የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ
በአዲስ አበባ ከተማ መዋቅራዊ ዕቅድ ላይ የተቀመጡት 15 ተርሚናሎች/ጣቢያዎች ሲሆኑ በዕቅዱ መሰረት ሥራ ላይ የዋሉት አምስት ብቻ መሆናቸውን ባወጣው ስትራቴጅ አስቀምጧል።
የተሰሩት ተርሚናሎች/ጣቢያዎች መገናኛ፣ ሳርቤት፣ አየርጤና፣ ዊንጌት እና ቦሌ የሚገኙ እንደሆነም ተገልጿል። ቀሪዎቹ የሲኤምሲ፣ የቦሌ ለሚ፣ የኮተቤ፣ የቤላ/ፈረንሳይ፣ የአቅም ግንባታ/ከስድስት ኪሎ በስተሰሜን፣ የፒያሳ፣ የቃሊቲ እና የቆጣሪ ተርሚናሎች እንዳልተገነቡም አስታውቋል።
በሌላ መልኩ በከተማዋ መዋቅራዊ ዕቅድ ላይ ያልተካተቱ ነገር ግን ለታክሲ እና አውቶብስ ተርሚናልነት እያገለገሉ ያሉ እንደ ሽሮሜዳ፣ አስኮ፣ ኮልፌ፣ ሜክሲኮ፣ አዲሱ ገበያ፣ ለገሀር፣ ሳሪስ፣ ቄራ እና ጦርሀይሎች ተርሚናሎች ይገኛሉ። እንደ ጦርሀይሎች እና አለርት ያሉ የታክሲ ጣቢያዎችም ይገኛሉ። አስራ አንዱ እንደመደበኛ ተርሚናል የመቆጠሩ ቢሆኑም አስፈላጊው የሆኑ እንደ መጠለያ፣የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች፣ለአውቶብስ እና ለታክሲ የተለዩ ማቆሚያዎች እና ሰፊ መግቢያ እና መውጫ የመሳሰሉ መሰረተ-ልማቶች ያልተሟላላቸው ናቸው።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የመኪና ማቆሚያ ጉዳይ ነው። በከተማዋ ውስጥ በመንገድ ዳርም ሆነ ከመንገድ ዳር ውጪ የመኪና ማቆሚያዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በብዛት የሚዘወተረው መንገድ ዳር መኪና ማቆም ነው ሲልም ቢሮ አስታውቋል።
በመንገድ ላይ ተሸከርካሪን ማቆም የመንገድ አውታርን በአግባቡ ለመጠቀም አዳጋች አድርጎታል፣ ደህንነት እንዲቀንስ እና የትራፊክ መጨናነቅ በተለይ በመጋጠሚያ መንገዶች እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ከዋና መንገድ ገባ ያሉ ጥቂት የመሬት ላይ እና የህንጻ መኪና ማቆሚያዎች አሉ። በአሁኑ ሰዓት የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ለመገንባት በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ የግንባታ ቦታዎች ተመላክተዋል።
በተለያዩ የከተማዋ የተለያዩ ስፍራዎች ላይ የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የተሸከርካሪ ማቆሚያ መሰረተ ልማቶች አሉ። በአማካይ እስከ 100 መኪና ማስተናገድ የሚችሉ ከዋና መንገድ ራቅ ያሉ መንገድ ዳር የመኪና ማቆሚያዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል። በሾላ ገበያ እና ሜክሲኮ ሸበሌ የሚገኙ የኹለት ትላልቅ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ህንፃዎች ግንባታ በ2012 እንዲጀመር ዕቅድ ተይዞ የሾላ ገበያው ግንባታ የተጀመረ ሲሆን የሜክሲኮ ሸበሌው የዲዛይን ስራው ተጠናቋል። በህዝብ ትራንሰፖርት ተርሚናሎች አካባቢ ለግልጋሎት ዝግጁ የሆነ የመኪና ማቆሚያ የለም።
ለዚህ እንደ መፍትሄ በስትራቴጀው የተቀመጠው ደግሞ በከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት እና ፈጣን የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ጣቢያዎች ላይ “Park and Ride” ስፍራዎችን ማመቻቸት በቀለበት መንገድ ክልል ውስጥ የመንገድ ዳር ተሽከርካሪ ማቆምን መቀነስ ወይንም መከልከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ከመንገድ ዳር ውጪ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ ላይ የተሸከርካሪ ማቆሚያ ህንፃዎች እና ስማርት የተሸከርካሪ ማቆሚያ ማልማት የተሸከርካሪ ማቆሚያ ሰተራቴጂ ማዘጋጀት ይገኙበታል።
ሌላው በፍጥነት እያደገ የመጣው የተሽከርካሪዎች ቁጥር እና የግል መኪና ባለቤትነት ከተማዋ እየገጠሟት ካሉት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ። በአዲስ አበባ ከተማ አብዛኛው የትራንስፖርት አማራጭ የህዝብ ትራንስፖርት እና የእግር ጉዞ ሲሆን፣ ከየትራንስፖርት አማራጮች 15 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑት የግል ተሽከርካሪዎች ናቸው። ካለው የመሰረተ-ልማት እድገት አንፃር የግል ተሽከርካሪ ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው። 60 በመቶ ለሚሆነው የመንገድ ትራፊክ መጨናነቅ እና ብክለት የግል ተሸከርካሪዎች አስተዋፅኦ እንዳላቸው ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013



