ኢትዮጵያ፣ ሚዲያና ዴሞክራሲ

0
1167

መገናኛ ብዙኀን መንግሥትን ተጠያቂ ከማድረግ ጎን ለጎን በአንድ አገር ውስጥ ለሚደረጉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውይይቶች መድረክ የሚፈጥር እንዲሁም ሦስቱ የመንግሥት አካላት እርስ በእርስም ሆነ በተናጠል የሚሠሩት ሥራ ግልጽነት እንዲኖረው የሚያደርግ የዴሞክራሲ መሣሪያ ነው። እነዚህ የዴሞክራሲ መሣሪያ የተባሉ ተቋማት ታድያ የየራሳቸው ርዕዮተ ዓለማዊ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል የሚሉት ኤፍሬም ማዴቦ፣ ሆኖም በሚሠሩት ሥራ ሁሉ ሊዘነጉት የማይገባ ያሏቸውን ወሳኝ ነጥቦች ዘርዝረዋል። ያለሚድያ የዴሞክራሲ ግንባታ አይታሰብም ሲሉም፣ የኢትዮጵያ ሚድያ ዋና ዋና ችግሮችን አንስተዋል።

‹‹ጋዜጣ ሳይኖር መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ ከመኖርና ጋዜጣ ኖሮ መንግሥት በሌለበት አገር ውስጥ ከመኖር የቱን ትመርጣለህ ብትሉኝ፣ ምርጫዬ ያለምንም ጥርጥር ጋዜጣ ኖሮ መንግሥት በሌለበት አገር ውስጥ መኖር ነው››

ቶማስ ጃፈርሰን
ሊብራል ዴሞክራሲን ተወዳጅ ካደረጉት ውስጥ አንዱና ትልቁ፣ መንግሥት የሚባለው ግዙፍ አካል የሕግ አስፈጻሚ፣ የሕግ አውጪና የሕግ ተርጓሚ አካል ተብሎ አንዱ ሌላውን ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ መቆጣጠር እንዲችል ተደርጎ መዋቀር አለበት የሚለው ቁልፍና መረታዊ መርህ ነው።

እነዚህ ሦስት አካላት እንዴት ሥራቸውን እንደሚሠሩና ምን እንደሚሠሩ ሕዝብ መረጃ ማግኘት አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ ከምርጫ ጀምሮ እስከ መንግሥት ምሥረታ ድረስና ከዚያም በኋላ ባለው ዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥም ሕዝብ ተሳትፎ ማድረግ አለበት። እነዚህን ኹለት ሥራዎች ማለትም ለሕዝብ መረጃ በማቅረብና ሕዝብ በአገሩ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው በማድረግ፣ የመገናኛ ብዙኀንን ወይም የሚድያን ያክል ሚና የሚጫወት ሌላ ተቋም የለም። ለዚህ ነው ቶማስ ጃፈርሰን ሜዲያ በሌለበት አገር መኖር አልፈልግም ያሉት!

ሚድያ መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ፣ በአካባቢና በብሔራዊ ደረጃ ለሚደረጉ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውይይቶች መድረክ በመፍጠር ሦስቱ የመንግሥት አካላት እርስ በእርስም ሆነ በተናጠል የሚሠሩት ሥራ ግልጽነት እንዲኖረው የሚያደርግ የዴሞክራሲ መሣሪያ ነው። ይህ መሣሪያነቱ ነው ከሦስቱ የመንግሥት አካላት ጎን አራተኛው አካል (The Fourth Estate) ያሰኘው። ሚድያና ዴሞክራሲ የሚደጋገፉና አንዱ ያለሌላው በነጻነት መኖር የማይችሉ፣ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ናቸው።

ሚድያ ምን ማለት ነው?
ሚድያ ወይም መገናኛ ብዙኀን ሲባል ጋዜጣ፣ መጽሔት፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ ድረ ገጽና ማኅበራዊ ሚድያ ይጠቀሳሉ። በጥቅሉ ሚድያ ማለት መረጃዎችን የሚሰበስብ፣ የሚያጠራቅም፣ የሚተነትን እና የሚያሰራጭ ተቋም ነው። ሚድያ አንድን መረጃ ተሰብስቦ ከተከማቸበት ቦታ ወደ ተጠቃሚው የሚያደርስም ተቋም ነው።

በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ በተለያየ ደረጃ ውሳኔ የሚወስኑ አካላት መረጃ እንዲለዋወጡ በማድረግ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በመረጃ ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ የሚያስችልም ተቋም ነው። በማኅበረሰብ ውስጥ ግልፅነት እንዲኖር ከማድረጉ በተጨማሪ ሙስናን ያጋልጣል፣ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል፣ ያስተምራል፣ ይቀሰቅሳል፣ያዝናናል፣ ወዘተ።

ሚድያ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ መንደር ውስጥ መኖር ያለበት የሕዝብ ዐይን፣ አንደበትና ጆሮ ነው። ሆኖም ግን ሚድያ የሕዝብ ዐይንና ጆሮ የሚሆነው በመጀመሪያ እሱ ራሱ ለማየትና ለመስማት ነፃነት ሲኖረውና ያየውንና የሰማውን በነፃነት የሚናገር አፍ ሲኖረው ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዐይንና ጆሮ ያለው ሚድያ አለ?
ኢትዮጵያ በታሪኳ ነጻ ፕሬስን የመሰለ የዴሞክራሲ ዋስትና ኖሯት አያውቅም። ኢትዮጵያን የመሩ መንግሥታት ሁሉ ነጻ ሚድያ ሲባል ሐሳቡ ራሱ የሚያንገፈግፋቸው ፈላጭ ቆራጭ መንግሥትታት ነበሩ። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ገነባሁ የሚለን የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝም ቢሆን የአገሪቱን ዋና ዋና የሚድያ ተቋማት በባለቤትነት የተቆጣጠረና ከራሱ ፕሮፓጋንዳ ውጭ ሕዝብ ሌላ ምንም አማራጭ እንዳይኖረው ያደረገ ፀረ-ሚድያ አገዛዝ ነበር።

የዘመናዊቱ ኢትዮጵያ መንግሥታት ሁሉ ፀረ-ሚድያ መንግሥታት በመሆናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚድያ ባህልና ክህሎት አልዳበረም። በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥታት ሚድያን በንብረትነት ይዘው የራሳቸው አገልጋይ ስላደረጉት የኢትዮጵያ ሚድያ የማኅበረሰቡ አገልጋይ ሆኖ አያውቅም። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ሜዲያ የእነዚህ መንታ ችግሮች ውጤት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚድያ ነጻነት አድጓል የሚል ዜና በተደጋጋሚ ይደመጣል። በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሚድያው ከዚህ በፊት የማይላቸውን ነገሮች ማለት ጀምሯል። ነገር ግን ሚድያ ነጻ ነው የሚባለው ትናንት ማለት የማይችለውን ዛሬ ማለት ስለቻለ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ሚድያው ነጻ ነው የሚባለው የአገሪቱን የሚድያ ሕግ ተከትሎ የሜዲያ ተቋሙ ራሱ በቀረጸው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ እየተመራ ከወገናዊነትና መንግሥትን ጨምሮ ከማንም ተፅዕኖ ነጻ ሆኖ፣ ማኅበረሰቡን ማገልገል ሲችል ብቻ ነው።

የሜዲያ ሕግ ሲባል ግን የሚድያን ነጻነት የሚያንቅ ሕግ ሳይሆን ይልቁንም በነጻነት ‹ነጻነት›ን እንዲሰብክ የሚያበረታታ ሕግ ማለት ነው። እንዲህ አይነት የሜዲያ ተቋም ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ የለም።

ሚድያ ከማንም ጋር የማይወግን የሕዝብ አገልጋይ ነው ሲባል የተቋቋመለት ዓላማ ወይም መርህ የለውም ማለት አይደለም። በዓለም ላይ ከምንም ጋር የማይወግን ሚድያ የለም፣ ሊኖርም አይችልም። ዛሬ በየትኛውም አገር የሚገኙ ሚድያዎች ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ዝንባሌ አላቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ነጻ ሚድያዎች የሰብዓዊ መብት፣ የፍትህ፣ የነጻነትና የዴሞክራሲ ተሟጋቾች ናቸው። ሚድያዎች የየራሳቸው ርዕዮተ ዓለማዊ ዝንባሌ ሊኖራቸው ይችላል፣ ሆኖም በሚሠሩት ሥራ ሁሉ ከዚህ የሚከተሉትን ነጥቦች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው ፡-

• የሚድያ ሥራ መንግሥትን ማገልገል ሳይሆን መንግሥትን ተጠያቂ ማድረግ ነው፤
• ሚድያ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እይታዎችንና አመለካከቶችን ከወገናዊነት በጸዳና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማቅረብ አለበት፤
• የአገርን አንድነት የሚጎዳና የግለሰቦችን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ዜና መዘገብ የለባቸውም፤
• በእውነተኛ ታሪክና በአስተያየት (Facts and Opinion) እንዲሁም በዘገባና በትንታኔ (News and analysis) መካከል ያለውን ልዩነት በተግባር ማሳየት አለበት፤
• ስህተት ሲሠራ ስህተቱን እና የእርምት እርምጃውን በፍጥነት ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት፤
• ሠራተኞቹ (ዘጋቢዎች) አንድን ዘገባ ከመዘገባቸው በፊት እውነትነቱን ማረጋገጥ የሚችሉ፣ ክህሎት ያላቸውና በሚሠሩት ሥራ የሠለጠኑ መሆን አለባቸው፤
• የአንባቢዎችን ወይም የተመልካቾችና የአድማጮችን ቁጥር ለማሳደግ ተብሎ ከሚሠሩ ስሜት ቀስቃሽ ዘገባዎችና ትርክቶች መራቅ አለበት። በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመረኮዘ ስሜት የሚኮረኩር ዘገባ ወይም ትርክት ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶችና የታሪክ እይታዎች ባሉበት አገር ውስጥ አደገኛ ነው
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሚድያ ችግር ብዙ ነው፣ ዋና ዋና የሚባሉት ከታች ተቀምጠዋል። እነዚህ ችግሮች በፍጥነት ዕልባት አግኝተው የኢትዮጵያ ሚድያ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ መጫወት የሚገባውን ቁልፍ ሚና መጫወት እንዲችል ካልተደረገ፣ ነጻ ሚድያ በሌለበት አገር ውስጥ ዴሞክራሲ መገንባት እንደማይቻል ዋናውን ባለድርሻ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ባለድርሻዎች ሊገነዘቡ ይገባል።

የሜዲያ ባለቤትነት
ኢትዮጵያ ውስጥ ኹለት ዓይነት የሚድያ ባለቤትነት አለ። አንደኛው የመንግሥት፣ ኹለተኛው ደግሞ የግል ባለሀብቶች ነው። የኢትዮጵያ ሚድያ የእነዚህ ኹለት ባለቤቶቹ ታማኝ አገልጋይ ነው። በግሉ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ሚድያዎች ገንዘብ ከመሰብሰብና በባለቤትነት የያዛቸውን ግለሰብ ወይም ድርጅት የፖለቲካ ዓላማ ከማራመድ በዘለለ የሚሠሩት ቁምነገር እምብዛም ነው። እንዲህ ማለት ግን የሚድያ ሚናና ኃላፊነት ገብቷቸው ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት የሚፍጨረጨሩ ሚድያዎች የሉም ማለት አይደለም።

በመንግሥት ስር የሚገኙ ሚድያዎችን በኹለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሚድያዎች ሲሆኑ ሌላው በክልል መንግሥታት ቁጥጥር ስር የሚገኙት ናቸው። የኹለቱም ሚድያዎች ሥራ ባለሥልጣኖችን ከማሞገስና የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ከመሆን ብዙም የዘለለ አይደለም።

በማእከልም በክልልም የሚገኙ ሚድያዎች መንግሥት አንድ ነገር አደርጋለሁ ብሎ ቃል ሲገባ ተሽቀዳድመው መዘገብ እንጂ፣ መንግሥት ቃል የገባው ጉዳይ መፈጸሙንና አለመፈጸሙን ተከታትለው ለሕዝብ አሳውቀው አያውቁም። ለዚህ ነው እነዚህ ሜዲድያዎች የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎች ናቸው የሚባሉት።
በክልል የሚገኙ ሚድያዎች የክልሉ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በክልሉ ውስጥ የሚገኘው የዋናው ብሔር አገልጋዮች ናቸው። ሚድያ ሙሉ በሙሉ በብሔር በተዋቀሩ ክልሎች ቁጥጥር ስር መሆኑ የሚያመጣው ጣጣ ምን እንደሚመስል በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተ የሚራገበውን አገር አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ መመልከቱ ይበቃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ በኩል የሚድያ አሰራርን በተመለከተ ሕግና ስርዓት የሚያስይዝ ተቋም መኖር አለበት። በሌላ በኩል ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኙ የሚድያ ተቋማት ነጻ በሆነ ቦርድ የሚተዳደሩበት ሁኔታ በፍጥነት ካልተፈጠረ፣ የዴሞክራሲ ጅምራችን ከወዲሁ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ለምሳሌ የሚቀጥለው ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ሊሆን የሚችለው የምርጫውን ሂደትና ውጤት ከማንም ተፅዕኖ ውጭ በነጻነት መዘገብ የሚችል ሚድያ ሲኖር ብቻ ነው። ዛሬም ግን በክልል ሆነ በማእከል ሥራቸውን በነጻነት መሥራት የሚችሉ ሚድያዎች የሉም።

ነጻ የፍትህ ተቋማት
ኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ የፍትህ ተቋሞች ስለሌሉ የሚድያ ተቋማት አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት አላግባብ በተከሰሱበት ጉዳይ ፍርድ ቤት በመመላለስ ነው። በሕወሓት/ኢሕአዴግ ሥርዓት ውስጥ በግልጽ እንደታየው መንግሥት ጋዜጠኞችንና የሚድያ ተቋም ባለቤቶችን ሰበብ ፈልጎ እየከሰሰ ፍርድ ቤት ያቀርባል። የመንግሥት መሣሪያ የሆነው ፍርድ ቤት ደግሞ ሕጉን ተከትለው ሥራቸውን በሠሩ የሚድያ አባላት ላይ የረጅም ጊዜ እስራት ይፈርድባቸዋል።

በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት ችሎታ ያላቸው ጋዜጠኞቿ እየታሰሩ ወይም ከአገር እየተሰደዱ ብቃት ያለው የሚድያ ተቋምም ጋዜጠኛም የሌሉባት አገር ሆናለች። ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣን የዴሞክራሲ እድገት ማየት የምንፈልግ ከሆነ፣ ለሚድያ ተቋሞች ሕጋዊ ከለላ መስጠት የሚችሉ ነጻ የፍትህ ተቋሞች መገንባት አለባቸው። የመንግሥት ባለሥልጣኖችም የሚድያ አባላትን በሆነ ባልሆነው እየከሰሱ ሚድያው በነጻነት ሥራውን እንዳይሠራ ማድረግን ማቆም አለባቸው።

የሚድያ ነጻነት
ኹለት አይነት የሚድያ ነጻነት አለ። አንደኛው የሚድያ ተቋሞች መንግሥትን ጨምሮ ከሌሎችም የግል አጀንዳ ካላቸው ቡድኖች ተፅዕኖ ነጻ ሲሆኑ ነው። ሌላው የሚሠራቸውን ሥራዎች ሁሉ ያለምንም መገደብ እንዲሠራ የሚያስችለው ነጻነት ነው። ለምሳሌ አንዱ መንግሥትን ተጠያቂ ማድረግ ነው። ሚድያ ይህንን ሥራውን ሲሠራ ለምን ሠራህ? ምን አገባህ? ማነህ አንተ? ምን ልታደርግ መጣህ? እያለ የሚያስፈራራው ኃይል መኖር የለበትም። እንዲህ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሕገ መንግሥቱ ላይ የተጻፈ የሚድያ ነጻነት ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ነጻነት በተግባር መገለጹን የሚያረጋግጡ ነጻ ተቋሞችም ነው።

ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የእርስ በእርስ ግጭት ተላቅቃ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በማድረግ ላይ የምትገኝ አገር ናት። የሽግግሩ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ይህ ሽግግር ከዚህ በፊት ከነበሩት ሽግግሮች እንደሚለይ ብቻ ሳይሆን እሳቸው እራሳቸው እንደሚያሸጋግሩን በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸውን አከበሩ ብሎ የሚያከብራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ስለተካሄደ ብቻ አይደለም፣ ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ መሆን አለበት።

ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ደግሞ የነጻ ሜዲያ መኖርን የግድ ይላልና፣ ዛሬ እርሳቸው የሚመሩት መንግሥት አገልጋይ የሆኑትንና በክልልም የአንድ ብሔር መሣሪያ የሆኑትን የሚድያ ተቋሞች ከታሰሩበት ሠንሰለት ፈትተው ነጻ ተቋሞች እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው። ይህንን ካደረጉ ብቻ ነው ተሻገርን የምንለው። አለዚያ እዚያው ነን!
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here