ዳሰሳ ዘማለዳ የካቲት 12/2012

0
610

 

ሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ብድር እያፈላለገ ነው

ሳፋሪ ኮም በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ለማግኘት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር  ለመጣመር እሞከረ ሲሆን ብድርም እያፈላለገ እንደሚገኝ አስታውቋል። ፈቃዱን ለማግኘት ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ሊያስፈልግ ይችላል ያለው ድርጅቱ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተሰማራ ትርፋማ ለመሆን እስከ 10 ዓመታት ድረስ ሊወስድበት እንደሚችል ይፋ አድርጓል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ5 ሺሕ በላይ ሴቶች በማህጸን ጫፍ ካንሰር በሽታ ለህልፈት እንደሚዳረጉ ተገለጸ። በሽታው ይዟቸው ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ታማሚዎቹ ወደ ህክምና ጣቢያ መምጣታቸው የበሽታውን አስከፊነት እንዳባባሰው ተገልጿል። የግንዛቤ ማነስ፣ በዘርፉ ላይ የሚታየው የህክምና እጥረት እንዲሁም ለምርምር ስራዎች በቂ ድጋፍ አለመደረጉ በሽታውን በሚፈለገው መጠን  መከላከል እንዳይቻል ማድረጉ ተጠቅሷል። በየአመቱ 7 ሺህ አዳዲስ ህሙሟን እንሚመዘገቡም ተነግሯል። (ኢዜአ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ የነበሩት የስመኘው በቀለ የመታሰቢያ ሐውልት በዛሬው ዕለት የካቲት 12/2012  ተመረቀ። የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር)፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እና የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር  ሮማን ገብረስላሴ በምርቃት ሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። የሐውልት ምርቃቱ ከኢትዮጵያ የሰማዕታት መታሰቢያ 83ኛ ዓመት ጋር በታላቅ ድምቀት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓት ተከናውኗል። ስመኘው በቀለ ሐምሌ 19 /2010  ጠዋት በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተሽከርካሪያቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ይታወሳል።ሐውልቱ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አማካኝነት የተሰራ ነው።(ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዘድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ጽኑ ህሙማንን ለመቀበል የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ እያጠናቀቀ እንደሚገኝ አስታወቀ። በጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ድንገት ወደ ሀገር ውስጥ ቢገባ በቫይረሱ የተጠቁ ጽኑ ህሙማንን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ የተመረጠው የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዘድ ሆስፒታል የቅድመ ዝግጅት ስራውን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ አስታውቋል።(ኢቲቪ)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

ግምታዊ ዋጋቸው ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን መደሃኒትና የመዋቢያ ምርቶችን በህገወጥ መንገድ ሲጓጓዙ በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረጉን የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ። ቅቤና ማርን ከባእድ ነገሮች ጋር ቀላቅለው ሲሸጡ የተገኙ 13 ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱንና 72 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝ ጠቅሷል።(ኢዜአ)
………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ራይዝ የተሰኘው ፕሮጀክቱ አንድ ሚሊየን ወጣት ጥንዶችን የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ የ20 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ፡፡ በቀጣዮቹ አምሰት ዓመታት በስድስት ክልሎች የሚተገበር አንድ ሚሊየን ወጣት ባለትዳሮችን ለመድረስ ታቅዷል ተብሏል። አማራ፣ኦሮሚያ፣ደቡብ፣አፋር፣ ሶማሊያ እና ትግራይ ክልሎች ደግሞ ፕሮጀክቱ የሚፈጸምባቸው ክልሎች ናቸው ተብሏል።(ኢትዮ ኤፍ ኤም)

………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………..

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የ4 መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን የውል ስምምነት ከተቆራጭ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ተፈራረመ።የተፈረሙት ፕሮጀክቶች የቆሼ- ሚጦ -ወራቤ፣ የጋምቤላ-አቦቦ-ዲማሎት፣ የግሸን መገንጠያ ዲዛይንናበግንባታ እንዲሁም የጎንጂ-ቆለላ (ቆሬ-አዲስ አለም)የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ናቸው ተብሏል።(የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here