አዳዲስ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ተደራሽነታቸው ተገምግሞ ፍቃዳቸው እንደሚታደስ ተገለፀ

0
719

ወደ አገር ውስጥ ገብተው በቴሌኮም አገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩት ኹለት ኩባንያዎች አገልግሎቱን ማቅረብ ከጀመሩበት ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ መጨረሻ ምን ያህል ተደራሽ ናቸው የሚለው ጉዳይ ታሳቢ ተደርጎ ፈቃዳቸው እንደሚታደስ ተገለጸ።

ይህንንም ተከትሎ የተጠበቀውን ያህል ያልተንቀሳቀሰ ኩባንያ ፍቃዱን እስከመንጠቅ የሚያደርስ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ዝግጅት እንደተደረገ የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሦስት ወር ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ዋና ዳይሬክተሩ ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) እንዳስታወቁት ባለስልጣኑ በያዝነው ወር መጨረሻ አሊያም በህዳር 2013 መጀመሪያ ላይ ጨረታው ወጥቶ ከተለያዩ ግምገማዎች በኋላ በመጪው መጋቢትና ሚያዚያ ወር አሸናፊው ይታወቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የኹለት ቴሌኮሙኒኬሽን ኦፕሬተሮች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል የሬጉላቶሪ ማዕቀፍ እና እስትራቴጂያዊ መርህ እንዳዘጋጀ አስታውቀዋል።

ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት አንዱ የሆነውን የኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ ለሚሰማሩ ፈቃድ መስጠት፣ መቆጣጠር፣ ፈቃድ ማሻሻል፣ ማደስ፣ ማገድ ወይም መሰረዝ ሲሆን።ይህን መሰረት በማድረግ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚያቀርቡት አገልግሎት ጥራት በመመሪያው ውስጥ የተቀመጡትን መስፈርቶች በመጠቀም በየጊዜው የሚለኩና አፈፃፀም ደረጃቸውም ተገምግሞ በአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነታቸው ልክ የፍቃድ ማደስ ሂደቱም እንደሚጤንና ርምጃም እንደሚወሰድ ሃላፊው አስታውቀዋል።

ባልቻ አክለውም ኦፕሬተሮቹ ወደ አገር ገብተው ሥራ ሲጀምሩ የዋጋ ቁጥጥር ስርዓት ይዘረጋል ያሉ ሲሆን ይህም ኦፕሬተሮች የታሪፍ ዋጋን አላግባብ እንዳይጨምሩም ሆነ እንዳይቀንሱ ያደርጋል ብለዋል።ከዚሁ ሁሉ በላይ በዋናነትም የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ታሪፍ መመሪያ በማዘጋጀት ተገልጋዮች ለሚጠቀሙት አገልግሎት ተመጣጣኝና ተገቢ ክፍያ የሚጠየቁበትን ሁኔታ ይፈጥራል።በተጨማሪም የባለስልጣኑ የውድድር መመሪያ ማዘጋጀት በቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች መካከል አግባብነት ያለው የገበያ ውድድር ስርዓት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል።

በሳምንቱ መጀመሪያ በተመሳሳይ የቴሌኮም ዘርፍ የማሻሻያ ስራዎች ሂደት ላይ ያተኮረ ውይይት በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተካሄደ ሲሆን በውይይቱም የአዳዲስ ኦፕሬተሮች መግባት ከፍተኛ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር ይጠበቃል የተባለ ሲሆን ለዚህም በጨረታው ሂደት አንድ ኦፕሬተር በተገደበ ጊዜ ውስጥ የት መድረስ እንዳለበት ተቀምጧል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንዳሉት ኦፕሬተሮቹ በመጀመሪያው ዓመት 25 በመቶ ያክል ተደራሽነታቸው መስፋት አለበት የሚለው ቅድመ-ሁኔታ በጣም ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል እንዲቀጥሩ ያስገድዳቸዋል ብለዋል።ይህም ፍቃድ ይዘው ገብተው በትንሽ ቦታ ተወስነው እንዳይቀሩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

ለሚሰጡት አዲስ ፍቃዶች የግብይት አማካሪ የመቅጠር እና ወደ ስራ የማስገባት ስራ መከናወኑን የገለፀው የኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ኹለቱ ካምፓኒዎች ጨረታውን አሸንፈው ወደ ስራ በሚገቡበት ወቅት በኢትዮ-ቴሌኮም ተደራሽነትና ሽፋን ያልተሰጣቸው ቦታዎች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ይደረጋል ተብሏል።በተጨማሪም የኦፕሬተሮቹ አገልግሎት ትምህርት ቤቶችን፣ ዩኒቨርስቲዎችን፣ የጤና ተቋማትንና የግብርናውን ሴክተር መደገፍ ከሚችሉበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ መሰራት የሚችልበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ እንዳለ ባልቻ አስረድተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ በሦስት የቴሌኮሙኒኬሽን ኦፕሬተሮች ይሰጣል ተብሎ በሚጠበቀው አገልግሎት ስራዎች ለቁጥጥር አመቺነታቸው ከፍ ይላል ያሉት ባልቻ ደንበኞች ነባር ቁጥራቸውን ሳይቀይሩ ወደ ሌላ አገልግሎት ሰጪ መዛወር የሚችሉበት አሊያም በነባር ቁጥሩ ከሦስቱም አገልግሎት አቅራቢዎች አገልግሎትን ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ እንሚፈጠር አስታውቀዋል።

አይ ኤፍ ሲ፣ ኮሊያጎ፣ ጆንስ ዴይ፣ ኧርነስት ኤንድ ያንግ እንዲሁም ጎንግ ኮሚኑኬሽን የተባሉት አለምዓቀፍ ኩባንያዎች ለሚሰጡት አዲስ ፍቃዶች የግብይት አማካሪ ሆነው ተቀጥረዋል ተብሏል።እስካሁን ለኦፕሬተርነት ፍቃዱ 12 ፍላጎት ያላቸው ድርጅቶች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከዚህም ውስጥ ዘጠኙ በቴሌኮም ኦፕሬተርነት የተሰማሩ፤ ኹለቱ የቴሌኮም ኦፕሬተር ያልሆኑና አንድ የኢንቨስተሮች የሽርክና ቡድን መሆናቸው ታውቋል።”ዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ በሚል ጥምረት ቮዳፎን፣ ቮዳኮም እና ሳፋሪኮም በአንድ ላይ”፣ ኢቲሳላት፣ ኤም ቲ ኤንና ኦሬንጅ ለፍላጎት መግለጫ መጠየቂያው ምላሽ በመስጠት ፍላጎታቸውን ካስተወቁት መካከል እንደሚገኙበት ባለስልጣኑ አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here