ሕግ አወጣጥ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት – ክፍል 2

0
1075

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።

በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ ሕግ ት/ቤት)
መግቢያ
ባለፈው ጽሁፍ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ መሰረተው የፌደራል መዋቅር እና የፌደራል ምክር ቤቶች ለማየት ሙከራ ተደርጓል። ሕጎች የማመንጨት ዋነኛ ሥልጣን ያላቸው የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች እና የሚንስትሮች ምክር ቤት ጋር ያለውን ሕግ የማርቀቅ እና የማመንጨት ሒደት ለማቅረብ ጥረት ተደርጓል። ሌሎች ሕግ የማመንጨት ሥልጣን ስላላቸው ግለሰቦች እና ተቋማትም ማብራሪያ ቀርቧል። የፌደራል ምክር ቤቶቹ በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ያላቸውን ሥልጣንም ለመለየት ተሞክሯል። ረቂቅ ሕጎች ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀረቡ በኋላ ያለውን ሦስት የንባብ ደረጃ፣ ብሎም አንድ ረቂቅ ሕግ ሆኖ እስከሚወጣ ድረስ ያለውን ሒደት ከአገሪቷ ሕገ መንግሥት እና የምክር ቤቱ የአሰራር ደንብ አንጻር በዝርዝር ለማየት ጥረት ተደርጓል።

በዚህ በኹለተኛው ክፍል በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ስለሚኖር ሕዝባዊ ተሳትፎ አጠቃላይ መርሆ፣ የሕግ መሠረት እና አስፈላጊነት ይብራራል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዴት እና መቼ በሕግ ማውጣጥ ሒደት ውስጥ ማኅበረሰቡ ሊሳተፍ እንደሚችልም ይቀርባል።

1. በሕግ ማውጣጥ ውስጥ የሚኖር ሕዝባዊ ተሳትፎ – የመርሆ እና ሕጋዊ መሠረት
የዴሞክራሲ ዋነኛ ጽንሰ ሐሳብ ሕዝብ እራሱን የሚያስዳድርበትን መዋቅር ማቆም ነው። ዲሞክራሲ አንድም በውክልና ሌላም በቀጥታ ተሳትፎ ይሆናል። የውክልና ዴሞክራሲ ዜጎች ጊዜ ጠብቀው በሚመርጧቸው እንደራሴዎቻቸው አማካኝነት መንግሥት የሚያቋቁሙበት እና በዚህ መንግሥት በሚባል ተቋም በሚሰጡ ውሳኔዎችም የሚተዳደሩበት አካሄድ ነው።

ማኅበረሰቡ መንግሥትን በምርጫ ካቋቋመ በኋላም በመንግሥት ውሳኔዎች ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ ሊያደረግ ይችላል። ሕዝብ መንግሥቱን አንዴ ከመረጠ በኋላ እጁን አጣጥፎ መቀመጥ ሳይሆን በየጊዜው በሚተዳድርበት ፖሊሲዎች እና ሕግጋት አወጣጥ እና አፈጻጸም ውስጥ ሊሳተፍ ይችላል። ይሄ በተቋቋመ መንግሥት ውሳኔዎች ውስጥ የሚኖር ተሳትፎ የተሳትፎ ዲሞክራሲ (Participatory Democracy) ተብሎ ሊጠራ ይችላል።

በተለያዩ የመንግሥት ስራዎች ውስጥ የዜጎች ተሳትሮ እንደ ሰብኣዊ መብት እውቅና አግኝቷል። ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው፤ የዓለም ዐቀፍ የፖለቲካና ሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን (አንቀጽ 25(1))፣ የአፍሪካ የሰብኣዊና ሕዝቦች መብት ቻርተር (አንቀጽ 13)፣ እንዲሁም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት (አንቀጽ 38) ዜጎች በእንደራሴዎቻቸው ወይም በራሳቸው በመንግሥት ሥራዎች ውስጥ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።

ኢትዮጵያ ከ1993 (እ.አ.አ.) ጀምሮ የዓለም ዐቀፍ የፖለቲካና ሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን አባል ስትሆን፥ 1998 (እ.አ.አ.) ጀምሮ ደግሞ የአፍሪካ የሰብኣዊ እና ሕዝቦች መብት ቻርተር አባል ሆናለች።

የፖለቲካና ሲቪል መብቶች ቃል ኪዳን ለመተርጎም በስምምቱ የተቋቋመው እና 18 ባለሙያዎችን ያካተተው የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የተሰኘ ስብስብ በአስተያየት ቁጥር 25 ላይ በሰጠው ትርጉም ይህ ዜጎች በመንግሥት ሥራ ውስጥ ያላቸው የመሳተፍ መብት የሕግ ማውጣጥ ሒደትንም እንደሚያካትት ገልጿል።

ይህ በሕጎች ውስጥ ዜጎችን የማሳተፍ የመንግሥት ግዴታ በዓለም ዐቀፍ ስምምነት እና በሕገ መንግሥቶች ውስጥ በጠቅላላ ቢደነገግም፣ ዝርዝሩ ግን የሚገኘው በተለያዩ ሀገራት የውስጥ ሕግጋት ውስጥ ነው። በተለይም በፓርላማ ውስጥ የሚኖሩ ተሳትፎዎች በፓርላማ መተዳደሪያዎች ውስጥ በዝርዝር ይቀመጣሉ። በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዎች ምክር ቤት ውስጥ የሚኖር ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚተዳደረው “የምክር ቤትን አሰራር እና የአባላቱን ሥነ ምግባር ለማስተዳደር” በወጣ ደንብ ቁጥር 6/2008 ነው።

2. በሕጎች ማውጣጥ ውስጥ የዜጎች ተሳትፎ ለምን?
ሀ) የመንግሥትን ተጠያቂነት እና ግልጽነት ማረጋገጥ – በሕጎች ውስጥ የሚኖር ተሳትፎ የመንግሥትን ተጠያቂነት እና ግልጽነት ያበረታታል። በሕግ ማውጣጥ ውስጥ የሚሳተፉ የመንግሥት ተቋማት ለሚያወጧቸው ሕጎች እና ሕጎቹም ለሚኖራቸው አስተዋጽዖ ለማኅበረሰቡ በቀጥታ የማስረዳት ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። መንግሥት ለሚያወጣው ሕግ ለተገዢው በቂ ማብራሪ ሊሰጥ ያሻዋል። ይኸውም በሕዝባዊ ተሳትፎ መድረኮች ሊረጋገጥ ይችላል።

ለ) የሕግ ቅቡልነት እና ውጤታማ ተፈጻሚነትን ማረጋገጥ – ሕግ በቀጥታ በመንግሥት ከሚጫን ይልቅ ሕዝቡ ተሳትፎ ካደረገ እና አስተያየቱን ከሰጠበት በተሻለ ማኅበረሰቡ ሊቀበለው፣ “የኔ ሕግ ነው” ሊለውና ሊገዛበት ይችላል። ዜጎች ባልተሳተፉበት፣ እምነታቸውን ባልጣሉበት እና “የኔ ነው” በማይሉት ሕግ ያለመገዛት ብቻ ሳይሆን ሕጎን የማጥፋትና ለማሻር የሚጥሩበት አዝማሚያ ይኖራል።

በሕጎች አፈጻጻም ላይ ማኅበረሰቡ እና የተለያዩ አካላት ከመንግሥት ጋር ትብብር እንዲፈጥሩ፣ ብሎም ሕጎቹን በማስፈጸም ሒደቶች ላይ ከመንግሥት ጋር በጋራ ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ያበረታታል – ሕዝባዊ ተሳትፎ። ቅቡልነት ያላቸው ሕጎች በመንግሥት እና በዜጎች መካከል መግባባት፣ ለጋራ ግብ የመሥራት አካሄድም ይፈጥራሉ። ይሄ ብቻ ሳይሆን በሕግ ማውጣጥ ሒደት ውስጥ የሚኖሩ የመንግሥት ተቋማት – ሕግ የሚያመነጨው አስፋጻሚውም ሆነ የሕግ አውጪ ምክር ቤቶች – በተሻለ በማኅበረሰቡ እምነት የሚጣልባቸው ይሆናሉ።

ሐ) የሕግ ጥራትን ማረጋገጥ – ሕግ ጥራት አለው የሚባለው ሕጉ የወጣው የሕግ ሽፋን የሚጠይቁ የማኅበረሰብ ችግሮችን ለመፍታት እና ነባራዊ ሁኔታዎችንም ያገናዘበ ሲሆን ነው። በማኅበረሰቡ ውስጥ ሕግ የሚሹ ጉዳዮች ሊታወቁ የሚችሉት ደግሞ በሕጉ ከሚገዛው ማኅበረሰብ ጋር ብቻ ሳይሆን የተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንወክላለን ከሚሉ የሲቪል ማኅበራት ብሎም በየዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር በሚኖር ውይይት እና ምክክር ነው። መንግሥት የፖለሲ አማራጮችን እና ሕግ የሚያሻቸውን ጉዳዩን በሚመለከት ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ይረዳዋል – ሕዝባዊ ተሳትፎ። ማኅበረሰቡ ችግሩን ከራሱ በላይ የመንግሥት ተቋማት እና ሹማምንት ሊያውቁለት እንደማይችሉ እሙን ነው።

መ) የሰብዓዊ መብትን ማረጋገጥ – በመንግሥት ፖሊሲዎች እና ሕግጋት ውስጥ የሚኖር ተሳትፎ እንደ ሰብኣዊ መብት እውቅና አግኝቷል። ይህ በተለይም “በሕግ ውስጥ ዜጎች ሊሳተፉ ይገባል” የሚል የሕግ ድንጋጌ በብዙ ሀገራት ሕገ መንግሥቶች በግልጽ እና በዝርዝር ተደንግጎ አይገኝም። ነገር ግን በአጠቃላይ የሰብኣዊ መብት እና ዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ብሎም የዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ሕጎች የማውጣጥ ሒደቶችን ጨምሮ ዜጎች በመንግሥት ሥራዎች ውስጥ ሊሳተፉ እንደሚገባቸው ያትታሉ።

መንግሥት ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ሦስት ኃላፊነቶች አለበት – የማክበር፣ የማስከበር እና የሟሟላት (የሚፈጸምበትን ሁኔታዎች የማመቻቸት)። ስለዚህ ዜጎችን በሕግ ውስጥ ማሳተፍ፣ በተሳትፎ ላይ የሚደረጉ ክልከላዎችን ማስቆም እና የሚሳትፉባቸውን የሕግና ተቋማዊ ማዕቀፎች ማውጣጥ፤ ኢትዮጵያ አባል በሆነችባቸው የዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች እና ሕገ መንግሥቷ ላይ የተጣለባትን ኃላፊነት መወጣጥ ነው።

ሠ) ፍትሕን ለማስፈን – ፍትሕ ሀገር ያላትን ዘርፈ ብዙ ሀብት ለዜጎች ያለአድሎ በእኩልነት ማከፋፈል (distributive justice) ብቻ ሳይሆን የሚከፋፈልበት ሒደት እንዴት መሆን አለበት የሚለውንም (procedural justice) ያካትታል። የሀገር መዋለ ነዋይ ከሚከፋፈልባቸው ማስፈጻሚዎች ውስጥ ሕግ ዋነኛው መሆኑ እሙን ነው። ስለዚህ ዜጎችን በሕግ ማውጣጥ ሒደት ውስጥ ማሳተፍ ፍትሕን ማስፈን ነው።

3. በፓርላማ የሕግ ማውጣጥ ሒደት ውስጥ የሚደረግ ሕዝባዊ ተሳትፎ – በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሒደት በተለየ
በፓርላማ ተሳትፎ የሚደረገብት ዋነኛ አጋጣሚ ረቂት ሕጎች ወደ ቋሚ ኮሚቴ ከተላኩ በኋላ፣ የቋሚ ኮሚቴዎቹ በሚያዘጋጁት ሕዝባዊ ውይይት (public hearing) ላይ ነው። ዋነኛው የተሳትፎ አካሄድ አስተያየት መስጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ቢሆንም በጽሁፍ አስተያየት፣ በነጻ የስልክ ጥሪ፣ የተለያዩ ቴክኖሎጂዮችን በመጠቀም፣ በፋክስና ፖስታም ማኅበረሰቡ በሚወጡ ሕጎች ላይ አስተያየቱን ሊሰጥ ይችላል። አሁን ላይ ምክር ቤቱ 10 ቋሚ ኮሚቴዎች እና 33 ንዑስ ቋሚ ኮሚቴዎች አሉት። ኮሚቴዎቹ ተጠያቂነታቸው ለምክር ቤቱ ሆኖ የምክር ቤቶቹ ሊቀ መናብርት ደግሞ ለምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ተጠያቂ ይሆናሉ።

ረቂቅ ሕግ በመጀመሪያ ንባብ ውይይት ከተደረገበት እና ለተጨማሪ ዝርዝር ምርመራ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ከተመራ በኋላ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ሕዝባዊ ውይይቶችን ማካሔድ ነው። ቋሚ ኮሚቴዎቹ ረቂቅ ሕግ ከተላከላቸው በኋላ ለመመርመር ከ20 ያላነሱ ቀናት ሊሰጣቸው የሚገባ ሲሆን እንደ ረቂቁ ስፋት እና ክብደት የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ጊዜውን ሊያራዝሙት እንደሚችሉ የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 57 ደንግጓል።
የጽሁፉ አቅራቢው ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ እንደሚያስረዱት ቋሚ ኮሚቴው በመጀመሪያ ረቂቅ ሕጉን ከተቀበለ በኋላ የሚያደርገው ረቂቁን ከላከው መንግሥታዊ ተቋም ከሚላክ ግለሰብ (ባለሙያ ወይም ሹመኛ ሊሆን ይችላል) ጋር ውይይት ማድረግ ነው።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ ለዚህ ውይይት እንዲረዳቸው ረቂቁን ወደ ምክር ቤቱ የተለያዩ ባለሙያዎች በመላክ ጥያቄዎች እንዲዘጋጁ ያደርጋሉ። እንደ ምክር ቤቱ የሕግ ባለሙያ ግን ብዙ ጊዜ ባለሙያዎቹ ረቂቁን መርምረው፣ ሕጉን ለሚያመነጨው አካል ጥያቄዎችን እና የውይይት ሐሳቦች ለማዘጋጀት የሚኖራቸው ጊዜ አጭር ነው። ጽሕፈት ቤቱ የቋሚ ኮሚቴዎቹን ለማማከር ከንቃትም ሆነ ከብዛት አንጻር በቂ የሚባል ባለሙያ እንደሌለው ደግሞ በጽ/ቤቱ በአንድ ኃላፊነት ላይ የሚሰሩ ሌላ ግለሰብ ይገልጻሉ።

ባለው አሠራር ቋሚ ኮሚቴዎች ረቂቁን ካቀረበው የሚንስቴር መስሪያ ቤት ወይም ሌሎች አካላት የሚመጡ ግለሰቦች ጋር ውይይት አድረገው በቂ ግንዛቤ ካገኙ በኋላ ሕዝባዊ ውይይቱን ያካሂዳሉ። ሕዝባዊ ውይይት የሚካሄደው የቋሚ ኮሚቴዎች ከባለሙያ እና አስረጂ ጋር ከመወያየታቸው በፊትም ሆነ በኋላ ሊደረግ እንደሚችል የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 167(4) ላይ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here