የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት በአዲስ ምዕራፍ፤ የመመሪያዎች አወጣጥን በሕግ መግራት!

በኢትዮጵያ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያዎች የሚጸድቁና የሚተገበሩበት መደበኛ ሂደት አልነበረም የሚወጡ መመሪያዎችም ተደራሽነታቸው ከቁጥር የሚገባ ባለመሆኑ ዓላማቸውን ሳያሳኩ ይልቁንም ከወጡበት አዋጅ ጋር የሚጣረሱ፣ ዜጎች ለመብት ረገጣና በደል እንዲዳረጉ ሰበብ ሆነዋል አዲሱ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ ግን ይህን ሙሉ ለሙሉ ሊለውጥ ይችላል የሚሉት ሚኒሊክ አሰፋ እና አብዱላጢፍ ከድር፣ በአዋጁ የተጠቀሱትን የሥነስርዓት ድንጋጌዎችም በማብራራት አስቀምጠዋል

ወደ መንግሥት የአስተዳደር ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት የሄደ ሰው በተቋማቱ ሠራተኞች ሊሰጡት ከሚችሉ ምላሾች ውስጥ ‹‹መመሪያው አይፈቅድም›› የሚለው ዋነኛው እና እጅግ የተለመደው ነው። ‹የቱ መመሪያ?›፣ ‹መቼ እና በየትኛው ሥልጣን የፀደቀው?› ለሚለው የዜጎች ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ መስጠት የተሳናቸው የአስተዳደር ተቋማትም፤ በተለያዩ አዋጆች መሰረት በተሰጣቸው ሥልጣን መመሪያዎችን እያወጡ እና እያስፈፀሙ ቆይተዋል።

በሕገ መንግሥቱ ግልፅ ዕውቅና የሌለው ይሁን እንጂ የአስተዳደር ተቋማት በሕግ አውጪው አካል በሚሰጥ የውክልና ሥልጣን (delegated legislative power) መሰረት የሚያወጧቸው መመሪያዎች በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ለዜጎች የተረጋገጡ መብቶች እና ጥቅሞች የሚተገበሩበትን ተጨባጭ ሂደት በመዘርጋት ረገድ ከዋናዎቹ አዋጆች ያልተናነሰ ሚና ያላቸው ናቸው።

ሆኖም በኢትዮጵያ ውስጥ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያ በሚያወጡበት ወቅት ምን አይነት ሂደቶችን መከተል እንደሚገባቸው የሚደነግግ ምንም አይነት ሕግ ያልነበረ በመሆኑ፤ ፍትሀዊነት የጎደላቸው መመሪያዎች ዘፈቀዳዊ በሆነ መልኩ ሲፀድቁና ሲተገበሩ ቆይተዋል። የአስተዳደር ተቋማት መመሪያዎች የሚወጡበት ሂደት ሥርዓት አልቦ የነበረ ከመሆኑም ባሻገር፣ በርካታ መመሪያዎች ወጥ በሆነ መልኩ የማይታተሙ፣ ለሕዝብ ተደራሽ ያልሆኑ እና መሠረታዊ በሆነ መልኩ ከእናት አዋጃቸው ጋር የሚጣረሱ መሆናቸው ዜጎች ስፍር ቁጥር ለሌለው የመብት ረገጣ እና በደል እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል።

አዲሱ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ እስከወጣበት ቀን ድረስ የመመሪያዎች አወጣጥን የሚመለከተው የኢትዮጵያ የሕግ ሥርዐት እና ልምድ ኋላቀር እና በዘመናዊ ዓለም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የሚክድ ሰው አይኖርም።ሕገመንግሥቱ የመብቶችን መከበር እና ሕገመንግሥታዊ ዴሞክራሲን በሚመለከት ከገባቸው ቃልኪዳኖች አንጻር ሲታይ፣ የአስተዳደር ሥነሥርዐት ሕግ አለመኖር ጨቋኝ እና ገደብ የለሽ ሥልጣን እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲዘረጋ ምክንያት መሆኑም ጥያቄ የለውም።

አገልግሎት የመስጠት እና መመሪያ የማውጣት ግዴታ ሲጣጣሙ

ዜጎች ወደ አስተዳደር ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት በሚሄዱበት ጊዜ በተደጋጋሚ ከሚሰሟቸው አሉታዊ ምላሾች መካከል ሌላኛው ደግሞ ‹‹ጉዳዩ መመሪያ አልወጣለትም›› የሚል የመብት ክልከላ ነው። በአዋጅ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ለማስፈፅም መውጣት የነበረባቸው መመሪያዎች በጊዜው ባለመውጣታቸው ምክንያት ዜጎች በአዋጅ የተረጋገጠላቸውን መብት በአስተዳደር ተቋማት ይነፈጋሉ። በዚህ ምክንያት ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዳያጡ እና መብታቸው እንዳይጣበብ ለማድረግ አዲሱ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ ኹለት ዋስትናዎችን አስተዋውቋል።

የመጀመሪያው ዜጎች የአስተዳደር ተቋሞች ማውጣት ያለባቸውን መመሪያ በተገቢው ጊዜ ውስጥ እንዲያወጡ መጠየቅ የሚችሉበት ሥርዓት ነው። እንዲህ ዓይነት ጥያቄ የቀረበለት የአስተዳደር ተቋምም በስልሳ የሥራ ቀናት ውስጥ መመሪያ የማውጣት ሂደቱን መጀመር አልያም መመሪያውን ማውጣት እንደማያስፈልገው በምክንያቱን አስረድቶ ጥያቄውን ውድቅ ማድረግ ይችላል። መመሪያ እንዲወጣ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ በሚሆንበት ጊዜ ውድቅ የማድረግ ውሳኔው እንደማንኛውም ውሳኔ በአዋጁ አንቀፅ 48/1/ እና 50(2) መሰረት ለፍርድ ቤት ክለሳ መቅረብ የሚችል ይሆናል ማለት ነው።

ኹለተኛው ዋስትና የአስተዳደር ተቋማት ሊያወጡ የሚገባቸውን መመሪያ ባያወጡም እንኳን ተቋማቱ በሕግ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ለዜጎች ሊሰጡ የሚገባቸውን አገልግሎት ወይም አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያስገድዳቸው ድንጋጌ ነው። ይህም መመሪያ አልወጣለትም በሚል ምክንያት ዜጎች አገልግሎት እንዳይነፈጉ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያ ባላወጡለት ጉዳይ ላይ ጭምር በአዋጅ የተቀመጠ አገልግሎትን የመስጠት ግዴታ እንዲኖርባቸው ያደርጋል።

‹እንደራሴ ያላፀደቃቸው – የሕዝብ ይሁንታ የሌላቸው› 

መመሪያዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚያወጣቸው አዋጆች በተለየ መልኩ በሕዝብ ባልተመረጡ የአስፈፃሚው አካል ሹመኞች እና ባለሙያዎች የሚወጡ መሆናቸው ይታወቃል። በመሆኑም መመሪያዎች ከመፅደቃቸው በፊት ለሕዝብ ውይይት ክፍት መሆን እና የተወሰነ ዴሞክራሲያዊ ሂደትን ማንፀባረቅ እንደሚጠቅባቸው እሙን ነው። ነገር ግን በአገራችን ያሉ የአስተዳደር ተቋማት መመሪያዎችን ከማውጣታቸው በፊት ከሕዝብ ወይም ከባለድርሻ አካላት ጋር ረቂቅ መመሪያዎችን የተመለከቱ ምክከሮችን ሲያደርጉ አይስተዋልም።

ምክክሮች ቢደረጉ እንኳን ፕሮፓጋንዳ በሚመስል መልኩ ሕዝቡ የመንግሥትን ሐሳብ እንዲቀበል ከማድረግ ባለፈ በምክክር ወቅት የሚሰጡ አስተያየቶችን ከግምት በማስገባት ረቂቆቹን ለማሻሻያነት የመጠቀም ልምድ ያልነበረ መሆኑም የአደባባይ ምስጢር ነው። ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎች እና ተቃውሞዎች ሲኖሩ እንኳ ‹ፀረ ሕዝብ› እና ሌሎች መሰል የፍረጃ ቃላትን በመጠቀም ሐሳቦች በነፃነት እንዳይነሱ ጫና መፍጠር የተለመደው አሠራር ነበር።

አዲሱ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ማውጣት የሚችለው አዋጁ ባስቀመጠው ሥነ-ሥርዓት መሠረት ብቻ እንደሚሆን ስለሚደነግግ በመመሪያ አወጣጥ ሂደት ላይ የሚጠበቀውን የዜጎችን ተሳትፎ በሚታይ መልኩ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል። በአዋጁ መሰረት ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም መመሪያ ከማውጣቱ በፊት ስለሚያወጣው መመሪያ ሰፊ ስርጭት ባለው ጋዜጣ፣ በተቋሙ ድረ ገጽ እና በሌሎች የመገናኛ ብዙኀን ላይ ማስታወቂያ ማውጣት እንዳለበት በአዋጁ ተቀምጧል። በማስታወቂያው የረቂቅ መመሪያውን ቅጂ ማግኘት የሚቻል ስለመሆኑና የሚገኝበትን ሁኔታ፣ በረቂቅ መመሪያው ላይ ሰዎች ያላቸውን አስተያየቶች መቼ እና እንዴት ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የሚገልጹ መረጃዎችን ማካተት እንደሚኖርበት በአዋጁ ተደንግጓል።

የአስተዳደር ተቋማት ለሕዝብ አስተያየት ክፍት ያደረጉትን ረቂቅ መመሪያ ለሚመለከታቸው የአስተዳደር ተቋማትና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአስተያየት መላክ እና ከ15 ቀናት በማያንስ የጊዜ ገደብ ውስጥ በመመሪያው ላይ ያላቸውን አስተያየት መቀበል ይኖርባቸዋል። የአስተዳደር ተቋማት ሪቂቅ መመሪያቸው ላይ ግብዐት ለመሰብሰብ የሚያስችል በቂ ጊዜ በመመደብ በመመሪያው ረቂቅ ላይ የጽሑፍ አስተያየት ከተቀበሉ በኋላ ማንኛውም ሰው የሚሳተፍበትን መድረክ በማዘጋጀት መመሪያው ላይ አስተያየት ያላቸውን ግለሰቦች እና ባለድርሻ አካላት ማወያየት ይኖርባቸዋል።

የአስተዳደር ተቋማት መመሪያውን ከማጽደቃቸው በፊት በረቂቁ ላይ የቀረቡ አስተያየቶችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለባቸው ሲሆን፣ የጽሑፍ አስተያየት ማቅረቢያና የውይይት መድረክ ማካሄጃ ጊዜ እስኪያልፍ ድረስ መመሪያውን ማጽደቅ እንደማይችሉ በአዋጁ በግልፅ ተደንግጓል። ይህም መመሪያዎች ከመጽደቃቸው በፊት በቂ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ እና ዴሞክራሲያዊ ሂደትን እንዲያልፉ በማድረግ መመሪያው በቀጥታ የሚመለከታቸው አካላት መመሪያው ላይ ያላቸውን አማራጭ እና የማሻሻያ ሐሳብ እንዲያቀርቡ እድል የሚሰጥ ነው።

በተጨማሪም በአዋጁ የአስተዳደር ተቋማት ረቂቅ መመሪያውን ከማጽደቃቸው በፊት ለአስተያየት ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የመላክ ግዴታ እንዳለባቸው የተቀመጠ በመሆኑ፣ ቀድሞ የነበረውን ቁጥጥር አልባ አሠራር ገደብ የሚያበጅለት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል የአስተዳደር ተቋማት ያወጡት መመሪያ መጀመሪያ ለሕዝብ ይፋ ከተደረገው እና ለውይይት ከቀረበው ረቂቅ መመሪያ ጋር መሠረታዊ ልዩነት ካለው መመሪያው ውድቅ ተደርጎ መመሪያ የማውጣት ሂደቱ እንደ አዲስ መጀመር እንዳለበት አዋጁ ማስቀመጡ፣ የአስተዳደር ተቋማት ከሕዝብ ዐይን እና አስተያየት የተሰወሩ መመሪያዎችን እንዳያጸድቁ ያደርጋል።

ሰኔ 29፡ የ‹ምስጢራዊ መመሪያዎች› መጨረሻ

ማንኛውም በፌዴራሉ መንግሥት የሚወጣ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ታታሞ መውጣት እንደሚኖርበት የተደነገገ ቢሆንም፣ በመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት የሚወጡ አብዛኞቹ መመሪያዎች ታትመው ለሕዝብ ተደራሽ የማይደረጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ቢታተሙ እንኳን ወጥነት ባለው መንገድ ተዘጋጅተው ለሕዝብ ተደራሽ የሚሆኑበት አሠራር አልነበረም። ይህ ሁኔታ መሠረታዊ የሆነውን የሕጋዊነት መርሕ የሚፃረር ሲሆን፣ ዜጎች አንብበው በማይረዱት እና በማያውቁት መመሪያ መብታቸው እንዲጣስ መንገድ ከፍቷል።

የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚጠቀሙባቸውን መመሪያዎች አትመው ለሕዝብ ተደራሽ አለማድረጋቸው ሳያንስ፣ ከተቋማቱ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ ዜጎች ጭምር መመሪያዎቹን መመልከት እንዳይችሉ የሚከለክሉ ተቋማት መኖራቸው ይታወቃል። ይህም መመሪያዎች ይፋ የሕግ ሰነዶች መሆናቸው ቀርቶ የፖለቲካ ምስጢሮች እንዲመስሉ አድርጓቸዋል።

ለማሳያነትም ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ዜጎች እና ኢንቨስተሮች ሲናገሩ እንደሚሰማው፣ በየጊዜው በሚቀያየሩ ምስጢራዊ መመሪያዎች የሚፈጥሩት ግራ መጋባት እና ውዥንብር የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች በዜጎች ላይ አላስፈላጊ እንግልት በመፍጠር ያልተገባ ጥቅም ለማካበት እንዲችሉ በር ከፍቷል።

አዲሱ የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅም ይህንን ችግር ከስሩ በሚፈታ መልኩ የአስተዳደር ተቋማት ያወጡትን መመሪያ ከነማብራሪያው ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመላክ ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው፤ እንዲሁም መመሪያዎቹ በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና በአስተዳደር ተቋማቱ ድረ ገጽ ላይ መጫን/መታተም እንደሚኖርበት ይደነግጋል።

በሚመለከተው የአስተዳደር ተቋም ድረገጽ ላይ ያልተጫነ/ያልታተመ መመሪያም ተፈፃሚነት የማይኖረው እንደሚሆንም አዋጁ በግልፅ አስቀምጧል። የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የወጡ መመሪያዎችም አዋጁ ከወጣበት ቀን አንስቶ ባሉ 90 ቀናት ውስጥ መመዝገበ እና ለሕዝብ ክፍት መሆን እንደሚገባቸው በአዋጁ የተደነገገ ሲሆን፣ በዚህም እስከ ሰኔ 29 ቀን 2012 ድረስ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተልከው ያልተመዘገቡ እና ለሕዝብ ክፍት ያልሆኑ የቀድሞ መመሪያዎች ተፈፃሚነታቸውን የሚያጡ ይሆናል።

ይህ ድንጋጌ ለሕዝብ ክፍት ባልሆኑ ‹ምስጢራዊ መመሪያዎች› ሲማረሩ ለነበሩ በዋናነትም በንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች እና ከመሬት ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሲጉላሉ ለነበሩ ዜጎች፣ ትልቅ እፎይታን እንደሚፈጥር ይታመናል። ስፍር ቁጥር በሌላቸው፣ ብዛታቸው እና ይዘታቸው በማይታወቅ መመሪያዎች አገልግሎት ሲሰጡ፣ ብሎም ሲነፍጉ የነበሩ የአስተዳደር ተቋማትም በግልፅ በሚታወቁ እና ተገማች በሆኑ መርሆዎች መሰረት አገልግሎት ለመስጠት ይገደዳሉ።

‹የሕገ ወጥ መመሪያዎች› እጣ ፈንታ

የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁ የዘፈቀደ ሥልጣንን እና ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር መሠረታዊ የሚባሉ የሥነሥርዓት ሂደቶችን እና መርሆዎችን የዘረጋ ሲሆን፣ እነዚህን መርሆዎች በመጣስ የፀደቀ መመሪያም በፍርድ ቤት ቀርቦ ሕጋዊነቱ የሚመዘን ይሆናል። አዋጁ በአገራችን በሕግ ሥርዓት ውስጥ ካስተዋወቃቸው ማዕቀፎች አንዱ እና በዋነኝነት የሚጠቀሰው የአስተዳደር ጉዳዮች የፍርድ ክለሳ ሥርዓት (judicial review) ነው።

የፍርድ ክለሳ ሥርዓት በአስተዳደር ተቋማት የተሰጡ ውሳኔዎች እና የፀደቁ መመሪያዎች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁን ድንጋጌዎች ጠብቀው የተሰጡ ወይም የፀደቁ መሆናቸው የሚመረመርበት የፍርድ ሂደት ነው።

ከላይ የጠቀስናቸውን በአዋጁ የተመለከቱትን የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተሉ፤ ወይም ከአስተዳደር ተቋሙ የሥልጣን ገደብ ውጪ የወጡ፤ እንዲሁም በማናቸውም መልኩ ሕግን የሚጥሱ መመሪያዎች በማንኛውም ሰው በሚቀርብ አቤቱታ መሰረት ለፍርድ ክለሳ ሊቀርቡ ይችላሉ። መመሪያው የሥነሥርዓት ድንጋጌዎች ሳይከተል በመውጣቱ ምክንያት የሚቀርብ የክለሳ አቤቱታ መመሪያው በጸደቀ በዘጠና ቀናት ለፍርድ ቤት መቅረብ የሚገባው ሲሆን፣ በቀሩት ኹለት ምክንያቶች መሰረት የሚቀርብ አቤቱታ ግን በማንኛውም ጊዜ ማንኛውም ያገባኛል የሚል ሰው አቤት ባይነት ለፍርድ ሊቀርብ ይችላል።

ፍርድ ቤቱም የክለሳ አቤቱታ የቀረበበትን መመሪያ መርምሮ መመሪያውን የማፅናት፣ በሙሉ ወይም በከፊል የመሻር ሥልጣን ይኖረዋል። በዚህም ከአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁ አንፃር ጉድለት ያለባቸውን መመሪያዎች በከፊል ወይም በሙሉ ውድቅ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻለዋል።

በቀጣይ ምን ይጠበቃል?

አዲሱ የፌዴራል የአስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ የመመሪያዎች ረቂቅ ከሚዘጋጅበት ጊዜ አንስቶ ፀድቀው ተግባር ላይ እስከሚውሉበት ጊዜ ድረስ ያለው ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በሕግ እና በዴሞክራሲያዊ መርሆች ላይ የተመሠረቱ ሂደቶችን ዘርግቷል። ምንም እንኳን አዋጁ አዲስ ከመሆኑ አንፃር በሕዝቡ እና በመንግሥት ሠራተኞች የእለት ተዕለት ሥራ እስከሚለመድ ድረስ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣ አሁን ያለውን የአስተደደር ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እንደሚቀይረው ይታመናል።

ሆኖም የሕግ ባለሙያዎች እና የሲቪል ማኅበረሰሰብ ድርጅቶችም በአዋጁ የተደነገጉ ሂደቶች እና መርሆዎች መከበራቸውን መከታተል እና ተጥሰው ሲገኙም በአዋጁ በተቀመጠው መሰረት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የክለሳ አቤቱታ በማቅረብ ተፈፃሚነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። የመገናኛ ብዙኀን ደግሞ በአዋጁ መሠረት የአስተዳደር ተቋማት ከዚህ ቀደም ሲሠሩባቸው የቆዩ መመሪያዎችን ከሰኔ 29 በፊት እንዲያስመዘግቡ ግፊት ማሳደር፣ ይሀን ያላደረጉ ተቋማትንም በመከታተል ለሕዝብ ማሳወቅ እና ሕዝቡ ውድቅ በሚሆኑ (ተፈፃሚነት በሌላቸው) መመሪያዎቸ እንዳይገዛ ግንዛቤ ማስጨበጥ ይጠበቅባቸዋል።

በዋናነት ግን ሁሉም የመንግሥት የአስተዳደር ተቋማት በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ለማክበር እና ለማስፈፀም ራሳቸውን በአቅም እና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ቀደም ሲሠራባቸው የቆዩ መመሪያዎችን ከሰኔ 29 በፊት በቀሩት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመላክ ማስመዝገብ እና ለሕዝብ ክፍት ማድረግ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የሚያወጧቸውን መመሪያዎችም የአዋጁን ድንጋጌዎች የተከተሉ እንዲሆኑ በዕቅዶቻቸው ውስጥ ለዚህ የሚያስፈልገውን የጊዜ ቆይታ እና የገንዘብ ሀብት ታሳቢ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

መንግሥት በአስተዳደር አዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ለማስፈፀም ከሚዲያ ፍጆታ የዘለለ ቁርጠኝነት ማሳየት ይጠበቅበታል። በቀጣይነትም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጡ ደንቦችን የአወጣጥ ሂደት በተመሳሳይ መልኩ የሚገዛ አዋጅ ማዘጋጀት ይኖርበታል።

[1]ሚኒሊክ አሰፋ (LL.B.) በተ..ድ የስደተኞች ተቋም ተባባሪ የሕግ ባለሙያ እና ተመራማሪ ናቸው

[1]አብዱላጢፍ ከድር (LL.M.) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዐዊ መብቶች የጥናት ማእከል መምህርበማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩየማኀበረሰብ አንትሮፖሎጂ ተቋም ዕጩ ዶክተር ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል

ቅጽ 2 ቁጥር 82 ግንቦት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here