‹‹የፌዴራል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሲያውጅ የክልሎችን ሥልጣን ጭምር ማገድ ይችላል››

0
971

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ መንግሥት መደበኛውን ስርአት ተጠቅሞ ሕግ ማስከበር የማይችል ሲሆን፣ ከተወሰኑ መብቶች ውጪ መብቶችን እንዲገድብ ሥልጣን የሚሰጥበት ሂደት ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ያለ ከሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በታወጀ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ እና መፅደቅ ይጠበቅበታል።

ይህ አዋጅ በአብለጫ ድምጽ የሚፀድቅ ሳይሆን በኹለት ሦስተኛ ድምፅ የሚፀድቅ እና ካልሆነ ግን ውድቅ እንደሚደረግ ሕገመንግሥቱ ይደነግጋል። ምክር ቤቱ በእረፍት ላይ ሆኖ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ካወጣ ደግሞ፣ ለተወካዮች ምክር ቤት በ15 ቀናት ውስጥ መቅረብ ይጠበቅበታል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ማኅበረሰቡ ሊወስድ የሚገባቸው እርምጃዎች የሰብዓዊ መብት ገደቦችን የሚያጠቃልሉ ናቸው። ከእነዚህ መካከልም የመሰብሰብ መብት አንዱ ሲሆን ኮቪድ19ኝን ለመከላከል ከሚመከሩት እርምጃዎች መካከልም ማኅበራዊ ጥግግቶችና ቅርርቦችን መቀነስ አንዱ ነው። ታዲያ እነዚህን ስብሰባዎች ለመገደብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ይሆናል፤ ሲሉ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ሚኪያስ በቀለ ይናገራሉ።

ብዙዎች ተሰብስበው አምልኮ እንዳያካሂዱ መከልከል፣ ተሰብስቦ ከሌሎች ጋር የማምለክ የሃይማኖት እና አምልኮ መብት መገደብ ነው የሚሉት ሚኪያስ፣ ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ቦታ እንዲቀመጡም ሆነ ከከተማ እንዳይወጡ መከልከል የነጻነት መብት እና የመዘዋወር መብትን መገደብ ነው ሲሉ ሕጋዊ አንድምታውን ያስረዳሉ። ሰው የሚበዛባቸውን የተለያዩ የንግድ ቦታዎች እንዲዘጉ ማስገደድም የኢኮኖሚ መብትን በሕግ መገደብ ይጠይቃል።

‹‹ስለዚህ ጉዳዩ እያየለ ከመጣ እና የማኅበረሰቡን ሕልውና አደጋ ውስጥ ከከተተ፣ ብሎም ማኅበረሰቡ በሚደረግለት ጥሪ ብቻ የመንግሥትን አቅጣጫዎች የማይፈጽም ከሆነ፣ መብቶቹን በሕግ ማገድ አስፈላጊ ያደርገዋል›› ሲሉ ሚኪያስ ያስረዳሉ። ‹‹መንግሥት የፀጥታ ኃይሉን በመጠቀም መመሪያዎቹን አስገድዶ ለማስፈፀም በሽታውን ለመቆጣጠር ለሚደረጉ የመብት ገደቦች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱ አስፈላጊ ይሆናል።›› ብለዋልም።

ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግሥት ማኅበረሰቡ እርምጃዎቹን እንዲወስድ ‹ጥሪ› ሊያስተላልፍ ይችላል። እንጂ ‹ሊያስገድድ› አይችልም የሚሉት ሚኪያስ፣ የተለመደው የሕግ ስርዓት የተገለጹትን መብቶች ጠብቆ ለችግሩ መፍትሄ ማፈላለግን ይጠይቃል ሲሉ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

ነገር ግን በዓለም ላይ ኮቪድ19ኝን ለመቆጣጠር ከተወሰዱ እርምጃዎች ለመረዳት እንደሚቻው፣ በተለመደው የሕግ ስርዓት እነዚህን የበሽታ መከላከል ሂደቶች ለመተግበር አስቸጋሪ ነው።

ለዚህ ምሳሌ የሚሰጡት ሚኪያስ መመሪያዎቹን አልፈጽምም የሚሉ ግለሰቦችን መንግሥት በቁጥጥር ስር ቢያውል በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት የመውሰድ፣ የእስሩን ምክንያት የማስረዳት፣ በዋስ የመልቀቅ የሚሉ መብቶች ይመጣሉ። ስለዚህ ይህ በአስቸኳይ አዋጅ የመንግሥትን ኃላፊነት፣ አቅጣጫዎቹን ለማይፈጸሙ ሰዎች መንግሥት የሚወስደው እርምጃ፣ የሚጣለው ቅጣት እና የመሳሰሉትን መለየት ያስፈልጋል።

በጤና ምክንያት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልልም ሊታወጅ እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ የሚደነግግ ሲሆን፣ የትግራይ ክልልም ቀዳሚውን እርምጃ ወስዷል። መጋቢት 17/2012 የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ ኹለት ሳምንት የሆነው የኮሮና ቫይረስን ተከተሎ፣ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ታስቦ የተደረገ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገብረ ሚካኤል ይፋ ያደረጓቸው የመብት ገደቦች በተለይም ከቦታ ቦታ መዘዋወርን የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ ይህም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ያጠቃልላል። የመሰብሰብ መብትን በተመለከተም ለቅሶ፣ ተዝካር እና የሕዝብ ገበያን የሚከለክል ሲሆን፣ ይህንንም መንግሥት ተከታትሎ እንደሚያስፈፅም አስታውቋል።

የክልሉ ሕገ መንግሥት መሰረትም ይህ የክልሉ ሥራ አስፈፃሚ የሚወጣው አዋጅ የክልሉ ምክር ቤት እንዲያፀድቀው ያስገድዳል። በዚህ መሠረትም ነው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ ለ15 ቀን በክልሉ ውስጥ የሚደረጉ ጉዞዎችን ጨምሮ እገዳዎቹን ያስተላለፈው።

በፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ታሪክ በጤና ምክንያት የታወጀ የመጀመሪያው የክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲሆን፣ በፌዴራል ደረጃም ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች በፀጥታ ችግር እንጂ በጤና ምክንያት አልታወጁም። በክልልም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች መቆየት የሚችሉት ቢበዛ ለስድስት ወር ብቻ ሲሆን፣ ማረዘም ቢያስፈልግ ወደ ምክር ቤት በማምጣት ማፀደቅ ያስፈልጋል።

ታዲያ እነዚህን አዳዲስ ሁነቶች ክግምት ውስጥ በማስገባት በሕገ መንግሥት ጥናት እና ምርምር ልምድ ያካበቱትን አደም ከበደ (ዶ/ር) አዲስ ማለዳ አነጋግራቸዋለች። አደም የሕግ ባለሞያ ሲሆኑ በተለይም በሕገ መንግሥት እና በምርጫ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትንታኔዎችን ይሰጣሉ። መሰረቱን ሆላንድ ሄግ ያደረገው የኮንስትትዩሽን-ኔት አርታኢም ናቸው። ከኢትዮጵያ ባለፈም በምሥራቅ አፍሪካ የፌዴረላዚም፣ የፖለቲካ እና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚሰጡት አደም፣ ከአዲስ ማለዳዋ ሐይማኖት አሸናፊ ጋር በኮሮና ቫይረስ እና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ የተወሰነ ቆይታ አድርገዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ፣ በመደበኛ የሕግ አሠራርን ተጠቅሞ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ነን ማለት ይቻላል?
መደበኛ ከሚባለው ውጪ የሆኑ እርምጃዎች እኮ እየተወሰዱ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ ንግድ ቤቶች እንዲዘጉ፤ ከሌላ አገር የሚመጡ ሰዎች በተለየ ስፍራ ተነጥለው እንዲቀመጡ እየተደረጉ ነው። መሰል ብዙና የተለያዩ እርምጃዎች በፌዴራል ደረጃ ተወስደዋል። እነዚህ ሁሉ ከመደበኛው የሕግ ስርአት ውጪ የሆኑ ናቸው።
የፌዴራል መንግሥት እስከ አሁን ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳያውጅ በተለይ መብቶችን መገደብ ላይ ያለው ሥልጣንና ሕጋዊነትን በተመለከተ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የተለዩ ስለሆኑ አስቀድሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት ነበረበት። መንግሥት ግን ወደዛ መግባት አልፈለገም።

ሁሉም ሰው ይግባባል በሚል ሒሳብ አልያም የሚቃወመው የለም በሚል መረዳት እየተንቀሳቀስ ያለ ይመስላል። በሕግ መሠረት መንግስት ከፈለገና ከሁኔታው አንጻር እርምጃ መውሰድ ይችላል። በሌሎች የኮቪድ19 ወረርሺኝ በተስፋፋባቸው አገራትም ተመሳሳይ አሠራሮች አሉ። ከዚህ በኋላ የሚመጣውንም ስለማናውቅ ሁኔታዎችን አስቀድ ማመቻቸት የተሻለ ነው።

የትግራይ ክልል በክልል ደረጃ ምክር ቤቱ ያጸደቀውን ወስደዋል። በክልሉ ያለውን ትራንስፖርት አግደዋል፣ በመገበያያዎችና በመሳሰሉ ስፍራዎች የሚኖረውን መሰብሰብ ቀንሰዋል። እና እነርሱ እርምጃ ወስደዋል ማለት ነው። ይህም መብታቸው ነው፤ ሕገ መንግሥቱም ይፈቅዳል።

የፌዴራል መንግሥት ግን ምንአልባት ተቃውሞ አይኖርም በሚል ሐሳብ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው። ከዚህ በኋላ ግን አጠናክሮ እርምጃ የሚወስድ ከሆነ፣ ለምሳሌ ቤተእምነቶችን የሚዘጋና መሰል እርምጃዎችን የሚወስድ ከሆነ፣ ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እወስዳለሁ ቢል፣ ሕጋዊነቱ ላይ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል።

የትግራይ ክልል ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁን ባለው ሕገመንግሥት መሰረት ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ፣ በጤና ምክንያት በክልል ደረጃ የታወጀ የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው ማለት ነው?
ወደኋላ ተመልሰን ስናይ ጋምቤላ እንዲሁም ቤኒሻንጉል ክልል በነበረ ያለመረጋጋትና ችግር የፌዴራል መንግሥት እርምጃዎች ሲወስድ ነበር። በእርግጠኝነት ግን ከጤና ጋር በተያያዘ ይህ የመጀመሪያ ነው።

በክልል ደረጃ በጤና ዙሪያ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይት ውሳኔ አልተወሰነም። በፌዴራል መንግሥትም ከተወሰነና ውሳኔው መጠናከር አለብን ብለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያውጁ ከሆነ፣ በጤና ምክንያት የመጀመሪያው ነው የሚሆነው፤ ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ጀምሮ።

በተያያዘ በጤና ጉዳይ የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በጸጥታ ምክንያት ከሚታወጀው ጋር በተለየ የሚታይበት የሕግ አግባብ አለ?
የማወጁ ስርዓት፣ ሁሉም አንድ ዓይነት ነው። ምክንያቱ ሳይሆን አዋጁ መሠረት ያደረገበት አካሄድ ማለት ነው። ምክንያቱ ግን ጸጥታ ወይም የጤና ጉዳይ ሊሆን ይችላል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ያንን በ15 ቀን ውስጥ ማጽደቅ አለበት እንጂ ልዩነት የለውም። ልዩነት የሚኖረው ያንን ለማስፈጸም በሚደረገው እርምጃ ነው። ለምሳሌ የሚገደቡት የመብት ዓይነቶች ግን ሊለያዩ ይችላሉ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሕግ ሳይሆን በአስፈጻሚ አካል ውሳኔ ነው አንዳንድ መብቶችን ሊገድብ የሚችለው። አሁን ያሉት እርምጃዎች በጣም ከባድ ባይሆንም መብትን ሊወስኑ የሚችሉ ናቸው። ከዚህ በኋላ ግን ጠንካራ እርምጃ የሚወሰድ ከሆነ፣ በተለይ የእምነት ተቋማትን የሚነካ ከሆነ፣ አዋጁን ማወጅ ሊያስፈልግ ይችላል። ከዛ በኋላ እንደ ሁኔታው የሚያስፈልገው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በአስፈጻሚው አካል ሊገደብ ይችላል። እንጂ አካሄዱና ስነስርዓቱ አንድ ዓይነት ነው።

እኛ አገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲባል ፍርሃት አለ። የማወጁን ጥቅምና ጉዳት ስናሰላ፣ የበለጠ ለሌሎች የመብት ጥሰቶች የሚገፋፋ ይሆናል ብሎ ማሰብ ይቻላል?
በሕዝቡ ዘንድ ያለው ፍራቻ ግልጽ ነው። ከዚህ በፊት እርምጃ የሚወሰደው ወይም ሕግ የሚከለክለውን በማድረግ ነው። እንዳንዴ በቂ ምክንያት ሳይኖር በማወጅ እርምጃ መውሰድ አለ። በዚህም ምክንያት ያለመተማመን ተፈጥሯል። ከዛም አንጻር ያንን በማገናዘብ ይመስለኛል መንግሥትም አሁን አዋጁን ለማወጅ ያልፈቀደው።
ነገር ግን አሁን ደግሞ ያለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተወሰደ ያለው እርምጃም ከሕግ ውጪ ነው። ከዚህ በፊት የነበረ የሕግ ጥሰትን አሁንም እንደገና ሕግን በመጣስ ማስተካከል አይቻልም። በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው እምነት በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም። በሂደት የሚመጣ እንጂ።

ለመንግሥትም ጥሩ ሁኔታ ነው። በእርግጥ ፍርቻው ቢኖርም አሁን ሕዝብም ተቀብሏል፤ የአዋጅ መታወጅ የሚከፍተው ነገር አለ። በእኔ እምነት ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የተለየ ነገር ያመጣል ብዬ አላስብም። በወረርሽኙ ምክንያት መብት የሚጣስ ከሆነ መጣሳቸው አይቀርም። ቢያንስ ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ቢሆን የተሻለ ነው።

ምርጫ ተቃርቧል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲመጣ ደግሞ ብዙ የሚስቀራቸውና የሚገድባቸው መብቶች አሉ። ይህ አዋጅ እንደ አጋጣሚ ተጠቅሞ ሌሎች መብቶች ላይ ተጽእኖ እንዳይኖርና የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ምን መደረግ አለበት?
ከምርጫው ጋር በተያዘ ምን ማድረግ ይቻላል መሰለሽ መንግሥት እርምጃዎችን በሚወስድበት ጊዜ ተጠያቂነት ሊኖረው ይገባል። በሕጉ መሠረት ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የሚቋቋም ኮሚቴ አለ። አካሄዱን የሚመረምር ቡድን እንደሚቋቋምም በሕጉ ተቀምጧል። ይህም ፓርላማው ሲያጸድቅ አብሮ የሚቋቋም ነው። ይህ የሲቪል ማኅበራትን ጨምሮ ሁሉንም የሚያካትት ከሆነ፣ ከጤና ውጪ አልፎ ሌላውን እንዳይካ ማድረግ ይቻላል።

ይህ ሁሉ የሚገናኘው ከዚህ በፊት ካለን ልምድና ፍራቻ ጋር ሲሆን የሚቋቋመው ቦርድ እንዳልኩት በመንግሥት ደረጃ ሁሉን ያካተተ መሆን አለበት። እንደውም አዋጁ በመደበኛ መንገድ አለመታወጁ ሊቆጣጠራቸው የሚችል አካል እንዳይኖር ያደርጋል። እና የሚቋቋመው መርማሪ ቦርድ ሁሉንም የሚያካትት ከሆነ፣ ጥሰቶችን ሊቀንስ ይችላል። ምርጫ ቦርድም በአትኩሮት እየተከታተል፣ ይገናኛል ወይ የሚለውን ማየት ነው። ፍርድ ቤቶችም አሉ፤ አዋጁን አካሄድ ሊከታተሉ የሚከታተሉ።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ችግሮችን ሊፈታ ይችላል እንዲሁም ሊፈጥርም ይችላል። አሁን የታሰበለትን ችግር እንዲፈታና አዳዲስ ችግር ግን እንዳይፈጥ በሚቋቋመው ቦርድም፣ በሲቪል ማኅበራትም፣ በሚድያም በኩል መከታተል ያስፈልጋል። ግን ያለአግባብ መጠቀም ሊኖር ይችላል በሚል እሳቤ አለማወጅ፣ ያለ አዋጅ መብቶች እንዲረገጡ ማድረግ ነው። ያ ደግሞ በራሱ ሕገ መንግሥትን የሚጥስ ይሆናል። የድሮውን ዓይነት አካሄድ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሳለ ሳያውጁ መብትን ማገድ ያው የድሮውን የመብት መጣስ ሂደት የሚቀጥል ነው የሚሆነው።

በሕይወት የመኖር መብት ጋር በተገናኘ፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሕዝብ በድህነትና ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ሕይወት ውስጥ የሚኖርባት አገር ናት። አሁን ያለንበት ሁኔታም በሕይወት የመኖር መብት ድረስ ሊሄድ ይችላል። መጽሐፉና ሕጉ ከሚለው በላይ ሰዋዊ ነገሮች አሉና፣ እንዴት ነው እነዚህን መብቶች የምናቻችለው?
ይሄ ከታወጀ በኋላ የሚወሰድ እርምጃ ነው። ለምሳሌ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ገጠር ነው የሚኖረው። በአዋጁ ሁሉን ማካተት አያስፈልግም። በዋነኛነት የሚጎዱት ትልልቅ ከተሞች ናቸው፤ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ። እንደ መንግሥት ገቢን የሚያቆም ውሳኔ ነው። እንቅስቃሴ ከተገታ አብዛኛው ሰው ገቢ ያንሰዋል። አማራጭ ነገሮች መኖር አለባቸው።

መንግሥት እርምጃ ካልወሰደ ደግሞ የጤና መብትም እኮ ከሕይወት ጋር የሚገናኝ ነው። ሲወስድ ደግሞ አንዳንድ ሰዎችን ገቢና ምግብ የማግኘት መብቶችን ይገድባል። እንዴት እናመዛዝን ደግሞ እንዳልኩት አካባቢያዊ መጠኑን በተቻለ መጠን መቀነስ ነው። መንግሥት በራሱና ካለው ሁኔታም አቅሙ በሚፈቅደው መጠን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ሲቪክ ማኅበራትን በማስተባበር እርዳታ ማሰባሰብ ነው።

ግን በጣም ከባድ ውሳኔ ነው። እርምጃውን ባወሰድ የሕዝብን ጤና አደጋ ውስጥ ይጥላል። ሲወሰድም በጥንቃቄ መሆን አለበት። ጎዶሎው እየተሞላና በመንግሥት በጀት እንዲሁም በጎ አዳራጊዎችን በማስተባበር ጉዳቱ መቀነስ አለበት። ከባድ ሁኔታ ነው ያለው። እርምጃ መወሰድ አለበት። ውጤቱም የሚያስከትለውን ችግሩን መቀነስ ነው። እንጂ አሁን ባለበት ሁኔታ በጸሎት ብቻ የምንድንበት አይደለም፤ አንዳንድ ዋና ዋና እርምጃ መወሰድ አለበት። በተለይ በተቻለ መጠን መቀነስ ነው። ከአካባቢ አንጻር አዲስ አበባ ዋና ዋናዎቹ ላይ ሆኖ፣ ሌላው ላይ እንደ ሁኔታው በሂደት እያዩና እያስተካከሉ መሄድ ይሻላል እላለሁ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ቢሆን የማይገደቡ መብቶች አሉ። ሌሎች አገራት ላይ አዋጁን ጥሰው የተገኙ ሰዎች የሚያዙበት ሁኔታ ስንከታተል ከባድ ቅጣቶችን ተመልክተናል። እሱን አይተን እንዴት ነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይጣሱት እንደ አንቀፅ 18 እና 25 ካሉት መብቶች ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል የጸጥታ ኃይል እንዲኖረን ማድረግ የሚቻለው?
እንኳን አስፈላጊ በሆነበት፣ ባልሆነበትም ሰዓት ጭካኔና ያለ አግባብ እስራቶች በአገራችን የፀጥታ አስከባሪዎች ዘንድ መቼም የተለመደ ነወው ብንል ማጋነን አይሆንም። ይህ የተቋማት ታሪካዊ ችግር ነው። የልምምድ፣ ማኅበራዊ ባህልና የአስተሳሰብም ጉዳይ ነው። እናም በረጅም ጊዜ የሚፈታ እንጂ አሁን በቶሎ የሚስተካከል አይደለም። በተለይ በዋና ከተማ በሽታው ሚስፋፋ ከሆነና የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጆ መብቶች የሚገደቡ ከሆነ፣ በምክር ቤቱ ተቋቁሞ የአዋጁን አፈፃፀም የሚመረምርና የሚከታተለው ቦርድ ትክክለኛ መመሪያ በማዘጋጀት ሁሉም ሰው የሚግባባበት ለተጠያቂነት የሚያመች ሁኔታን በተቻለ መፍጠር ነው።

ነገር ግን አንገብጋቢ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈጣን ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል። ይህም ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት። ዋናው ግን መመሪያ አውጥቶ በዛ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ነው። መመሪያውንና አቅጣጫውንም የሚያስፈጽሙ አካላት እንዲያውቁት ማድረግ ደግሞ ሌላው የቤት ስራ ነው። ሕጸጾች አይኖሩም ማለቴ ግን አይደለም፤ ይኖራሉ።

አዋጁ ያስፈልጋል ተብሎ ከታመነና ሁኔታው የሚፈቅድ ከሆነ እርምጃ ቢወሰድ ይሻላል። ከተወሰደ በኋላም ያለውን ችግር እንዲፈታ፣ አዳዲስ ችግር እንዳይፈጥር በሚወጣ መመሪያ መሠረት በመናበብና በኃላፊነት መንቀሳቀስ እጅግ ጠቃሚ ነው። ሲቪክ ማኅበራት፣ ምርጫ ቦርድና ሁሉም በዋናነት ከሚቆጣጠረው ጋር አብረው የሚከታተሉበትን ሁኔታ መፍጠር ነው የተሻለ ብዬ አስባለሁ።

የምርጫ ሕጎች ተንታኝ እንደመሆንዎ እና የምርጫ 2012 ሂደቶችን በቅርበት ሲከታተል እንደነበር ሰው፣ መጪው ምርጫ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚራዘም ይመስልዎታል?
እንደሚታወቀው ብዙ ግፊት አለ፤ በተለይ ከተቃዋሚ ፖርቲዎች። የክረምት ጊዜ ነው፣ ለመንቀሳቀስ የሚከብድ ሁኔታ ነው ሲሉ ነበር። ወረርሽኙ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ፣ ከቀደሙት ጋር ተደማምሮ ማራዘሙ ሊያስፈልግ ይችላል። ዋናው ይህ ነገር ምን ያህል ይቀጥላል ነው።

ለእኔ ከዚህኛው በላይ እንደውም መሃል ክረምት ላይ መሆኑ በራሱ ምክንያት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። መንግሥት ሕጉን መከተል አለብኝ ሲል ነበር፣ ይህ ምንአልባት ሌላ ምክንያት ሊሰጠው ይችላል። ይህ ደግሞ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ፣ ኹለት ነው ሦስት ሳምንት ወይም ኹለትና ሦስት ወር ነው የሚቆየው የሚለውን ማወቅ አንችልም። ይህ ነገር ከቀጠለ ግን ተደማምሮ በምርጫው ቀነ ገደብ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ አይቀርም።

ምርጫው ይካሄዳል እያለ ያለው መንግሥት ነው። ተቃዋሚዎች አሁን አይፈልጉም። ሕጉ አንድ መንግስት ከተመረጠ በኋላ በስልጣን ላይ ሊቆይ የሚችለው አምስት ዓመት ነው ቢልም በስምምነት ከሆነ፣ በተለይ ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ ለማርዘም ይቻላል። በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወቅት የመምረጥ እና የመመረጥ መብቶች ሊገደቡ ይችላሉ። እና ሁኔታው አጠቃላይ ሁኔታው ከፈቀደ ማራዘም ይቻላል።

ከዛ በላይ ከሁኔታው አንጻር ብቻ ሳይሆን ለተዓማኒነቱ፣ ተፎካካሪነት ግልጽነቱ የሚሻለው ቢራዘም ያለው ጥቅም ይሻላል ባይ ነኝ። መንግሥትም ‹‹ለበሽታው ብዬ ነው እንጂ በተቃዋሚዎች ግፊት አይደለም ምርጫውን የገፋሁት›› ብሎ ራሱን ሊከላከል ይችላል ብዬ ጠብቃለሁ፤ እንደ አገር ጥቅም ግን ምርጫው ከዛ በኋላ ቢሆን የተሻለ ነው።

እንደዛ የሚሆን ከሆነ፣ የሽግግር መንግሥት እንጠብቅ ወይስ ያለው ፓርላማ ነው የሚቀጥለው?
ምርጫው ቢራዘም ያለው መንግሥት ይቀጥላል። ግን ወሳኝ የሚባሉ የፖሊሲ ለውጦች፣ ዋና ዋና ሕጎችንና መሰል ወሳኝ ውሳኔዎችን ማጽደቅ አይችልም። አዳዲስ ፖሊሲዎችን ሳያወጣ እንደ አስፈጻሚ አካል፣ የወጡ ነገሮችን እያስፈጸመ የሚያስቀጥል መንግሥት ይሆናል፤ ያው ባላደራ እንደሚባለው ማለት ነው።

የሽግግር መንግሥት፤ አሁም ያለው መንግሥት እንዲቋቋም ይፈልጋል ብዬ አላምንም። በሕግም ደረጃ ሕገ መንግሥታችን ይህን ሁኔታ በግልጽ አያስቀምጠውም። ሆኖም በሌሎች አገራትም እንዳለው ልምድ ከሆነ እንዲህ ያለ ሁኔታ ከተፈጠረና ምርጫ መራዘም ካለበት፣ ያለው መንግሥት ይቀጥላል። ነገር ግን እንዳልኩሽ ሊለወጡ የሚችሉ ሕጎችና ፖሊሲዎችን ማውጣት ሳይሆን ማስፈጸም ላይ እየሠራ ይቀጥላል።

በክልልና በፌዴራል መንግሥት በየራሳቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው የሚፈጥረው ምን አዲስ የሕግ ክርክር ይኖራል? ደግሞ ክልልም ፌዴራል መንግሥቱም በተመሳሳይ ጊዜ በተመሳሳይ አደጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጁ የማን ይፀናል?
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንጻር፣ ለምሳሌ የትግራይ ክልል የወሰደው እርምጃ አለ፤ ሌሎች ክልሎችም ሊወስዱ ይችላሉ። አሁን አዲስ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው የሚተባበሩት የሚለው ነው። የፌዴራል መንግሥቱ ይሄ ነገር የማያስፈልግ ነው ቢል ወይም ለምሳሌ ትግራይ ክልል ወደ መቀሌ በረራ አይኖርም ቢል፣ እንዴት ነው የሚሆነው? የሚለውና ሌሎች አዳዲስ ጥያቄዎችን ይፈጥራል።

ከዚህ ቀደም በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በገዢው ፓርቲ መዋቅር ነበር የሚንቀሳቀሰው። አሁን ያ ነገር ተቀይሯል። ከፓርቲው ውጪ የሆነ መንግሥታትን (የክልል እና የፌዴራል) እያገናኘ የሚያነጋግር አካል ያስፈልጋል። ይህም አዲስ ጉዳይ ሊፈጥር ይችላል። በዚህ ላይ ሕግና ፖሊሲ ይወጣል ቢባልም እስከ አሁን የወጣ ነገር አላየንም። እንዲህ ያሉ የተለያዩ ውሳኔዎች ሲመጡ ግን ከፓርቲው ውጪ ያለ፣ ስርዓት ያለው ተቋም ያስፈልገናል። መንግሥታት እየተነጋገሩ መግባባት ሊፈጥሩበት የሚያስችላቸው መንገድ መኖር አለበት።

ይህን ገለልተኛ መድረክ የመፍጠር ሚናን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊወጣ አይችልም?
ለጊዜው ይችላል፤ ነገር ግን ይህ በምክር ቤት ሳይሆን የአስፈጻሚ አካላት መሪዎችን የሚያካትት ፤ ቶሎ ቶሎ ውሳኔ መሰጠት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ምክር ቤቱ አንድ ጊዜ ይፈቅዳል እንጂ፣ ዋናው እንቅስቃሴ እርምጃ ቶሎ ቶሎ መወሰድ ነው። አሁን ላይ ተመልክተሸ ከሆነ በክልሎቹ መካከል በቋሚነት ብዙ ንግግር አይደረግም፣ ፈጣን ምላሽ የሚፈልግ ስለሚሆን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ማድረግ ይከብዳል።

ብዙ አገራት፣ የክልልና የፌዴራል መንግሥት የሚመሩ አካላትን በቋሚነት በመገናኘት የሚነጋገሩበትና የሚወያዩበት አሠራርና አውድ አላቸው። እኛም አገር ቀድም ይህን የተመለከተ መመሪያ ይወጣል ተብሎ ነበር፤ ግን አልሆነም። የትግራይ ክልል ሕገ መንግሥቱ ለይ ያልተጻፈ መደረግ የለበትም እያለ ሲቃወም ነበር። በዛም ምክንያት ይሆናል የቀረ ይመስለኛል።

ግን ከዛም ውጪ ቢሆን በሕግም ባይሆን፣ በመሰባሰብ መነጋገር ይኖርባቸዋል። በተለይ በክልል ደረጃ የፌዴራል መንግሥቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅና፣ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ መሰባሰብ አይቻልም ቢባል፣ የፌዴራል መንግሥት ሁሉም ቦታ የማስፈጸም እቅም የለውም። የክልሎችን ፖሊስና አስፈጻሚ አካላት መጠቀም አለበት። ያንን ማስተባበር ያስፈልጋል። እናም እንደ ፓርቲ አባል ሳይሆን እንደ ክልልና ፌዴራል መንግሥት መሪ፣ የሚነጋገሩበት አውድ ያስፈልጋል።

የክልል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እያለ የፌዴራል ሲታወጅና መደራረብ ሲፈጠር፣ የትኛው ነው የበለጠ ኃይል የሚኖረው የምትለዋን አይተን እናብቃ?
እሺ፤ ሕገ መንግሥቱ ለክልሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጁ የሚፈቅድላቸው የተፈጥሮ አደጋ እና የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል ችግር ሲያጋጥማቸው ብቻ ነው። በርግጥም ሊቃረን የሚችልበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ አስቀድሞ እንዳልነው የትግራይ ክልል እንቅስቃሴ ተገትቷል። ለምሳሌ በረራዎች ወደ ትግራይ አይገቡም ወይም ከሌሎች ክልሎች ባሶች አይመጡም ቢል፣ የፌዴራል መንግሥት አይሆንም ሊል ይችላል። በዚህ ሊጋጩ ይችላሉ። ሕገ መንግሥቱ ላይም የተጻፈ ነገር የለም።

እንደ መርህ ግን፣ የፌዴራል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሲያውጅ፣ ማንኛውንም መብት መገደብ ይችላል። ከዚህ ውስጥ አንዱ የክልሎችን ሥልጣን ነው። ሕገመንግሥት ላይ የማይገደቡ መብቶች ከተባሉት አንቀፅ አንድ፣ 18 እና 25 ውጪ ያሉት በሙሉ ይታገዳሉ። ስለዚህ መደራረቡ ይኖራል። ነገር ግን ከሕግ በላይ አብሮ የመሥራትና የመናበብ ነገር ቅድሚያ ቢሰጠው ጥሩ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 73 መጋቢት 19 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here