ደብሊን፤ ጊነስ ቢራና የአየርላንዳውያን አበርክቶ

Views: 228

ቤተልሔም ነጋሽ ባለፈው ሳምንት የጀመሩትን የአየርላንድ ጉብኝት በዚህ ሳምንት ያጠቃልላሉ። የዚህኛው መጣጥፋቸው የሞሃር ገደሎችን፣ የጊነስ ቢራ ታሪክ ሥፍራ እንዲሁም መዘክራቸውን ከማስጎብኘታቸው ባሻገር ከአገሬው ወግ ጀባ ብለዋል።

 

 

(ክፍል ኹለት)
ደህና ብራ ሆኖ ከርሞ አስተናጋጅ ጓደኛዬን ይህን አየር ጠባይ ነው የምታማርረው እስክል፡ “ባክሽ እድለኛ ሆነሽ ነው፤ እኔ በቆየሁባቸው ወራት እንዲህ ያለ ብራ ቀኖች አላየሁም” ሲል የቆየሁበት ኹለት ሳምንት አልፎ አልፎ ከነበረው የጠዋት ላይ ነፋስ በስተቀር ብርድም ሳይኖር ጭራሽ ጃኬት የሚያስወልቅ ሞቅ ያለ የሚያምር ሆኖ ከርሞ ማምሻውን በማድሪድ አድርጎ አዲስ አበባ የሚመለሰው ኢቲ 713 አገሬ ሊመልሰኝ ባለ ቀን፣ የወትሮውን አየር ሳላይ እንዳልሔድ ይመስል ቀኑን ሙሉ ካፊያ ሆኖ ዋለ። ለመጨረሻ ከተማዋን ልሰናበት ለቡና ቀጠሮ ወደያዝኩበት ሳመራ ንፋሱ እየገፋኝ ካፊያው ብን እያለ ነበር። ተመልሼ በሰዓቴ ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ለመሔድ ስወጣም ካፊያው ጠንከር እንደማለት አድርጎት ሻንጣዬን፡ መግፋት መከራ ነበር።

ደብሊንን ለቅቄ ከመውጣቴ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ከማውራቴ በፊት ባለፈው ሳምንት ጽሑፍ ስለጎበኘኋቸው ተጨማሪ ቦታዎች ባጭሩ ላስቀምጥ
የሞሃር ገደሎች (Cliffs of Moher) የሞሃር ገደሎች በሚል የሚጠሩትን የተፈጥሮ ውብ ቦታ ለማየት ስሔድ ምናልባት ከደብሊን ውጪ አረንጓዴና ውብ የሆነችውን በርካታ ፊልሞች የተቀረፁበት ውብ መልከዓ ምድር ለማየትም ጭምር ዕድል አግኝቻለሁ። የሞሃር ገደሎች የሚገኙት ክሌር ካውንቲ በሚሰኘው የአየርላንድ ደቡብ ምዕራብ ክፍል ሲሆን እዚያ ለመድረስ ከደብሊን የኹለት ሰዓት ተኩል የአውቶብስ ጉዞ ማድረግ ይጠይቃል ገደላቱ በተለያየ አንግል የተለያየ ከፍታ ሲኖራቸው 155 ሜትር አማካይ ከፍታቸው እንደሆነ ይገለፃል። ሃሪ ፖተርን የመሳሰሉ እውነት የማይመስሉ የተፈጥሮ ውብ ሥፍራዎችን የሚያሳዩ ፊልሞች የተቀረፁበትን ስፍራ በ2018 አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ጎብኝቶታል።

በአትላንቲክ ውቅያኖስ ጥግ ውሃው በሩቅ የሚታይባቸው ሦስት ገደላማ ከፍታዎችንና አንድ ጥንታዊ ሕንፃ ያለበት ከቦታውና ከአየርላንድ ጋር የሚሔዱ ልዩ ልዩ የስጦታ ዕቃዎችን የሚገኙባቸው የቱሪስት ሱቆችና ምግብ መጠጥ ያለባቸውን ቦታዎች የያዘ ነው ሥፍራው። በሚገባ ተደልድሎ የተዘጋጀ የእግር መንገድና መቀመጫ ሥፍራዎች፣ ወደ ገደሉና ራቅ ብሎ ወደ ሚታየው ያማረ ሰማያዊ ውቅያኖስ እንዳትጠጉ ጭምር የሚያስጠነንቁ መልዕክቶችና አጥሮችም አሉት። በተረፈ ቦታው ደርሳችሁ “በአንድ ወቅት ሕዝቦች የዓለም መጨረሻ እዚህ ነው ብለው ያስቡ ነበር” የተባለለትን የዓለም ጥግ የመሰለ ውብ ሥፍራ በቃላት መግለጽ እንዲህ በቀላሉ የሚቻል አይደለም።

የጊነስ ቢራ ታሪክ ሥፍራ
የጊነስ ቢራ ጠመቃ ታሪክን የሚያወሳውና በከተማው ከሚጎበኙ ሥፍራዎች አንዱ የሆነው ስቶር ሃውስ እነሱ (Home of Guinness) የሚሉት በርካታ ቱሪስቶች የሚያዩት ሌላ ሥፍራ ነው። ደብሊን ደርሳችሁ ጄምስ ስትሪት የሚገኘው የጊነስ ቢራ ታሪክ ቦታ ሳትደርሱ ምኑን ደብሊንን አየን ትላላችሁም ይባልለታል፤ ዝነኝነቱን ለመግለጽ። ኢትዮጲያውያን ጓደኞቼ ሳይቀሩ ደብሊን እንደምሔድ ሲሰሙ ሳታይው እንዳትመጪ ብለውኛል።

ታዋቂው የጉዞና ተዛማጅ ጉዳዮች ድርጅት Trip Advisor ድረ ገጽ እንደሚለው ጊነስ ስቶር ሃውስ የአየርላንድ ቁጥር አንድ በርካታ ጎብኚዎች የሚጎርፉለት ሥፍራ ነው። ቤቱ የተመሰረተውም ታዋቂ የቢራ ማብላያ ያለበት ሥፍራ ነው። በአስጎብኚ እንዲሁም በቪዲዮዎችና ፎቶግራፎች እንዲሁም ፈጠራ የታከለባቸው ገለፃዎች የተሞላ ሰባት ወለሎች ያሉት ነው የሚጎበኘው ቤት፤ የጊነስ ቤት የሚሉት ሥፍራ። በዓለም ታዋቂ የሆነውን ጥቁር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቀለማትንም የያዘ ቢራ ታሪክ ከተነሳበት ጀምሮ ያለፉትን 250 ዓመታት ታሪኩን በአጭሩ ለማስቃኘት ሲያስብ በየደረጃው ከገብስ አመራረጥ እስከ ውሃና ብቅል እንዲሁም ማብላላት ሒደት እስከ የእንጨት በርሜል እያንዳንዱ ግብዓት የራሱ ክፍል ተሰጥቶት፣ አሠራሩና ሒደቱ የሚተረክበት ነው። ስበት ቡና ቤት Gravity Bar መጨረሻ ላይ ጉብኝታችሁ ሲያበቃ ከፍ ካለ የመስታውት ግድግዳ ብቻ ከሆነው ባር ውስጥ ጊነስ እየጠጣችሁ ደብሊንን ቁልቁል በስፋት እንድታዩ ጭምር እየተጋበዛችሁ ነው። ከዛ በፊት ግን ሞራሉ ላለው 20 ዩሮ የመግቢያ ክፍያ ጋር የተሰጠውን ሦስት ዓይነት ቢራ መርጦ የመጠጣት ዕድል ተጠቅሞ ቁጭ ብሎ የዲጄ ሙዚቃ የሚከሰክስበት ክፍልና የራሱን ቢራ ቀምሞ የመቅመስ ዕድል ያለበትም ክፍል የጉብኝቱ አካል ነው። ከዛም በሬስቶራንቱ በቢራና ከወይን ቅመማ ጭምር የሚዘጋጁ የአይሪሽ ባሕላዊ ምግቦችን መብላት የተጨማሪ ጉብኝት አካል ነበር።

በነገራችን ላይ ከጊነስ መስራች አርተር ጊነስ (1725 – 1803 እ.ኤ.አ.) እና ቤተሰቡ ታሪክ ጋር በጉብኝቱ ወቅት ከሚነገረው ታሪክ መሃል በወቅቱ በሽታ በሰው ልጅ ላይ ክፉኛ ሰለጠነበት ዘመን በተለይ ሕፃናት ተወልደው የማደግ ዕድላቸው ከመትረፍ ጋር እኩልና ከዛም በላይ የነበረ መሆኑ እውነት ነው። የአርተር ጊነስ ባለቤት 21 ልጆች ወልዳ የነበረ ሲሆን ያደጉት 11 ነበሩ። እነሱ በትረካቸው እንደሚሉት ይህቹ ሴት የዕድሜዋን 16 ዓመት እርጉ ጊነስ በአሁኑ ወቅት ከቤተሰብ ንብረትነት ወጥቶ ትልቅ ኩባንያ ሲሆን ባለቤትነቱ በመስራቹ ወራሽ ቤተሰቦችና የስደት (የአየርላንዳውን አበርክቶ) መዘክር/EPIC Emigration Museum በደብሊን ከሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ከተመሰረተ ቅርብ ጊዜ ያስቆጠረው (2014 እ.ኤ.አ.) የኢሚግሬሽን ሙዚየም አንዱ ነው። የስደት ታሪኩ ከጥንት የጀመረ ሲሆን በተለይ ክፉ ረሃብና ድኅነት እንዲሁም በቅኝ ግዛት ውስጥ ያለ ለዜጎች ዕድልና ነፃነት መስጠት ያቆመ ሥርዓትና ፍትሕ እጦት አየርላንዳውያን በሺዎች እየሆኑ በመርከብና በሌላውም የጉዞ መንገድ በዓለም እንደ ጨው ዘር እንዲበተኑ ከተፈረደባቸው የዓለም ሕዝቦች ተርታ እንዲሰለፉ አድርጓቸዋል። በሙዚየሙ መግቢያ ላይ የተቀመጠች አንዲት አነስተኛ ሻንጣ ላይ “ሕይወታችሁንና የኖራችሁለትን ሁሉ በዚህች ትንሽ ሻንጣ መክተት ትችላላችሁ? ያለ ምንም ነገር አገራቸውን ጥለው ተሰደዱ፣ ግን ዓለምን ለወጡ ዛሬ ደግሞ እነሱን የሚዘክር ሙዚየም ቆሟል?” ይላል። ዓለምን ለወጡ እውነተኛ አባባል ነው። በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ አውስትራሊያ ከሳይንስ እስከ ሕክምና ግኝቶችና ሥነ ጽሑፍ በየአገራቱ ገብተው አገራቸው አድርገው ዜጎች የሆኑ አየርላንዳውያን አበርክቶታቸው ብዙ ነው። በሙዚየሙ 15 የተከፋፈሉ ክፍሎችም ይህንን አበርክቶ ይዘክራሉ። ሁሉንም ለመዘርዘር ጊዜና ቦታ ባይበቃን ባራክ ኦባማንና ጆን ኤፍ ኬኔዲን ጨምሮ 22 አሜሪካውያን ፕሬዚዳንቶች (አሜሪካ እስከዛሬ ከነበሯት ፕሬዚዳንቶች ግማሽ ያህሉ) ዘር ሃረጋቸው ከአየርላንድ የሚመዘዝ ነው። በሥነ ጽሑፍ ብትሉ 5 ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ካላት አየርላንድ 4 የሥነ ጽሑፍ ኖቤል አሸናፊዎች መውጣታቸው አይገርምም? ዊሊያም በትለር ዬትስ፣ ሳሙኤል ቤኬት፣ ሲሙስ ሄይኒና ጆርድ በርናንድ ሾው በዓለም በእንግሊዝኛ ሥነ ጽሁፍ የሚታወቁ የተደነቁ አየርላንዳውያን ናቸው።
በሥነ ጽሑፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም የኖቤል ተሸላሚዎች ሲኖሯቸው ለመጥቀስ ያህል፣ ጆን ሂዩም በ1998 በተደረገው የሰላም ስምምነት አስተዋጽዖ ካበረከቱት መሃል ሆኖ የሰላም ሽልማት ተጋርቷል። ሲያን ማክብራይድ የተሰኘው በመንግሥት ሥራ በተለያየ ሥልጣን ያገለገለው አየርላንዳዊ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች መመሥረት ላደረገው አስተዋጽዖ፣ ማይሪድ ማጉዊር ከቤቲ ዊሊያምስ ጋር ለአየርላንድ ነፃ መውጣት ላደረጉት አክቲቪዝም የኖቤል የሰላም ሽልማት ተቀብለዋል።

ይሔ ሙዝየም በጣም ትክረትን ሳቢ በሆነ በቴክኖሎጂ የዕድገት ደረጃቸውን በሚያሳይ መልኩ የተደራጀ ነው። ቪዲዮዎች ፎቶግራፎች፣ የዚያን ጊዜውን እውነታ የሚያሳዩ የግለሰብ ታሪኮች የሚያስመስሉ ፊልሞች ወዘተ ጉብኝቱ ለስደት ታሪኩ የተሟላ ስዕል እንዲሰጥ ተደርጎ በጥሩ ሁኔታ የቀረበበት ነው።

ከአገሬው ጋር ወግ – እንደ ማጠቃለያ
ወደ መመለሻዬና የአየርላንድን ሌሎች ገጽታዎች ከአገሬው አንደበት ወደ ሰማሁበት ገጠመኝ ስመለስ፤ በካፊያ ውስጥ ከንፋስ እየተጋፋሁ ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የሚወስደኝ ታክሲ ፍለጋ ከቤት ብዙ ሳልርቅ ላየሁት ታክሲ ምልክት ሳሳይ መጣሁ ብሎኝ ታጠፈ። ጥግ ይዘው አቁመው በፍጥነት ሻንጣዬን ሊጭኑ ሲወጡ ሳይ አረጋዊ ናቸው። በኋላ 71 ዓመት እንደሆናቸው ሲነግሩኝ ጠንከር ባለው ትራፊክ የልጅ ልጆቻቸውን ፎቶ ጭምር እስኪያሳዩኝ ወግ አድርተን ነበር።

ሲጀምሩ የምሔድበትን አገር (የምገባበትን የኤርፖርቱን ተርሚናል አውቀው መንገዳቸውን ሊያስተካክሉ) በመጠየቅ ነበር። አገሬን ስናገር የረሃብ ጉዳይ ተነሳ፤ አልፈረድኩባቸውም ።
አየርላንድ ራስዋ ሙዚዬም ያቆመችለት ክፉ የረሃብ ታሪክ አላት “The great famine” ይሉታል። ሙዚየም ማቆም ብቻ ሳይሆን ደንበኛ የገበያና የቱሪስት ቦታ ደብሊን እምብርት ላይ መሆኑ ሳያንስ ቀኑን ሙሉ የረሃብ ኢግዚቢሽኑን በሴንት ግሪን ሾፒንግ ሴንተር ኹለተኛ ፎቅ ላይ ይጎብኙ የሚል ትልልቅ ፖስተር በረጅም እንጨት ላይ ለጥፈው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች አስቀምጠዋል።

ስለ ረሃቡ ምንም አንል ስል መልሼ የምታምር አገር ጥሩ እንግዳ ተቀባይ ተግባቢ ሕዝብ አላችሁ ብዬ አድናቆቴን ስገልጽ። ወደ ኋላ በመመልከቻው መስተዋት እያዩ “you speak perfect English” ሲሉኝ ትምህርት ቤት የተማርኩት እንግሊዝ አገር ነው ብዬ መለስኩ። ሁሌ የሚቀርብልኝ ጥያቄ የምሰጠው መልስ ነው (በዛውም ቀላል ሰው እንዳልመስላችሁ ለማለት ነው።

ትራፊክ ዝግ ሲያደርገን (በነገራችሁ ላይ ትራፊክ መብራቱ በየ 50 ሜትር ተተክሎ መሔድ ይናፍቃችኋል። መንገዳቸው ጠባብ መሆኑ መሰለኝ። ግን አይጨናነቅም ያዝ ለቀቅ ቶሎ ቶሎ ነው) እሁድ ሆኖ እንደዛ የመዘጋጋቱ ምክንያት የሴቶች እግር ኳስ ግጥሚያ ስለነበር እንደሆነ ነገሩኝ። ትናንት ቅዳሜም ብዙ ሰው ማሊያ ለብሶ ሲሔድ አይቻለሁ አልኳቸው። አይ የትናንቱ እንኳን የአማተር ግጥሚያ ብጤ ነው። ሴት ብሔራዊ ቡድናችን ግን አንበሶች ናቸው አሉኝ። ደስ አለኝ።

በዚያ ምክንያት በአገሪቱ የሴቶች ደረጃና ማኅበረሰቡ የሚሰጣቸውን ቦታ፡ ሚስታቸው ሁሌም ቆፍጣና መሆናቸውን ሲነግሩኝ “ሁልጊዜ ማድረግ ያለብኝንና የሌለብኝን የምትነግረኝ እሷ ናት። 35 ዓመት በትዳር ቆየን፣ ሳስበው ሁሌም ትክክል በመሆኗ መሠለኝ ለዚህ የበቃነው” እያሉ እያሳሳቁ ሲያወሩኝ።

ከዛ በኋላ የመጣውን ለውጥ ያስረዱኝ ወንድና ሴት የልጅ ልጆችቻቸውን በማርሳል አርት ዩኒፎርም የተነሱትን ፎቶ እያሳዩ ነበር። ሴቷ ጥቁር ቀበቶ መድረስ ትፈልጋለች፤ ወንዱ እንኳን እጅግም ነው አሉ። እየሳቁ ሴቷ ትገጥመኛለች እኔ ያለፍኩበት ስለሆነ ሆቢውን ስለተከተለችልኝ ደስ ብሎኛል አሉ። መጀመሪያ ላይ አሳየኋት በዛው ቀጠለችበት እያሉ።

በወጣትነታቸው ዘመን ግን የሴት ቦታ ጓዳ ነው ልጅና ማጀት የሚል አስተሳሰብ በስፋት እንደነበር አልሸሸጉም። ጭራሽ ልጅ ሆነው ሴቶች ከነርስነትና ከአስተማሪነት ውጪ ባለው ሥራ ከተሰማሩ ሲያገቡ ሥራ ለቀው ቤት እንዲቀመጡ በሕግ ይደረጉ እንደነበር ነገሩኝ።
ሌላው ቀርቶ ለሴቶች ቀን ያወጣው የኹለተኛው ዓለም ጦርነት ወንዶቹን ወደ ጦር ሜዳ ሲወስድ አማራጭ በማጣት ሴቶችን ለፋብሪካ ሥራ ሲዳርግ ጦርነቱ ሲያልቅ ውለታቸው ተረስቶ “ሥራቸውን መልሱ” ተቃውሞ ከተሞችን ማጥለቅለቁን ነገሩኝ።

ዛሬ የለም የሴት መብት ተረጋግጧል አሉ። የመጀመሪያዋን ሴት ፕሬዜዳንት ሜሪ ሮቢንሰንን ከዓመታት በፊት ሲመርጡ ስለነበረው ሁኔታ እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው። ከመመለሳቸው በፊት “እንዴት ያለች ጎበዝ ዓለማቀፍ ጠበቃ መሰለችሽ፤ እሳት!” አሉና የሚገርምሽ አብሯት የተወዳደረው ጅል ነው። እንድታሸንፍ የረዳት ያው ማኅበረሰቡ ብዙ ለውጥ ቢኖርም ለመምረጥ ምናልባት ሊያመነታ ይችል ነበር። ከዛ ምርጫ ቅስቀሳ prime time ላይ በቲቪ የሚተላለፍ ዝነኛ ፕሮግራም ላይ ቀርቦልሽ ብመረጥ “እንዲህ አደርጋለሁ እንዲህ እሠራለሁ” ሲል ቆይቶ ስለተቀናቃኝህ ሜሪ ሮቢንሰን ምን ታስባለህ ሲባል ‘የምመክራት ወደ ቤቷ ተመልሳ ቤት ሆና ልጆችዋን እንድታሳድግ ነው’ አላለም! ሴቶቹ ከጫፍ እስከጫፍ ሆ ብለው ወጥተው መረጡአታ! ለነገሩ አላሳፈረችንም ምርጥ ሥራ ነው የሠራችው” አሉ በሳቅ ታጅበው። እሳቸው ይህንን ሲሉ ምን ትዝ አለኝ የሴቶች መብትና ጥያቄ ይመለከተኛል እንደሚል ሰው የታዘብኩት ተቃርኖ ነው። አየርላንድ በሴቶች መብት እሳቸው እንዳሉት ብዙ ርቀት ተጉዛ የተሻለ ቦታ ላይ ብትገኝም ዛሬም ጽንስ ማስወረድ ሕገ ወጥ ነው፣ በሌላ አግባብ አገሪቱ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን በመፍቀድ ከአውሮፓ ግንባር ቀደም ናት።

ከዚያ ስለአየርላንድ ሥጋና ወተት እንዲሁም የእህል ምርት ሲነግሩኝ እንግሊዝን ቀጥ አድርገው መያዛቸውን በኤክስፖርት የአገራቸውን ኢኮኖሚ መልሶ እንዲያንሰራራ ማድረጋቸውን ነገሩኝ።

ጥሩ ሥጋ እንዳላቸው መስማቴንና ማየቴን ነግሬ የአውሮፓ የቴክኖሎጂ ማዕከል Europe’s Silicon Valley ለመሆን ስለጀመሩት ጉዞ ጠየቅኩ። ልክ ነው አሉ። ልጃቸው በአይቲ መሠማራቷንም ገለፁልኝ። ፌስቡክን ጨምሮ አማዞንና ሌሎች ኩባንያዎች ብዙ ሺሕ ሠራተኞቻቸውን የያዙ ማዕከላትን መሽርቷል።

የሚከብዱ ሻንጣዎቼን ሲጭኑ በትህትና ቆይ ቁጭ በይ ጋሪ ላምጣልሽ ሲሉ ከዛም እሳቸው ባልገቡበት ይቅርታ እዚህ ለመድረስ ብዙ ሰዓት ፈጀን ሲሉኝ እኔም አስሬ ሳመሰግናቸው ቆይቼ የ71 ዓመቱን አዛውንት ተሰናብቼ በማድሪድ ስፔን አድርጎ አገሬ የሚመልሰኝን የኔውን አኢቲ ፍላይት ፍለጋ ወደ ተርሚናሉ ዘለቅኩ።

አዲስና ተጨማሪ ነገር ያገኘሁበትን የደብሊን/አየርላንድ ጉብኝት ማስታወሻ ሳበቃ መጓዝ ምን ያህል አዕምሮ የሚከፍት፣ አስተሳሰብን የሚያሻሽል ስለመሆኑ ለማስረገጥ የማርክ ትዌንን አባባል ጠቅሼ ነው።
“መጓዝ ጅምላ ፍረጃን፣ ጠባብ አስተሳሰብንና ጥላቻን ይገድላል፤ በዚህ ምክንያት ለብዙ ሰዎች ያስፈልጋቸዋል።”

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 48 መስከረም 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com