ደሃ እና ኮሮና

ኮቪድ19 ኮሮና ቫይረስ የሰውን ልጅ በምንም መልኩ ሳያበላልጥ ኃይሉን አጠንክሮ አሁንም ከወራት በኋላ ማስጨነቁን አልቀነሰም። ወረርሽኙ ያደጉ አገራትን ዝም ሲያሰኝ፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራ ደግሞ የሚኖረው ጫና በፍርሃት እየተጠበቀ ይገኛሉ። በአሜሪካ ሳይቀር ከፍተኛ ተጠቂ የሆኑት በድህነት ውስጥ ያሉ ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው። ሽመልስ አረአያም ይህን ነጥብ በማንሳት፣ ፖሊሲ አውጭዎቻችን ውሳኔ ሲያስተላልፉ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የተለየ ትኩረት ይስጡ፣ እርስ በእርስ በተማበርና መደጋፉንም አንዘንጋ ብለዋል።

 ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ አጠቃላይ በዓለም ላይ በኮቪድ19 የተጠቁት ሰዎች ብዛት ኹለት ሚሊየን ሲጠጋ በቫይረሱ ውድ ሕይወታቸውን የተነጠቁ ደግሞ መቶ ሠላሳ ሺሕ ተቃርቧል። ከዚህ ጠቅላላ ተጠቂዎች ውስጥ ሠላሳ በመቶ እንዲሁም ከሟቾቹ ኻያ ከመቶ የአሜሪካ ድርሻ ነው። በዚህም የዓለም ልዕለ ኃያሏ አገር የቫይረሱ ዋና ማእከልነትን ከጣሊያን ከተቀበለች ጀምሮ፣ በአስደንጋጭ የተጠቂና ሟቾች አሃዝ እየተጥለቀለቀች ትገኛለች።

ወረርሽኙን ለመከላከል ሥራም ኹለት ትሪሊየን ዶላር መመደቧ ተሰምቷል። ቻይና በግዛቷ ውስጥ በተቆጣጠረችበት በተቃራኒው አሜሪካውያን በእንዲህ ባለ ሁኔታ በተጠቂዎች መጥለቅለቃቸው ባለሥልጣናቶቿ ሳይቀር በቫይረሱ ፊት አቅማቸው መፈተኑን በተለያየ ወቅት በሚሰጧቸው የተደበላለቁ መግለጫዎች ታይተዋል። ቻይና ቫይረሱን በግዛቷ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ካስመዘገበችው ስኬት በመነሳት፣ ቫይረሱ የዓለም ልዕለ-ኃያልነት እንዲሸጋሸግ ሊያመቻች ይችላል ሲሉ ባለሙያዎች ትንበያቸውን አስቀምጠዋል። ይህንንም ያሉት ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጦርነቱ እጅግ የተዳከሙት እንግሊዝና ፈረንሳይ ልዕለ ኃያልነታቸው ለአሜሪካ አሳልፈው ያስረከቡበትን ክስተት በማውሳት ነው።

በቫይረሱ የሚለከፉ ሰዎች እለታዊ አሃዝ ከቀደመው ቀን ጋር ሲነፃፀር የሚያሳየው መስመር ያለማቋረጥ ቀጥ ብሎ መምዘግዘጉን ተያይዞታል። የተጠቂ አሜሪካውያን አጠቃላይ ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን የሟቾችም አሃዝ እንዲሁ ከሌሎች ሲነፃፀር በማደግ በየዕለቱ በከፍተኛነት የሚመዘገብ ሆኗል።

በአሜሪካ ግዛቶች መካከል ሲነፃፀር፣ ቫይረሱ በኒውዮርክ በከፋ ሁኔታ ዱላውን አሳርፏል። በዚህም ከሌሎች አገራት በሚነፃፀር መልኩ ከተማዋ ብዙ ታማሚ ተሸክማለች። በመሆኑም የጤና ተቋማት እጅግ በጣም ተፈትነዋል፤ ይህንንም ተከትሎ የሟቾችም ቁጥር በመብዛቱ በከተማዋ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ በመገናኛ ብዙኀን በተላለፈው ሰዎችን በጅምላ መቅበር መላው ዓለም ደንግጧል።

አሜሪካ በዚህ አይምሬ ወረርሽኝ ቁም ስቅሏን እያየች ባለበት በዚህ ወቅት ሌላ ፈተናም ከፊቷ ተደቅኗል። ይኸውም ‹የቆዳ ቀለም መረጃ ምን ይጠቁማል› በሚል ርዕስ ዘአትላንቲክ ላይ የተጠቂዎችና ሟቾች ማንነት መረጃ በግርድፉ ባቀረበው ዘለግ ያለ ዘገባ፣ ወረርሽኙ በዋናነት ጥቁሮች ለይቶ እየመታ እንዳለ ተገልጾአል።

በዚህም የተከፉ የሚመስሉት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በትዊተር ገፃቸው ‹‹በቆዳ ቀለምና ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች በቫይረሱ ማን በዋናነት እንደሚመታ መካድ አንችልም። ይህም ፖሊሲ አውጭዎች ውሳኔ በሚያሳልፉበት ጊዜ በጣም ተጋላጭ ለሆነ ማኅበረሰብ ትኩረት እንዲሰጡ ጠቋሚ አመላካች ነው።›› ሲሉ ሐሳባቸውን ገልፀዋል።

ከተለያዩ ግዛቶች ታማሚ የሆኑ ሰዎች መረጃ ሲመረመር ነጮችን በተነፃፃሪነት እምብዛም እየተጠቁ አለመሆኑንና በሚገርም ሁኔታ በተለያዩ ግዛቶች በነዋሪነት ስብጥራቸው አናሳ የሆኑት ላቲኖዎችና ጥቁር አሜሪካውያኖች የቫይረሱ ተቀዳሚ ሰለባ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ጥናቱ እንደጠቆመው በኒውዮርክ ከተማ 32.1 በመቶ ነጭ፣ 29.1 ከመቶ ላቲኖ፣ 24.3 በመቶ ጥቁር እና 14.0 በመቶ እስያ ዝርያ ያላቸው ነዋሪዎች ሲገኙ፣ በከፍተኛ ሁኔታ የቫይረሱ ተጠቂዎች መረጃ የሚያሳየው ግን የላቲንኖዎች (45.8 ከመቶ)፣ እስያውያንን (23.4 በመቶ)፣ የነጮች (21.2 በመቶ) እና ጥቁሮች (8 ከመቶ) መሆኑን ነው።

ይህም ነጮች በሚበዙባቸው ቦታዎች የሚኖሩት ጥቁሮችና ላቲኖዎች በቫይረሱ በመጀመሪያው ረድፍ መጠቃታቸውን ያሳያል። አብዛኞቹ ተጠቂዎች ሕጋዊ መኖርያ ፈቃድ የሌላቸው ላቲኖዎችና ቤት አልባ  የሆኑ ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው። ዘገባው አያይዞ እንደገለፀው፣ ከጠቅላላ ቤት አልባ አሜሪካውያን ውስጥ አርባ ከመቶ ያህሉ የጥቁሮች ድርሻ ነው።

አብዛኛዎቹ ጥቁሮች በድህነት የሚኖሩ ሲሆኑ፣ በዚህም በዋነኝነት ቫይረሱን ለመቆጣጠር የሚያገለግለው ከእንቅስቃሴ የመገታት ማስጠንቀቂያን ለመተላለፍ ይገደዳሉ። ሁሉም ነዋሪ በቤት ውስጥ ተሸሽጎ እንዲቆይ ትዕዛዝ ቢተላለፍለትም እነኚህ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ለዕለት ጉርስ ከሚያሟሉበት የአነስተኛ ክፍያ ሥራቸው ተለይተው ለቀናት ቤተሰባቸውን እየመገቡ መቀመጥ እጅጉኑ ውድ ስለሚሆንባቸው፣ ይህንን የዕለት ጉርሳቸው ፍለጋ ሲወጡ በቀላሉ የቫይረሱ ሰለባ ይሆናሉ። ሲከፋም ውድ ሕይወታቸውን ይነጥቃቸዋል። ቀድሞውኑ የጎሰቆለ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና የጤና ሁኔታዎች ውስጥ የሚኖሩ በመሆናቸው፣ በዚህ ላይ የመጣባቸው ወረርሽኝ የበለጠ ይከፋባቸዋል።

በድህነት ውስጥ ይኖራል የሚባለው የኅብረተሰብ ክፍል እንደየአገራት የኑሮ ደረጃ (አንፃራዊ) ሲሆን ለብዙዎቻችን በአሜሪካም ድሃ ስለመኖሩ ሐሳቡ የሚዋጥልን አይደለም። ይሁንና ሃምሳ ሚሊዮን የሚጠጉ አሜሪካውያን (ከጠቅላላው ሕዝብ 16 በመቶ) በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ ይገለፃል።

በዚህም በአገራችን በየዕለቱ የሚገለፁት የተጠቂዎች አሃዝ እየጨመረ ሲሆን፣ በሌሎች አገራት እንደታየው በሙሉ አቅሙ ወደማጥቃት ሲሸጋገር እንደ አሜሪካውያኖች በዋናነት ሰለባ የሚሆኑት በኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ ደካማ የሆኑትና ውጭውን ካልጎበኙ የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት የሚከብዳቸው ወገኖቻችን ናችው።

የዚህ ጽሑፍ አላማም ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ለቫይረሱ በቀላሉ መጋለጥ ከፍተኛውን ሚና ስለሚጫወቱ ፖሊሲ አውጭዎቻችን ውሳኔ ሲያስተላልፉ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የተለየ ትኩረት እንዲሰጡ ለመጠቆም ነው። ምክንያቱም ቫይረሱ ጨርሶ ካልተሸነፈ በአብዛኛው በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ወገኖቻችንን ተጠቅሞ በሕይወት እስከቆየ ድረስ ውሎ አድሮ ሁሉንም ማስገበሩ አይቀርም። በመሆኑም ለእነኚህ ወገኖቻችን ከመንግሥት ጎን ሆነን ከእያንዳንዳችን ምን እንደሚጠበቅብን ከማየታችን በፊት ‹ድሃ የሚባለው ማነው› የሚለውን መረዳት ያሻናል።

ድሃ የሚባለው ማንነው?

የድህነት መገለጫዎች በሚመለከት በሚቀርቡ ሐተታዎች ‘ድህነት’ በተለያዩ ማሳያዎች ይቀርባል። በመሆኑም ድህነትን ከቁሳዊ ሀብቶች እጥረት፣ ከሰብዓዊ ልማት (ለምሳሌ የትምህርትና ጤና አገልግሎት ተደራሽነት) እንዲሁም ከማህበራዊ ግንኙነት ጋር ተዛማጅነቱን በማጥናት በተለያየ አገባቦች ትርጉም ይሰጡታል። ድህነት በቁሳዊ ሀብቶች እጥረት በዋናነትም ለራስ ከሚሆን የገቢና ፍጆታ ቁሶች መጓደል ባለፈ ከሕጻናት ደኅንነት ጋር የተዛመዱ ቁሶችን ማጣት ያካትታል።

በዚህም ሕጻናት ያለዕድሜያቸው በሞት መቀጨታቸው የድህነት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። በሌላ በኩል በማኅበራዊ ግንኙነት በኢኮኖሚ አቅሙ ዝቅተኛውና በሌላው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል በሚኖር የኢኮኖሚ ልዩነት መነሻ በ‹ዝቅተኝነት› መታየት ወይም ለ‹ማኅበራዊ መገለል› መዳረግ ሲከሰት ነው ብለው የሚገልጹም አሉ።

የሆነው ሆኖ አንድ ሰው ከሚኖርበት ቦታና ወቅት አንፃር መታየት እንዳለበት የሚጠቁመው ትርጓሜ በስፋት ተቀባይነት አግኝቷል። በዚህም መሰረት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት የዓለም ባንክ ይፋዊ ትርጓሜ ‹አንድ ሰው መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ከሚያስፈልገው አነስተኛ ደረጃ በታች ወርዶ ቢገኝ ድሃ ተደርጎ ይወሰዳል› ይላል።

በእነኚህ አገራት የኑሮ ደረጃ መሰረት አንድ ሰው መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እንዲያስችለው ‹በቀን ቢያንስ 1.90 ዶላር ማግኘት እንዳለበትና ከዚህ በታች የሚያገኝ ከሆነ ከድህነት ወለል በታች እንደሚኖር ይወሰዳል› በማለትም ያስረዳል። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተሠሩ ‹አመርቂ› ተግባራት የተነሳ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩትነደ ዜጎች ድርሻ መቀነስ እንደተቻለ በማውሳት፣ የመንግሥት መረጃን መሰረት አድርገው የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ።

በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ ዜጎች ከጠቅላላ ሕዝቡ የ24 ከመቶ ድርሻ እንዳላቸው ይገመታል። ይኸውም አገሪቱ በተከታታይ ባስመዘገበችው እድገት የተነሳ  ከ20 ዓመታት በፊት ከነበረበት 45 ከመቶ መቀነስ መቻሉንም የመንግሥት ዘገባዎች ያመላክታሉ። እዚህ ጋር ቢያንስ ኹለት ነገሮች ግልፅ መሆን አለባቸው። ከ20 ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከስልሳ ሚሊየን ያላለፈ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በድህነት ውስጥ ይኖር ነበር ማለት ነው።

አሁን የአገሪቱ ሕዝብ ከመቶ ሚሊዮን በተሻገረበት በተመሳሳይ አሃዝ የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም ከድህነት ወለል በታች ይገኛሉ። ሌላኛውና ዋናው ጉዳይ በዚህ ኑሮ ሰማይ በነካበት ወቅት የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በምን አይነት ተዓምር የዕለት መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሙላት እንደሚበቃ፣ በዚህ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚያልፉት ዜጎችና ፈጣሪ ብቻ ናቸው የሚያውቁት።

በሌላ በኩል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ውስን የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት የሚኖራቸው ሲሆን፣ በዚህም ‹ለመገለል› እና ‹አነስ ተደርጎ ለመቆጠር› ተጋላጭ መሆናቸውን የተካሄዱ ጥናቶች ያመለክታሉ።

በአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት አማካኝነት በኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ገቢ የሚተዳደሩ እንደዚሁም የተፈጥሮ አደጋ (ለምሳሌ ድርቅ) መቋቋም የማይችሉ የከምባታ፣ ሃዲያና ሃላባ የተመረጡ አርሶ አደሮች ለአምስት ዓመታት የተደረገላቸውን ድጋፍ ያስገኘላቸው ጥቅም በሚመለከት ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ስለተሳተፍኩ፣ ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር የሚዛመድ በግሌ ያጋጠመኝን መጥቀስ እችላለሁ።

ለእነኚህ አርሶ አደሮች የተደረገው ድጋፍ ከድህነት ወጥተው ቤተሰባቸውን መመገብ እንዲችሉ ብድር በማመቻቸት የሰብልና እንስሳት ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ ነበር። በዚህም አብዛኛዎቹ የድጋፉ ተጠቃሚዎች አስከፊ የነበረውን የኋላ ታሪካቸውን ቀይረው በወቅቱ በአካባቢው እጅግም የተከበሩ እንደሆኑ ከራሳቸው አንደበት ለመረዳት ችያለሁ።

ሀቢባ (ሥማቸው የተቀየረ) የሚባሉ የሃላባ ወረዳ ሴት እማወራ አርሶ አደር ከድጋፉ በፊትና በኋላ ሰለነበረው የኑሯቸው ሁኔታ በእንባ ነበር የገለፁልኝ። የኑሮ ሁኔታቸው ከመቀየሩ በፊት በአንድ ወቅት ስላጋጠማቸው ክስተት ሲያስረዱ ‹‹በአካባቢው የጎረቤት በሬ ይጠፋል። በሬው የጠፋባቸው ጎረቤትም የእኛ እጅ እንዳለበት በመጥቀስ ተከስሼ እንደእኔው ከተጠረጠሩ ሌሎች ጋር በማላውቀው ሁኔታ አዋጥተን እንድከፍል ተደርጌያለሁ። ለዚህ ክስ የበቃነው በድህነታችን የተነሳ ሆኖ ነው እንጂ በሬውን የትኛውንም የቤተሰቤ አባል ለዐይንም አላየነውም›› ሲሉ ያስታውሳሉ፣ በእንባ።

በውኑ በወቅቱ እኔም ተደምሬ ማልቀሴን አልረሳውም። አሁንስ ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሚመስል ስጠይቃቸው ‹‹አሁን በአካባቢያችን የሚመሰረት ማንኛውንም ማኅበር ውስጥ እኔ በአመራርነት ካልገባሁበት ማኅበሩ የሚበተንባቸው ይመስላቸዋል›› አሉ። ሃገራትም በኢኮኖሚ አቅማቸው ተሰሚነታቸው እንዲሁ ስለሚለያይ እስከመቼ ድረስ አገራችንን የድህነት ጫፍ ላይ አስቀምጠን ከትውልድ ትውልድ እንደምናሸጋግራት ሳስብ እንደ ሬት ይመርራል።

ዘኢኮኖሚስት መጽሔት ላይ የድህነት መጠን የሚለካው ምን ያህል ገንዘብ አለኝ በሚለው ብቻ ሳይሆን ስንት ሰው ያውቀኛል በሚልም ጭምር ነው የሚል ሐሳብ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ይኸውም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ውስን ወይም ምንም የቅርብ ጓደኛ የለኝም የሚሉት የተሻለ ተከፋይ ከሆኑ የሥራ ባልደረቦቻቸው በአሃዝ እንደሚበልጡ በጥናት ተመላክቷል።

በተያያዘ ከቤተሰብ ቤተሰብ በሚኖር የገቢ ልዩነት የተነሳ በወላጆች እና በልጆች መካከል የተበላሹ ግንኙነቶች እንደሚኖሩ እንደዚሁ ተጠቅሷል። በዚህም በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ከሆኑ ቤተሰብ የሚኖሩ ልጆች ቢያንስ በሳምንት ለአንድ ጊዜ ከአንዱ ወላጅ ጋር እንደሚጣሉ በዚህም በልጆችና በወላጆች መካከል መጥፎ ግንኙነት እንደሚፈጠር ተብሎም ተገልፆአል። እንግዲህ በድህነት የተነሳ ወላጅ ከልጁ ለዚህ  ከደረሰ የተጫጫነንን የድህነት ሸክም በግዜ መላ ካልዘየድን እርስ በርሳቸን እንደሚያባላን አይጠረጠርም።

ለምን ድሃ ሆንን?

‹የበለፀጉ አገራት እንዴት ሀብታም ሆኑ?› በማለት ይጠይቃሉ፣ ሀዮን ቻንግ የተባሉ የደቡብ ኮርያ የምጣኔ ሃብት ምሁር ‹Kicking Away the Ladder› በተሰኘው እጅግ ተነባቢ መጽሐፋቸው። በዚህ ስሜት ቀስቃሽ በሆነ ሥራቸው የበለፀጉት አገራት እንደኢትዮጵያ ያሉ አገራት ከድህነት ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት የዓለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚመክሩዋቸው ‹ጥሩ ፖሊሲዎች› እንዲሁም ‹የተቋማት አደረጃጀቶች; የግድ እንዲተገብሩ ጫናና ግፊት ይደረግባቸዋል ይላሉ።

እነዚህ ፖሊሲዎች በእንግሊዝኛው Washington Consensus ፓኬጆች በመባል ይታወቃሉ። እንግዲህ ከአገራቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እምብዛም የማይታረቁ መጤ የፖሊሲ ፓኬጆች ናቸው። ከአገራችን ተሞክሮ በመነሳት በዚህ ዙርያ በቀጣይነት እንደማስነብባችሁ ለማሳወቅ እወዳለሁ። በመሆኑም ቻንግ ያቀረቡት መደምደሚያዎች እጅግም እውነታ ያዘሉና ቀልብ ሳቢ ናቸው። ይኸውም ያደጉ አገራት ወደ ላይ ለመውጣት የተጠቀሙበትን መሰላል በመሰባበርና በማጥፋት እነሱን ለመጠቀም እየሞከሩ ያሉት በማደግ ላይ ያሉ አገራት እነሱ እራሳቸው የተጠቀሙባቸውን ፖሊሲዎች እና ተቋማት እንዳይጠቀሙ ለመከላከል ይሯሯጣሉ በማለት ይከሷቸዋል።

ይህ የሚያመለክተው የበለፀጉ አገራት በማደግ ላይ ላሉት የተሳሳተ ፖሊሲ እንዲከተሉ በማድረግ ሃብታቸውና ግዜያቸውን አባክነው እዚያው ባሉበት እንዲያውም በባሰ የድህነት ማጥ ውስጥ እንዲኖሩ “ደባ” የሚመስል ነገር እንደሚፈጽሙባቸው ነው። ነገር ግን በቤተሰብ ደረጃም ብዙዎች በዝቅተኛ ኢኮኖሚ የሚኖሩ ሰዎች በራሳቸው ለድህነት ውለታ መዋል በሚመስል መልኩ በቀጣይነት የበለጠ በድህነት ማጥ ውስጥ እንዲማቅቁ የሚያደርግ ድርጊቶችን በማከናወን ሲጠመዱ ይታያ።

ይኸውም በኢኮኖሚ ዝቅተኛ የሆኑ ብዙውን ጊዜ ድህነትን በሚያጠናክሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ እንደሚያተኩሩ ለማመላከት፣ ለምሳሌ ከሚያገኙት ገቢ ሁሉንም ለዕለታዊ ፍጆታ በማዋል በጣም ትንሽ ይቆጥባሉ። በዚህም ለወደፊቱ ኑሯቸው ጠቃሚ የሆነ ኢንቨስትመንት አያካሄዱም። ከፍተኛ የሆነ የካሽ እጥረት ስላለባቸው ለዕለት ፍጆታቸው ብድር በከፍተኛ ወለድ ለመውሰድ አያመነቱም።

በዚህም ለዛሬ ፍጆታቸው የወሰዱት ብድር የወደፊቱ ኑሯቸው በእጅጉ ያቃውስባቸዋል። በዚህም የበለጠ ድህነት ውስጥ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። ከዚህ አንፃር በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ድህነትን ይበልጥ በሚያባብሱ ሁኔታዎች ውስጥ ሕይወታቸውን ይገፋሉ ማለት ነው። በተጨማሪም እጅግ በጣም በሚያሳዝን መልኩ በብዙ ምክንያቶች መነሻነት ድሃው ማኅበረሰብ ብዙ የመውለድ ፍላጎት ያለው መሆኑ ነው።

በሥነ-ሕዝብ ሽግግር ፅንሰ ሐሳብ መሰረት በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ማኅበረሰቦች በብዙ ምክንያቶች የተነሳ ብዙ ልጆች ይወልዳሉ። ከላይ እንደተገለፀው ብዙ ቁጠባ ስለሌላቸው በእርጅና ዘመን የሚጦራቸው ልጅ ውስን እንዳይሆን መፈለጋቸው ተብሎ ይገለፃል። በማደግ ላይ ያሉ አገራት ውስጥ አብዛኛው በግብርና የሚተዳደር እንደመሆኑ፣ ዘርፉ የሚፈልገው ሰፊ ጉልበት ከግዢ ይልቅ በቤተሰብ ጉልበት ለመሸፈን ባላቸው ፍላጎትም እንደሆነ ይጠቅሳል።

በተጨማሪም በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በዋናነት ለጎሳና ኋላቀር እንዲሁም ባህላዊ አስተሳሰብ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡ ከሌሎች ተገዳዳሪ ጎሳዎች በቁጥር በልጦ ለመገኘት እንደወላጅ ግዴታቸውን ተወጥተው ሊያሳድጓቸው በማይችሉት ሁኔታ ብዙ ልጆችን በማፍራት ከቤተሰባቸው አልፈው ለማኅበረሰቡ በአጠቃላይ ለአገርም እዳ ያሸክማሉ።

አሁን በአገራችን ያለው ሁኔታም በዚህ ረገድ ሊታይ የሚገባው ነው። በተለያዩ ተቋማት እንደተገለፀው የአገራችን ሕዝብ በሚቀጥሉት 38 ዓመታት ውስጥ በእጥፍ በማደግ 210 ሚሊዮን እንደሚሆን ሲታይ፣ ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ ማሰብ እንዳለብን ይነግረናል። በዚህም ኋላቀርነት የተላበሸ የሚመስለው አስተሳሰባችንን ቀይረን ዘመኑን የዋጀ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ከራሳችን አልፈን አገር ላይ የምንከምረውን እዳ ለመቀነስ ቆም ብለን ማሰብ አለብን።

ለጋራ ድል እንተባበር

ቀድመን እንዳነሳነው፣ በአሜሪካ የኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቫይረሱን በቁጥጥር ስር ለማድረግ የተመከረው ከቤት ያለመውጣት እገታ እጅግ ውድ ሲሆንባቸው ተመልክተናል። በዚህም የተባለውን የጥንቃቄ መልዕክት በመተላለፍ የዕለት ጉርስ ፍለጋ በአደባባይ ሲወጡ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነዋል። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን ከጠቅላላ የአገሪቱ ሕዝብ አንፃር አናሳ ድርሻ ቢኖራቸውም፣ በኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኝነት የተነሳ በከፋ ሁኔታ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሲሆኑ ታይቷል። ከዚህ የምንረዳው ስር በሰደደው ድህነታችን የተነሳ በአገራችን የሚገጥመን ፈተና ከዚህ የሚብስ እንጂ የሚያንስ አለመሆኑን ነው።

እንግዲህ ይህን በተሸከምንበት ሁኔታ ነው ከዚህ ወረርሽኝ ጋር ለማይቀረው ፍልሚያ የተሰለፍነው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ይህ ቫይረስ የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት በመሆኑ የሁሉንም ቤት ማንኳኳቱ አይቀርም። ስለዚህም ሁላችንም ቫይረሱን ድል ለመንሳት በአንድነት ካልቆምን በቀር በግለኝነት ‘እኔ ተጠንቅቄ እድናለሁ’ የሚል ሐሳብ ካለን፣ ፈፅሞ ማናችንም በተናጥል ልናመልጥ አንችልም። ነገር ግን በጠዋቱ የቫይረሱ ሰለባ በመሆን ግብግብ የሚገጥሙት በኢኮኖሚ አቅማቸው እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሆኑት ወገኖቻችን ሆነዋል።

እነዚህ ወገኖቻችን እንዳየነው አብዛኞቹ ከኢኮኖሚ አቅማቸው ጋር ያልተጣጣመ የቤተሰብ ቁጥር የሚያስተዳድሩ በመሆኑ ለቀናት ከቤት ሳይወጡ ማሳለፍ ቅንጦት ይሆንባቸዋል። በቤታቸውም የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት በየትኛውም አግባብ ሳምንት እንኳን መቆየት ይከብዳቸዋል። ረሃብ አያስቀምጥም። ስለዚህ ለልጆቻቸው መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት የማይፈነቅሉት ድንጋይም አይኖርም።

ባለፈው ሳምንት የቫይረሱ ስርጭት ጣሪያ በነካበት ጊዜ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ስለሚችል መንግሥት ለተጎጂ የሥራ ዘርፎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች እገዛ ለማድረግ ካሁኑ ተፍ ተፍ ማለት እንዳለበት የሚጠቁም ጽሑፍ አውጥቼ ነበር። ይህ ግን ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም። ለራሳችን ጭምር እንደሆነ በማመን ሁላችንም መተባበር ግዴታችን ነው። ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኛነታችን አንገታችን እንድንሰብር ቢያደርገንም፣ የጨነቀ ቀን ሲመጣ አውሬያዊ ባህርይ ገንፍሎ መውጣቱ አይቀርም።

ስለዚህ በለጋሽ አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍ የበለጠ እንዲጠናከር ሁላችንም ሚናችን መጫወት አለብን። አለበለዚያ የቀን ጉዳይ ቢሆን እንጂ፣ ከቫይረሱ ለመዳን ቀለብ አከማችተንና በር ቆልፈን ብንቀመጥ በረሃብ ዱላ የተገረፉ ወገኖቻችን ያጡትን ለማግኘት በሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል እስከተደበቅንበት ላለመምጣታቸው ዋስትና የለንም። ስለዚህ ለራሳችን ከምናደርገው ባልተናነሰ የዕለት ጉርሳቸውን በዚህ ቫይረስ ለተቀሙት ወገኖቻችንም ማሰብ አለብን። አገራችንንም ከዚህ ከከፋ አደጋ ፈጣሪ ይጠብቅልን!!!

ሽመልስ አርአያ በአሁኑ ወቅት በጀርመን ሀገር ከሚገኘው ጊሰን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ እጩ ሲሆኑ ቀደም ብለው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነት አገልግለዋል። በaraya.gedam@gmail.com አድራሻ ማግኘት ይቻላል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here