የአንበጣ መንጋን ለመከላከል 12 ሄሊኮፕተሮች አገር ውሰጥ ገቡ

0
641

በኢትጵያ ከሰኔ 2011 ጀምሮ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ሥርጭት ለመቆጣጠር 12 የሚሆኑ የኬሚካል ርጭት እና የቅኝት ሂሊኮፕተሮች የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት( FAO) እና በመንግስት አማካኝነት በኪራይ ወደ አገር ውሰጥ መግባታቸውን የግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበራ ለማ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የኬሚካል ርጭት እና ቅኝት የሚያካሂዱ ሂሊኮፕተሮች ስድስት ያህል የነበሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ብቻ ቀርቶ እንደነበር ያታወሳል።በአሁኑ ወቅት 12 ያህል ሂሊኮፕተሮችን በዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት አማካኝነት ለግብርና ሚኒስትር እንደሰጠ ከአበራ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የበረሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽን ለማጥፋት በአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ዙሪያ በቂ ክህሎት ያካበቱ የእሥራኤል ባለሙያዎች ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያንን በማሠልጠን የአንበጣ መንጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች እንደሚሰማሩ እና ይህንን ተግባር የሚፈጽሙ አራት ባለሙያዎችን የያዘ ግብረ ኃይል ማክሰኞ ህዳር 1/2013 አዲስ አበባ የገባ ሲሆን የሁለት ሳምንታት ቆይታ እንደሚኖውም ታውቋል።

የእሰራኤል መንግሥት ከባለሙያዎች በተጨማሪ 27 ድሮኖች እና ኹለት ጄኔሬተሮችንም ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ድሮኖች በመጠቀም በሌሊት የኬሚካል ርጭት በማድረግ የመከላከል ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዘው የመጡ ሲሆን በድሮኖቹ በመታገዝም የዳሰሳ ጥናት በማድረግ መረጃዎችን በመሰብሰብ ውጤታማ የመከላከል ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችል ተገልጻል። በተመሳሳይ የጀርመን መንግሰት በGIZ በኩል ሦስት የቅኝት ድሮኖችን በጥቅምት ወር ድጋፍ ማድረጉም የሚታወስ ነው።

ቡድኑ በቆይታውም ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ በሚቀጥለው ቅዳሜ ህዳር አምስት ቀን ወደ ጅግጅጋ በማምራት የመጀመርያ እንቅስቃሴውን እንደሚያደርግ ተነግሯል።

ጅግጅጋ ከፍተኛ የሆነ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ በአሁኑ ሰዓት ያለበት ስፍራ በመሆኑ ባለሙያዎቹ ከኹለት ቶን በላይ የሚመዝኑ የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎች እና ኬሚካሎች እንዲሁም ለሥራው የሚያግዙ ዕቃዎችን በመያዝ የአንበጣ መንጋውን በቶሎ ለማስወገድ የሚያግዝ ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ከእሥራኤል መንግሥት በጠየቁት መሠረት የተላኩት እነኚህ ባለሙያዎች የኹለቱን አገሮች ትብብር እና ወንድማማችነት ማሳያ እንደሆነ።

የበረሃ አንበጣው በአገራችን በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደተከሰተ ይታወቃል ። መንግሥት በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን አንበጣ መንጋ ለማጥፋት በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት እና በሰው ኃይል መንጋውን በተለያዩ ባህላዊ መንገዶች የማጥፋትና የማባረር ሥራ እያከናወነ ቢሆንም እስከ አሁን በባለፈው የምርት ዘመን ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ሰብል በአንበጣ መንጋ ውደሙን ከግብርና ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የግብርና ሚኒሰትር ዴኤታ የሆኑት ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) አሁን አንበጣ ከተከሰተባቸው አምስት ክልሎች መካካል አራቱ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከአንበጣ እንደፀዱ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።አሁን አንበጣ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እያደረሰ ያለው በሱማሌ ክልል ሲሆን 12ቱን ሂሊኮፕተሮች በመጠቀም ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ እና ሦስት አራተኛ ያህሉን ስፍራም ለማፅዳት እንደተቻለ ለማወቅ ተችሏል።

በሱማሌ ክልል የአንበጣ መንጋ አስቸጋሪ የሆነው በሱማሌ ላንድ እና በፑንት ላንድ በኩል ስለሚገባ መሆኑን አስረድተው፣ አክለውም አንበጣው በግለሰብ ደረጃ ጉዳት ያደረሰ ቢሆንም እንደ አገር ግን ተጋኖ እንደሚወራው ለክፉ የሚሰጥ አይደለም ብለዋል።

አገሪቷን ሙሉ በሙሉ ከአንበጣ መንጋ በቅርብ ነፃ እንደምትሆን ተናግረው ከውጭ አገር ካልመጣ በስተቀር ለሁለት እና ለሶስት ዓመታት ከአንበጣ መንጋ ስጋት ነፃ እንሆናለን ሲሉ ማንደፍሮ(ዶ/ር) ተናግረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 106 ኅዳር 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here