የአዲሱ የትምህርት ዘመን እጣ ፈንታ በዘመነ ኮቪድ

0
958

ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ለመገናኛ ብዙሃን በጣም ቅርብ የሆኑ ትሁት እና አንጋፋ የትምህርት ባለሙያ ናቸው።የልዩ ድጋፍ ትምህርት እና የትምህርት ሎሬት ሲሆኑ፣ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ዝግጅት ላይ ላቅ ያለ ሙያዊ አበርክቶ እያደረጉ ያሉ ጉምቱ የዘርፉ ሊቅ ናቸው።
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የፍርሃት ቆፈን ባሰፈነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ሆነ በአገር ዐቀፍ ደረጃ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንዲሆኑ ተገደዋል።

በወረርሽኙ ድባብ ውስጥም ቢሆን ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት የቻሉ አገራት መኖራቸው ተስፋ የሰጠ ተግባር ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትም ወደ መክፈት መሄዳቸው ስለማይቀር ትምህርት ከመከፈቱ በፊት አስቀድሞ ምን ማድረግ ይገባል በሚል የአዲስ ማለዳው ዳዊት አስታጥቄ ከፕሮፌሰሩ ጋር ቆይታ አድርጓል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ትምህርት ላይ ያሳደረውን ተፅእኖ ለመቋቋም የተለያዩ አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ። በእኛስ አገር ወረርሽኙ በትምህርት ስርዓቱ ላይ ያስከተለን ጫና እንዴት መቋቋም ይገባል?
በኢትዮጵያ ደረጃ ትምህርት ቤት ከመከፈቱ በፊት እና ከተከፈተ በኋላ በሦስት መልኩ ዝግጅት መረግ አለበት።
የትምህርት ሚኒስቴር ራሱን የቻለ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጀምሮ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ የሚወርድ ግብረ ኃይል ማቋቋም ይኖርበታል። በግብረ ኃይሉ ውስጥም የትምህርት፣ የጤና፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ (ICT) ባለሙያዎች እንዲሁም የሥነልቦና ባለሞያዎችን ያካተተ መሆን ይኖርበታል።

ይሄ መሆን የሚገባው የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ችግር ዘርፈ ብዙ በመሆኑ ነው። ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር ያስከተለ ወረርሽኝ በመሆኑ በእነዚህ ባለሙያዎች መመራት ይኖርበታል።

በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በቤት ከወላጆቻቸው ጋር ነው ያሉት፣ እንዴት ባለ ሁኔታ ማሳለፍ አለባቸው ይላሉ?
በወረርሽኙ ሁሉም ተጠቂ ነው። ነገር ግን በአንድ በኩል ወረርሽኙ ይዞ የመጣው መልካም አጋጣሚ አለ። በሥራ አጋጣሚ ተወጥረው የከረሙ ስለነበር ወላጆች ለልጆቻቸው በቂ ጊዜ አልነበራቸውም። ስለዚህ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ከልጆቻቸው ጋር አብሮ በመጫወት ስለ ሥነምግባር፣ ባህል በመወያየት እንደ አቅማቸው ሊሠሩ የሚችሏቸውን ሥራዎች በጋራ በመሥራት የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲጨብጡ ማድረግ ተገቢ ነው።

ይህም በፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። የቤት ውስጥ ክህሎት (home skills) እንዲኖራቸውም ጥሩ ጊዜ ነው። ረጅም ጊዜ ስለበሽታው ከማውራት እንደነዚህ አይነት ተግባራት ላይ ማተኮር ሊኖር የሚችል የሥነልቦና ጫናንም ይቀንሳል። በአዕምሮ የነቁ እና የተዘጋጁ መሆን አለባቸው።

ይህን አይነት ዝግጁነት ከሌለ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ሊቸገሩ ይችላሉ። ልጆችም ትምህርት ቤት መሄድ ለመሄድ እንዲሁ።

መቼም የወረርሽኙ መስፋፋት ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱ አይቀርም። ይህ ከሆነ ደግሞ ትምህርት ቤት ይከፈታል። ስለዚህ የሚቋቋመው ግብረ ኃይል ምን ማድረግ አለበት? ምንስ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ይሆናል?
በመጀመሪያው ደረጃ ምንም አይነት ተግባር ከመጀመሩ በፊት አስቀድሞ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የዳሰሳ ጥናት መካሄድ ይኖርበታል። ግብረ ኃይሉ በአሁን ጊዜም መንግሥት እያደረገ ያለው ላይም መወያየት አለበት።

ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ትምህርት እየተሰጠ ያለው በርቀት በመሆኑ ግብረ ኃይሉ ይህንን መገምገም ይኖርበታል። ምን ያክል ተደራሽ ነው? ካልሆነስ ምን መደረግ አለበት ከሚለው ጀምሮ ሥራ ሊሠራ ይገባል። ይህንን ሁኔታ ከከተማ እስከ ገጠር ድረስ ዘልቆ መዳሰስ ይፈልጋል።

በኹለተኛ ደረጃ ግብረ ኃይሉ ሊሠራ የሚገባው ሥራ የትምህርት ቤት ወይንም የትምህርት ተቋማት አመራሮች ከቁሳቁስ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብአትን ከማሟላት እና ለትምህርት ዝግጁ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ እየተሠሩ መቆየት ያለባቸው ሥራዎች ይኖራሉ። ይሄ እንግዲህ የዝግጅት ጊዜ ነው።

ሁሉም ትምህርት ቤቶች ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ መፀዳጃ ቤት እና የመማሪያ ክፍሎች ዝግጁነት ጨምሮ መምህራን ሌሎች የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችንም አካቶ በጤናም፣ በሥነልቦናም መዘጋጀት ይገባል።

ከዚህ ሌላ የአካባቢን ማኅበረሰብ በመያዝ መወያየት እና ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ግድ ይላል። ትምህርት ቤት እንደ ድሮ አይሆንም። አሁን አዲስ ልማድ (ኒው ኖርማል) ስለሚሆን ለየት ባለ መልኩ ዝግጅት ማድረግ ይፈልጋል። ወረርሽኙ ሰዉን የተለየ ጫና ላይ ጥሏል፤ ወላጆችንም ልጆችንም(ለተማሪዎች)።

ትምህርት ቤት ሲከፈት ከቀድሞው በተለየ አኳኋን መሆን ይኖርበታል። ምንድነው የተለየ ሁኔታን የሚጠይቀው?
በ‹ኒው ኖርማል› እንደዚህ ቀደሙ ተማሪዎች መቀበል ሳይሆን በእንክብካቤ ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ መሆን አለበት።
በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ብዙ ጫና ያረፈባቸው ተማሪዎች ይኖራሉ። ለዚህ ነው ትምህርት ቤቶች ፈጣን ምላሽ በሚሰጥ እና አካታች በሆነ መልኩ መዘጋጀት የሚጠይቀው። የታመመ ካለ ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ፣ በበሽታው ቤተሰቡን ያጣ ካለ ድጋፍ ማድረግ፣ አካል ጉዳተኞችን በተለየ ሁኔታ ተቀብሎ ማስተናገድን ይጠይቃል።

ይህንን ማድረግ ከትምህርት ቤቱ ጥበቃ ሠራተኛ ጀምሮ በፍፁም ፍቅር ተቀብለው ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል። የትምህርት ቤቱ ርዕሳነ መምህራን እና መምህራን ጭምር በቂ ዝግጅት ማድረግ አዎንታዊ ከባቢን መፍጠር ይኖርባቸዋል።

በዚህ ‹ኒው ኖርማል› የትምህርት አቅጣጫው ቀደም ሲል ከነበረው እውቀት ተኮር ሥራ ወጣ ብሎ አጠቃላይ የተማሪዎችን ጤንነት እና ደኅንነት እንዲሁም ሥነልቦናዊ ትምህርት ላይ ያተኮረ መሆን አለበት። ከዚያ በኋላ ነው የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ማተኮር የሚገባው።

እዚያ ላይ የጤና ሚኒስቴር የሚሰጠውን የጥንቃቄ መመሪያዎች በፍፁም ቁርጠኝነት ለመተግበር ትልቅ ጥንቃቄ ያሻል። ለምሳሌ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ። ይህን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል መመካከር ያሻል።

የተማሪዎችን መግቢያ እና መውጫ ሰዓት እንዲሁም የእረፍት ሰዓትን ማለያየት፣ የባንዲራ ስነስርዓትን ማስቀረት፣ የፈረቃ ትምህርት ዘይቤን መተግበር እና ሌሎችንም አማራጮች ለመጠቀም እንደየአካባቢው እና የትምህርት ቤቱ ሁኔታ ለመተግበር የሚቋቋመው ግብር ኃይል አስቀድሞ መወያየት ይኖርበታል።

በአንድ መማሪያ ክፍል ውስጥ እስከ 60 የሚደርሱ ተማሪዎች በአንድ መቀመጫ ደግሞ 3 እና 4 ተማሪዎች ተቀምጠው አየተማሩ ባለበት ሁኔታ፣ አካላዊ መራራቅን እንዴት እውን ማድረግ ይቻላል?
አካላዊ መራራቅን በተለይ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ግብረ ኃይሉ ሊሠራ ከሚገባቸው ተግባራት ውስጥ ዋነኛው የትምህርት ቤቱን፣ የአካባቢውን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት አድርጎ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል መሥራት ነው።

ለምሳሌ የበሽታው ስርጭትም ሆነ የተማሪ ክፍል ጥምርታ ከቦታ ቦታ ይለያያል። ስለዚህ አንዳንድ ቦታ ቸኩሎ አለመክፈት ሊኖር ይችላል። የሚከፈትባቸው ቦታዎች ላይ እስከ ሦስት ፈረቃ ማድረግ ግድ ሊል ይችላል። ይህ እንግዲህ እስከ ወረዳና ትምህርት ቤት ድረስ የሚቋቋመው ግብረ ኃይል የዳሰሳ ጥናት ውጤት ነው የሚሆነው።

ይህ ሁሉ የሚደረገው ተማሪዎችን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሽታውን ይዘው ወደ ቤት እንዳይሄዱ እና ቤተሰቦቻቸው እና ማኅበረሰቡን እንዳይበክሉ ጭምር ነው።

በሚከፈትበት ጊዜ መፀዳጃ ቤት እና ውሃ አስፈላጊ ነው። ለዚህም በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባል። ከትምህርት ቤት ውጪ ያለው መስተጋብር ላይም ጥንቃቄ ይፈልጋል።
የሰብዓዊ ሁኔታ ማየት፣ የመምህርን ሁኔታ፣ የክፍል ውስጥ መማር ማስተማር ሁኔታ እና ምናልባትም ተማሪው ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ ቀጥታ ወደ ትምህርቱ ሳይሄዱ የሥነ ልቦና ትምህርት መስጠትን ይጠይቃል። እርስ በእርስ ተመጋግቦ መሥራትን፣ ተማሪዎችን ማዳመጥ፣ ‹understand caring time› የሚባል አይነት ሥነ ዘዴ ይጠበቃል ።

ሌላው በወላጆችና በትምህርት ቤት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነትን በተመለከተ ትልቅ ሥራ መሥራት ይገባል። በጋራ ውሃ እና መፀዳጃ ቤቶችን መገንባት ማስተካከልም ያስፈልጋል።

ተማሪዎችም ሲመጡ የሥነልቦና ጫና ውስጥ ሆነው ነው፡፡ ቤት ውስጥ የሞተ ወይም የታመመ ሰው ሊኖር ይችላል። የኢኮኖሚ ጫናው ውስጥ ሆነው ሥራ ያጡ ወላጆች ሊኖሩ ይችላሉ። ስለዚህ የመረዳት የመደገፍ ሥራ ያስፈልጋል።

ለዚህም ከወዲሁ ሥልጠና መስጠት ያሻል። ካለበለዚያ በተማሪና በመምህራን መካከል ግጭት ሊከሰት ይችላል። አንድ መምህር ከሚያስተምረው የትምህርት ዓይነት ውጪ በቂ የሥነልቦና ሥልጠና መውሰድ ይኖርበታል።

ትምህርት ቤት ተዘግቶ መቆየቱ በራሱ ለመምህራንም አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሮባቸዋል። ወደ ሥራ ሲመለሱ ደግሞ ተጨማሪ እና የተለየ ሥራ ይጠብቃቸዋል። ይህን አይነት አስቸጋሪ ሁኔታን ለመቋቋም ምን መደረግ አለበት?
መምህራንም እንደ አንድ የኅብረተሰብ አካል የበሽታው ድባብም ሆነ የኑሮ ውድነቱ ደቁሷቸው ነው ሥራ የሚጀምሩት። በዛም ላይ ደግሞ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። የፈረቃ ትምህርት ተግባራዊ ይሁን ከተባለ የተወሰነ ማበረታቻ ሊዘጋጅላቸው ይገባል።

ተማሪዎች ከተለያየ ቤተሰብ የሚመጡ እንደመሆኑ የተለያየ ደረጃ ጫና (level of stresses) ይዘው ስለሚመጡ፣ ይህ ደግሞ በተማሪዎች ዘንድ ልዩነት እንደሚፈጥር ተረድተው ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ለዚህም ተጨማሪ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ከሥነ ልቦና ሥልጠና ባሻገር የአይ ሲ ቲ ሥልጠና መስጠት ያስፈልጋል።
ምክንያቱም በኒው ኖርማል ትምህርት የተለየ ገፅታ ስለሚኖረው ምናልባትም በአካል ተገኝቶ ከማስተማር በተጨማሪ በቴክኖሎጂ ተደግፎ ማስተማር እና የትምህርት መርሃ ግብሩን መጨረስ ሊያስፈልግ ስለሚችል ነው። ለወደፊቱ ኹለቱንም የደባለቀ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ሊኖር ይችላል።

ሌላው በኒው ኖርማል የትምህርት ስርዓቱም አብሮ መለወጥ ይኖርበታል። በዚህም ትምህርት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሊሆን ይገባዋል። የቀረውን በርቀት ወይንም በሌላ ዘዴ መስጠት ይገባል።

በወረርሽኙ ምክንያት የትምህርት ስርዓቱ በብዙ ነገሮች ይቀየራል። ለአብነት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን የሚቀበሉበት ሁኔታና ምዘና እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችስ ምን መልክ ሊኖራቸው ይገባል?
የትምህርት ምዘና ስርዐቱም አብሮ ሊቀየር ይገባል። እንደዚህ ቀደሙ ማጠቃለያ ፈተና ሰጥቶ ‹አልፏዋል! ወድቀዋል!› ብሎ መወሰን ሳይሆን በተከታታይ የምዘና ስርዓት በየጊዜው እየተመዘኑ ክፍተቶቻቸው ላይ ድጋፍ እያደረጉ መሥራት ያስፈልጋል። እንዲሁም ሁሉም ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል እንዲያልፉ መሠራት ይገባል። ይህ ማለት ግን ዝም ብለው ወደሚቀጥለው የክፋ ደረጃ ይተላለፉ ማለት አይደለም።

ተማሪዎችን መጣል በወረርሽኙ ጫና ውስጥ ያሉ ወላጆችንም ሆነ ተማሪዎች ይበልጥ ሊጎዳ ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ብዙ አገሮች አጠቃላይ ግምገማ የሚባለውን ስርዓት ካስቀሩ ቆይተዋል። በተከታታይ የምዘና ስርዓት በየጊዜው እየተሰጠ ስለሚካሄድ መውደቅ የሚባል ነገር አይታሰብም። መውደቅ የሚባል ቃል እራሱ ቀርቷል።

በዚህ ዓመት ከብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች በስተቀር ሌሎቹ ወደሚቀጥለው የክፍል ደረጃ እንዲዘዋወሩ መደረጉን እንዴት አገኙት? የትምህርት ሚኒስቴርን ውሳኔ እንዴት አገኙት?
እንደሚታወቀው በወረርሽኙ ምክንያት ትምህርት አስቀድሞ መጋቢት ወር አጋማሽ ገደማ ዝግ ሆኖ ነው የቆየው። በዚህም የኹለተኛ ወሰነ ትምህርትን በርቀት እና በቴሌግራም በመላክ ሲሰጥ ነበር። ይህ ምን ያክል ተደራሽ እና ውጤታማ ነበር የሚለው ላይ እንደ ትምህርት ባለሙያ ተዐቅቦ አለኝ።

ምን ያክል ተማሪ ወይንም የተማሪ ወላጅ ዘመናዊ ስልክ አለው? የሚለውን የመብራት ሁኔታን ወዘተ ስናስብ ተገቢ ውሳኔ አይመስልም። ግን ደግሞ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለም።

አሁንም ቢሆን ግን የሚቀጥለውን የትምህርት ደረጃ ከመጀመራቸው በፊት መሠረታዊ የሚባሉ የትምህርት ይዘቶችን ማስተማር ያስፈልጋል። ከሌላው ጊዜ በተለየ የትምህርት ድጋፍም ያስፈልጋቸዋል።

ለብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችም ቢሆን ፈተና ከመውሰዳቸው በፊት መሠረታዊ እና አንኳር የሆኑ የትምህርት ይዘቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ካዘጋጁ በኋላ ፈተና መስጠት ይሻላል። በእርግጥ መንግሥት ማካካሻ እንዲሰጥ ወስኗል። ግን ማካካሻው አንኳር ጉዳዮች ላይ ብቻ ሊሆን ይገባል። የሚሰጠው ፈተናም ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆን ይገባዋል።

ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ ደግሞ ስለ ወረርሽኙ ተከታታይ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሠራት ይኖርበታል። ያውቃሉ ብሎ መተው አይገባም። ቤተሰብ ከሚነግራቸው በላይ ነቃ የማለት ነገር ይኖራል።

በዚህ ኒው ኖርማል (አዲሱ ነባራዊ ሁኔታ) ወላጆች ልጄ ሄዶ በሽታ ይዞ ሊመጣ ይችላል ብለው በመፍራት ልጆቻቸውን ላይልኩ ይችላሉ።
ትምህርት ቤትን ለመክፈት ብዙ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ካልሆነ ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ለዚህ ነው እንደ አሜሪካ ባሉ አገራት ፕሬዚዳንት ትራንፕ ትምህርት ቤት ለመክፈት ሐሳብ ሲያቀርቡ ብዙ የተቃውሞ ድምፅ የተሰማው።

በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት ደብተር እና ዪኒፎርም ወዘተ መግዛት የማይችሉ ቤተሰቦች ስለሚኖር ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀት ይገባል።
በትምህርት ስርዓቱ ለአይ ሲ ቲ ትምህርት ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ማድረግ እንዳለብንም ትምህርት የሰጠ ነው። እንኳን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ቀርቶ ዩኒቨርስቲ የሚገቡ ተማሪዎች እንኳ በትክክል ኮምፕዩተር ነክቶ የሚያውቅ እና ኢሜል መላላክ እንኳን በቅጡ የማይችሉ ስላሉ፣ በቂ ትኩረት ይፈልጋል። መምህራን እንዲሁ ማብቃት እንዳለብን ይሰማኛል። መምህራን በሚገባ ማበረታታት ያስፈልጋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here