሊሰጡን ይችላሉ።
በየዓመቱ ምን ያህል ነዳጅ ታሰራጫላችሁ?
አሁን የገበያውን 42 በመቶ ነን። አቭዬሽ ከወሰድክ 52 በመቶ ነው የምናቀርበው። የቀረውን ቶታልና ኦይል ሊቢያ ናቸው የሚያቀርቡት። ኹለቱ ተደምረው ነው የእኛን ያህል የሚሆኑት።
እንደ ነዳጅ አከፋፋይ ማኅበራት ፕሬዝዳንትነትዎ ደግሞ፣ በሥራ ላይ ባሉ ኩባንያዎች እና በመንግሥት ተቆጣጣሪ አካል መካከል ጥርት ያለ የተለየ መስመር አይተዋል?
ቁጥጥሩ አካባቢ ችግር አለ። እሱን በተመለከተ ዓለማቀፍ አማካሪ ቀጥረን፣ አስጠንተን፣ አንድ ወጥ መሆን አለበት። ነዳጅን በሚመለከት ቁጥጥር የሚያደርግ አንድ ተቋም ወይም ባለሥልጣን መኖር አለበት፤ ሪፖርትን ለፓርላማ ወይም ቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርብ፤ በኬንያ እንዳለው። አሁን አንድ አካል ፈጥረዋል። ግን ይፋ አልተደረገም።
እስከ አሁን ይህንን ጉዳይ አንደኛ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሊቆጣጠር ይሞክረዋል፣ ኹለተኛ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚስኒቴር ሊቆጣጠረው ይሞክራል። የፋይናንስ ሚኒስቴርም እንደዛው ይሞክራል። እነዚህ አራት ተቋማት የየራሳቸው እጅ በየቦታው አላቸው። እነዚህ አዳዲስ ወደ ሥራው የሚገቡ ሰዎች፣ እዚህ ይሄዳሉ እዛ ይሄዳሉ፣ አሠራሩ ግራ አጋቢ ነው። ለዚህ ነው እኛም ሐሳባችንን ሰጥተን አማክረናቸዋል። በቅርቡም አዲስ የሚፈጠረው አካል ይፋ ይደረጋል፤ ይህም በግልጽነትና በኃላፊነጽ የሚሠራ ባለሥልጣን ይሆናል። ያኔ አንድ ወጥ ይሆናል።
ወደ ኖክ እንምጣ፤ ከእርስዎ ጋር በተገናኘ፣ እርስዎ ብዙ እንደሠሩ ይነገራል። ኖክን ስኬታማ ለማድረግ ያደረጉትና የሠሩት የተለየ ነገር ምንድን ነው?
እኔ ከወጣትነቴ ጀምሮ የማውቀው ስለ ነዳጅ ኢንደስትሪው ነው። አመራ አለ፣ እሴት አለ እና ሰዎች አሉ። ይህ ኢሕአዴግ ስላለው ወይም ሰዎች የተናገሩት አይደለም። ይሄ በሼል ሲስተም የተማርኩት ነው።
አመራር ስንል የሚያሳየው መልካም አስተዳደር የሚለውን ነው። ይህም ተቋሙ ከራሱ ባለድርሻው ጋር ያለው ግንኙነት ነው። ሠራተኛ፣ ደንበኛ ወይም ምርት አቅራቢ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚሠራው በኮንትራት ነው። ፍትሐዊነት፣ ተጠያቂነት፣ የራስን እሴትና የተናገሩትን መኖር ነው። የትኛውንም የእኛንሉሥሪያ ቤት ባልደረቦች ብታናግር ይህን ያውቃሉ፣ ነግረናቸዋልም።
በዚህም በጣም ጥብቅ ቁጥጥር አለ። መልካም አስተዳደር ማለት እሱ ነው። ይህም ተቋምህ ከሌሎች ጋር ያለው ጠቅላላ ግንኙነት ነው።
ሌላው አፈጻጸም ነው። ይህም ተልእኮን የመፈጸም ብቃት ነው። ማንኛውም የምትሠራው ሥራ የተሟላ መሆን አለበት። ማንኛውም አገልግሎት ፈልጎ ወደዚህ ተቋም የሚመጣ ሰው፣ እነዚህ ሰዎች ጥሩ ናቸው ብለው መሄድ መቻል አለባቸው።
የቡድን ሥራም ነው። ሥራ ለብቻው የሚጠናቀቅ አይደል። የራህን ድርሻ የተወሰነ ሠርተህ ታስተላልፋለህ፣ የቡድን ሥራ ነው። በዛ ላይም ደንበኛ ተኮር ነው።
አንዱ ፍልስፍናችን ደግሞ ሠራተኛው ለራሱ ብሎ ድርጅቱን እንዲንከባከብ፣ እኛም ደግሞ ለራሳችን ብለን ሠራተኛውን እንድንንከባከብ ነው። ሥልጠና፣ ብቃትን ማሳደግ አለ። አካታችንም እንደዛው።
ማን ምን እንደሆነ አያገባኝም፣ ብሔር አልጠይቅም። እዚህ የሚቀጠረው አንድ ነገር አምርቶ እሴት የሚጨምር ሲሆን ብቻ ነው። ሌላው አካባቢ ነው። እኛ በምንሠራው ኅብርተሰቡ መጎዳት የለበትም፣ መጠበቅም አለብን። የእነዚህ ነጥቦች ናቸው እንደ አምድ ወይም ምሰሶ ሆነው ያቆሙን።
እኛ በየዓመቱ ግብና እቅድ አለን። በየዓመቱ መጀመሪያ እያንዳንዱ ሠራተኛ ከደሞዙ ጋር የሚያገኘው ደሞዝና ጭማሪ አለ። በዓመቱ ማብቂያና በአዲስ ዓመት መጀመሪያም ሁሉንም በአንድ ላይ አገኛቸዋለሁ። የዓመቱን እቅድ እነግራለሁ። ለቀጣይ ዓመት ካሳኩ ደሞዝ እንደምጨምር ቃል እገባለሁ። ለዛ ነው ኖክ ያደገው። ይህም ከሼል የተዋስኩት ልምድ ነው።
ስለኩባንያው ያለፈው ዐስር ዓመት ሂደት እና ያለፈው በጀት ዓመት የፋይናንስ እንቅስቃሴው ምን ይመስል እንደነበር ቢነግሩን?
በአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፍን ስናይ፣ ስንጀምር በአንድ ቀን 11 ማደያ ነበር የከፈትነው። አሁን 250 አለን። ከ1 ሺሕ በላይ ደንበኞች አሉን፤ አየር መንገዱን ጨምሮ። ወሳኝ የሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይም አለን። ምክንያቱም ሁሌም ሥራ ላይ እንዳሉ እርግጠኛ መሆን ስላለብን።
የሰው ኃይላችን ብዙዎቹ ወጣት ናቸው፤ አብዛኞቹ ከዩኒቨርሲቲ ናቸው። እንዲሁም የንግድ ተቋማት አሉ።
ከእኛ ጋር ተያይዞ ቀጥተኛ ተቀጥረው የሚገኙት 200 ሠራተኞች ናቸው። ነገር ግን ከእኛ ጋር ተያይዞ ያለው ከ20 ሺሕ በላይ ይሆናሉ። 1 ሺሕ የሚሆኑ ቦቴ የሚያመላልሱ አሽከርካሪና ረዳቶች አሉ፣በእያንዳንዱ ማደያ ላይ ሃምሳ ሠራተኞች አሉ። የመኪና ቅባቶችን የሚያሰራጩም አሉ።
ከፍተኛ ግብር ከፋይም ነን። ባለፈው ዓመት 500 ሚሊዮን ነው የከፈልነው፣ ይህም ኮርፖሬት ታክስ ብቻ ነው። 800 ሚሊዮን በላይ በጠቅላላው ስለከፈልን ነው የተሸለምነውም። የተጣራ ትርፋችንም በዚህ ዓመት ቢሊዮን እናተርፋለን ብለን እናሰባለን፣ ግን እንዳሰብነው ላይሆን ይችላል፣ ከባድ ሁኔታዎች ነበሩ። ባለፈው ግን 760 ሚሊዮን ነው የተጣራ ትርፋችን።
ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ከሜድሮክ ጋር ምን ያህል ትደጋገፋላችሁ?
ኖክ ራሱን የቻለ ተቋም ነው። በዚህም ከሜድሮክ ጋር የሚያገናኘን ነገር የለም። ሼክ መሐመድ አሊ አላሙዲ ለእኛ ባለድርሻ ናቸው። እስከ ኖክ በራሱ የቆመ ነበር። በመጀመሪያ የውጪ ምዛሬ የምናገኘው፣ ባሉን የደንበኞች ብዛትና ዓይነት ነው። በዛ መሠረት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ድረስ ጥሩ ምንዛሬ አግኝተናል ብዬ አስባለሁ። የተጎዳን አይደለንም። ወደ ውጪ መላክ ላይም ገብተናል። በራሳችን እንደፈለግነው እንድናድግ ይረዳናል ብለን ስላሰብን፣ ዘንድሮ እንልካለን ብለን አስበናል።
የወደፊት እቅዳችሁ ምንድን ነው?
የእኛ ግብ ኢትዮጵያን መሻገር ነው። በነገራችን ላይ ጅቡቲ ኩባንያ ከፍተናል። ከኢትዮጵያ የባሰ የከፋ አስተዳደር ስላለ፣ እድገት ግን አላሳየንም። አሁን ቀጥሎ ወደ ኬንያ የመሄድ እቅድ አለን። ያን ልናደርግ የምንችለው ነጻ ሆነን፣ ትርፋማ ስንሆን ነው።
ከቴክኖሎጂ አንጻር ነዳጅ ለመቅዳት አዳዲስ አሠራሮች በዓለማችን ተዋውቀዋል። በዚህ ዘርፍ ምን ላይ ደረሳችሁ?
በነገራችን ላይ እሱን በተመለከተ ክሬዲት ካርድ አለን። ልክ እንደ ንግድ ባንክ እንደሚያደርጉት ካርድ ለደንበኞቻችን እንሰጣለን። ገንዘቡን እኛ ጋር ይከፍላሉ፣ ከዛ ከፈለጉት ማደያ ይቀዱበታል። ነጻ ስርዓት ሲኖር፣ ቅድሚያ አገልግሎት መስጠት እንጀምራለን። በሲስተም ደንበኛው በሚቀዳ ጊዜ ከባንክ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ገንዘብ እንዲተላለፍ ማድረግ ይቻላል። ነዳጅ የትም ቦታ ማጣት የለበትም የሚል ነው። ሌላው አገር የሚሆነው ይህ ነው። ይህንንም በቀላል ማድረግ ይቻላል።
የፖለቲካው አለመራጋጋት የንግድ ሥራው ላይ የፈጠረው ተጽእኖ ምንድን ነው?
በጣም ተጎድተናል። በተለይ በምርት አቅራቢው መስመሩ አስቸጋሪ ነበር። ምርት ቶሎና በሰዓቱ አይደርስም። ማደያዎቻችንን እንኳን መቆጣጠር አልቻልንም። ሰዎች እርስ በእርሳቸው ለመነጋገር ፈቃደኛ አልነበሩም። የማይታወቀውን አካል ፍራቻ ነበር። ሰዎች ሕግን በእጃቸው አድርገው ብዙ ጥፋት አድርሰዋል። ከባድ ጊዜ ነበር። መንግሥት አሁንም ሰላምና ደኅንነትን ማረጋገጥ አለበት፣ ኢኮኖሚውንም ለማሻሻል።
ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012