በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ በጊንጪ ከተማ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነው ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከፍተኛ የክልሉ እና የፌዴራል ባለሥልጣናት በተገኙበት ዛሬ ይመረቃል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በጊንጪ ከተማ የተገነባው ከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ስምንት ነጥብ አራት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጭ 85 በመቶ ከፈረንሳይ የልማት ባንክ የተገኘ ሲሆን 15 በመቶው በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳሬክተር ሞገስ መኮንን ተናግረዋል።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው ኹለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች የተገጠሙለት ሲሆን 100 ሜጋ ዋት መሸከም የሚችል ኤ.አይ.ኤስ ሲስተም (Air Insulated System) የሆነ የማከፋፈያ ጣቢያ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወደ ማከፋፈያው የሚሄደው ገቢመስመር ከገፈርሳ ወደ ጌዶ ከተዘረጋው መስመር ላይ 0.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥንድ ገቢ መስመር አለው ወጪ መስመርሩ ደግሞ አስር ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት ብለዋል።
ከአዲስአበባ በ83 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት በጊንጪ ከተማ የተገነባው የኃይል ማከፋፈያ በ2008 ዓመተ ምህረት ነሀሴ ወር ተጀምሮ ሐምሌ 2012 ተጠናቋል። ፕሮጀክቱ ለ200 ሰዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጥሯል ሲሉ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳሬክተሩ ገልጸዋል።
የግንባታው ተቋራጭ ላርሰን ኤንድ ቱርቦ የተባለ የህንድ ኩባኒያ ሲሆን አማካሪው ኤም ቪ ቪ ዲከን የተባለ የጀርመን እና የስዊዘርላንድ ኩባንያ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች። የግንባታው ተቋራጭ እና አማካሪ ድርጅቶች ወደ ሥራው የገቡት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያወጣውን ዓለምአቀፍ ጨረታ ተካፍለው መሆኑን ሞገስ አስታውሰዋል።
ለጊንጪ ከተማ እና ለአካባቢው ያለውን የኃይል አቅርቦት ችግር እንደሚያስተካክል እና ያልተቆራረጠና አስተማማኝ ኃይል ለመስጠት እንደሚያስችል እንዲሁም በአካባቢው ለመገንባት ለታቀዱት ፋብካዎች እንዲሁም የወንጭ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች በቂ ኃይል ያቀርባል ሲሉ አሳውቀዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ያለዉ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ሺሕ 528 ሜጋ ዋት መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል። በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን ከ17 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል በማለት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የዋና ሥራ አስፈፃሚ የቴክኒክ አማካሪ ኢንጂነር አንዳርጌ እሸቴ ገልጸዋል።
ኢንጂነር አንዳርጌ አያይዘውም በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት የዘለለ ዕድሜ ቢያስቆጥርም የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋኑ ግን ከ44 በመቶ አላለፈም ብለዋል። እንደ አማካሪው ገለፃ ከዚህ በፊት የነበረው የኢነርጂ ፖሊሲ የግል ባለሃብቶች በኃይል ልማት ዘርፉ ላይ እንዲሳተፉ የሚጋብዝ ባለመሆኑ ለኃይል ማመንጨትና አቅም ማነስ እና የተደራሽነት ሽፋኑ ዝቅተኛ መሆን ምክንያት ሆኖ ነው በማለት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሚውል በርካታ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ያላት ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የግል ባለሃብቱ በአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ በዲቼቶና ጋድ የፀሃይ ኃይል እና በኮርቤቴ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳታፊ መሆን መጀመራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላው አገሪቱ የዲዝል መጠባበቂያ ኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ 23 ማመንጫ ጣቢያዎችን እንደሚያስተዳድር አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013



