ወልቃይት እንደ ናጎርኖ ካራባክ የንትርክ ቀጠና የማድረግ አዲስ እንቅስቃሴ

በኢትዮጵያ ባለው ፖለቲካ የለውጥ ጉዞ በርካታ ክስተቶችን ለመየት ተችሏል፡፡ ልዩልዩ ተግዳሮቶችንም አስተናግዷል፡፡ለውጡ በሥልጣን ላይ በነበረው ሕወሓት አማካኝነት በተለይም በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መሃከል የተፈጠሩት የማንነት ጥያቄዎች እንዴት ይመለሱ የሚለው የጁሃር ሳዲቅ የጽሑፉ ማዕከል ነው፡፡

ናጎርኖ ካራባክ በቅርቡ የዓለምን ትኩረት በእጅጉ በሳበው በአዘርባጃንና አርሜኒያን ጦርነት ስሟ በሰፊው የሚነሳ ከተማ ነች። ኹለቱም የባለቤትነት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባት ቦታ ነች። ቦታዋ አዘርባጃን ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከ1988 ጀምሮ በኹለቱ መካከል ደም መፋሰሶችም አላጣትም ነበር። ለዚህ ምክንያቱ የቴሪቴሪ ባለቤትነት ጉዳይ ነበር።

ታዲያ ላልተወሰኑ አመታት ተዳፍኖ ቢቆይም መጨረሻ ጦርነት ይገላግለን ብለው በርካቶችም ሞተዋል ቆስለዋል ንብረት በኹለቱም በኩል ከፍተኛ መሰረተልማት ወድሟል ።ከሁሉ በላይ በኹለቱ በኩል ያለ ሕዝብ የሚያተርፈው የጥላቻ አመለካከት የማይነቀል መሆኑ ከጦርነቱ በላይ አደገኛ ነው።

ታዲያ በአገራችን በወልቃይትና ፀገዴ በሌሎችም ቀደም ብሎ በሕወሓት ንብረትነት ተወስደው የነበሩ ቦታዎች የባለቤትነት ጥያቄ ከድንፋታ ከጉልበት ከፅንፈኝነት በዘለል ረጋ ተብሎ እንደአገር ችግሩ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ሊፈታ ይገባል። ለዚህም ፅሑፍ ያነሳሳኝ ይኸው ነውና ወደዛው ልለፍ።

በቅርቡየፌደራል መንግሥቱና የሕወሓት ባለሥልጣናት መካከል እንደፌደራል መንግሥቱ አባባል ሕግ የማስከበር ዘመቻ ያለው ጦርነት እየተካሄደ መሰንበቱ ይታወቃል። ጦርነቱ አሁንም መቋጫው ላይ አልደረሰም ሕወሓት በመሸገበት ቦታ ሆኖ የሞት ጣእር ላይ በመሆኑ የሞት ሽረት ትግል እያደረገ ነው ማለት ይቻላል።
የፌደራል መንግሥቱ በሕወሓት ላይ በወሰደው ፈጣን እርምጃ በስተጀርባ ሕወሓት እያደረገው በነበረው የተስፋፊነት ፍላጎት በመግታት የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ሚና ሰፊ እና ከፍተኛ ነበር ማለት ይቻላል፤ ተመስክሮለታልም ።

ሆኖም በሌላ መልኩ ከዚህ የሚሊሺያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካደረጉ በኋላ ቀደም ብሎ በሕወሓት ተይዘው ከነበሩ እንደወልቃይት ፀገደ ራያ ጠለምት ወዘተ የመሳሰሉ ቦታዎች ከሕወሓት ሚሊሺያ ካስለቀቁ በኋላ እነዚህን አወዛጋቢና አጨቃጫቂ ቦታዎች በአማራክልል መንግሥት ቁጥጥርስር መሆናቸውን ሲገለፁ ክልሉ ልዩ ኃይል ለርስት ማስመለስ/ለብቀላ እንጂ ለአገር ሎአላዊነት አይደለም የሚሉ ሰፊ ሐሳቦች ሲንፀባረቁና ሲስተዋሉ ነበር ።

በተለይ የፌደራሉ መንግሥት ነፃ የወጡት በሕወሓት ቁጥጥር ሥር የነበሩት ቦታዎችን በተመለከተ ምናምን …ትግራይ ብሎ በመግለፁ የተነሳው ግርግርም ከፍተኛ ነበር ።ሆኖም በዚህ ርእስ ለማንሳት የምፈልገው ነገር ወለወቃይት የማን ነው ?የሚለው በደንብ ታሪካዊ ዳራው ስለሚታወቅ እሱን ለመዳሰስ ሳይሆን ስለዚህ ችግር ትክክለኛ እንቆቅልሹ እንዴት ይፈታ/ ቢፈታስ ይሻላል የሚለውን ብቻ ነው።

በዚህ መልኩ ለማየት ስለወልቀይት ሕወሓት እንዳደረገው እናድርግ ? ወይንስ ሌላ አማራጭ እንጠቀም ?ለመሆኑ ሕወሓት ለምን ወልቃይትን ፈለጋት ? እንዴትስ ሊዛት ቻለ የሚለውን ላስቀድም ? ሕወሓቶች ወለወቃይት ጠገዴን ወደትግራይ አካልት ሲጠቀልሉ ምንም አይነት ታሪካዊ ዳራ ሳይኖራቸው ትግራይን ለማስገንጠል በቁምም በእውንም ሲቃዡ ለነበሩለት አላማ ለማስፈፀም ሲሉ ነው።

ብዙ ነገሩን ያደረጉት በአዲስ መልክ የያዝዋቸው ዞኖች በተፈጥሮ ከሰሜኑ ክፍል እጅግ ለምለም የሚባሉትን ቦታ መያዝ አስፈላጊ ነበር፤ ለወደፊቱ ቅዠታቸው፤ መፍቻ ለማድግ ።ታዲያ ይህንን ቅዠታቸው ለማሳካትና እውን ለማድረግ የተለያየ ፖለቲካዊ ውንብድናውን ሲጠቀም እንደነበር ማስረጃዎች አሉ።

ለምሳሌ ያህል፤ ወልቃይት ጠገዴ ሌሎችንም ለመያዝ የሕወሓትቡድን የተጠቀሙት ነባር አባል እና የፋይናንስ ኋላፊ የነበሩት ገብረመድህን አርአያ በዲሴምበር 22, 2015 ኢትዮ-ሚዲያ እና ጎልጉል ድረ-ገፅላይ“በወልቃይትጠገዴ፤ጠለምት በአማራው ላይ ሕወሓት የፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል” በሚል ባወጡ ትጥልቅ ሰነድበ ገጽ 2 ላይ፤  “በሪጅን 1 የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው፣ በአባቱ ወልቃይት ፀገዴ፣ በእናቱ ሽሬ የሆነው መኮንን ዘለለው፣ የተወጠነውን ትልእኮ ይዞ ወልቃይት ፀገዴ ፣ፀለምት እየተዘዋወረ ሕዝቡን በመሰብሰብ ይህ መሬት የትግራይ መሬት ስለሆነ እናንተ ከእንግዲህ ወዲህ የሰሜን ጎንደር ዜጎች አይደላችሁም፣ የትግራይ መሬት ስለሆነ እንኖራለን ካላችሁ ትግሬዎች መሆናችሁን አምናችሁ ተቀበሉ፤ የትግራይ ዜጎች አይደለንም፣ ሰሜን በጌምድር የትግራይ አይደለም ካላችሁ ደግሞ የድርጅቱን የሕወሓትን ውሳኔ ተጠባባቁ ብሎ ነበር።

ተሰብሳቢዎቹን ለማስፈራራት ሞከረ። ቀጥሎም የምታምኑበትን አሁን ተናገሩ በማለት ቢያስጠነቅቅም ከሕዝቡ በኩል ያገኘው መልስ ግን አንድ እና አንድ ነበር።ነገር ግን የቀረበውን ሐሳብ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ የወልቃይት ፀገዴ እና የፀለምት ሕዝብ፣እኛየሰሜንበጌምድር (ጎንደር) አማሮች እንጂ ትግሬዎች አይደለንም፣የታሪካችን ሥር መሰረቱ የበጌምድ ርአማሮችነን።

ይህ ቆመህ የምትናገርበት መሬት ሰሜን በጌምድር ይባላል። ከጥንቱ ታሪካችን ብትነሳም ይህ መሬት ታሪካዊነው። ያለፉት የኢትዮጵያ ነገሥታት ከጥንት ጀምሮ እስከ አሁኗ ሰዓት በመንግሥት እውቅና ያገኘየ ጎንደር፣«”የበጌምድር” ጠቅላይ ግዛት እየተባለ የሚጠራ ነው።

ዋና ከተማችን ደግሞ ጎንደር ነው። የእናንተም ትግራይ ጠቅላይ ግዛት ይባላል፣ ዋናከተማው ደግሞ መቀሌነው።ስለዚህ እናንተ የተሓህት ታግዮች ጉዳዩን ብታሱብበት ጥሩ ነው። ወደ እርስበርስ ግጭ ያመራል። በተጨማሪም ታሪካዊ የወሰን ክልል አለን፣ እሱም ተከዜ ወንዝ ነው።

የትግራይ እና በጌምድር የድንበር ክልሉ ተከዜ ወንዝ ነው። ከጥንት ጀምሮ የኹለቱ ኢትዮጵያውያን የድንበር ወሰን መሆኑን ልናረጋግጥ እንፈልጋለን በማለት በአንድነት ድምፅ ሕዝቡ ራሱ አረጋገጠ።”በማለትገልፀውታል።

እንግዲህ ይህንን ካልኩኝ ሕወሓት ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉትን ዞኖች የያዘበት ምንም አይነት ታሪካዊ ቅቡልት የሌለው መሆኑ ነው ከላይ እንዳየነው ሕዝቡ የወሰነበት ሳይሆን ሕወሓት የተባለው ማፊያ ቡድን የወሰነው ውሳኔ መሆኑ ብቻ ነው። ቀደም ብሎ ከተከዜ ማዶ ያሉ ትግሬዎች እና ከተከዜ ወዲህ ያሉ አማሮች በተለያ የንግድ እና ማህበራዊ ጉርብትና በቋንቋም ተቀራራቢ ማንነት መጋራት መቻላቸው ሕዝቡን ራሱን መመልከት በቂ ነው።

በአንድ ወቅት በቀድሞ የኢህአደግ ፓርላማ ለዓስርተ ዓመታት ያገለገሉ ከዛም ተቃዋሚ ሆነው በ1997 ምርጫ ተሳትፈው ከነበሩ አንድ ምሁር ጋር ተገናኝተን ሻይ ቡና እያልን ስለሕወሓትና በአማራክልል ስላደረሰው ጭቆና አነሳን በዚህ ውይይችን ሰሜንን ከነሱ ጋር በነበርኩበት ወቅት ተመላልሼበታለሁ ተከዜ ወንዝ ድልድዩ ላይ ትግራይ ሪፐብሊክ የሚል አርማ ነበረው እና የጥግራይ መጨረሻ ድንበሯ መሆኑ ነው በማለት የነገሩኝን አስታውሳለሁ።

ቀጠል አድርጌ አሁን ያ የግድግዳ ፅሁፍ/አርማ አለ? ስላቸው፤ አሁን ያጠፉታል የሚል እምነት አለኝ፤ ከዛ በኋላ ወደ ሰሜን ሄጄ አላውቅም በማለት መለሱልኝ ይሄ የሚያሳየው ሕወሓት ራሱን ከመጠን በላይ አስፍቶ አፋር ገሚሱን ቤንሻጉል በኩል የተወሰነ ይዞ ራሴን ቻልኩ በቃኝ የሚል ቅዠት ነበረው ከሁሉም የወልቃይት የጠለምትና ጠገዴ ትልቅ መርዝ የተከለበት ቦታ ነው ።

ከሁሉ በላይ ሕወሓት እነዚህ ወንድማማች ሕዝቦች ለመለያየትና ለመከፋፈል የሠራበት መንገድ የከፋ ነው ።ሕወሓት በእጅጉ ከሠራቸው ሥራዎች አማራ የሆኑ ወልቃይቴዎችን አፈናቅሏል፤ ወዘተ ግፎችን ፈፅሟል።

ሆኖም ግን ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአማራ አክቲቪስቶችና ከትግራይ አክቲቪስቶች ጭምር ሌሎች ብሔርተኛ አክቲቪስቶች ተደምረውበት የወልቃይት እና የሌሎች ዞኖች በተመለከተ እየወጡ ያሉ ክርር ያሉ አመለካከቶች ለአገሪቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሚያስብል ሲሆን፤ ራሱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ለሚለው ሕወሓት ደግሞ እሰይ ስለቴ ሰመረ የሚል ዜማ እንዲያዜም ይፈቅዳል።

ባለፈው በአንድ ፅሑፌ ላይ ሕወሓት የተከለው መርዝ ከባዱ ተግዳሮት መሆኑን አመላክቼ ነበር። ይህንን ያልኩበት ምክንያት የብሔር ትርክቶችና አክራሪ ብሔርተኝነት ዋና መንስኤዎች ናቸው፤ ብዬም አምናለሁ። በምትኩ ግን የማስመሰል ኢትዮጵያ ሳይሆን እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ፈውስ መሆኑን አምናለሁ።
ከዚህ አኳያ ከወልቃይት ጋር ተያይዞ የሚነሱ አጀንዳዎች እንደው ጭር ሲል አልወድም ካልሆነ በቀር ወቅቱም ግዜውም ነው ብዬ። አላምንም በመጀመሪያ ሕወሓት የተባለው ቡድን ከሁሉም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሳንዱች ሆነ እንጂ ጨርሶ ፍፃሜ አላገኘም። ይህ ቡድን በሕይወት ካለ እንቅስቃሴው ፈፅሞ አያቆምም ልክ እንደእባብ።

ስለዚህ ይህ በሆነበት ተጨባጭ ወልቃይት የኔ ነው ብሎ ባንዲራ መትከል ወዘተ ሌላ ፓራዶክስ ሳጥን ከመክፈት ውጪ ዘላቂ መፍትሄ ሆኖ አልታየኝም። ሕወሓት አስገድዶ ስለወሰደው እኛም ይህንን እናድርግ የሚባልበት አሠራር ካለ በትክክል ጠ/ሚኒስትሩ አስቀደውም ያሉትን ሕገ መንግሥት በትክክል አሁን ነው መቅደድ ያለባቸው።

ምክንያቱም ማንም ከሕግ በላይ መሆን ስለሌለበትና መሆን ስለሌለበት በሌላ ጎን ሕገ መንግሥቱ መፍትሄ አይሰጥም የሚል ቡድን አለ ለዚህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ መፍትሄ የማይሰጥበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። መጀመሪያ ከፊታችን የተደቀኑ አገራዊ ጉዳዮች ፈር ማስያዝና በዛው ጎን ለጎን ደግሞ የኹለቱም ክልል አመራሮች ደግሞ የሚወያዩበት መድረክ መፍጠር ይቻላል።

በተጨማሪም ከድንበር ኮሚሽኑ ጋር ከሰላም ሚኒስትር ጋር በመሆን በቅድሚያ የተፈናቀሉትን መመለስ ነባራዊ ኑሯቸው እንዲመሩ ማድረግ ፤ ሕዝቡን ማማከር እንደ አማራጭ ሰላማዊ መንገድን መጠቀሙ የተሸለ ነገርን በሕዝቦች መካከል ይፈጥራል። ነገር ግን በኹለቱ አካላት መካከል ያለው ለሌላ ብጥብጥና ሁከት ጥሪ ማድረግ የበለጠ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ዞራ ዞራ ይሆናልና መንግሥት ግራ ቀኙን የሚያመጣው ኮንስኬንስ ተገንዝቦና አይቶ ፖሌካዊ /መንግሥታዊ ውሳኔ ማሳለፍ ግድ ይለዋል።
ይኸም ማለት የተባሉት ቦታዎች ከኹለቱም ኃይሎች ነፃ በማድረግ በፌደራል መንግሥት ቁጥጥር ሥር አድርጎ ነገሮችን ማረጋጋት ሕዝቡን እንደፈለጉ ወጥተው የሚገቡበት ሁኔታዎችን ማመቻመች ይጠበቅበታል ።

ለአማራ ሕዝብም በርካታ ታሪካዊ ፖለቲካዊ ጂኦግራፊያዊ መሰል መረጃዎችና ማስረጃዎች ስላለ በየትኛውም አካሄድ ተጎጂ አያደርገውም ። ይሄ ማለት አማራ ሕዝብን መጉዳት ሳይሆን ለወደፊቱ ለሕዝቦች አብሮ መኖር መቀጠል የተሻለ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።

ውሳኔው በቡድኖች በስብስቦች መካከል ከሆነና ልክ ሕወሓት እንዳደረገው እኛም ከሕግ አግባብ ውጪ የሚባል ከሆነ አዝማሚያው የሕወሓትን መርዝ ከማሰራጨት ከማስፋፋት ባሻገር ልክ እንደ ናጎርኖ ካራባክ የአርሜኒያና አዘርባጃን ጭቅጭቅ /ውዝግብ እንዳይመራን ያሰጋል። መንግሥትም በወሰደው የሕወሓት ለሕግ የማስገዛት ዘመቻ ላይም ታሪክ ያበላሻል ርስት ማስመለስ የሚለው ሚዛኑ እንዲደፋ ያደርጋል ጥንቃቄ ይሻልና ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ላይ ትኩረታችን ቢሆን እያልኩ ለዛሬው በዚሁ ልሰናበት ።
በጁሃር ሳዲቅ (ጋዜጠኛ)
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!!

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here