ውይይቶችን በመገናኛ ብዙኀን ማስተላለፍ እና ስለ ፓርላማ ለማኅበረሰቡ ማሳወቅ – በሕግ ማውጣጥ ውስጥ የሚኖር ሕዝባዊ ተሳትፎን ለማበረታታት

0
1147

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም ላያንጸባርቅ ይችላል።

በሚኪያስ በቀለ
(አምቦ ዩንቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት)
1. ውይይቶች በሚዲያ ማስተላለፍ
በሕግ ማውጣት ውስጥ ሕዝባዊ ውይይት ከሚካሄድባቸው ዓላማዎች ውስጥ መንግሥት ለሚያወጣቸው ሕጎች በቂ ማብራሪያ የሚሰጥበትን አጋጣሚ መፍጠር አንዱ ነው። በሕጎች ውስጥ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ተሳትፎ የመንግሥትን ተጠያቂነት ብሎም ግልጽነት ያረጋግጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ በሕግ ማውጣጥ ሒደት ውስጥ በመሳተፍ አሻራውን ማሳረፉ ለሕጎች ቅቡልነት እንዲቸራቸው፣ ‹‹የእኔ ሕጎች ናቸው›› ብሎ እንዲገዛባቸው ብቻ ሳይሆን በሕጎቹ የማስፈጸም ሒደት ውስጥም ከመንግሥት ጋር ትብብር እንዲያደግ ያግዛል። ምክር ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትም በተሻለ በማኅበረሰቡ እምነት እንዲጣልባቸውም ምክንያት ይሆናል። በእነዚህ ምክንያት የቋሚ ኮሚቴን ስብሰባዎች ጨምሮ የተለያዩ የምክር ቤት ስብሰባዎች ግልጽ መሆን አለባቸው። ስብሰባዎች ለሚዲያዎች ብሎም ለተለያዩ አካላት ክፍት መሆን አለባቸው። ዝግ ስብሰባዎች የሚካሄዱት የተለዩ ሁኔታዎች ሲኖሩ ብቻ ነው።

በኢትዮጵያ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 58(5) ብሎም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ደንብ አንቀጽ 17 ላይ ማንኛውም የምክር ቤቱ ስብሰባዎች በመርኅ ደረጃ በግልጽ መደረገ እንደሚገባቸው ያስቀምጣሉ። ዝግ ስብሰባዎች ሊካሄዱ የሚችሉት በምክር ቤቱ 1/3ኛ አባላት ወይም በአስፈጻሚው አካል ጥያቄው ቀርቦ ከግማሽ በላይ የምክር ቤቱ አባላት ከደገፉት ብቻ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ ብሎም የምክር ቤቱ ደንብ አንቀጽ 18 ይገልጻል።

የቋሚ ኮሚቴዎች የሚያዘጋጁዋቸው ሕዝባዊ ውይይቶች ለሕዝቡ በቀጥታ ቢተላለፉ፣ የተነሱ ሐሳቦች እና የተያዙ ቃለ ጉባኤዎች በዜና መልክ ቢነገሩ ማኅበረሰቡ በሒደቱ የተሻለ እምነት እንዲያድርበት፣ ለወደፊት ውይይቶችም ተሳትፎ እንዲደረግ ያበረታታል።
በኢትዮጵያ ባለው ልምድ አጠቃላይ ስብሰባዎች በቀጥታ የሚተላለፉት እየተመረጡ ነው። ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ እና የሀገሪቷ ጠቅላይ ሚንስትር የሚገኙባቸው ስብስባዎች ብዙውን ጊዜ የሚዲያዎችን ቀልብ ይስባሉ። በቋሚ ኮሚቴ የሚዘጋጁ ሕዝባዊ ውይይቶችም በተመሳሳይ ረቂቅ ሕጎቹ ካላቸው የሕዝብ ትኩረት አንጻር ታይተው በሚዲያ እንደሚተላለፉ የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ይገልጻሉ። እንደ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አገላለጽ ሚዲያዎች ሕዝባዊ ውይይቶችን እንዲዘግቡ ጥሪ ቢደርግላቸውን አብዛኛውን ጊዜ ግን ሚዲያዎች ትኩረት እንደማይሰጡ ይገልጻሉ። አክለውም ሚዲያዎች በሚመጡበት ጊዜም ተገቢ የሆኑ የውይይቱን ሐሳብ በጥልቀት ከመዘገብ ይልቅ ‹‹በዚህ አዋጅ ላይ ይሄ የቋሞ ኮሚቴ ውይይት አደረገ›› በሚል ብቻ የተገደበ፤ የውይይቶቹን ይዘት እና የተነሱ ሐሳቦችን ያጠቃለሉ ሪፖርቶች ሳይቀርቡ ይቀራሉ። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አክለውም የምክር ቤቱ ዋነኛ ሥራዎች በየሳምንቱ ‹‹በአዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ላይ እንዲታተሙ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ስምምነት መኖሩን ይገልጻሉ።
የአንድ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑ የምክር ቤቱ አባል በበኩላቸው ሚዲያዎች ለሕዝባዊ ውይይቶች ትኩረት እንደማይሰጡና ጥሪ ተደርጎላቸው እንደሚቀሩ፣ የሚመጡትም ተገቢውን ሽፋን እንደማይሰጡ ይናገራሉ። የኮሚቴዋ ሰብሳቢ አክለውም የሚጠሩት መገናኛ ብዙኀን ከመንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ብቻ በመሆናቸው የተመረጡ አጀንዳዎች ብቻ ለማኅበረሰቡ እንዲገለጹ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።

ምክር ቤቱ የራሱን የቴሌቭዥን ስርጭት የመጀመር እቅድ አለው። በ2012 ዓ.ም የራሱን ሚዲያ የመጀመር እቅድ መያዙን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ከምክር ቤቱ ዓመታዊ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቢገልጹም ይህ ሳይሆን ቀርቷል። ይህ የሚመለከተው ክፍል ኃላፊ የሆኑት የምክር ቤቱ የሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ ምክር ቤቱ የራሱን የቴሌቭዥን ጣቢያ ለመጀመር ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆናቸውን ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያስረዳሉ።

አክለውም በየአዳራሾች ውስጥ ቪዲዮዎ ለማስተላለፍ የሚረዱ እቃዎችን እየተገጠሙ እና ፕሮግራሞችም እየተሰሩ መሆኑን፤ እና በ2013 ዓ.ም ውስጥ ለመጀመር ዓላማው እንዳላቸው ይገልጻሉ። ምክር ቤቱ የራሱን ቴሌቭዥን መጀመሩ ተከትሎ የተለያዩ አጠቃላይ እና የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች በቀጥታ ስለሚተላለፉ በዚህ ረገድ ያለው ክፍተት እንደሚፈታ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የምክር ቤቱ አባላትም ሆኑ የጽ/ቤቱ ኃላፊዎች ያምናሉ።

2. ማኅበረሰቡን ስለ ምክር ቤቶች እና የተሳትፎ መብትና አካሄድ ማሳወቅ
ማኅበረሰቡ በሕግ አወጣጥ ሒደት ውስጥ እንዲሳተፍ የፓርላማን እና እንደራሴን ምንነት፣ የተቋሙን አሰራር በተለይም በሕግ አወጣጥ ውስጥ ስለሚኖር የተሳትፎ አካሄድ ሊያውቅ ይገባል። ይሄ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡ የሕግ ማውጣጥ ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ውሳኔዎች ውስጥ የመሳተፍ የሰብዓዊ መብት እንዳላቸው ጠንቀቆ ሊገነዘብ ይገባል። የፓርላማ አሰራር የማሳወቅ ኃላፊነት በዋነኛነት የምክር ቤቶች ቢሆንም ሌሎች መንግሥታዊ የሆኑ ብሎም የሲቪክ ተቋማት የራሳቸው ድርሻ አላቸው። የተለያዩ ሀገራት ፓርላማዎች መረጃዎችን ከማቀበል በተጨማሪ ስለ ተቋማቸው ማኅበረሰቡን ለማስተዋወቅ እንዲረዳቸው የሕዝብ ግንኙነት የሚባል ክፍል ያቋቁማሉ።
ዜጎች በመንግሥት ውሳኔዎች ውስጥ ስላላቸው የመሳተፍ መብት፣ ስለ ፓርላማ ብሎም በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ሕዝባዊ ተሳትፎ ስለሚካሄድበት ሒደት ማኅበረሰቡን ለማሳወቅ የተለያዩ አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ።

ሀ) በሥነ ዜጋ ትምህርት
ዜጎች ቀደም ብለው፣ ከልጅነታቸው ጀምረው ስለ ፓርላማ እየተማሩ ቢያድጉ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ያገባኛል ባይ እና ሀገራዊ ውሳኔዎች ላይ የመሳተፍ ተነሳሽነት ሊኖራቸው ይችላል። የተለያዩ ሀገራዊ ‹‹ስለ ሀገሬ ያገባኛል›› የሚል እና ንቁ እና ተሳታፊ የሆነ ዜጋን ማውጣጥ ዓላማቸው አድርገው የሲቪክ የትምህርት ዘርፍ (በኢትዮጵያ የሥነ ዜጋ ትምህርት የሚባለውን ትምህርት) ይሰጣሉ። መንግሥት በትምህርቱ ዘርፍ ፖሊሲን እንሚያወጣ አካል ይህ ኃላፊነት አለበት።

የኢሕአዲግን ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ የሥነ ዜጋ ትምህርት በመጀመሪያ መሠጠት የጀመረው በ1985 ዓ.ም ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ሲሆን ሥሙም ‹‹የሥነ ዜጋ›› የሚል ብቻ የነበረ ሲሆን፣ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ሌሎች የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ክፍሎችም እንደተቀላለቀሉት እና ሥሙም ‹‹የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር›› በሚል እንደተስተካከል አቶ ያማዳ የተባሉ አጥኚ በሥነ ዜጋ መማሪያ መጻሕፍት ላይ በሠሩት ጥናት ላይ ገልጸዋል።

ነገር ግን የትምህርቱ ዘርፍ በተለያዩ ምክንያቶች በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ንቁ እና ተሳታፊ የሆነ ዜጋ የማፍራቱን ግብ ሳይመታ ቀርቷል። አቶ እንዳልካቸው ባዬ የተባሉ ተመራማሪ እንደሚገልጹት፤ የትምህርት ዘርፉ በይዘቱ በሀገር ውስጥ ኩነቶች ላይ ብቻ በመወሰኑና አማራጭ የውጪ ተሞክሮዎችን ስለማያሳይ ብሎም በሒደቱ የሲቪክ ተቋማትን ስለማያሳትፍ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት አመለካከት እና ፖሊሲ ከማሳወቅ የዘለለ አስተጽዖ እንዳይኖረው ሆኖአል።

አቶ እንዳልካቸው የሥነ ዜጋ ትምህርት በሀገሪቷ የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ስላለው አስተዋጾዖ በሠሩት ጥናት፤ ተማሪዎች በመርኅ ከሚማሩት በተለየ የትምህርት ቤት አስተዳደሮች ዲሞክራሲያዊ አለመሆን፣ ፕላዝማ በመሰሉ ተማሪዎችን በማያሳትፉ አካሄዶች ትምህርቱ መሰጠቱ፣ የተማሩትን ለመተግበር የማያስችል ሀገሪቷ ያላት ደካማ የዲሞክራሲ ባህል፣ ያለው አነስተኛ የትምህርት ተደራሽት እና አርዓያ የሚሆኑ መምህራን መጥፋት ሌሎቹ የትምህርት ዘርፉ የታለመለትም በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ንቁ እና ተሳታፊ ዜጋ የማነጽ ግቡን እንዳይመታ ካደረጉት ኩነቶች መካከል መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ለ) ምክር ቤቱ በሚያዘጋጃቸው ኩነቶች
ፓርላማዎች ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ የማስተማር ኃላፊነት አለባቸው። ፓርላማዎች በዘመቻ መልክ፣ በሚታተሙ ጽሁፎች፣ በመገናኛ ብዙኀን ወይም በኢንተርኔት ብሎም ከሲቪል ማኅበራት ጋር በቁርኝት ማኅበረሰቡን ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ ለማሳወቅ ጥረት ሊያደርጉ ይችላሉ። ስለ ፓርላማ ማኅበረሰቡን የማሳወቅ ኃላፊነት ያለበት ዋነኛው ክፍል የሕዝብ ግንኙነት ነው። የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምክር ቤቱ በዚህ ዘርፍ የሚሠራውን ሥራ ሲያስረዱ፤ በተለያዩ ደረጃ እና ዘርፍ ያሉ ተማሪዎች ወደ ፓርላማው እየመጡ እንዲጎበኙና የተለያዩ ስብሰባዎችን ገብተው እንዲታዘቡ እንደሚመቻች ይገልጻሉ። ነገር ግን ተማሪዎቹ ከማየት በዘለለ ስለ ፓርላማ አሰራር ገለጻ የሚያገኙባቸው አጋጣሚዎች አናሳ መሆኑን አይሸሽጉም። የምክር ቤቱ የሚዲያ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከመምጣጡ በፊት ተማሪዎች ቢያንስ በሳምንት አንድ ቀን ለግማሽ ቀን ያክል ምክር ቤቱን ይጎበኙ እንደነበር ያስታውሳሉ። ምክር ቤቱ ስለ ፓርላማውና አሰራሩ ማኅበረሰቡን ከማስተዋወቅ ጋር በተያያዘ ከሚዲያ፣ ዩንቨርሲቲዎች ብሎም ከሲቪክ ማኅበራት ጋር ምንም ቋሚ እና ወጥ የሆነ ግንኙነት የለውም።

ሐ) በምክር ቤቱ የቴክኖሎጂ አካሄዶች
የምክር ቤቱ ድረ ገጽ እንደ መረጃ ምንጭነቱ የምክር ቤቱን የሥራ ድርሻ፣ ኃላፊነት፣ በዜጎች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ፣ እንዲሁም ዜጎች በፓርላማው ሥራ ውስጥ እንዴት ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሊያስቀምጥ ይገባል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለምክር ቤቱ ታሪካዊ አመጣጥ አጠር ካለ ገለጻ፣ የምክር ቤት አባላት እና ድርጅታዊ መዋቅር በዘለለ ዝርዝር የግንዛቤ ማስጨበጫ ይዘት አይገኝበትም። ይህ ብቻ ሳይሆን ድረ ገጹ (www.hopr.gov.et) የሚሠራበት ጊዜ አነስተኛ ነው።
ከድረ ገጽ በተጨማሪ ፓርላማዎች በማኅበራዊ ድረ ገጾቸው ላይ ለተጠቃሚዎች ሳቢ በሆነ መልኩ ስለ ፓርላማው ሊያስተምሩ ይችላሉ። ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሉት የፌስቡክ፣ የትዊትርም ሆነ የዩትዩብ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ስለ ምክር ቤቱ እና አሰራሩ የሚያስዋውቁ ይዘቶች ሲካተቱ ብዙም አይስተዋልም።

ማኅበረሰቡን ስለ ፓርላማ እና ሕዝባዊ ተሳትፎ የማሳወቅ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ እየተሰሩ አለመሆኑን የሚያምኑት የምክር ቤቱ የሚዲያ ኃላፊ በበኩላቸው በቅርቡ 16 ያክል ፕሮግራሞችን ያካተተ የራሳቸው መገናኛ ብዙኀን በሚያቋቋምበት ጊዜ ምክር ቤቱ ማኅበረሰቡን ስለምክር ቤቱ ለማሳወቅ የሚሰራው ሥራ በተሻለ እንደሚካሄድ ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ።

የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በበኩላቸው ምክር ቤቱ ማኅበረሰቡን ስለፓርላማው በማስተዋወቅ ላይ ክፍተት እንዳለ ገልጸው፣ ማኅበረሰቡ ስለፓርላማው በዋነኛነት ሊገነዘብ የሚችለው ስራዎቹ እና ስብሰባዎቹ በየሚዲያዎች በሚተላለፉበት ጊዜ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ። ኃላፊው አክለውም ከውጪ ሀገር ልምዶች እያጣቀሱ የተለያዩ ኩነቶችን በማዘጋጀት፣ የፓርላማ ሙዝየምን በማሰነዳት እና በቋሚነት ሳምንታዊ የሆኑ ሥራዎችን በመሥራት ስለ ፓርላማው እና የአሰራር ሒደቱ የማስተዋወቅ ሒደቶች ሊጎለብቱ እንደሚገባ ያምናሉ።

ማኅበረሰቡ በሕግ ማውጣጥ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ ለሚደረጉለት ጥሪዎች ላለመሳተፉ ዋነኛ ምክንያት የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎች አናሳ መሆናቸው መሆኑን የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብሎም የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያነጋገራቸው የምክር ቤት አባላት ያምናሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 120 የካቲት 13 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here