የሴቶች ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር የአድራሻ ለውጥ አደረገ፤ በወር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለቢሮ ኪራይ ይከፍላል

0
713

የሴቶች፣ ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ይገለገልባቸው የነበሩ ሦስት ቢሮዎችን በመልቀቅ በአንድ ህንጻ ላይ መሥራት እንዲችል አዲስ ቢሮ መከራየቱን ገለጸ።

ከዚህ ቀደም የሚኒስቴሩን ሦስት ዘርፎች ሠራተኞቻቸው በተለያየ ቢሮ የሚሠሩ ሲሆን፣ አሁን ግን በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሴኤ) ጀርባ በሚገኘው ‹‹ቤተ ብርሃን›› በተባለ ሕንጻ ላይ አዲስ ቢሮ መከራየቱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የቢሮውን ኪራይ ከስምምነት ላይ የተደረሰው በነሐሴ ወር 2012 ጀምሮ ሲሆን፣ የቢሮው አጠቃላይ ስፋት አራት ሺሕ ካሬ ሜትር እንደሆነም በሴቶች ወጣቶች እና ሕጻናት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አድነው አበራ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ለኪራይ ስንት ያወጣ እንደነበር አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ፣ ብሩን ለመግለጽ በመቆጠብ፤ በአሁን ወቅት ግን በካሬ ሜትር 300 ብር እንደተከራየ ነው ያስታወቀው። ይህም ማለት የሴቶች፣ ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴር በአንድ ወር ለቢሮ ኪራይ ብቻ 1 ሚሊዮን 200 ሺሕ ብር እንደሚያወጣ ለማወቅ ተችሏል።

በሚኒስቴሩ ውስጥ የሚገኙ የሴቶች ዘርፍ፣ የወጣቶች ዘርፍ እና የሕጻናት ዘርፍ በአንድ ሕንጻ ላይ ሁሉንም አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተከራይተው በተናጠል እንደሚሠሩም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በሦስት ዓመታት ውስጥ የራሱ ሕንጻ ለማስገባት በመንግሥት በኩል ውጥን የታያዘለት መሆኑን የገለጹት የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዋና ኃላፊ አድነው፣ ‹‹ከዚህ በፊት የተከራየናቸው ቢሮዎች አንዳንዶቹ ከጤና አንጻር አመቺ አልነበሩም፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለኪቪድ 19 አጋልጠው የሚሰጡ በጣም የተጨናነቁና ጠባብ በመሆናቸው ቢሮ እንድንከራይ አስገድዶናል።›› ሲሉ የቢሮውን መከራየት አስፈላጊ ምክንያትነት ጠቅሰዋል።

የቢሮው መከራየት በተለይም ሠራተኛው በአንድ ላይ ሆኖ እንዲሠራ ከማድረግ ባሻገር ሥራዎችን በጋራ ለመገምገም አዳጋች መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስረድተዋል። አክለውም ‹‹ከቢሮ ጥበት የተነሳ ሠራተኛውን በፈረቃ እስከማሠራት ደርሰን ነበር›› በማለትም አስታውሰዋል።

በአሁን ወቅት በሚኒስቴሩ ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ቁጥር አራት መቶ እንደሚሆን የገለጹት አድነው፣ እስከ ዛሬ ድረስ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱም ዘርፎች በአንድ ላይ ሆነው ሠርተው አያውቁም ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩት የሴቶች፣ ወጣቶችና ሕጻናት ሚኒስቴርን በኃላፊነት የመሩት ሚኒስትሮች በተለያየ ቦታ ተበታትኖ ይሠራ የነበረው ሠራተኛው በአንድ ቢሮ እንዲሠራ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት አድነው፤ ከብዙ ልፋት በኋላ የተሳካው ግን አሁን ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ በተከራየው ሕንጻ ላይ ለሠራተኛ ቢሮ ከማዘጋጀት በተጨማሪም ሠራተኛው አጫጭር ሥልጠናዎችን እንዲያገኝ የሚያስችል መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዳለው ጠቁመዋል።

‹‹ከዚህ ቀደም ለሚኒስቴሩ ሠራተኞች አዲስ አበባ ውስጥ ለሚሰጡት የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎች ለመስጠት የግድ ሆቴሎች እና አዳራሽ እንድንከራይ ያስገድደን ነበር።›› ያሉት አድነው፣ አሁን ግን ተጨማሪ ወጪ እንዳናወጣም ይታደገናል ነው ያሉት። በአሁን ወቅት ሚኒስቴሩ የተከራየውን አዲስ ሕንጻ ለሠራተኞች እና አገልግሎት ለሚሰጣቸው አጋር አካላት ምቹ ለማድረግ የተለያዩ የጥበብ አውደ ርዕይ ስፍራዎችን ለማዘጋጀት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም አንስተዋል።

እንዲሁም የሕጻናት መዋያ ወይም ‹‹ዴይኬር›› አሁን ላይ በኮቪድ 19 ምክንያት አገልግሎት እየሰጠ ባይሆንም፣ በሚኒስቴሩ በኩል ይህንን ለማስጀመርም እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ አድነው አያይዘው አስታውቀዋል። በአሁን ወቅት ሁሉም የሚኒስቴሩ ሠራተኞች ከነበሩበት የተለያዩ ሦስት ሕንጻዎች ላይ መልቀቃቸውንና ወደ አዲሱ ቢሯቸው ማቅናታቸውንም አድነው ገልጸዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here