“የሕገ መንግሥት ማሻሻል አገር ከተረጋጋ በኋላ መሆን ይገባዋል”

0
523

ሙሉጌታ አረጋዊ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ለስድስት ዓመታት በትርፍ ጊዜ መምህርነት ሕገ መንግሥት፣ የመገናኛ ብዙኀን ሕግ፣ የሕግ ፍልስፍና እንዲሁም የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግን በማስተማር እንዲሁም የምርምር ሥራዎች ላይ የማማከር አገልግሎት በመስጠት ይታወቃሉ። በይበልጥ በተለይ በአገር ውስጥ እና የውጪ መገናኛ ብዙኀን ላይ ንቁ ተሳታፊ ሲሆኑ በሚሰጡትም በሳል የሕግ ትንታኔና አስተያየትም ይታወቃሉ።
መቀሌ የተወለዱት ሙሉጌታ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሕንዶችና ሚስዮናውያን በሚያስተምሩበት በአፄ ዮሐንስ ትምህርት ቤት አጠናቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በመጀመሪያ ዲግሪ የፍልስፍና ትምህርታቸውን ተከታትለው ለመጨረስ አንድ መንፈቅ ሲቀራቸው በ1976 በወቅቱ መንግሥት ታሰሩ። በ1983 የመንግሥት ለውጥ ሲመጣ ከእስር ተፈተዋል።
ከእስር ቤት መልስ ሙሉጌታ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የትምህርት ዘርፍ ለውጠው በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አጠናቀዋል። የሥራውን ዓለምም በመቀላቀል ለዐሥር ወራት በኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ሠርተዋል።
ወደ ሰሜን አሜሪካ በማቅናት በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኘው ዋሽንግተን የሕግ ኮሌጅ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሕግ ትምህርት አጠናቀዋል። ለሁለት ዓመት ተኩል በኢትዮጵያ ኮሚውኒቲ በ‹ካውንስለርነት› ያገለገሉት ሙሉጌታ፥ የራሳቸውን የሕግ አገልግሎት መስጫ ቢሮ በመክፈት እስከ 2008 ድረስ ለ16 ዓመታት በአሜሪካ አገልግለዋል።
ከሥነ ጽሑፍ ጋር ያላቸው የበዛ ቀረቤታ ”በሕይወቴ በጣም የሚያስደስተኝ ማንበብ ነው” የሚሉት ሙሉጌታ በሚያነቧቸው መጻሕፍት በጣም እንደሚደመሙ እንዲሁም በዛ ደረጃ እንዴት ሊጻፍ ይችላል በሚል ራሳቸውን በተደጋጋሚ ይጠይቁ እንደነበረ ተናግረዋል። ሥነ ጽሑፍን ማድነቅ ዝንባሌና ፍላጎታቸው መሆኑንም ሙሉጌታ በአንክሮ ይገልጻሉ። የመጀመሪያ ጽሑፋቸውን 1980ዎቹ አጋማሽ በ‹በኢትዮጵያ ሔራልድ› ላይ በእንግሊዘኛ ያሟሹት ሙሉጌታ ለኢትዮጵያ ሬዲዮ በርካታ የእንግሊዝኛ ጽሑፎችን አበርክተዋል።
“እንደ አንድ የማኅበረሰቡ አባልነቴ ድምጽ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖሬን ለማሳወቅ ነው ሥነ ጽሑፍ የማበረክተው” የሚሉት ሙሉጌታ ከነባራዊው እውነት በመነሳት ‹ኤክስፐርመንታል› የሆኑ ሁለት የረጅም ልቦለድ ሥራዎች አበርክተዋል፡- ‹ዲቪ ሎተሪ›ን በ1993 እና ‹አብራክ›ን በ2011 አበርክተዋል።
ስለከፍትኛ ትምህርት፣ ሕገ መንግሥት እንዲሁም ተያያዥ ወቅታዊ የሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከሙሉጌታ አረጋዊ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ወስጥ ያለውን የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት እንዲሁም አሰጣጥ በተለይ እርሶዎ ከሚያስተምሩበት የሕግ ትምህርት ቤት አንጻር እንዴት ያዩታል?
[በአገራችን] ትምህርት [ጥራት] በአጠቃላይ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው። በንጽጽር የሕግ ትምህርት በተሻለ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፤ ነገር ግን የሕግ ትምህርት ቤቱም ቢሆን ከችግር አላመለጠም። በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ መርሐ ግብር ከፍተኛ ፈተና ውስጥ እንዳለ ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ለምሳሌ እኔ ራሴ በተጨባጭ በተደጋጋሚ በመጀመሪያ ዲግሪም ሆነ በሁለተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጽሑፍ ላይ ያጋጠመኝ የሌላ ሰው ሥራን በመውሰድ እንደራስ ቆጥሮ ማቅረብ ተጠቃሽ ነው።
ተማሪዎቹን ብትወስድ ከፍተኛ የመማር ፍላጎት አላቸው፤ ይሁንና በአጠቃላይ በራሳቸው ተናሽነት ቀርቶ የተሰጣቸውን የተግባር ሥራ ለመሥራት እንኳን አያነቡም። ተግባራዊ ሥራዉ ከዚህ በፊት ተሰጥቶ ከሆነ በወቅቱ ጥሩ ውጤት ያስመዘገበውን ተማሪ ጽሑፍ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግበት ቃል በቃል ገልብጦ የማቅረብ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ብሩህ አእምሮ ያላቸው ካሉበት ደረጃ አንጻር የማይጠበቁ ተማሪዎችም አሉ። ከሚሰጣቸው የተግባር ሥራ ባሻገር ብዙ በርካታ መጻሕፍትን አንብበው የሚገዳደሩ አሉ፤ ይሁንና ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነው። የእኔም ቢሆን ትኩረቴ እንደነዚህ ዓይነት ተማሪዎችን መርዳት ላይ ነው።
ሌላው በመምህራንም ላይ ቢሆን ችግር አለ። የትርፍ ሰዓት ሥራ የሚያሳድዱ፣ ተማሪዎችን የሚያሰቃዩ፣ ለተማሪው መጥፎ አርዓያ ሆነው የሚወሰዱ እንዲሁም ከውጤት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ችግር ያለባቸው መምህራን አሉ።
የትምህርት ነጻነትን በተመለከተ በጣም ከፍተኛ ችግር አለ። ተማሪውም፣ መምህሩም ሆነ አስተዳዳሪዎቹ ይፈራሉ፤ ሁሉም ወገን ለምን እንደሚፈራ ደግሞ አያውቅም። በዚህ ምክንያት ብዙ የምርምር ሥራዎች ሲሠሩ አይታይም ምክንያቱም ፍርሃቱ ስላለ። የኑሮ ጫና መኖርም እንዲሁ ተጠቃሽ ነው።
እርሶዎ ሓሳብዎትን በድፍረት በመናገርዎት፣ በመጻፍዎት እና መብትዎን ለማሰከበር በሚያደርጉት ጥረት ያጋጠመዎት ችግር አለ?
እኔ ለእንደዚህ ዓይነት እርምጃዎች አልመቻቸውም ምክንያቱም በትርፍ ሰዓት ሠራተኛነቴ እኔ በተመቸኝ ሁኔታ እንጂ እነሱ በፈለጉበት ሁኔታ አይደለም። በአጭሩ በዩኒቨርሲቲውና በእኔ መካከል አስገዳጅ የሆነ ግንኙነት የለም። በመሆኑም ‹‹ይህን አድርግ፤ ይህንን አታድርግ›› የሚባል ነገር ውስጥ አይገቡም። እኔም ሕይወትም ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርሱ ዕድሉን አልሰጣቸውም።
ሕገ መንግሥታዊነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ቦታ እንዴት ያዩታል?
ሕገ መንግሥታዊነት በአጭሩ የመንግሥትን ሥልጣን መገደብ ማለት ነው። ይህንንም ለማድረግ ሥልጣኑ ይከፋፈላል እንዲሁም ይገደባል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ይህንን በአንቀጽ 8 ላይ የሕዝብ ሉዓላዊነት በማለት በግልጽ አስቀምጦታል። ይህ መሠረታዊ መርሕ ነው። በአጭሩ የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን ያሳያል።
ራስን በራስ ማስተዳደር ዴሞክራሲ ነው። እንደዚህ ዓይነት ዴሞክራሲ ግን አሁን ማድረግ አይቻልም፥ አቴንስ ላይ ቀርቷል። ስለዚህ አሁን ያለው ወኪሎች የሕዝብን ፍላጎት ያራምዳሉ።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱን የተረዳንበት መንገድ በራሱ ችግር አለበት። ሁለተኛ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታዊነትን ተቃዋሚዎችን፣ ጋዜጠኞችን ወዘተ የሚጨቁኑበት መሣሪያ ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊነት በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እንጂ በተግባር የለም።
የዴሞክራሲና የግለሰብ ነፃነት መርሖዎች ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጤ መሆናቸው ወይም እንዲዋሐዱ አለመደረጋቸው ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ማነቆ ሆኗል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ሕግ ሊኖር የሚችለው ኢትዮጵያ በደረሰችበት ደረጃ ልክ ነው። ለምሳሌ ማንበብና መጻፍ የማይችል ሕዝብ ሊኖር የሚችለው ሕግ በቃል በይትበሃል በአብዛኛው የሚተላለፍ ነው። “በሕግ አማላክ” እንደሚባለው ሕግ የሆነ ኃይል እንዳለው ትረዳለህ። ከዚህ ጆሮ ጠገብ ዕወቀትና ግንዛቤ ተወጥቶ ነው ወደ ዘመናዊ ሕግ የተገባው።
የእኛ ሕገ መንግሥት ከአሜሪካ እንዲሁም ሌሎች ሕጎች ደግሞ ከአውሮፓውያን የተቀዱ ናቸው። ይሁንና ታሪካችንም ሆነ ባሕላችን የሚያሳየን ሥልጣን በኃይል ሲያዝ ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የልኂቃን ጨዋታ ነው። ዴሞክራሲን ከየትም ልናመጣ አንችልም፣ አልተማርንም፤ መንግሥትንም የምንቆጣጠርበት ምንም ዓይነት መንገድ የለም።
በአጭሩ ዴሞክራሲ ከሉዓላዊነት ጋር፣ ከእርስ በርስ ግንኙነት ጋር እንዲሁም ሐሳቡ ዓለም ዐቀፋዊ በመሆኑ ድንበር የለውም።
ባህሎቻችንስ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ናቸው ብሎ መደምደም ይቻላል?
በሚገባ! ምንም ጥያቄ የለውም። ለአብነት የሕፃናት አስተዳደግን እና በቤተሰብ እና በአገር ደረጃ የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል የሚባሉትን የሴቶች ተሳትፎ ብንመለከት በጣም ኋላቀር መሆናችንን ያሳያሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሊያግባቡን ከማይችሉ የታሪክ፣ የማንነት፣ የዘር እና መሰል ትርክቶች ወጥተን በሕገ መንግስታዊ መርሆዎች ላይ የተመሰረተ አንድነት መገንባት ያስፈልገናል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ይሁንና በኢትዮጵያ ሁሉም ነገር የሚወሰነው በልኂቃን (በተማረውና ገንዘብ ባለው ሀብታም) ነው። እነዚህ ልኂቃንና ሲስማሙ ሰላም እናገኛለን።
ሕገ መንግሥታዊነትን በተመለከተ ትልቁ ችግር ምንድን ነው?
ትልቁ የኢሕአዴግ ችግር ሕገ መንግሥትን ተግባራዊ አለማድረግ ነው። በምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻልን የመቀበል ዝንባሌ አልነበራቸውም። በራሱ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሕገ መንግሥት መሻሻል ሥርዓት አለው። እኔ የምለው ሕገ መንግሥቱን አያውቁትም ነው።
አሁን ካለው የለውጥ ሂደት አንፃር በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎች ይኖራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሥር ከሰደደው የጥላቻ ፖለቲካ እና መራራቅ አንፃር መንግሥት እና ፖለቲከኞቻችን ምን ዓይነት ሂደት ቢከተሉ የተሸለ ውጤት ይኖራል ብለው ያስባሉ?
በንድፈ ሓሳብ ደረጃ ማሰብ ከባድ አይደለም። ለምሳሌ ሰላም እንሆናለን ብለን ካሰብን፤ አገር ይረጋጋል ብለን አሰብን ማለት ነው። ነገር ግን ሕገ መንግሥት ማሻሻል አገር ከተረጋጋ በኋላ መሆን ይገባዋል። ከዚህ በኋላ ኢሕአዲጎች እንደጀመሩት ተቃዋሚ መቃወም ትችላለህ፥ መብትህ ነው፤ ሕገ መንግሥቱን እናከብራለን። ይህ ማለት ምርጫ እናካሒዳለን ማለት ነው። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ ሳይቀየር ፍትሓዊና ነፃ ምርጫ ታካሒዳለህ። ሕገ መንግሥት መለወጥ የሚቻለው የእውነት ወካይ መንግሥት ከተፈጠረ በኋላ መሆን አለበት።
አንዳንድ ምሁራን ቅድሚያ መስጠት የሚገባው ሰላምና መረጋጋት መሆኑን በመግለጽ አሁን እየተደረጉ የሚገኙ የሕግ ማሻሻያ ሒደቶችን ይተቻሉ። በእነዚህ ላይ ያለዎት አቋም ምንድን ነው?
እኔ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ነው ሰላምና መረጋጋት ከተፈጠረ በኋላ መሻሻል ይገባዋል ያልኩት፤ የሌሎቹን ሕጎች ማሻሻል በተመለከተ ከሰላምና መረጋጋት ጋር አብሮ ይሔል። ምክንያቱም የሕጎቹ መሻሻል ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ያግዛልና። ለምሳሌ የሲቪል ማኅበራት ሕግ ተሸሽሎ ሊጸድቅ ነው። ጸድቆ ወደ ተግባር ሲገባ አገርን የማረጋጋት ሚና ይኖረዋል። ስለዚህ ሁለቱንም አብሮ ማስኬድ ይቻላል።
በመጀመሪያ ደረጃ የሲቪል ማኅበራት፣ የሚዲያ፣ የፀረ ሽብርተኝነት ወዘተ ሕጎች ኢሕገ መንግሥታዊ ናቸው። ከሕገ መንግሥት ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም። ሲጀመርም መኖር ያልነበረባቸው ናቸው። ሕገ መንግሥቱ የፈጠራቸው አይደሉም። የመንግሥትን ጉልበት መቀነስ አገር ለማረጋጋርት ያግዛል። ስለዚህ የሕጎቹ መቀየር ወይም መሻሻል ተስፋ ይሰጣል።
የሕግ ማሻሻል ሒደቱንስ እንዴት ይመለከቱታል? እርስዎስ በማሻሻል ሒደቱ ውስጥ ምን ተሳትፎ እያደረጉ ነው?
በሕግ ማሻሻል ሒደት ውስጥ እንድሳተፍ ተጋብዤ ነበር፤ ይሁንና አልተቀበልኩትም ነበር።
ለምን?
[ኢሕአዲጎችን] ስለማላምናቸው ነበር። እውነተኛ የማሻሻል ፍላጎት መኖሩን እርግጠኛ አልነበርኩም። ማመን የጀመርኩት ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ማነጋገር ስጀምር ሁሉም ደስተኞች ናቸው። ስብሰባም ሲጠሩ ይሳተፋሉ፣ ይከራከራሉ።
የሚዲያ ሕግን ያስተምራሉ ለሚዲያው ቅርብ እንደመሆንዎት አሁን ያለውን የሚዲያ እንቅስቃሴ እንዴት ይገመግሙታል?
የመገናኛ ብዙኀኑን መነቃቃት ወድጄዋለሁ። ልብ አድርግ! ሕጉ አልተለወጠም፣ መንግሥት አልተለወጠም ይሁንና ስሜቱ ብቻ ተቀይሯል። ስለዚህ ለከባቢው ያለን ስሜት ተለውጧል። ከዚህ በፊት የነበረው የፍርሃት ሥሜት ፈጽሞ የለም።
ሁሉም ለውጡን ወደ ተሻለና ወደሚፈለገው ደረጃ እንዲያድግ ለማገዝ እንዲሁም ሁሉን ዐቀፍ እንዲሆን የሚዲያው ሚና ምን መሆን አለበት?
መገናኛ ብዙኀን የተለያየ ሓሳብ የሚስተናገዱበት መሆን አለበት። የመንግሥት ሚዲያን በተመለከተ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አለበት። የግሉ ይህ ጫና ላይኖርበት ይችላል። የግሉም ቢሆን ግን የአገር ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ሚና ለመጫወት፤ ብዝኀ ሓሳብ ማስተናገድ ይገባዋል።
ሁለተኛው ሚዲያው ይሔን የተገኘ አጋጣሚ መጠቀም መቻል አለበት። ይህም ማለት በኃላፊነት፣ ሚዛናዊ ሆኖ፣ ሙያዊ ሥነ ምግባሩን ጠብቆ ግዴታውን መወጣት ማለት ነው።
ሌላው “ሰው የሚፈልገው ምንድን ነው?” ብቻ ሳይሆን “ሰው መፈለግ ያለበት ምንድን ነው?” የሚለውን መለየት ይገባዋል። ሚዲያው ተመሪ ብቻ ሳይሆን መሪም መሆን መቻል አለበት። ስለዚህም እንደዚህ ዓይነቱን ሚና ለመጫወት “በአገራችን መሠረታዊ ነገር ምንድን ነው? የትኛው ችግር ላይ ነው መሠራት ያለበት?” በሚል የራሱንም አጀንዳ መቅረጽ ይኖርበታል።
ብዙ ጊዜ የሕዝብ ፍላጎት ተጽዕኖ የሚያርፍበት በጉልበት ነው። ጉልበተኛው ደግሞ መንግሥት ነው። ስለዚህ ነው በመጀመሪያ ሚዲያ መንግሥትን መቆጣጠር አለበት ብለን የምናስበው። ሚዲያው በራሱ በቀጥታ አይደለም በመንግሥት ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው ነገር ግን ሕዝቡን በማሳወቅ፥ ሕዝቡ እንዲጠይቅና ተጽዕኖ እንዲያሳድር በማድረግ ነው።
የሚዲያው ዋና ዓላማ ለሕዝብ መረጃን ማቀበል ነው። በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መረጃ የምታቀብለው መረጃውን መሠረት ያደረገ ውሳኔ እንዲወሰን ለማስቻል ነው። በዚህም የሕዝብ ፍላጎት ወደ ፊት የማስኬድ ወይም የማሳደግ ተስፋው ይሰፋል። ሚዲያው “እነዚህ ባለሥልጣናት ትክክል አይደሉም” ብሎ ካስተማረ በሚቀጥለው ምርጫ ባለሥልጣናቱን ያባርራል ማለት ነው። ስለዚህ ይህንን ኃላፊነት ወስዶ የተለያዩ ሓሳቦችን ያለአድልዎ በማስተናገድ ሚዲያው ሁሉንም እየተከታተለ ማኅበረሰቡን መጥቀም፣ መረጃ ማቀበልና ማስተማር ይችላል።
በሚዲያው በኩል ያሉ ጉድለቶች ምንድን ናቸው?
ሚዲያው ገና እየጀመረ እንደመሆኑ የገንዘብ አቅም ችግር ይኖራል። ሌሎች ብዙ ውስንነቶችም እንዳሉ ግልጽ ሆኖ ሳለ ለእኔ መረጃ ወይም ዜና ያለው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ አይደለም። ዜና ያለው በየቀበሌውና በየክፍለ ከተማው ነው። ሚዲያው እነዚህ ነገሮች ላይ ስለማይሰራ ብዙ ዜና የለውም። ወደ ቀበሌና ክፍለ ከተማ ወርዶ በሚሠራበት ጊዜ የሰውን ልብ ያሸንፋል፤ ተቀባይነትም ይኖረዋል። ያን ጊዜ ሕዝቡም ይከተለዋል። ውስንነቱን በተመለከተ በሁሉም ዘርፍ እንዳለ ሆኖ ጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ግን የበለጠ መሠራት እንዳለበት ይታመናል።
አሜሪካን አገር በጥብቅና ሙያ እንደማገልገልዎት በዚህም የፍትሕ ሥርዓቱን በቅርብ እንደማወቅዎት በኢትዮጵያ ውስጥ በሕግ ትግበራ የጎደለ ወሳኝ ነገር ምንድን ነው?
የፍርድ ቤት ነፃነት ነው። በአሜሪካ የፍትሕ ሥርዓቱ ገለልተኛ ነው ሲባል በትክክልም ገለልተኝነቱን በተግባር ታያለህ። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ለሕግ ያለው አክብሮት አስገራሚ ነው። የሕግ ተግባራዊ መደረግ፣ የዳኞች ተደማጭነትና ተከባሪነት ያስገርማል። የሕግ መጓደል ችግር የለም፤ ችግር እንኳን ቢኖር በይግባኝ ይታያል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here