ቁርጡ ያልተለየው የዓለም ምጣኔ ሀብትና አፍሪካ

0
1155

በአፍሪካ እንደ አኅጉር አንድ ገበያ በመፍጠር ሂደትና ጥረት ውስጥ ሥማቸው ከሚነሳ ሰዎች መካከል ናቸው። አንድ ገበያ ለመፍጠርም የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት እንዲኖር ለማስቻል በሚደረጉ ድርድሮች፣ የኢትዮጵያ ቀዳሚ ተጠቃሽ ባለሞያ እና ተደራዳሪም ናቸው። ሙሴ ምንዳዬ። በኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመልቲላተራል ንግድ ግንኙነት ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
የሕግ ባለሞያ የሆኑት ሙሴ፣ ከሉላዊነት አንጻር አፍሪካ በምጣኔ ሀብት ትንሣኤዋ የሚሆንበት ዋዜማ ላይ ናት ሲሉ፣ ብቸኛው በዚህ ተስፋ ላይ ያጠላው ጥላ የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሆኑን በማጠየቅ ነው። የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው እኚህን ባለሞያ በአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ዙሪያ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ስምምነት ምን ትጠቀማለች በሚለውና ስምምነቱ ወደፊት እንዴት ይታያል በሚለው ዙሪያ ሐሳባቸውን እንደሚከተለው አጋርተዋል።

ኮቪድ 19 ሲከሰት የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ምን ዓይነት ሁኔታ እና ደረጃ ላይ ነበር?
የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት የተጀመረው ከዓመት በፊት ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ነበር። ይህም የሆነው በወቅቱ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጠቅላላ ጉባኤ ነው። በዛም 28 የአፍሪካ አገራት ስምምነታቸውን ሲያረጋግጡ 54 አገራት ስምምነቱን ፈርመዋል፣ ከኤርትራ በቀር። ቀጣዩ እርምጃ የሚሆነው ያረጋገጡ አገራት ከታሪፍ ነጻ በሆነ መንገድ ሊገበያዩ የሚፈልጉትን ምርትና አገልግሎት ማሳወቅ ወይም ማስገባት ነው። በስምምነቱም መሠረት ለደሃ አገራት ከምርትና አገልግሎቱ 90 በመቶ የሚሆነው ለ10 ዓመት ከቀረጥ ነጻ ይደረጋል።
ለአብዛኞቹ ምርቶች አሁንም እየተካሄዱ ያሉ ድርድሮች አሉ። አሁንም በጨርቃ ጨርቅ፣ በስኳር፣ በተሽከርካሪዎች እና በነዳጅ ዙሪያ አለመግባባቶች አሉ። ለምሳሌ አንዳንድ አገራት ልብስና ጨርቃ ጨርቅ መቶ በመቶ በአፍሪካ የተመረተ መሆን አለበት ይላሉ። አንዳንድ አገራት በአንጻሩ ጥጥ አስገብተው ጨርቃጨርቅ የሚያመርቱ በመሆናቸው፣ የግብይት መጠኑ ላይ ማስተካከያ ቢደረግ ይላሉ።

እስከ አሁን 90 በመቶውን በአገራቸው ብቻ የተዘጋጁትን ያቀረቡ አገራት በአንድ ጎን በነዛ ምርቶች ላይ ጥገኛነታው አነስተኛ ነው፣ አልያም በምርቱ ተወዳዳሪነት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ኢትዮጵያ ግን 90 በመቶ የምትሰጠው የሥሪት አገር ምንጭ ሕግ (origin for argumentative items) ፍጻሜ ሲያገኝ ነው።
አሁን ላይም ኢትዮጵያ የትኛዎቹን ምርቶች በ90 በመቶ ከቀረጥ ነጻ ታቅርብ በሚለው ዙሪያም የመለየት ሥራ እየተሠራ ነው።
በአገልግሎቱ ዘርፍ አራት አገራት 90 በመቶ ሰጥተዋል። እነዚህም ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ዛምቢያ ናቸው። ኢትዮጵያም በአገልግሎቱ የምትሰጠው አላት፣ ግን ጊዜ ያስፈልገናል። አንዳንዴ እንደ ምርት የሚመደቡትም ከአገልግሎት ጋር የሚገናኙ ናቸው።

በኪጋሊ ከተደረገው ስብሰባ በኋላ በአደራዳሪዎች ተጨማሪ ሰባት ስብሰባዎችን አድርገናል። ይህም የተካሄዱ ስብሰባዎችን ቁጥር 17 ሲያደርሰው በሚኒስተር ደረጃ አምስት ውይይቶች ተካሂደዋል። እቅዱም በ2020 የሥሪት አገር ምንጭ ድርድርን (origin negotiation) ከፍጻሜ ማድረስ ነው። ከዛም አገራት 90 በመቶ ይሰጣሉ።

ግንቦት ወር 2020 ላይ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለማከናወን እቅድ ተይዞ ነበር። በየአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትም የንግድ እንቅስቃሴ አሁን ሐምሌ ላይ ሊጀመር እቅድ ተይዞ ነበር። ነገር ግን ሳይታሰብ ኮቪድ 19 ተከሰተ። ጠቅላላ ጉባኤዎች ምስጢራዊ መሆን አለባቸውና በዌብነር ወይም በዙም ስብሰባዎችን ማካሄድ የሚቻል አይደለም። ሆኖም ውይይቶችና ድርድሮች በዙም ቀጥለዋል።

ብዙ አገራት 90 በመቶ ከቀረጥ ነጻ ምርቶችን በመስጠታቸው ከግብር የሚገኙትን ገቢ እንዳያጡ ይሰጋሉ። በአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት የትኞቹ አገራት ናቸው የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑት?
እንደ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ያሉ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከፍታ ላይ የደረሱ አገራት ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡት የተለያዩ ምርቶች አሏቸው። ለተወሰነ ጊዜ እነዚህ አገራት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። በረጅም ጊዜ ግን ሁሉም የአፍሪካ አገራት ምርታቸውን በማሻሻልና የውጪ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በአገር ውስጥ ኢንቨስትመንትንም ከፍ በማድረግ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት እንዲጀመር ከተደረገ በኋላ በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በአጭር ጊዜ እንዲያድግ ማድረጉ አይቀርም። ምክንያቱም እያንዳንዱ አገር በጠቅላላ የአኅጉሩን ገበያ ማግኘት ይችላል። በዚህ ግዙፍ ገበያ ውስጥ ዓለማቀፍ ኢንቨስትመንት ራሱ ፍላጎት ሊያሳድር ይችላል። ከሚፈጠረው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳም የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ሳይቀር ያድጋል።
የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተወዳዳሪ መሆን አለበት። ያለምንም ጥርጥር የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት የጉምሩክ ገቢን መቀነሱ አይቀርም። የኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራ ጋር የምታደርገው የንግድ ግንኙነት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ወደ አፍሪካ አገራት የምትልካቸው ምርቶች መጠንም አነስተኛ ነው። በጠቅላላ ከውጪ ከምታስገባው ምርትም 4.6 በመቶው ብቻ ነው ከአፍሪካ የምታስገባው፣ ይህም 16 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው።

ከዚህም ግማሽ የሚሆነውም በዝርዝር ሲታይ ከሞሮኮ የሚገባው ማዳበሪያ፣ ከሱዳን የምታስገባው ነዳጅ እና ሽንኩርት ተጠቃሽ ናቸው። የእነዚህ እቃዎች ቀረጥ ዜሮ ነው። ስለዚህም ከፍተኛ የሚባል የጉምሩክ ገቢ አናጣም ማለት ነው።

በእኛ ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር በምታደርገው ከቀረጥ ነጻ የሆነ ግብይት፣ በዓመት 920 ሚሊዮን ብር የቀረጥ ገቢ ስታጣ ኖራለች። 10 በመቶ ከቀረጥ ነጻ አገልግሎትንም ለኮሜሳ ሰጥታለች። ሆኖም ግን ይህ ኪሳራ ለገበያ በሚቀርቡ ምርቶች ብዝኀነት እንደሚካካስ እናምናለን። ቀረጥ ዜሮ ሲሆን መደበኛ ያልሆኑ ድንበር ላይ የሚካሄዱ ግብይቶች ሕጋዊ ይሆናሉ። ግብይትና ንግድም ከምዕራቡ ዓለምና ከእስያ ወደ አፍሪካ ይዞራል።

በአንጻራዊነት የተሻለ ምርታማነት የሚታይባቸውን እቃዎች ትኩረት የሚሹና ጥንቃቄ የሚፈልጉ በሚል እየመደብናቸው ነው። እነዚህ ልንወዳደርባቸው የምንችል በመሆናቸው ግን በረጅም ጊዜ ነጻ የምናደርጋቸው ይሆናሉ። ኢትዮጵያ በውድድር የተሻለ ጥቅም የምታገኝባቸው ምርትና አገልግሎቶች ታድያ ጥበቃ ይደረግላቸዋል። የምግብ ዋስትና ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉትም እንደዛው።

እነዚህን ዘርፎች ነጻ በማድረግ ከውጪ የምናስገባው ላይ ልንተማመንና ጥገኛ ልንሆን አንችልም። ለዜጎች የየእለት ኑሮ ወሳኝ የሆኑ ምርቶችም ሆኑ ዘርፎች፣ ለምሳሌ እንደ ግብርና ያሉም በተመሳሳይ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

በዚህም መሠረት ጥበቃ የሚደረግላቸውም እቃዎች፣ አገልግሎቶችና ዘርፎች በመለየት የመጀመሪያውን ረቂቅ አዘጋጅተናል። በተለይም በጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ፣ አልባሳትና ስኳር ምርቶችን በሚመለከት ከንግድ ምክር ቤቶች፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከማኅበራት ጋር እየተነጋገርን ነው።

ምርቶችና አገልግሎቶች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ሲባል አልያም 90 በመቶ ከቀረጥ ነጻ ይቀርባሉ ብሎ ለመለየት ምን ዓይነት መስፈርት ነው የምትጠቀሙት?
ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ የሆነችባቸው ምርቶች ትኩረት የሚሹና ጥንቃቄ የሚፈልጉ በሚል በተለያየ ምድብ ላይ ሆነው ጥበቃ ይደረግላቸዋል። ተስፋ ሰጪና እያደጉ ያሉ ዘርፎች ለምሳሌ እንደ ግብርና ያሉ እንዲሁም ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርት ከፍተኛ ድርሻ የሚወስዱትም በዛው ውስጥ ይካተታሉ። የግብር ገቢ ደረጃ፣ የምግብ ዋስትና እንዲሁም ማኅበራዊ ተጽእኖውም ከግምት ውስጥ ይገባሉ።

የኢትዮጵያ የትኞቹ ዘርፎች ናቸው በየአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ተወዳዳሪ የሚሆኑት?
እነዚህ ጉዳዮች በምስጢር የሚያዙ ናቸው። ለምሳሌ ከሌሎች አፍሪካ አገራት በተለየ ኢትዮጵያ በቆዳና የቆዳ ምርቶች የተወዳዳሪነት ጥቅም አላት። የጫማ፣ ቡና እና ሰሊጥ በአፍሪካ ገበያ የተሻለ ፍላጎት አለ። ለምሳሌ ሱዳን ቡና አታመርትም ነገር ግን ተጠቃሚ ናት። ስለዚህ እነዚህን ጥቅሞች መጠበቅ አለብን።
መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጠው ከሥራ እድል ፈጠራ እና ዓመታዊ ጠቅላላ ምርትን ከፍ ከማድረግ አንጻር ሲሆን፣ የግል ዘርፉ ደግሞ ትርፍ ማሳደግ ላይ ያተኩራል። እናም ከቀረጥ ነጻ እቃዎችን ከማቅረብ በፊት ተጨማሪ ምክክር ያስፈልጋል።

በአፍሪካ የወጪና የገቢ ምርት በኮቪድ 19 ምክንያት ተፈትኗል። የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችንም በሚመለከት አፍሪካ ወደራሷ ገበያ ማተኮር እንዳለባት ነው። የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ይህን ክፍተት ይሞላል ብለው ብዙዎች ይሞግታሉ። በአንጻሩ ደግሞ በወረርሽኝ ሰሞን መጀመሩና ይፋ መደረጉ ወረርሽኙን ያሰራጫል የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አፍሪካ በወረርሽኙ ብዙ አልተጎዳችም የሚል አስተሳሰብ አለ። በዚህ መሠረት ከሆነ የአፍሪካ የውስጥ ለውስጥ ንግድ የሚካሄድበት ጊዜ አሁን ነው። አሁን ላይ የሚወጡ መረጃዎች ደግሞ በአፍሪካ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ እንደሆነ ነው የሚያሳዩት። ያደጉ አገራት ከወረርሽኙ ሲያገግሙ አፍሪካ ቀጣይ በወረርሽኙ ክፉኛ የምትጎዳ ብትሆንስ የሚለውንም አናውቅም።

በአፍሪካ ኅብረት ኹለተኛው ሐሳብ ውሃ የሚያነሳ ነው። ኅብረቱ ደኅንነት እና ጤና ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ባይ ነው። ከሉላዊነትም አፍሪካ ተጠቃሚ መሆን አለባት የሚል ጽኑ እምነት አለው። ለምሳሌ ብዙዎቹ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ከእስያ ይልቁንም ከቻይና የሚመጡ ናቸው። በእነዚህ አገራት ቀውስ የተከሰተ እንደሆነ ጉዳቱ በአፍሪካ ይታያል። ኢንዱስትሪዎቻችን ከቻይና ከሚመጡ ግብዓቶች ውጪ መንቀሳቀስ አይችሉም።

ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር እንደውም ኢትዮጵያ ከቀሪው ዓለም ጋር ያላት ትስስር ውስን ነው። በድምሩ ዓለም ዐቀፍ ቀውሶች በአፍሪካ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ያሳድራሉ።

ስለዚህም እንደ ቻይና ያሉ አገራት ምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ ካልጀመረ በቀር በአፍሪካ የምርት እና ንግድ እንቅስቃሴ ፈጣን ሊሆን አይችልም። ዓለማቀፍ ምጣኔ ሀብት ካልተነቃቃም የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ሥራ መጀመር ምንም ተጽእኖ አይኖረውም። እንዳልኩት ብዙዎቹ ኢንዱስትሪዎቻችን በተለይ ከእስያ በሚገቡ ግብዓቶች ላይ መሠረት ያደረጉ ናቸው።

የአፍሪካና የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትም እርምጃም የዓለማቀፍ ምጣኔ ሀብት እንደሚነቃቃበት ጊዜ የሚወሰን ነው። በዛም ላይ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ፍላጎትም ሆነ ገዢ አይኖርም።
የዓለማቀፉ ምጣኔ ሀብት ወዴት እያመራ እንደሆነ እስከ አሁን አልተለየም። ለዓለም ንግድ ድርጅት ሳይቀር ይህ አልተገለጠለትም። እያንዳንዱ አገር ከውጪ ያስገባ የነበረውን ምርት በአገር ውስጥ ምርት እየተካ ነው ያለው። ሁሉም አገራት ማለት ይቻላል እንዲሁ ምርቶችን እያከማቹ እያስቀመጡም ነው፣ ምክንያቱም ዓለማቀፉ ንግድ አሁን ባለበት ቢቆይ እንኳ፣ የማጓጓዝና የሎጂስቲክ ጉዳይ ላይ ሰልፉ ብዙ ጊዜ የሚወስድ ነው።

እንደማሳያ ለምሳሌ በኮቪድ 19 ወቅት ኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የምታቀርበው የግብርና ምርት መጠን ጨምሯል። ስለዚህ የዓለም ምጣኔ ሀብት ጉዳይ ወደፊት የሚሄድበት አቅጣጫ ይሄ ነው ብሎ ማወቅና መወሰን አይቻልም።

ብዙ አገራት በሁሉም ዘርፎች ራሳቸውን ለመቻል ወስነዋል። ፋብሪካዎችን እየተከሉና የምርት አቅጣጫዎችንም እየቀየሩ ይገኛሉ። የዓለም ንግድ ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት በኮቪድ 19 ምክንያት ድምሩ 800 የሚደርሱ ምርትና አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ገደብ ተደርጎባቸዋል። በዓለም ንግድ ድርጅት በኩል የገቢም ሆነ የወጪ ምርት እንቅስቃሴ ማገድ ይችላል። ይህም ከሰዎች ደኅንነት ጋር የተገናኘ ሲሆን ነው። የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትም ይህን ዓይት አሠራር ተግባራዊ ያደርጋል።

አገራዊ ብሔርተኝነት ከሉላዊነት እንዲሁም ከቀጠናዊ አስተሳሰብ ልቆ እየተገኘ ነው ማለት ይቻላል?
በትክክል አዎን። ይሁንና ዓለማቀፍና ቀጠናዊ የሆኑ የንግድ መሣሪያዎች ለምሳሌ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት ያሉት አይዘጉም። ምክንያቱም ግብይትን ማእከላዊ ማድረጊያ አውድ ያስፈልጋል። አፍሪካ ብቻም ሳይሆን የሠለጠኑ አገራትም ጭምር ንግድና ግብይትን የሚከታተሉበት ተቋም ያስፈልጋቸዋል።

የአፍሪካን የንግድ ግብይት ማእከላዊ ማድረግን ከሉላዊነት አንጻር ስንመለከተው፣ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተለያየ ዕይታ ነው ያላቸው። ይህም የአፍሪካ ኅብረትንም ይጨምራል። መዳኘት ከባድ ቢሆንም የአፍሪካ አገራት አሁንም ለአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ዝግጁ ናቸው።

በተለያዩ የኢንተርኔት መንገዶች ግንኙነት እናደርጋለን። ሁሉም አገራት ንቁና ለጉዳዩም ትኩረት የሰጡ ናቸው። ሆኖም የወረርሽኙ መዛመት ከዚህ የሚከፋ ከሆነ የሚቀየሩ ነገሮች ይኖራሉ።
ይህ ማለት ኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከቀጠለ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ወደ ሥራ አይገባም ማለት ነው?
በ2021 መጀመሪያ ላይ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ወደ ሥራ ይገባል ብለን እንጠብቃለን። ይህም በሐምሌ ታስቦ የነበረው እቅድ መተላለፉን ተከትሎ የተያዘ ጊዜያዊ እቅድ ነው። የአፍሪካ ኅብረት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤም ከግንቦት ወደ ኅዳር ተሸጋግሯል።

አፍሪካ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ማደግ እንዳለባት ጥርጥር የለውም። ይህም በአገር ውስጥ አልያም በውጪ አምራች ድርጅቶች እውን ሊሆን ይችላል። የአሜሪካ ወይም የቻይና አንድ ኩባንያ በሕጋዊ መንገድ በአፍሪካ ቢከፍት፣ በአፍሪካ ለአፍሪካ የሚሠራ አንድ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም እያመረተ ነው ማለት ነው። የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትም ዓለማቀፍ የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ወደ አፍሪካ ይስባል።

አንድ በኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ሰዎችን ዓላማ አድርጎ በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረ የቻይና ኩባንያ፣ አሁን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ሰዎች ያሉበትን ገበያ ማግኘት ይችላል። እንደ አፍሪካዊ አገር፣ ለውጪ ገበያ የምናቀርበው ጥሬ እቃ ይዘን ለመቆየት፣ ሥራ እድልን እና ኢንዱስትሪ መስፋፋትን ማገዝና ከፍ ማድረግ አለብን።

ከአፍሪካ ጥሬ እቃ የሚገዙ ምዕራባውያን እና ቻይናን የመሰሉ ያደጉ አገራት በዚህ ደስተኛ ላይሆኑ ይችላሉ። የአውሮፓ ኅብረት ለአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ጥሩ ድጋፍ ነው ያለው። የቀረው ዓለምም መጥቶ በአፍሪካ መዋዕለ ንዋዩን ፈሰስ በማድረግ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት በፈጠረው እድል ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ወደፊትም እያንዳንዱ አፍሪካ ከቀሪው ዓለም ጋር የምታደርገው የንግድ ድርድርና ስምምነት የሚካሄደው እንደ አንድ አፍሪካ፣ ሁሉንም የአፍሪካ አገራት ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ነው። ከአውሮፓ ኅብረት፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይና እና ከሌሎችም ጋር የምንነጋገረውና የምንዋዋለው እንደ አንድ አኅጉር ነው።

በአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ማበረታቻዎች ምክንያት ከአፍሪካ ለውጪ ገበያ በተለይም ለአደጉ አገራት የሚቀርቡ ምርቶች ወደ አፍሪካ ተመልሰው በአፍሪካ ውስጥ እንዲንሸራሸሩ ይሆናል። በዓለማቀፉ ገበያ ላይ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ተጽእኖ ታድያ ምንድን ነው የሚሆነው?
የዓለማቀፉ ገበያ ለአንዳንድ ዘርፎች ከፍተኛ ፍላጎት ሲያሳይ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ፍላጎቱ ሊቀንስ ይችላል። በኢትዮጵያ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው የሚፈለገው ጥሬ ምርት ፍላጎት ይጨምራል። አንዳንድ ያለቀላቸውና ከውጪ የምናስገባቸው ምርቶች መጠን ደግሞ ይቀንሳል።

ይህም የሚሆነው በአንድ ጎን በምርቱ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ስለምንችል ነው አልያም ከውጪ ካስገባንም ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ከአፍሪካ አገራት ስለምናስገባ ነው። ስለዚህ የአፍሪካና የዓለማቀፉ ገበያ ግንኙነት ምርቶች በአፍሪካ በሚመረቱ እንዲሁም በማይመረቱ የምርት ዓይነቶች ላይ መሠረት ያደረገ ነው።

መሠረተ ልማት ለአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ተግዳሮት ሊሆን ይችላል የተባለ ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ምን ያህል እድል ይፈጥራል?
ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በትልቁ የሚጠቅም ነው የሚሆነው። ችግሩ የአየር ላይ ጭነት አገልግሎት በውሃ ላይ ካለው አንጻር በዋጋ ውድ ነው። በቶሎ የሚበላሹ ምርቶችን የሚያቀርቡ የአፍሪካ አገራት አየር ላይ ጭነትን ሊጠቀሙ ይችላሉ፣ ግን ሁሉም አፍሪካ አገራት ይህን ለማድረግ አቅም ያላቸው አይደሉም።

መሠረተ ልማት ለአፍሪካ ትልቁ ተግዳሮት ነው። ምርቶችን ዳካር ከመላክ ይልቅ ወደ ቻይና ቤጂንግ መላክ ይቀላል። ከአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ቀጥሎ በአፍሪካ ኅብረት የተያዘው እቅድ በአፍሪካ የሚያቆራርጥ የባቡር መስመርና የመንገድ ዝርጋታ ነው። ነጠላ የአየር ትራንስፖርት ገበያም የዚህ አንድ አካል ነው።

የአፍሪካ አቭዬሽን ኩባንያዎች በአፍሪካ ዙሪያ ስለበረሩ ክፍያ አይጠየቁም። አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሱዳን የአየር ክልል ለመብረር ክፍያ ይጠየቃል። ብዙ የአፍሪካ አገራት በፈረሙትና በተስማሙበት በአፍሪካ ብቸኛ የንግድ የአየር ገበያ መሠረት ግን ለሁሉም የአፍሪካ አቭዬሽን አገልግሎት ሰጪዎች ነጻ ይደረጋል። አፍሪካዊ ላልሆኑት ግን ክፍያ ይኖራል።

ከአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ሥራ መጀመር በኋላ የዚህ የመሠረተ ልማት ችግር በግልጽ የሚታወቅና ተጽእኖው የሚገለጥ ይሆናል። የአፍሪካ የውስጥ ለውስጥ ንግድ በዚህ የመሠረተ ልማት ችግር ምክንያት በፍጥነትና በቅጽበት ላያድግ ይችላል። በጊዜ ሂደት ግን ተጽእኖው መፍትሄ ያገኛል። የንግድ እንቅስቃሴው ራሱ መሠረተ ልማት ላይ የሚፈጠረውን ኢንቨስትመንት ያፋጥናል።

የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትን እንዴት ያየዋል?
የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ በአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት በተደረጉ ስምምነትና ድርድሮች ውስጥ ሁሉ ተወክሎ ነበር። በስምምነት ሂደቱም ካሉት 36 የቴክኒካል ኮሚቴ አባላት ውስጥ ሁሉም በሚባል ደረጃ የኢትዮጵያ ተቋማት ተወክለዋል። በዋናነት ሥራውን በሚያንቀሳቅሰው ኮሚቴም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሚኒስትሮችንና ኮሚሽነሮችን ያካተተ ነው። በኢትዮጵያም በሁሉም የክልል መንግሥታት ተንቀሳቅሰን ስለአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነት ግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተናል።

በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ንቁ የሚባል አይደለም። በተደጋጋሚ የትኛው ዘርፍ ነጻ እንዲሆንና ጥበቃ እንዲደረግለት እንደሚፈልጉ ጠይቀናቸዋል። ምላሽ ግን አልሰጡም። መንግሥት የሚያቅደው ከሥራ እድል ፈጠራ እና ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገት አንጻር ነው። የግሉ ዘርፍ ግን ስለእያንዳንዱ ዘርፍ በዝርዝር ያውቃል። ያም ሆኖ ለእኛ መልስ እየሰጡን አይደሉም።
የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ የሚከታተለውና ምላሽ የሚሰጥበት ብቸኛው ጉዳይ የነዳጅ ዋጋ ለውጥ ነው። ቀላል የሆነ አውቶማቲክ የኢኮኖሚ መለዋወጥን በዚህ ይጠብቃሉ። በገበያ ስርዓቱ ውስጥ በጥልቀት ሊፈጠር ከሚችለው መሠረታዊ ለውጥ ይልቅ ትንንሽ የምጣኔ ሀብት ለውጦች ላይ ያተኩራሉ። በእኛ በኩል ግን አሁንም ጥረት እያደረግን ነው።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ይፋ ባደረገችው አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ውስጥ ይህን የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትን ግቦች አካታለች?
የአገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው አሁንም ድረስ የተብራራ፣ በቁጥር የተደገፈና የተቀናጀ ሰነድ የተዘጋጀለት አይደለም። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ እንደውም የተሻለ የተብራራ ነው። ሆኖም መንግሥት በአንዳንድ ዘርፎች ላይ በአገር በቀል እቅዱ አቅጣጫ መሠረት እየወሰነ ነው። ይህ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ የዓለም ንግድ ድርጅት እና የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትን እንደ ውጪአዊ ተዋንያን ነው የሚያየው።

አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ማሻሻያው የአገር ውስጥ ስልታዊ እቅድ ነው። ስለዚህ የአገር ውስጥ ዘርፎችን ነው የሚደግፈው።
የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትን እና የዓለም ንግድ ድርጅትንም ለአገር ውስጥ ማሻሻያዎች እንደ ደጋፊ ነው የሚቆጥረው። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትን ተግባራዊነት በሚመለከት የትግበራ ስልቶችን አዘጋጅተናል። ይህም ስልታዊ እቅድ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ገበያ ስምምነትን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻልና ምን ዓይነት ተቋማትን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ መንገድ የሚያሳይ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 89 ሐምሌ 11 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here