የሩብ ዓመቱ የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ በተገኘ ብድር መሸፈኑ ተገለፀ

0
419

በ2013 ባለፉት ሶስት ወራት በነበረው የፋይናንስ አፈፃፀም ሂደት ላይ ያጋጠመውን የበጀት ጉድለትን ለመሙላት መንግስት አንዳች የሆነ ብድርን ከውጭ አበዳሪዎች እንዳልጠየቀና ጉድለቱን ለመሸፈን ከብሄራዊ ባንክ ወጪ በማድረግ በግምጃ ቤት ሰነድ አማካኝነት ከግል ባንኮች በመበደር እንደተሸፈነ የገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ አስታወቁ።

የመጀመሪያው ሩብ አመት እንደተፈራው ሳይሆን አውንታዊ የሆነ አድገት መታየቱን የፋይናንስ ሚኒስቴሩ አህመድ ሽዴ ያስታወቁ ሲሆን መንግስት ኮሮናንም እየተዋጋ በሩብ ዓመቱ ከወጪ ንግድ 499.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንዳገኘ ያሥታወቁት ሚንስትሩ በገቢ ደረጃ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 80.8 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ እንደተሰበሰበና፤ 97 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገ ገልፀዋል። በታክስ ገቢ አሰባሰቡ ላይ ከታየው እመርታም አንዱ በኤክሳይስ ታክስ ላይ እየተተገበረ ባለው የአሰራር ስርዓት የመጣ እንደሆነ ሚንስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊትም ይጠበቅ እንደነበረው በ2013 ዓ.ም የበጀት ዘመን የኮሮና በሽታና የበረሃ አምበጣ በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ መከሰቱን ተከትሎ ኢኮኖሚው ላይ የመንገጫገጭና ከዚህ ቀደም እንደነበሩት የበጀት ዓመታት የበጀት ጉድለት አንዱ ችግር ሆኖ ሊከሰት እንደሚችል የተጠበቀ ሲሆን ፤ ከዚህ ቀደም የሚያጋጥመውን የበጀት ጉድለት አብዛኛውን ጊዜ ከሁለትዮሽ የብድር ምንጮች እና ከበይነ መንግሥታት የገንዘብ ተቋማት በሚገኝ ገንዘብ ሲሸፈን እንደነበር የሚታወቅ ቢሆንም ። በ2013 በጀት ዓመት ግን አብዛኞቹ ብድር አቅራቢ ሀገራት ራሳቸውም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመቋቋም ጥረት በማድረግ ላይ እንደመሆናቸው መጠን ሌሎች ድጋፍ የሚሹ ሀገራትን ለመደገፍ አቅም የላቸውም ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

መንግስት ኮሮናን ለመካላከል በጀርመንና ጃፓን መንግስታት ከተደረገለት የ131 እና 13 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ውጪ በሩብ አመቱ ውስጥ 447.6 ሚሊዮን ዶላር ጠቅላላ ድጋፍ እንዳገኘ ያስታወቁት የፋይናንስ ሚንስቴሩ ይህም መንግስት እየተገበረ ላለው ገበያን የማረጋጋትና የዋጋ ግሽበት የመቀነስ ተግባር ትልቅ ሚና እንዳለው አህመድ ሽዴ ጨምረው አስታውቀዋል።

ሀጂ ኢብሳ የገንዘብ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት ከሆነ እንደ ሩብ ዓመት የታየው የበጀት ጉድለት የጎላ አለመሆኑና የኮቪድ-19 በሽታ እና ሌሎችም ቸግሮች እንዳሳደሩት ጫና ክፍተቱ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችል ነበር ብለዋል።መንግስት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ብድር አቅራቢዎች የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ያደረገው እንቅስቃሴ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለውና የውጭ ብድር ጫና ከመቀነስ አንፃር የሚበረታታ ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

አሁን ላይ መንግስት የውጭ ብድር ጫና ከመቀነስ አንፃር የተለያዩ አማራጮችን እየወሰደ ያለ ሲሆን ብዙዎቹ ከውጭ አገራት ጋር በተገናኘ እየተገኙ ያሉ ድጋፎች በእርዳታ መልክ እየተደረጉ ያሉና ብድርም ቢሆን እንኳን በልዩ ሁኔታ በሚታይ መልኩ እየቀረቡ ያሉ ናቸው ሲሉ ሀላፊው ገልፀዋል።

አጠቃላይ የሀገሪቱ የበጀት ጉድለት በ2013 ዓ.ም 125 ቢሊዮን ብር እንደሆነና ይህንንም ለመሙላት ከሀገር ውስጥና ከውጭ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን ሲሆን ከዚህ ውስጥ 78 ቢሊየን ብሩ ከሀገር ውስጥ የተለያዩ ምንጮች በብድር የሚሰበሰብ ሲሆን ቀሪው የበጀቱ አካል ደግሞ ከውጭ አበዳሪዎች እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ጨምረው አስታውቀዋል።

መንግስት በ2013 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ሥራዎችና አገልግሎቶች የሚያስፈልገውን ጠቅላላ ብር 476 ቢሊየን 12 ሚሊየን 952 ሺህ 445 እንዲሆን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንዲተላለፍ ማፅደቁ ይታወሳል።

ሄኖክ ሰማው (ረ/ፕ) በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ሲሆኑ መንግስት ከሀገር ውስጥ በተገኘ ብድር የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ያደረገውን ጥረት የሚበረታታ ነው ያሉ ሲሆን ነገር ግን ይህ አማራጭ ለአጭር ጊዜ የሚያገለግል እንጂ ዘላቂ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።መንግስት ከሀገር ውስጥ ባንኮች መበደሩ የሌሎች ባላሀብቶችን ብድር የማግኘት እድል የሚሻማና በተለይም አነስተኛ ተቋማት በግል ባንኮቹ የሚያቀርቡት የብድር ጥያቄ ቶሎ እንዳይመለስ ሊያደርግ የሚችል ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰንዝረዋል። እንደ ባለሙያው እምነት ከሆነ መንግስት ሀብትን አብቃቅቶ መጠቀምና ወለድ የማይታከልባቸውን የውጪ የብድር አቅርቦቶችን መፈለግ አለበት ብለዋል ሄኖክ።

ቅጽ 2 ቁጥር 102 ጥቅምት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here