በትግራይ የሚገኙ ጡረተኞች ክፍያቸውን በንግድ ባንክ በኩል እንዲያገኙ ተደረገ

0
919

በደደቢት ብድር እና ቁጠባ ተቋም በኩል የጡረታ ክፍያ ይከፈላቸው የነበሩ በትግራይ ክልል የሚገኙ ጡረተኞች የጡረታ ክፍያቸውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲከፈላቸው መደረጉን የመንግሥት ሠራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የመንግሥት ሠራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ጥላሁን በቀለ በትግራይ ክልል የሚገኙ ጡረተኞች የጡረታ ክፍያን ከደደቢት ብድር እና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ የማዘዋወር እቅድ የነበረን ቢሆንም አሁን ግን በክልሉ በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ እና የብድር እና ቁጠባ ተቋሙ የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ በመታገዱ ክፍያውን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መክፈል ጀምረናል፤ ንግድ ባንክንም የመረጥነው በአገር አቀፍ ደረጃ ባለው ተደራሽነት ነው ብለዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ አክለውም ከደደቢት ብድር እና ቁጠባ ተቋም የአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ አብዛኛዎቹ የጡረታ ተከፋዮች ወደ ባንክ የመዞር ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም በዋነኛነት ግን በኢትዮጵያ በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ክፍያው ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዞሯል ሲሉ ገልጸዋል።
ክፍያውን በባንክ ለመፈፀም በመጀመሪያ ከንግድ ባንክ ጋር በመነጋነር ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተን በትግራይ ክልል ለሚገኙ እና በደደቢት ብድር እና ቁጠባ ተቋም በኩል የጡረታ ክፍያ ሲቀበሉ ለነበሩ 60 ሺሕ ጡረተኞች ልዩ የንግድ ባንክ አካውንት ተከፍቶላቸው ከታሕሳስ 2013 ጀምሮ ክፍያቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መከፈል ተጀምሯል ብለዋል።

በመቀሌ የባንክ አገልግሎት በመጀመሩ በከተማው የሚገኙ ጡረተኞች ክፍያቸውን መውሰድ ችለዋል በሌሎች የትግራይ ከተሞች የሚገኙት ደግሞ የባንክ አገልግሎት እንደተጀመረ ክፍያቸውን ይቀበላሉ በማለት ተናግረዋል። ጡረተኞቹ አገልግሎቱን በባንክ እንደሚያገኙ የሚገልጹ ማስታወቂያዎችም አስነግረናል ብለዋል።
ወደ ባንክ ሲሄዱ የክፍያ መቀበያ ደብተር ለማመሳከሪያ ደግሞ መታወቂያ ወይንም በተቋሙ የሚሰጣቸውን የክፍያ መቀበያ ካርድ ይዘው መቅረብ አለባቸው ብለዋል።
እነዚህን ማስረጃዎች ይዘው ወደ ባንኩ ሲቀርቡ ባንኩ ቀድሞ ከተከፈተው ልዩ የባንክ አካውንት ጋር አመሳክሮ ክፍያቸውን ይፈጽምላቸዋል፤ የባንክ ደብተራቸውም ይሰጣቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ከደደቢት የብድር እና ቁጠባ ተቋም ጋር ከ15 ዓመታት በላይ አብረው እንደሰሩ ገልጸው ብድር እና ቁጠባ ተቋማት እስከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርደው ስለሚሰሩ በተመሳሳይ መልኩ በአማራ ክልል ለሚገኙ ጡረተኞች በአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም በኩል ክፍያ እንደሚፈጽሙ አሳውቀዋል።

የመንግሥት ሠራተኞች ማሕበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የብድር እና ቁጠባ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ባልነበሩበት እና ባንኮች እንደዛሬው በሁሉም ወረዳዎች ተደራሽ ባልሆኑበት ጊዜያት ኤጀንሲው ራሱ የጡረታ ክፍያ ይፈጽም እንደነበረ አስታውሰዋል።

በሦስተኛ ወገን እንዲሁም በክልሎች የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ቢሮዎች እና በፖስታ ቤት ጭምር ጡረታ ክፍያ ይፈጽም ነበር። አሁንም ድረስ በፖስታ ቤት የሚደረጉ የጡረታ ክፍያዎች አሉ ከዚህ አሠራር ለመውጣት እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረው ወደ ባንክ አሠራር የመጣው በቅርቡ ከአምስት እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት ባንኮች ዝግ ስለነበሩ ለጡረተኞች ያልተከፈለው የህዳር ወር ክፍያ በውዝፍ እንደሚከፈላቸውም ገልጸው ኤጀንሲው ግን ቀድሞ ወደ ብድር እና ቁጠባ ተቋሙ አካውንት ገንዘቡን ገቢ አድርጎ ስለነበር በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ክፍያ መከፈሉን ስላወቅን የማጣራት ሥራ መቀሌ ባለው የክልል ቢሮ በኩል እየተሰራ እንደሆነ አዲስ ማለዳ መረጃውን ለማግኘት ችላለች።

ከዚህም ጋር ተያይዞ አካውንቱን ካገደው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጋር በመነጋገር ወደ ብድር እና ቁጠባ ተቋሙ አካውንት ገቢ ያደረግንበትን መረጃ በማቅረብ ገንዘቡ ተመላሽ ሆኖ ወደ ንግድ ባንክ አካውንት ገቢ ሆኖልናል ሲሉ ገልጸዋል።

ደደቢት የብድር እና ቁጠባ አክሲዮን ማሕበር ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ውስጥ በመሳተፋቸው ምርመራ ለመጀመር የሚያስችል በቂ ማስረጃ ተገኝቶባቸው ሀብቶቻቸው እና የባንክ አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ ካገደባቸው 34 ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 113 ታኅሣሥ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here