በጉጂ፣ ቦረና፣ ባሌ እና ምዕራብ አርሲ መቼቱን አድርጎ ‹‹ሲንቄ/ሲቆ ባህላዊ ስርዓት ምንነትና በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ ያላት ሚና›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ጥናታዊ መፅሐፍ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 30/2013 በካፒታል ሆቴል ተመርቋል።
በምርቃት መርሃ ግብሩ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) በንግግራቸው ፤ ባህልና ከውበት አንፃር ብቻ ሳይሆን ለችግር መፍቻ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከጦር መሣሪያ ይልቅም እንደ ሲንቄ ያሉ ባህሎችና ስርዓቶች ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
መፅሐፋ የተዘጋጀው ለትውልድ ለማሸጋገር ብቻ ሳይሆን፣ ከኦሮሚያ ባሻገር እንደ አገር ለማሳወቅና እንዲያገለግል ለማስቻል እንደሆነ አንስተዋል። ‹‹ለዓለምም ትልቅ ስጦታ ነው እየሰጠን ያለነው›› ሲሉ አክለው፤ መፅሐፉ በኢንግሊዘኛ ቋንቋ ተተርጉሞ እንዲቀርብ ሥራዎች መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም እሴቱን ከማስተዋወቅና ከማዳበር፣ ለትውልድ በመፅሐፍ ከትቦ ከማቆየት ጎን ለጎን፤ ሌሎች ክልሎችም ‹‹እኛ ጋር ምን አለ?›› ብለው እንዲነሳሱ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ከበደ በሲሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለሀብት ናት ሲሉ አስታውሰዋል።
ሲንቄም ከዚህ መካከል አንዱ መሆኑንና፣ ሴቶች በማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ቦታ ዝቅ ከሚያደርጉት አንፃር የሴቶችን ተሳትፎ አጉልቶ የሚያሳይ ስርዓት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ጥናታዊ መፅሐፉ በዋናነት ኹለት ነገሮችን ያጠይቃል ያሉት ከበደ፣ በአንድ በኩል ሴቶች ማንኛውም ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው፣ ጥቃት ሲደርስም አጥፊውን ለቅጣት የሚያቀርቡበት ስርዓት ነው ብለዋል።
በተጓደኝ በማኅበረሰብ ውስጥ ፀብና ግጭት ሲኖር ሰላምን ለማስከበር ያገለግላል ብለዋል።
ጥናታዊ መፅሐፋን የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ አዘግጅተዉታል።
ሲንቄ ለኦሮሞ ሴቶች በጋብቻ ቀን የምትሰጥ ከተመረጠ እንጨት የምትዘጋጅ ቀጭን በትር ናት።



