የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሲቪል ማኅበራት ታሪክ

0
1312

ይህ ፅሁፍ “ስለ ፓርላማ፣ ሕግ አወጣጥ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እና ሲቪክ ማኅበራት” በ‘ግሎባል ሪሰርች ኔትዎርክ ኦን ፓርላሜንት ኤንድ ፒዮፕል ፕሮግራም’ (Global Research Network on Parliaments and People) ድጋፍ እና በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (Forum for Social Studies) አሰተባባሪነት የተሠራ ጥናታዊ ጽሁፍ አካል ነው።
በዚህ ጽሁፍ ላይ የተካተቱ ማናቸውም ሐሳቦች የድጋፍ አድራጊውንም ሆነ የጥናቱን አስተባባሪ አቋም አያንጸባርቁም።

ሶለን ገመቹ (አምቦ ዩንቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
1. መንደርደሪያ
ከሦስት ሳምንት በፊት በዚሁ ዓምድ ሥር የሲቪል ማኅበራት ጽንሰ ሐሳብ በሚል ርዕስ የሲቪል ማኅበራት ምንነት ላይ ያለውን የተለያየ ግንዛቤ ለማሳየት ሞክሬ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ደግሞ የኢትዮጵያ የዘመናዊ ሲቪል ማኅበራትን ታሪክ በማስቃኘት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ዘርፉ ያለውን ግንዛቤ፣ ዘርፉ የሚሰራበትን የፖለቲካ ምኅዳር እንዲሁም ማኅበራቱ ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽሙበትን አቅም ለመገምገም ጥረት ይደረጋል።

በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት የሚተዳደሩበት አዋጅ (ቁጥር 1113/2011) “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት” የሚባሉትን ትርጓሚ ሲሰጥ “ቢያንስ ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመሠረት፣ የመንግሥት አካል ያልሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ከማናቸውም የፖለቲካ ድርጅት ያልወገነ እና ሕጋዊ ዓላማን ለማሳካት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ አካል” ይላቸዋል። እነዚህ ድርጅቶች፤ የሙያ ማኅበራት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና የድርጅቶች ኅብረቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

የሃይማኖት ተቋማት፣ እድር፣ እቁብ እና መሰል ባሕላዊ ስብስቦች እንዲሁም በሌላ ሕግ መሠረት የተቋቋሙ ማኅበራት እና ተቋማት በዚህ አዋጅ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ አልተካተቱም። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው እነኚህ ኢ-መደበኛ የሲቪል ማኅበራት ፈቃደኝነት ላይ የመመስረት፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ የመሆን፣ ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት እና ተመዝግቦ የመንቀሳቀስ ቅድመ ሁኔታዎችን ስለማያሟሉ ነው።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት አገራችንን ወደ አሳታፊ ዲሞክራሲ ማሸጋገር ይችላሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ታሪክ እንደሚነግረን አገሪቱ ለረጅም ጊዜ በተማከለ ንጉሣዊ እና አምባገነናዊ የሶሻሊስት ስርዓት ውስጥ የቆየች መሆንዋን ነው። እነዚህ መንግሥታትም ይከተሉ የነበረው ፖሊሲ የእዝ ኢኮኖሚ ነበር። ከ1983 የደርግ መንግሥት ውድቀት ማግስት ጀምሮ በአገሪቷ ውስጥ ዲሞክራሲን ለማስፈን እና ነጻ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የዘመናዊ ሲቪል ማኅበራት ዲሞክራሲን በማምጣት የልማት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ያስችላሉ ተብሎ ታምኖባቸዋል። በዚህ ምክያት እነዚህ ማኅበራት በሲቪልነት፣ በበጎ ፍቃደኝነት፣ በኢኮኖሚ ነጻነት፣ በዜግነት፣ በመብቶች፣ በሕግ የበላይነት እና ዲሞክራሲያዊ ውክልና መርሆዎች ላይ መመስረት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ከሚጠበቅበት ዓላማ እና ከሌላ አገራት ተሞክሮ አንጻር ኋላቀር በሚባልበት ደረጃ ላይ ነው። ለዚህ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሰው በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ የተማከለ ንጉሣዊ እና ወታደራዊ አስተዳደር ሥር ያዳበርነው ሥነ ልቦና እና የፖለቲካ ባህል ነው። የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ታሪክ እንደሚያስረዳው የሲቪል ማኅበራት እንደ ፖለቲካ ተቀናቃኝ የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩን ነው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ አሁንም የሲቪል ማኅበራትን ምንነት ለመረዳት፣ ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽሙበትን የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር እና ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽሙበትን አቅም ለመገንባት እየታገሉ ይገኛሉ።

የሲቪል ማኅበራት ከመንግሥት እና ከገበያ ውጪ ሆነው የተለያዩ ማኅበረሰባዊ ፍላጎችን ለማስከበር የሚሠሩ ሁሉን ዓይነት ማኅበራት እና ድርጅቶች ይጨምራል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የሲቪል ማኅበራት መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ብለን ኹለት ቦታ ልንከፍላቸው እንችላለን። መደበኛ የሲቪል ማኅበራት የምንላቸው በአገሪቱ ሕግ መሰረት ሕጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው፣ ለሕጋዊ ዓላማ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችና ማኅበራትን ሲሆን፤ ኢ-መደበኛ የሲቪል ማኅበራት ደግሞ በአገሪቱ ሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ ያልተካተቱ የሃይማኖት እና የጎሳ ማኅበራት ብሎም የራስ አገዝ ቡድኖች ናቸው።

ዘመናዊ የሲቪክ ማኅበራት በኢትዮጵያ ውስጥ ከመተዋወቃችው በፊት ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ እና የጎሳ ማኅበራት ብሎም የራስ አገዝ ቡድን አደረጃጀትቶች እንደነበሩ የታሪክ እና የባህል አጥኚዎች ይነግሩናል። እስካሁንም ድረስ እንደ እድር፣ እቁብ፣ ሽምግልና፣ ደቦ፣ ወዘተ የሚባሉ የራስ አገዝ ቡድን አደረጃጀቶች ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። በዋነኛነት ግን ዓላማቸው ግለሰቦችን፣ ቤተሰቦችን እና ኅብረተሰቦችን ራስ ማስቻል ነው። እነዚህ ራስ አገዝ ቡድኖች የአጥኚዎችን ትኩረት ስላላገኙ ብዙ የጽሁፍ ማስረጃዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

2. የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሲቪል ማኅበራት ታሪክ በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት
ጄፈሪ ክላርክ ከዓለም ባንክ የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ ጋር በመተባበር ባደረገው ጥናት ላይ እንደጠቆመው ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት መታየት የጀመሩት በ1920ዎች ውስጥ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የከተሞች መስፋፋት እና የኢኮኖሚ እድገት መታየት በመጀመሩ ነበር።

የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት ያለውን ፍላጎት ለማሟላት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሚና ከግምት ውስጥ አስገብቶ እንቅስቃሴ እንዲጀምሩ ተደረገ። ዘመናዊ ትምህርት እንዲስፋፋ የተደረገው ጥረት አፍርቶ የተማረው የማኅበረሰብ ክፍል መንግሥት እየሰጠ ያለውን ማኅበራዊ አገልግሎት በቂ አለመሆን መተቸት ጀመረ። ይህን የመንግሥት ማኅበራዊ አገልግሎት እጥረት በተወሰነ ደረጃ ለመሙላት አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (Local NGOs) በ1950ዎቹ ውስጥ ኢትዮጵያ ውስጥ መታየት ጀመሩ። የአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለእነዚህ ድርጅቶች እውቅና ለመስጠት ስለ ፈለገ በ1952 የሲቪል ማኅበራት ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተቱ ተደረገ። በዚህ የሕግ ማዕቀፍ መሰረት በቀደምትነት የተቋቋሙት የንግድ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር (National Bar Association) በመንግሥታዊ አስተዳደር ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበራቸው።

ዓለም ዐቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (International NGOs) ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋውቁት 1965-1966 በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ነው። እነዚህ ዓለም ዐቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድርቁ ያስከተለውን የጉዳት መጠን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። ሃይማኖታዊ ድርጅቶችም በተመሳሳይ የድርቁን ጉዳት ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው።

በ1965 የረሃብ ጊዜ ተሳታፊ ከነበሩ ድርጅቶች መካከል የተወሰኑት መረጃ ለመለዋወጥ እና የእርዳታ ማቅረቡን ሥራ ለማቀናጀት ተስማሙ። በወቅቱ የተከሰትው ድርቅ እየተባባሰ ሲሄድ የክርስቲያን በጎ አድራጎት ፈንድ የሚባል የባንክ ሒሳብ ተከፍቶ ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመረ። በዚህ መልኩ የተጀመረው ትብብር በሒደት የክርስቲያን ረድዔት ማኅበር (Consortium of Christian Relief and Development Association/CCRDA) በመባል የሚታወቀውን ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ኅብረት አቋቋሙ። የዚህ ኅብረት መቋቋም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በኃይለ ሥላሴ መንግሥት እና የሲቪል ማኅበራት መካከል የተቀናጀ ሥራ እንዲሠራ አስችሏል። ይህን ቅንጅት ለማሳለጥ በ1966 እርዳታ ማስተባበሪያ እና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ተመሰረተ።

3. የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሲቪል ማኅበራት ታሪክ በደርግ ዘመነ መንግሥት
በ1966 ንጉሳዊው አስተዳደር በሕዝባዊ እና ወታደራዊ አመጽ ከተገረሰሰ በኋላ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት የማርክሲስት ርዕዮተ ዓለምን አንግቦ ሥልጣን ያዘ። የደርግ መንግሥት በሚከተለው የማርክሲስት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ኢምፔርያሊስት (imperialist) በሚላቸው ምዕራባዊ ዓለም ዐቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ላይ እምነት ስላልነበረው በተቻለ መጠን ቁጥጥር ለማድረግ ሞክሯል። በዚህ የደርግ መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር ምክንያት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተቋቋሙት እና ራሳቸውን ችለው በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ይፈጥሩ የነበሩ የሲቪል ማኅበራት እንዲጠፉ ወይም የመንግሥትን አጀንዳ አስፈጻሚ እንዲሆኑ ተደረጉ። በዚህ ምክንያት ብዙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሥራ አቆሙ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ ደርግ ዘመን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተጨቆኑበት ጊዜ እንደሌለ ይነገራል። በወቅቱ በአነስተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የሙያ ማኅበራት፣ የመገናኛ ብዙኀን ድርጅቶች፣ የትምህርት ዘርፍ፣ የግል ንግድ ድርጅቶች፣ ወዘተ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ጭቆና ይደርስባቸው ነበር። በዚህ ወቅት ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ካላቸው ትናንሽ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ውጪ ይሄ ነው የሚባል አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (local NGOs) አልነበሩም። የነበሩትም መሪዎቻቸው ከአገር እንዲባረሩ፣ እንዲታሠሩ ብሎም እንዲገደሉ ሆኗል።

በ1976-1977 በተከሰተው አስከፊ ድርቅ ምክንያት የተከተለው ችግር ከመንግሥት አቅም በላይ በመሆኑ የደርግ መንግሥት ቁጥጥሩ እንዲቀንስ እና የውጭ አገር በጎ አድራጊ ድርጅቶች በብዛት እንዲገቡ እንዲፍቅድ ተገደደ። ብዙዎቹ ዓለም ዐቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ከመንግሥት ይልቅ አገር በቀል በሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች በኩል እርዳታ እንዲከፋፈል ግፊት ያደርጉ ነበር። ይህ የሆነው በደርግ መንግሥት ፖሊሲ ላይ ባላቸው ጥርጣሬ ምክንያት ነው።

በዚሁ ድርቅ በተከሰተበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት የነበረበት ጊዜ ነበር። በደርግ ቁጥጥር ሥር የነበሩ አካባቢዎች ላይ እርዳታ የሚያቀርቡት አቅም ያላቸው ዓለም ዐቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ከአገር በቀል የሃይማኖት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ብሎም የተባበሩት መንግሥታት የበጎ አድራጎት ተቋም ነበር። የአገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅቶች (Local NGOs) ሚና ከዓለማቀፍ እርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የእርዳታ ቁሳቁስ ከማከፋፈል ያለፈ አልነበረም። በአንጻሩ በአማጺያን በተያዘው አካባቢ የአማጺ ድርጅቶቹ ሰብኣዊ አገልግሎት ክንፍ ብቸኛዎቹ አገልግሎት ሰጪዎች ነበሩ። እናም የትግራይ እርዳታ ድርጅት (TRA)፣ የኤርትራ እርዳታ ድርጅት (ERA) እና በዝቅተኛ ደረጃ ደግሞ የኦሮሞ እርዳታ ድርጅት (ORA) የምግብ እና የአደጋ ጊዜ ቁሳቁሶችን በተወሳሰበና ከማዕከላዊ መንግሥቱም ሆነ ከዓለም ዐቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ያከፋፍሉ ነበር። ይህም የአማጺ ድርጅቶችን አቅም ለመገንባትና እና እራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ነበረው። በተጨማሪም በማኅበረሰቡና በአማፂ ድርጅቶቹ መካከል መተማመንን ለመፍጠር አስችሏል።

4. እንደ ማጠቃለያ
የቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ እና የደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ዘመናዊ የሲቪል ማኅበራት ታሪክ እንደሚያስረዳን የሲቪል ማኅበራት ሚና ከሰብኣዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር የተቆራኘ ነበር። በዚህ ምክንያት እስካሁን ድረስ ያለው የሲቪል ማኅበራት አረዳድ እንደ እርዳታ አቅራቢ ድርጅትነት ተደርጎ ተወስዶአል። ይሄ እሳቤ ድርጅቶቹ ዘላቂ ልማት በማምጣጥ ረገድ ያላቸው ሚና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። ሌላው እስካሁን የቀጠለው ችግር ዘመናዊው የሲቪል ማኅበራት ዘርፍ በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ተጽዕኖ ሥር ሙሉ በመሉ መውደቁ ነው። ምንም እንኳን መንግሥታዊ ያልሆኑ ዘመናዊ አገር በቀል ድርጅቶች የተዋወቁት በ1950ዎቹ ቢሆንም በአገሪቱ ዘላቂ ልማት ላይ ሚና መጫወት የጀመሩት ከ1983 የደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ እንደበረ ይነገራል።


ቅጽ 2 ቁጥር 121 የካቲት 20 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here