ዜጎችን መጠበቅ ያልቻለ መንግሥት እንዴት ሌሎችን መክሰስ ይቻለዋል !!!

መከሰስ ያለበት ሃገር እየመራ ያለው መንግስት ወይንስ የማናውቀው ኦነግ ሸኔ ?

የ2010 ለውጥን ተከትሎ የአብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት የበርካታ ለውጥ ፈላጊ ድምጾች እፎይታ የሰጠ ጉዳይ ነበር። ይሁንና እፎይታው ፀሀይ እንደበረታበት ጉም ቀስ በቀስ ሳስቶ ሳስቶ ባዶ ከመሆኑም የተነሳ የዜጎች የመኖር ህልው በከፋ ሁኔታ ሊያሽቆለቁል ችሏል አልፎ ተርፎም ሞት ሲበረታ፤ ብሔር ተኮር ጥቃት ሲባባስ እና በእርስ በእርስ ሽኩቻ የዜጎች መፈናቀል ለማተናገድ ጊዜ አልወሰደበትም። ጭራሽ ዜጎች የሚተማመኑበት መሪ በማጣት የሰቆቃ ሕይወትን ጋዜጠኛ ጁሀር ሳዲቅ እንዲህ አትቶታል

በመጀመሪያ ደማቸው ደመ ከልብ ለሆነው በገዛ አገራቸው ከመተከል እስከ ጉራፈርዳ… ጉድሩ ….እና የሰሞነኛው የጉሊሶ ወረዳ ጭፍጨፋ በጥብቅ እያወገዝኩ የተሰማኝን ሀዘን እገልፃለሁ ..በመቀጠል ማነው አገር እየመራ ያለው ?.ይሔን ኹሉ አገራዊ ምሥቅልቅል ከምን ሊመጣ ቻለ ? ምንሥ መደረግ አለበት ? የመሉትን ጥያቄዎች አሳጥሬ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ትኩረት አድርጎ ምክክር ያሥፈልገናል፤ እና የዜጎች ሞት ይብቃ ሥል በዚህ ፅሑፌ አሳሥባለሁ ።ሕወሐት ከሥልጣን ተወግዶ ብልጽግናው ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት አልታየም ለዚህ ደግሞ ሕወሐትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚቸኩሉ አሉ ሆኖም አገራችን የተከተለችው የሽግግር ሂደት ድርድርን ውይይትን እና ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመረኮዘ እንዳልነበር በርካቶች ይሥማማሉ። እኔም እሥማማበታለሁ እዚህ ላይ የሕወሐት ሚና ትንሽ ነው እሱም የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ ነው። ታዲያ በዚህ የተነሳ ዜጎች በብሔራቸው፤ በሃይማኖታቸው፤ በማነነታቸው፤ ሲገደሉ፤ ሲፈናቀሉ ማየት ቀሥበቀሥ እንደ የመናውያንና ሶርያውያን እየተለማመድነው የመጣ ኹነት ሆኗል። መጀመሪያ አካባቢ የሽግግር ሂደት ላይ ያጋጥማል እንታገሥ የሚሉ የተወሰኑ ምኹራን ድጋፋቸው ለአዲሱ ሀይል ሆኖ ጊዜ እንሥጠው ሲሉ እሥኪ እንየው ብለን ተሥማምተን ነበር። ሆኖም ግን አኹን የብልጽግናው ደም በሶፍት ማፅዳት ግን ከገዳይም በላይ ነውና ከንግዲህ ተቀባይነት የለውም።ምክንያቱም ብልጽግናው ከበቂ በላይ መዋቅር ሰርቷል ።……ይህንን በደንብ እናውቃለን…..ሥለዚህ የፖለቲካ ድጋፍ ካልሆነ በቀር እነዚህ የመሰሉ እንዝላልነት ለዜጎች መሞት ምክንያት ሆኗል ማለትእችላለሁ።

…በትንሹ አዲሱ ዓመት ከያዝን ጀምሮ በጥቂት ወራቶች ብቻ በርካታ ዜጎቻችን ተገድለዋል፤በርካቶችም ተፈናቅለዋል፤ በጣም የሚያሥቀው የብልጽግናው ተላላኪዎች እና ባለሥልጣናቶች ለነዚህ ድርጊቶች የሚያነሱት ክሥ ነው። ይገርምላችኋል ሕወሐት የሚባለው እኔም የምሥማማበት አፋኝ ነበር። የሚታወቅ ነገር ነው። ግን ተሸንፎ መቀለ የከተመ ድርጅት ነው። …. ደግሞም አከርካሪው መተነዋል፤ ..ተሸንፎ ፈርጥጧል፤ ብለው ያረጋገጡልን ራሳቸው ብልጽግናዎች ናቸው ታዲያ ሁሌ ክሳቸው የሕወሐት እጅ አለበት የሚሉት ነገር ነው የሚገርመው። ተራ አሉባልታ መሆናቸውና አብዛአኛዎቹ ክሶች ምንም አይነት ማረጋገጫ የሌለው መሰረተ ቢሥ መሆኑ ነው።

ሌላው ሕወሐት ወደ ሥልጣኑ ለመምጣት ነው ብለው ወሬው የዜና ሟሟሻ የሚያደርጉት ነገር ይገርማል። ሕወሐት ወደ ሥልጣኑ መመለሥ ላያሥብ ይችላል ብዪ አልልም። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለቀ/ከጨረሰ በኋላ ሊሆን ይችላል። ሥለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጭራሽ አያሥበውም….ይሕ ማለት ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ብልጽግናውን ይወዳል ማለት አይደለም። ምክንያቱም አኹን ላይ ገዥው ፓርቲ ከቀድሞ ሕወሐት የተለየ ነገር እንደሌለው፤ አገር ሕዝብ መጠበቅ ዴሞክራሲ ማሥፈን እንዳልቻለ ደግሞ መካድ አይቻልም።በመጀመሪያ የሕወሐት ጉዳይ ፈፅሞ እንዳያበቃ እንዳያልቅ የሚፈልገው ራሱ ብልጽግና መሆኑ ነው። የፌደረሽን ምክር ቤት ለበርካታ ጊዜ ውሳኔዎች ወሥኖ በተደጋጋሚ ሀሳባቸው እንደ እሥሥት ሲለዋውጡ ተሥተውሏልም። ሶማሊን ክልልን ሲመታ ያልታየው የሥልጣን ጥመኛ ወደ ትግራይ ሲዘልቅ የትግራይ ሕዝብ ማሥክ ነው የምንልከው በማለት በፌደረሽኑ የሚሳለቅ መሪ ያስብለዋል። ዞሮ ዞሮ ጦር የሚያማዝዘው በጀት እገዳ እና ሴፍቲኔት ሲያቋርጥ የትግራይ ሕዝብ እየጠቀምኩት ነው ሊልህ ሲመጣ ይገርማል።…….አብዲ ኢሌ በክልሉ ኹከት ቀሥቅሷል ተብሎ ሲታሰር ምነው ሽመልሥ ኮረዳውን እረሱት ብለውም ቢጠይቁ አልተሳሳቱም።…በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ፍትጊያ አንድ አገር ሆነን እንደ ኹለት አገር ነው። ….ሥለዚህ በሰላማዊ መንገድ መፈታት ያሥፈልገዋል….ሕወሐት በህጋዊነት በምርጫ ቦርድ ህጋዊ ሰውነት መያዙ መረሳት የለበትም። ሥለዚህ የፌደራል መንግሥት ለክልሉ መንግሥት እውቅና ሲነፍግ ….ሕወሐትም ለፈደራል መንግሥቱ ጊዜው ያለፈበት መንግሥት ካለ በኋላ ቁማርተኛ/የሽፍታ መንግሥት በማለት ወንጅሏል።

በዚህ አገር ውሥጥ ሕወሐት ብቻ አይደለም።ፕሮፖጋንዳ የሚሰጡት የብልጽግና አመራሮች ጭምር ነው። ከዚህ ሀቅ መውጣት አንችልም። ከዚህ አኳያ ሳየው ለኹሉም ነገር ሕወሐት መክሰሥ ተጠያቂ ማድረግ አልሥማማበትም።ሥለዚህ የኹለቱ ፓርቲዎች ጉዳይ ወደ መሀል መጥቶ ማለቅ መቻል አለበት።ካልሆነ ጦርነት የኔ ምርጫ አይደለም። የኹለቱ ፓርቲዎች እንጂ….ሌላው ኦነግ ሸኔ የሚል ያልታወቀ ታርጋ መሥማታችን ነው።ሆኖም ሥለዚህ ቡድን ማንነት የሚያውቁት ብልጽግናዎች ብቻ መሆናቸው እንቆቅልሹ ምንድነው? የአሜሪካ ድምፅዋ ፅዮን ግርማ (ጃል መሮ) የተባለው የአማፂ ቡድን መሪ ሥለ ኦነግ ሸኔ ሥለተባለው ቡድን ማንነት ሥትጠይቀው የሰጣት ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር ‹‹ ኦነግ ሸኔ የሚባል ሰራዊት አናውቅም እኛ ጋር እንደዚህ የሚባል ድርጅት የለንም እንኛ የምንመራው አገር ውሥጥ የነበረው የኦሮሞ ሰራዊት ብቻ ነው የምናውቀው እኛ ችግራችን አብይ ከሚመራው መንግሥት ጋርና እሥከ አፍንጫው ከታጠቀው መንግሥትን ከሚጠብቀው ከአገሪቱ ሰራዊትጋር ብቻ ነው። ሕዝብ ለምን ብለን ነው የምንገለው እኛ በምንገኝበት ወለጋ በርካታ አማራዎች ገበረዎች ነበሩ ለምን አልገደልናቸውም ሕዝብ ከገደልን ለማን ነው የምንሞተው የምንታገለውሥ›› በማለት ኦነግ ሸኔ የተባለ ሰራዊት የለም ሲል አረጋግጠዋል ።ከዚህ ቀደም ጠ/ሚትሩ ለኦነግ መረጃ ያቀብሉ እንደነበር ከዚህ ቀደም ቢቢሲ አማርኛ ዘግቦ ነበር በሕወሐት ዘመን የኢንሳ አመራር በመሆን ከፍተኛ የጃሚንግ አፈና ሲመራ እንደነበርም በነ አበበ ገላው አፈትልኮ የወጣው ቪዲዮ አረጋግጧል።

ዛሬም ቢሆን ኦነግ ሸኔ አያደራጁም/አያውቁትም ብሎ ለማለት ያጠራጥራል። ከአገር ውጪ የነበረው የኦነግ ሰራዊት ትጥቅ ሳያሥፈታ በመቀለ አድርገው ወደ አገር ያሥገባው እንዲኹም ወደ ክልሉ ልዩ ሀይል የቀላቀለው ይኸው አኹን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መሆኑንም መካድ የሚቻል አይደለም።……በአጫሉ ገዳይነት ሲከሰሥ የከረመው ይኸው ኦነግ ሸኔ በኋላ ድርጅቱን ክደው መጥተዋል ተብሎ ሲለፈፍም ሰምተናል። በነገራችን ላይ በአገሪቱ ለተፈጸሙ የግድያ ተግባሮች የነ ጃል መሮ ቡድን ምንም ሀላፊነት ሲወሥድ አላየንም።……….ሸኔውም ማን እንደሚመራውም አይታወቅም ….ሥለዚህ ሸኔ ያለው የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ውሥጥ ሆኖ የሚመራ መሆኑ ብቻ ነው።

ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማሳያ የምናደርገው የታዘብነው በተደጋጋሚ ዜጎች እያዩአቸው በዜጎች ላይ ተደርበው ጥቃት በመፈፀም እና ዜጎችን ለመታደግ ዳተኛ በመሆን ነው።…የጉሊሶው ውንብድና ተከትሎ ነዋሪዎች በልዩ ሀይሉ ምንም መፍትሔ እንደማይሰጣቸው ገልፀዋል…. .በነገራችን ላይ ኹሉም እያልኩና እየደመደምኩ አይደለም ምርጥ ለሞያቸው ሟች የሆኑ አሉ ….ሆኖም ሸኔው እዛው የተሰገሰገ ለመሆኑ ….ከላይ ያሉት እውነታዎች የሚናቁ አይደሉም። የሻሸመኔው ከንቲባ አጫሉ በተገደለ ወቅት ለተከሰተው ግድያ ኢንተርቪው በሰጡበት ወቅት ያሉትን በደንብ ቃል በቃል አሥታውሳለሁ እንዲህ ነበር ያሉት ‹‹በሻሸመነ ኹከት በተፈጠረ ጊዘ ለኦሮሚያ ፖሊሥ እና መሥተዳደር ተጨማሪ ሀይል እንዲታዘዝልን ደውዪ አሳውቀያለሁ ነገር ግን በሰአቱ መድረሥ ሥላልቻሉ ብዙ ንብረት ህይወት ወድሟል›› ………..በማለት ነበር ያሥረዳው በነጋታው ከንቲባው መታሰራቸው ሥሰማ አፍሪያለሁ ችግሩ ወታደሩ የሚመራው ሀይል ወይሥ የከንቲባው? … የሌላቸው ሀይልሥ ከየት እንዲያመጡት ነው የሚፈለገው? …..ሥለዚህ እኔ በበኩሌ ልዩ ሀይሉ ተጠያቂ አደርጋለሁ ።ይህ የሚሆንት ምክንያት ልዩ ሀይል በራሱ አገሪቱ ብሔራዊ መከላከያ ፈደራል ፖሊሥ በመመልመል አካቶ አንድና ወጥ ማድረግ ሲቻል ብሔርና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የወሮ በላ ድርጅት ሕጋዊ መሥሎ አይታየኝም። ……በኹሉም ቦታ ያሉ ልዩ ሀይሎች ብሔርተኞች ናቸው። ምክንያቱም የተደራጁት በክልል ሕገ መንግሥቶች ነውና የክልል ሕገ መንግሥት ቅድሚያ ለክልል ነው።

ሥለዚህ ወገንተኝነቱ የበዛ ነው። ለዜጎች ለአገሪቱ ቀውሥ የሚመሥለኝ ይህ አገራችን እየተከተለችው ያለው አደረጃጀት ነው ብዪ አምናለሁ። በመተከል እኮ መንግሥት ልዩ ሀይል መከላከያ ዜጎችን መጠበቅ ሳይችሉ ሲቀሩ ሕዝብን መሳሪያ በማሥታጠቅ በል እንካ ተጫረሥበት የሚል አሥቂኝ መንግሥት ነው ነው የገጠመን። ከዚሁ ሳልወጣ ሰሞኑን በመተከል በጉራፈርዳ እና በጉሊሶ የተከሰቱት የተደረጉት ግድያዎች መንግሥት የለም ወይ? የሚያሥብሉ ከመሆናቸው የሰሞነኛው የጉሊሶ ጭፍጨፋ ደግሞ የብልጽግናው ግድየለሽነትና ከደህንነት አካሉ እንዝላልነት የተነሳ ነው የተከሰቱ።

ሥለ ጉሊሶ ወረዳ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ባለሥልጣናቱ በሰጡን ዘገባ ብንነሳ …..ህዝቡን የፈጀው ሥብሰባ ጠርተው ነው። ለዛውም ትምህርት ቤት ውሥጥ እና ይሔን ኹሉ ነገር ያለመንግሥት ፈቃድ እንዴት ሊያካሂድ ቻለ? ልዩ ሀይል ተብዪውሥ የት ሄዶ ነው? ..ብዪ መጠየቅ የግድ ብሎኛል። ሌላው መከላከያው ማኅበረሰቡ እባካችኹ ሕይወታችን አደጋ ላይ ጥላችሁን አትሂዱ እየተባሉ መሔዳቸው የትኛው አጣዳፊ ትእዛዝ ደርሷቸውሥ ነው? …ሕዝቡ እንዲህ እያላቸው እነሱ ጥለው የወጡት በምን ተማምነው ነው? ….ብቻ ሆድ ይፍጀው ትል ነበር አክሥቴ ።ሥለዚህ የሆነ አካል ኹከቱን የሚፈልገው ይመሥለኛል። እሱም በኔ እይታ ምናልባትም ገዥው መንግሥት የገባበት የሥልጣን ጥም ለማርካት ኹከቱ የአፈና መዋቅራቸውን ለመዘርጋት ሊጠቀሙበት አይችሉም ማለት ያልጠረጠረ ተመነጠረ እንድል ያሥገድደኛል።…..አንተ ወይም ወንድምህ ሲሞት መጥተው የሀዘን መግለጫ ከችግኝ ጋር ይተክሉልሀል ከዛም ሰላም ሚኒሥትር ….የሰብአዊ መብት ኮሚሽን …ፈደራል ፖሊሥ የተባሉ ተቋማት በሰልፍ ተሰልፈው በየተራ እየመጡ መግለጫ በመሥጠት የባጡን የቆጡን በማውረድ ጆሮህን ያደሙታል። ነገር ግን ችግኝም ያለሰው እንደማይኖር ሊያውቁት ይገባል። …..ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ሊገቡ ይገባል። ዜጎች በፈለጉበት የመኖር፤ የመሥራት፤ የማምለክ ፤ቤተሰብ የመመሥረት፤ በሕይወት የመኖር፤ ዋሥትና ሊያገኙ ይገባል ዜጋው ግብር ከፍሎ ሰላም ካላገኘ፤ መንግሥትም ይህንን ማድረግ ካልቻለ በግልፅ በሚገባ ቋንቋ ሥልጣኑ ሊያሥረክብ ይገባል። ታዲያ ምን ሊፈይድ? ምን ሊሰራ?….ደሞ እኮ በኋላ መጥተው ጂኖሳይድ እንዳትሉ ወዘተ እያሉ ሙድ እየያዙ የሚያለምጡት ነገርሥ? …..ባጠቃላይ ከታዘብኩት የፖሊሥ ሀይሉም ይኹን መከላከያው ሕዝቡን እየጠበቁት አይደለም ሰው በሰላም ወጥቶ በሚቀጥለው ሬሳው እንደ እቃ ተጠቅልሎ ሲመጣ ኹሉ አይተናል። አሁን ንዝንዙ ግልምጫው እና ጣት መቀሳሰሩ ለኢትዮጵያ ሰላምን ዲሞክረሲን የዜጎች ሕይወትን ሊታደግ አይችልም ሥለዚህ በመፍትሔው ብናወራ ይሻለል።…..ሥለ መፍትሔው ልበል……በአገራችን የፖለቲካ መረጋገት የለም እሙን ነው፤ ብልጽግናውም ጉዞው ወደ ብልግና ተቀይሮ ኹሉንም ካልዋጥኩ ባይ ሆኗል ይሔ አካሔድ አንድ አንድ የፖለቲካ ልሂቃን ማሥማማት አልቻሉም። እንዲኹም የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን እርሥ በርሥ የሚሐዱበት የተቃርኖ መሥመር ሌላኛው ውሥብሥብ ነገር ነው።

ሆኖም ለኢትዮጵያ እና ለህዝቧ ከተባለ የማይሥተካከል የማይቀራረብ አሳብ የለም። በፈጣሪ ፈቃድ….. ከዛ በተረፈ ብልጽግናው ለዛሬ ወንበሩ ምሰሶ መሆን የቻሉ፤ ዛሬ በአገሪቱ ለሕወሐት መወገድ ከፍተኛ አሥተዋፅኦ ያደረጉ እንደ ለማ መገርሳ፤እና እንደ አወዛጋቢው ጃዋር መአመድ፤…..ሕወሐትን እድሜ ልኩ የታገለው እና ብልጽግናው በአዲሥ አበባ እና በመላው አገሪቱ የተከተለው፤ፖሊሲ የተቃወመው ብረቱ እሥክንድር ነጋ ፤የሽግግር ሰነድ ማዘጋጀት ወንጀል ሆኖ ፅፏል ተብሎ የታሰረው ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያለው፤ ….በቀለ ገርባ በታሰሩበት ኹኔታ አገር ማረጋጋት የማይታሰብ ነው። አንዱ የሃገሪቱ ቀውስ ይሄ ነው…..ባይ ነኝ ስለዚህ ገዢዉ መንግስት ድርድርን መሸሽ መፍራቱን አቁሞ

የአዉሮፓ ኅብረት, የአፍሪካ ህብረት, የኢትይጵያ ቅዱስ ሲኖዶስ, ያወጡትን የአገራዊ እርቀ ሰላም መግለጫ መቀበል እንዲሁም በእንደራሴዉ ምክር ቤት ግልፍተኞቹ ያነሱት ሐሣብ ትቶ የተወሰኑ አባላት ያነሱት የእርቀሰላም ሐሣብ ወደ መሬት በማዉረድ አገር ከመፍረስ ማዳን አለበት እላለሁ 100% እርስ በርስ በተሿሿሙበት ፓርላማ ተመርቶ የሚጓዝ ከሆነ የደርግ መንግስት የሠራዉ ስህተት የሚደግም ይሆናል. ….. የሙፌ ወደ ጀርመን መግባት ስትሰማ እና የሰላም ሚኒስቴር ምክትል ደኤታ በገዛ ፈቃዳቸዉ ስልጣን ማስረከባቸዉ ስትሠማ ለምን ኢትዮጵያችን ኹነኛ መፍትሄ ያሻታል ብዬ እንዳነሣሁ የሚገባችሁ ይመስለኛል.

ለማንኛዉምስለዚህመፍትሄው ከተፈለገ ብዙ ያልተስማማንባቸው ጉዳዮች አሉ ለዛሬው ለዜጎች መሞት ምክንያት የሆኑ እንደ ህገ መንግስቱ በፌደራል መንግስቱ እና በህውሃት መካከል ያለው የሌጂቲሜሲ ጉዳይ የተቋማት ገለልተኝነት ጉዳይ …ሃገራዊ ምርጫው …በታሪክ …በርእዮተ አለም …..ፌደራሊዝም….የክልል መዋቅሮች..ሽግግሩ በራሱ ..የአዲስ አበባ ጉዳዮች ዙሪያ ወዘተ ከጠርሙሱ ያመለጡ ጂኒዎቻችን ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ የተሳካ ሰላማዊ አሻጋሪ ፖለቲካ ለመገንባት ትልም ካላት ከምርጫ በፊት በእስር ያሉት ተፈተው ሃቀኛ እና አካታች አገራዊ እርቀሰላም /መግባባት እና ድርድር ውይይት ያስፈልጋል እላለሁ ሁሉም አካልም ሆደ ሰፊ መሆን ይጠበቅበታል ለዚህደግሞ ነገሮች ወደ መል ለማምጣት ገለልተኛ አካል ተቋቁሞ ሊሰራበት ይገባል …..በዚህ ረገድ ተሰሚነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶች ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች ገለልተኛ ምሁራን ወዘተ ሊያስቡበት ይገባል …ያለዚያ መጪው ምርጫ እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ ከምንግዜም በላይ አስከፊ ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት ሳይቃጠል በቅጠል ሊበላል ይገባል ።

ለሟች በተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ተመኘሁ ።
ኢጥዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!!

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here