ከደረጃው ዝቅ የተደረገም ሆነ ደሞዙ የተቀነሰበት የቅድመ መደበኛ ርዕሰ መምህር የለም -ትምህርት ቢሮ
ቁጥራው ከ180 በላይ የሚሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአስሩም ክፍለ ከተማ የሚገኙ የቅድመ መደበኛ ርዕሰ መምህራን ከመመሪያ ውጭ ከደረጃችን ዝቅ ተደርገን ደሞዛችንም እንዲቀነስ ሆኗል ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ሀብት ልማት ቢሮ በሰጣቸው የመደብ መታወቂያ ቁጥር ሕጋዊነት መሰረት ከ2007 ጀምሮ በደረጃ እድገት መመሪያ መሰረት ተወዳድረው እድገትም አግኝተው እየሠሩ ነበር። በታህሳስ 17 /2012 የፌደራል ፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ምደባ የሰጠ ሲሆን በዚህም የመምህራን፣ ርዕሳነ መምህራንና ሱፐር ቫይዘሮች የJEAG ምዘናና ደረጃ ምደባ ሰጥቷል። ለቅድመ መደበኛ ርዕሳነ መምህራን ምደባ ሳይሰጥ ለ8 ወራት ያህል ያለምንም መፍትሄ እየተጉላላን ነው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
‹‹ለጊዜያዊነት ከደረጃችን ዝቅ ብለን ቦታውን በማስተባበር ከደሞዛችንም ተቀንሶ እንድንሰራ ተደርገናል፤ ይህም አግባብነት የሌለው ነው፤ አንድ ሰራተኛ ጥፋት ሲያጠፋ እና መመሪያው በሚያዘው መልኩ ነው ከስራ ዝቅ የሚደረገው እኛ ግን ከደረጃችን ዝቅ እንድንል ተደርገናል›› ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የቅድመ መደበኛ ርዕሰ መምህርነት መደብ ተመዝኖ ከመጣ በውድድር ብቻ ብልጫ ካገኛችሁ በርዕሰ መምህርነት ተመድበው መስራት ይችላሉ መባላችንም ተቀባይነት የለውም። ስለሆነም እኛ ተወዳድረን የተቀጠርን በመሆናችን በድጋሚ ትወዳደራላችሁ መባል ተገቢ አይደለም ብለዋል ቅሬታ አቅራቢዎቹ።
በ2012 በተደረገው ጥናት ሁሉም የሥራ መደብ የተቀመጠለት ሲሆን በአዲስ አበባ የሚገኙት የቅድመ መደበኛ መደብ ሳይቀመጥ በእኛ በኩል እስኪጠና ጠብቁ ተብለናል ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
እኛ የፖለቲካ ሹመኛ አመራር አይደለንም የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች እኛ አሁን መደቡ ተጠንቶ ቦታችን ላይ ሆነን ነው መቀጠል የምፈልገው ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ዘላለም ሙላቱ እንደሚያነሱት ደግሞ ማንኛውም በፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች ደረጃ እንዲወጣላቸው ተደርጎ የመደበው ለሁሉም መደብ ያስቀመጠውም የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሲሆን የቅድመ መደበኛ ርዕሰ መምህራን ምደባ አልወጣም፡፡ ያልወጣለት ምክንያትም የቅድመ መደበኛ ርዕሳነ መምህራን የሚገኙት በአዲስ አበባ ላይ ብቻ የሚገኙ በመሆናቸው እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
በእኛ በኩል ትምህርት ሚኒስቴር ላይ ግፊት እያደረግን ነው ጥያቄያው ተገቢ ነው ነገር ግን ውድድር ግቡ ተብለና ማለታቸው ተገቢ አይደለም እኛ በሌለ መደብ እንዴት ነው የምናወዳድራቸው ሲሉም ምላሻቸውን ሰጥተዋል።
በመሆኑም አሁን ስራቸውን በማስተባበር እና ሲቪል ሰርቪስ ባወረደው አቅጣጫ በኃላፊነታቸው መቀጠል ይችላሉ ብለዋል ዘላለም።
በመሆኑን በአደስ አበባ ትምህር ቢሮ በኩል የአደስ አበባ ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ በጋራ በመሆን ደረጃውን በአስቸኳይ እንዲያወጣ ጠይቀናል፡፡
ተጠንቶ እስኪመጣ ድረስ ሰርኩላር በማድረግ ለጊዜው ግን እንደ መፍትሄ አቻ መመህራኖቻቸው በደረሱበት ደረጃ ጥቅማ ጥቅማቸውን እንዲያገኙ ነው ያደረግነው፡፡ ከደረጃችን ዝቅ ብለናል ማለታቸው ግን ስህተት ነው ፡፡
ጥያቄያቸውን ግን ለትምህርት ቢሮ እና ለፐብሊክ ሰርቪስ ልከናል ጥናቱ ሲጠናቅ መፍትሔ እንዲያገኙ ይደረጋል ያሉት ዘላለም፤ ደረጃው ሳይጠና ተወዳደሩ የሚል ነገር አልመጣም መደቡ ተጠንቶ እና ጸድቆ ሲመጣ ሁኔታዎች የሚፈቱት ይሆናል ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 96 ነሐሴ 30 2012



