ኅዳር ሲታጠን

0
1019

የኀዳር ወር በገባ በ12ተኛው ቀን ዛሬም ድረስ ያልጠፋ እንደ ባህልም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ባህል አለ ፤ ቆሻሻ ማቃጠል። በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም ድረስ ኀዳር 12 ቀን ሲመጣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ባይሆንም አሁንም ድረስ ቆሻሻዎች ሰብስቦ የማቃጠል ተግባር እየተመለክትንም እንገኛለን። ይህም የሆነበት የራሱ ታሪካዊ ዳራ እንዳለው በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎችም ሲናገሩ የምንሰማው ጉዳይ ነው።

ቅድመ ታሪክ
በአጼ ዳግማዊ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት ጊዜ በኅዳር ወር የወረርሽኝ በሽታ ተከስቶ ነበር። በዚህ ወር ውስጥ መላው ኢትዮጰያንን ያዳረሰ በመሆኑም ወረርሽኙ የተለያዩ ስያሜዎችንም ተሰጥቶታል። ከነዚህ መካከል የኅዳርር በሽታ፣ የባቡር በሽ ታ(በባቡር አማካኝነት ነው የገባው ተብሎ በመታመኑ ) ወይም ክፉ ቀንም ተብሎ በታሪክ ይጠራ እንደነበርም መረጃዎች ያሳያሉ።

ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ወረርሽኝ ቢከሰትም ቆሻሻ የማቃጠል ተግባር ግን አዲስ እንዳይደለ ይልቁንም የቆየ ልማድ እንደነበር የሃይማኖት አባቶች በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ላይ ሲናገሩም እንሰማለን። ከነዚህም መካከል ይህንን የተናገሩት የሥነ መለኮት መምህር የሆኑት ዲያቆን ዳንኤል ሠይፈደሚካኤል ናቸው።

በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት የተፈጠረውን ወረርሽኝ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ብሎም የሚያደርሰውን ጉዳት እስከወዲያኛው ለማስወገድ ኅብረተሰቡ በአዋጅ ተጠራርቶ አካባቢውን በማጽዳት እና እርስ በእርሱም ቆሻሻ የማዋቃጠል ልማዱ እና ተግባሩ እንደቀጠለ ይነገራል።

የኅዳር በሽታ ተብሎ የሚጠራው ወረርሽኝ ቆሻሻ የማቃጠሉን ተግባር እና ልማድ በየዓመቱ ኅዳር 12 ቀን ላይ በገባ ቁጥር ይከወናል። ይህ ብቻም አይደለም ፤ የበጋ ወራትን ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን በሽታ ለመከላከል ቆሻሻ የማቃጠል ተግባር በይበልጥ እንደተስፋፋ እና ተግባራዊ ሊሆን እንደቻለ ነው የሥነ መለኮት መምህር የሆኑት ዳንኤል ያስረዱት።

የኅዳር በሽታ ከኅዳር ሰባት እስከ ሃያ ባሉት ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ታምራት ገብረ ማርያም የባህሉን ጅማሬ ለአዲስ ማለዳ ያስረዳሉ።

ቅድመ ታሪኩንም ሲያስረዱ እንዲህ በማለት ነበር ‹‹በታሪክ የጥናት ትኩረት ከሚሰጥባቸው የማኅበራዊ ታሪክ ዘርፍ ውስጥ የሕክምና ታሪክ (Medical History ) አንዱ ነው።ምንም እንኳን በአገራችን በስፋት ጉዳዩ የማይዳሰስ ቢሆንም ወሳኝ በሆኑ ወረርሽኞች (Pandemic) ላይ ጥናቶች መረጃዎች ግን ይገኛሉ።›› በማለት ይቀጥላሉ። ‹‹ከነዚህም ውስጥ በአውሮፓ የአንደኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ የተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ (Spanish Flu) ወይም በአገራችን የኅርዳ በሽታ በመባል የሚታወቀው ነው›› ይላሉ። በአገራችን ረዥም ታሪክ ውስጥ በነበሩ ጦርነቶች ረሃብ ተክትሎ የተለያዩ ወረርሽኝ ተከስተዋል።

‹‹ከነዚህም ውስጥ ጉንፋን፣ ፈንጣጣ፣ ተቅማጥ፣ ተስቦ፣ ምች የመሳሰሉት በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሱ እንደነበር ይገልጻል›› ያሉት ታምራት ‹‹እንዲህ ዓይነት በሽታዎች ቸነፈር፣ ዕልቂት፣ መቅሰፍት በመባልም ይጠራሉ›› ሲሉም በወቅቱ የተከሰቱትን የተለያዩ ወረርሽኞች በማስታወስ ነበር ያወሱት።

እንደ ታሪክ ማጠቃሻም ሲያስረዱ ‹‹ለዚህም ማስረጃ ይሆን ዘንድ ጀርመናዊ ጆብ ሉዶልፍ በ1698 አምሃሪክ፣ላቲን ዲክሽነሪ በሚለው መዝገበ ቃላት ላይ ጉንፋን የሚለው ቃልን አስፍሮ እናገኛለን።ይህም በወቅቱ ፈታኝ እንደሆነ ነው የሚያሳየው።›› ሌላው ይላሉ የታሪክ ባለሙያው፤ ‹‹በ18ተኛው ክፍለ ዘመን በንጉሠ ነገሥት እያሱ ቀዳማዊ ዜና ማዋል እደተመለከትነው የንጉሡ ልጅ እና ልዕልት ተክለሐይማት እና ሕዝቡ በዚህ በሽታ አካባቢያቸውን ለቀው እንደሄዱ ይገልጻል። ሌላም የታሪክ ማጣቀሻ ያነሳሉ መምህር ታምራት በኋላም በዳግማዊ እያሱ ዜና መዋል ብዙዎች እንደሞቱ እና መቀበሪያ ቦታ እስኪታጣ መድረሱንም ይጠቁማል።

‹‹በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በትኩሳትና በተስቦ ምክንያት ከበጌምድር ማኅደረ ማርያም የአጼ ቴዎድሮስ ሚስት እናት እንደተሰደዱ ሲገልጽ፤በተመሳሳይ በምጽዋ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ይገልጻሉ።›› ሲሉ ነበር የታሪኩን ሥረ መሠረት ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ከ1889እስከ 1891 ክፉ ቀን ተብሎ የተጠራውን ረሃብን ተክትሎ ዶክተር ዎርትስ፤በተከሰተው ወረርሽኝ ብዙ ሰው መሞቱን ሲጠቁም ፤ የአጼ ምኒሊክ አማካሪ የነበረው አልፍሬድ ደግሞ በበሽታው 20 ሺሕ የኢትዮጵያ ጦር እንደተጠቃ ይገልጻሉ።

በመቀጠልም በአገራችን በተከሰተው ወረርሽኝም የአንደኛው የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተነሳው ወረርሽኝ ስፓኒሽ ፍሉ ሲሆን መነሻው በውል አይታወቅም።
የመጀመሪያው ምልክቱ ግን ከወደ አሜሪካ ከሚገኘው የጦር ካምፕ በሚያዚያ 11 1918 እንደታየ የታሪክ ድርሳናት እንደሚጠቁም ታምራት ለአዲስ ማለዳ ይጠቁማሉ ።በኋላም በወታደሮች አማካይነት እንደተስፋፋ መርሴ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በሽታው በንፋስ እንደሚተላለፍም ገልጸዋል።በሽታው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወለጋ በደረሰበት ጊዜም ‹‹ዱኩባ ቂሌንሳ›› የሚል ስም መጠሪያ ተሰጥቶት ነበር ትርጓሜውም የንፋስ በሽታ እንደማለት ነው።

የበሽታው ምክልትም ሳል፣ ጉንፋን፣ከፍተኛ ትኩሳት፣ ህመሙ ሲበረታ ማስለቀስ፣ ተቅማጥ እና በበሽታውም ከሦስት እስከ አራት ቀን ውስጥ የተጠቃ ሰው ካለም ይሞታል ይህ ካልሆነ ግን ረዘዥም እድሜ እንደሚኖር ነው የታሪክ ባለሙያው ያስረዱት።

ወደ አገራች እንዴት ገባ?
የኅዳር ወር በሽታ ወደ አገራችን የገባው በኤደን ባህረ ሰላጤ በኩል ሲሆን ወደ ሌሎች ክፍለ አገሮች የተስፋፋው ባሉት የንግድ ቦታዎች አማካኝነት እንደሆነም ነው የሚነገረው፡፡

በሽታው ኹለት ዓይነተ ደረጃ ነበረው የሚሉት የታሪክ መምህሩ ታምራት፤የጀመሪያው ዙር ላይ ግንቦት አካካቢ ላይ ምልክቶች ታዩ። የተስፋፋው ግን በክረምት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜም አብዛኛው ሰው በሽታውን አያውቀውም ነበር። ይልቁንልም የፈንጣጣ በሽታ ሊሆን እንደሚችል ነበር የሚገምተው ።በዚህም ሳቢያ ወደ 100 የሚሆኑ የውጭ አገር የሕክምና ባለሞያች በጅቡቲ በኩል አድርገው የፈንጣጣ ክትባትም ይዘው ወደ አገራችን ገብተው ነበር።ይህም የሆነው ሕዝቡ በሽታው ፈንጣጣ ነው ብሎ በመገመቱ እንደሆነ ነው ታምራት የሚጠቅሱት።

ይሁን እንጂ የኅዳር ወር በሽታ ኹለት ዓይነት ደረጃ ያለው በመሆኑ በኹለተኛው ዙር ግን በሽታው ከመስፋፋቱ የተነሳ የውጭ አገር ከፍተኛ ባለሥልጣነት ጨምሮ የአገራችን መኳንንትና ሹማምንቶችም በበሽታው ተጠቅተው ነበር።

በበሽታው ሕይወታቸውን ካጡ መካከልም በወቅቱ ከንቲባ የነበሩት ወሰኔ ዘ አማኑኤል ፣የሀዲስ ኪዳን መምህር የነበሩት አለቃ ተገኝም ሞተዋል። በአገራችን በቀዳሚነት የዘመናዊ ትምህርትን ከተከታተሉት ውስጥ አያውቁሽ እና ልጃቸው አሰገደችም ይገኙበታል ።

ተፈሪ መኮንን ወይም አጼ ኃይለ ሥላሴ በበሽታው ተጠቅተው ስለበነር በወቅቱ የሥልጣን ሽግግር ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ሲባል እሳቸውን ለማዳን ብዙ ነገሮች ተደርገው ነበር፤ከነዚህ ውስጥ ሥጋ ወደሙን እንዲቀበሉ መደረጉም በታሪክ ተቀምጧል ወይም እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት መሰረት የቁርባን ሥርዓት ተፈጽሞላቸዋል።

ሌላው የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ውስጥ ለሕክምና ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የውጨ አገር ባለሙያዎች ሲሆኑ ከመጡት ባለሙያዎች መሀከልም ከስምንቱ አራቱ መሞታቸውም በታሪክ ይዘከራል።

ኅዳር 12 ምን ተከሰተ?
በ1911 ኅዳር 12 በዚህ ቀን በተከሰተው ወረርሽኝ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ተቀጥፏል፤ በአዲስ አበባ ውስጥ እንኳን ከተመለከትን የሞተው ሰው ቁጥር እጅግ ብዙ እንደነበር በታሪክ ይወሳል። በአንድ ቀን ውስጥ ማለትም በኅዳር 12 ከሞተው አጠቃላይ አስር ሺህ ሕዝብ ቁጥር ስድስት ሺሕ ሕዝብ በአንድ ቀን ሕይወቱን ያጣው በአዲስ አበባ የሚኖረው እንደነበርም ይገለጻል።

በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ የብዙ ሰዎች ሕይወት የጠፋ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበት ከዘመድ እና ጎረቤት ጋር መጠያየቅ ፣አብሮ መብላትና መጠጣት የተፈራበትም ዘመን ነበር። በወረርሽኙ ሳቢያ ማንም ከቤቱ የማይወጣበት ጊዜ እንደነበርም የታሪክ ባለሙያዎቹ ያስታውሳሉ።

ከመጠያየቅ መራቅ የባሰም ነገር ነበር ፤አንድ ሰው ሲሞት በባህላችን መሰረት አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ የሚለውን ቃል ለመፈጽም ይደረግ የነበረው የቀብር ሥነ-ሥርዓትም አይከወንም ነበር። የሚገርመው የበሽታው አስከፊነት ስለጨመረ በበሽታው የሞተውን ሰው የሚቀብር ሰው አይገኝም ነበር። አስከሬኑም ቤተክርስቲያን ሄዶ ለመቅበር አቅም ያጣ ቤተሰብ ደግሞ እዛው ግቢው ውስጥ ይቀብር እንደነበርና አንድ ቤተሰብ ሙሉ የሚያስታምማቸው በማጣት ቤተሰቡ በሙሉ ያልቅ እንደነበርም ነው የሚታወሰው።

አንድ ሰው የሞተበትን ዘመዱን ለመቅበር ጉድጎድ ቆፍሮ ሬሳውን ለማምጣት ቤቱ ሄዶ ሲመጣ በቆፈረው ጉድጎድ ሌላ ሰው ተቀብሮበት ያገኛል አንዳንዶች ደግሞ የሚቀብሩበት ጉድጎድ ጥልቅ ስላልነበር አስከሬናቸውም አውሬ ይተናኮለው ነበር።

በሽታው ገዳይ ከመሆኑ የተነሳም ለቀብር የተዘጋጀ ቦታ ላይ ሰዎች ተቀብረው ይገኙበት ነበር፤ በየጊዜው እና እንደነገሩ እንዲቀበር ከማድረግ አልፎ ተርፎም በተቀበሩት ሰዎች አማካኝነት በሽታው እንዳይተላለፍ ራቅ ወዳለ ቦታ ወይም ሥፍራ ተወስደው የቀብር ሥነ ስርዓታቸው ይፈጸም ነበር። ከዚህ ውጪም በወቅቱ የነበረው የከተማው ማዘጋጃ ቤትም ከአስከሬናቸው ከሚወጣው ፈሳሽ አማካይነት ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ ለማድረግ በተቀበሩበት ቦታ ላይም ኖራ እንዲለብስ ይደረግ እንደነበር የሚያስታውሱ ታምራት ናቸው።

በኅዳር 12 ቀን ደግሞ ከበፊቱ ቀናት የሚበልጥ ሰዎች ሞተዋል። በአጠቃላይ በሽታው ከኅዳር ሰባት እስከ ሃያ በቆየበት ጊዜ 40,000 የሚያህሉ ሰዎች እንደሞቱ የታሪክ ባለሙያዎች ንግግር በቂ ማስረጃ ነው።

የኅዳር በሽታ በቤተ እምነቶች ላይም ፈተና ሆኖ እንደነበርም በታሪክ ይወሳል። በዚህም ምክንያት ምዕመናን እንኳን ወደ ቤተክርትያን ሄደው ጽሎት እና ልመናቸውን እንዳያደሱ እስከማድረግም መድረሱም የማይረሳ ታሪክ እንደሆነ ይነገራል።

በአጠቃላይ በኅዳር በሽታ በኢትዮጵያ 40 ሺሕ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በዓለም ላይ ደግሞ እስከ 50 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።
ከዚህ ጊዜ በኋላ በዘልማድ ኅዳር 12 ቀን ላይ ቆሻሻ በመሰብሰብ ያቃጥሉ ነበር በተለይም በበሽታው የተጠቁ ሰዎች አካባቢያቸውን በማጽዳት ቆሻሻ በማቃጠል ሲያሳልፉ ነው የሚታየው።

በአዲስ አበባ በኅዳር 12 ቆሻሻ የማቃጠል ልማድ ኹለት ዓይነት እንደሆነ የታሪክ ባለሙያ የገለጹ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ አንደኛው ምክንያት ሃይማኖታዊ ትርጓሜ ያለው ሲሆን ይህም ፍቺ የኀዳር ሚካኤል ቀን መላዕክት የሥላሤን መንበር ያጥናሉ ተብሎ በመታመኑ ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ ካህናት በምድር ለወባ እና ወረርሽኝን ለማጥፋት ምድሪቱን በዕጣን ያጥናሉ የሚለው ፍቺ እንደሆነ በማስረዳት እንደዚህ ዓይነት ወረርሽኝ ሲመጣ ዕጣን ማጣናቸው ታሪካዊ ዳራውን እንደሚያስታውስ ነው የሚጠቅሱት።

ሌላው ቆሻሻ የማቃጠል ባህል የመጣው ቆላ አካባቢ የሚኖረው ኀብረተሰብ ሳሮችን በማቃጠል ሲጀምር ሌላውም የእሱን ጭስ እየተከተለ ይህንን ልማድ እንዲተገበር እንዳደረገ የተጻፉ ታሪኮች መኖራቸውን በምስክርነት ይጠቅሳሉ – የታሪክ መምህሩ ታምራት።

በአጠቃይ በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ በአዲስ አበባ አንድ አምስተኛ የሆነው የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕይወቱ ሲያልፍ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 40 ሺሕ ሰዎች ሕይወታቸውን በህዳር በሽታ ሊያጡ ችለዋል በዓለማችን ደግሞ እስከ 50 ሚሊዮን ሰዎች መሞታቸው ይገለጸል።

ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ ወረርሽኙ ከየት እንደተቀሰቀሰ በውል የታወቀ ነገር የለም። እንዴት እንደጠፋም በውል የሚታወቅ ነገር የለም የሚሉት ታምራት፤ በእኛ አገር ደረጃ ጸሓፊያን በኀዳር 12 ቀን ወይም የሚካኤል ቀን በታጠነው ዕጣን ምክንያት ሞት እንደቀነሰ እና ይህም መለኮታዊ ሥራ ነው በማለት ሲፅፉ የውጭ አገር ጸሓፊያን ደግሞ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሙሉ በመሞታቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የሚገልጽት።

የበሽታው መከሰት በአገራችን ብዙ የቀየራቸው ልማዶች ነበሩ፤ ለምሳሌ ያህል እንኳን እንግዳ አለመቀበል፣በር መዝጋት ፣ የሃይማኖት አባቶችም ከአዲስ አበባ ወደ ሌሎች ክልሎች ማቅናተቻውም አዲስ ነገር እንደሆነ የታሪክ ባለሙያው ሲያስታውሱ በተለይም በወቅቱ የነበሩት ፓትርያርክ አቡነ ማቲዎስ ንግሥት ዘውዲቱን እና ራስ ተፈሪን ትተው ከአዲስ አበባ ወደ መናገሻ መሄዳቸው በዙዎችን ጭምር የአስከፍቷቸው እንደነበር ይናገራሉ ። በተቃራኒው ደግሞ የታዩ መልካም ተግባሮችም ነበሩ እንደ የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ ፣ሙሴ ሴደር ኩዊስት ያሉ ሰዎች ውሃ እና ምግብ በማቅረብ እስከ ሞት ድረስ በሕክምናው ሲያገለግሉ ቆይተው ሕይወታቸው አልፏል።
የታሪክ ባለሙያ ታሪካዊ ዳራውን በዚህ መልኩ ያስረዱ ሲሆን አሁን አሁን ላይ ግን ቆሻሻ ማቃጠል የቀነሰበት እና የማይበረታታበት ጊዜም ላይ እንገኛለን።

የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን በበኩሉ ቆሻሻን የማቃጠል ተግባር ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ቢመጣም እንደ አጠቃላይ ግን ቆሻሻን ማቃጠል ተገቢ አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።

በኮሚሽኑ የአካባቢ ጥበቃ እና የአካባቢ ብክለት ዳይሬክተር የሆኑት ለሜሳ ጉደታ ሲያስረዱም ቆሻሻ መቃጠል የለበትም ይልቁንም በአግባቡ መወገድ ነው ያለበት ይላሉ። በተለይም ደረቅ ቆሻሻ መቃጠል የሌለበትን ምክንያት ሲያነሱ ፤ቆሻሻ ከማቃጠል ይልቅ ፕላስቲኮቹን ለብቻ፤ወረቀቶችን ለብቻ እና ሊበሰብሱ የሚችሉ እና የማይችሉ ተብሎ መለየት አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ለምሳሌ ይላሉ ለሜሳ ሲያስረዱ፤ እንደ ፕላስቲክ ያሉ ቆሻሻዎች ሲቃጠሉ ከፍተኛ የሆነ የአየር ብክለት ያመጣሉ በዚህም አደገኛ የሚባሉ በካይ ኬሚካሎችን ወደ አየር ይለቃሉ። በዚህ ብቻ አይበቃም ፤በዚህ ሳቢያ ሰዎች ለካንሰር በሽታ ይጋለጣሉ፤ በተበከለው አየር ምክንያትም የመተንፈሻ አካላቸው ላይ እክል ይገጥማቸዋል።ሌላው ደግሞ ፤ቆሻሻዎች በሚቃጠሉብት ወቅት ካርቦን ሞኖክሳይድ እና ካቦንዳይኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃሉ ይህም በራሱ የሙቀት መጠንን በመጨመር ያራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ከመኖሩ በተጨማሪም ቆሻሻ ሀብት መሆኑ ያልገባቸው ብዙ ሰዎች በመኖራቸውም ሪሳይክል ወይም ዳግም ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉትን ቆሻሻዎች ያለማወቃቸውም ኢኮኖሚው ላይም የሚያሳርፈው ጫና ቀላል የሚባል አይደለም ይላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here