ዘመናዊው የቄራ ግንባታ በሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ምክንያት ተስተጓጎለ

0
423

በ2012 ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ነበረበት

የአዲስ አበባ የቄራዎች ድርጅት በሃና ማርያም አካባቢ ሊያከናውነው የነበረውን ዘመናዊ የቄራ ግንባታ በሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ምክንያት ግንባታውን ለመጀመር መቸገሩን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ። ባጠናቀቅነው የ2012 በጀት ዓመት ግንባታው ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም በሕገ- ወጥ መሬት ወረራ ምክንያት ግንባታው እስከአሁን አለመጀመሩን ድርጅቱ ለአዲስ ማለዳ አስታወቋል።

ግንባታውን ለማከናወን ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ያሉት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሰኢድ ኢንድሪስ፤ ለግንባታው የአማካሪ ድርጅት መረጣ ተከናውኖ በእኛ በኩል የወሰንን ቢሆን ቀጣይ ስራዎች ለመከወን ግን የግድ የመሬቱ ጉዳይ መፍትሔ እንደሚስያስፈለገው ነው የጠቆሙት።
የአማካሪ መረጣው ቢጸድቅም ከድጅቱ ጋር የስምምነት ፊርማ አልተፈራረምንም ያሉት ሰኢድ ምክንያቱ ደግሞ የመሬቱ ባለቤትነት ማረጋገጫ ባለመገኘቱ ትልቅ እንቅፋት ስለሆነባቸው እንደሆነ ሰዒድ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልጸዋል።

ሃያ ሔክታር በሚሰፋውእና ለቄራዎች ድርጅት ተብሎ የተወውን መሬት የከተማ አስተዳደሩ አጸድቆ በሰጠን መሰረት ቦታውን አጥረን ወደ ተግባር ልንገባ ስንል ህጋዊ ነን የሚሉ 52 አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጆች ነዋሪዎች ቦታው ላይ ያሉ ሲሆን በኋላ ግን ወደ 6መቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች በቦታው ላይ መስፈራቸውን ነው የገለጹት።
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደር አመራር መቀያየርም ተክትሎ እና ለውጡ ከመጣም በኋላ ቦታው ላይ የሰፈሩ ሰዎች እንዳሉ ቢታወቅም ቀድመው የነበሩ ናቸው ወይም አይደሉም የሚለውን ለመመለስ ግን ጥናት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያስታወቁት።

በዚህ ዙሪያም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከከላፍቶ ክፍለ ከተማ እና ከነዋሪዎቹ ጋር በጋራ ሆነን ወይይት አድርገን ነበር ያሉት ሰኢድ፤ ነዋሪዎቹም የከተማ አስተዳደሩ በሊዝ አዋጅ መስተናገድ ያለበት ተለይቶ በሊዝ አዋጅ ያስተናግደን የሚል የመፍትሔ ሃሳብ አቅርበው እንደነበርም አስታውቀዋል።
በአሁን ወቅት ቦታው ላይ ያሉትን ሰዎች ተገቢውን መፍትሔ እንዲሰጣቸው እና አስፈላጊው ካሳ ከተሰጣቸው ሊነሱ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መግባባት ላይ ደርሰን ለካቢኔ ጥያቄውን አቅርበን ነበር ሲሉም ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ከነዋሪዎች ጋር መገናኘት ስላልተቻለ በቀጣይ ከነዋሪዎች ተወካዮች ተመርጠው ችግሩን በመነጋገር እንዲፈታ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም የካቢኔውን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ሰኢድ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ሊያስገነባ ያቀደው ዘመናዊ የቄራ ግንባታው ሲጠናቀቅ ለ1ሺ 500 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ይጠበቃል። የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በአሁን ወቅት 1500 ቋሚ ሠራተኞች እንዳሉት ከድርጅቱ ለማወቅ ተችሏል።  የፕሮጀክቱ ግንባታ ከ2009 ጀምሮ እስከ 2012 ለማጠናቀቅ የታቀደ ቢሆን አሁን ችግሩ መፍትሔ ባለመገኘቱ ግንባታው እንዳልተጀመረ ከድርጅቱ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ፕሮጅክቱን ለመገንባት ከፈረንሳዩ የልማት ድርጅት 70 ነጥብ 5 ዩሮ ድጋፍ የተገኘ ሲሆን ተጨማሪ ወጪዎች ካሉ ግን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል ወጪው ሊሸፈን እንደሚችል ሰኢድ አስታውቀዋል። በዘመናዊው ቄራ ግንበታ ውሰጥ የእርድ አገልግሎትን ታሳቢ በማድረግ ተረፈ ምርቶችን ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ፣በባዮ ጋዝ ኃይል የእንስሳት ገበያን እና የቄራውን ስራ ተመጋጋቢ ለማድረግ ታስቦ ግንበታን ለማከናወን ውጥን ተይዞለት ነበር። ግንባውን ለማከናወን ከከተማ አስተዳሩ የተሰጠው ቦታ 20 ሄክታር ነበር።

ቅጽ 2 ቁጥር 97 መስከረም 2 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here