የኮቪድ 19 ክትባት አሁናዊ ሁኔታ

0
929

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መኖሩ ከተረጋገጠ ድፍን አንድ ዓመት ከኹለት ሳምንታት አሳልፏል። ወረርሽኙን ለመከላከላልም ያስችላል የተባለ መፍትሔ ሲፈለግ ቆይቶ በአሁን ሰዓት መከለከል ያስችላል የተባለለት ክትባት መሰጠትም ተጀምሯል።

ኢትዮጵያም የኮቪድ 19 ቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግለውንና ‹አስትራዜኔካ› የተባለውን ክትባት ተቀብላለች። ኹለት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብልቃጦችን ነው ‹ኮቫክስ› ከተባለው ዓለም ዐቀፍ የክትባት አቅርቦት ጥምረት ያገኘችው።
ይህን ተከትሎ ክትባቱ በኢትዮጵያ መሰጠት የተጀመረው ወረርሽኙ በኢትዮጵያ ተገኘ በተባለ ልክ በዓመቱ መጋቢት 04/2013 ጀምሮ ነው። የጤና ባለሞያዎችና ተደራራቢ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች ቅድሚያ በመስጠት ክትባቱ ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተሰራጭቷል። ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የተለያዩ አመራሮችም ‹እናንተም ተከተቡ› ብለው አረአያነት ለማሳየት ክትባቱን ሲወስዱ ተመልክተናል።

ክትባቱ እና ያለው ውዝግብ ?
የኮቪድ 19 ክትባት ከተጀመረ በኋላ የተለያዩ መረጃዎች በመሠራጨት ላይ ይገኛሉ። አዲስ ማለዳም በዕድሜ የተለያዩ ሰዎችን በክትባቱ ዙሪያ በመጠየቅ የተወሰነ ዳሰሳ ለማድረግ ሞክራለች።
አዲስ ማለዳ ዕድሜያቸው 75 ገደማ የሚሆኑ አንድ እናት ጋር ቀረብ ብላ ‹ክትባቱን ይከተባሉ ወይ?› ብላ ጠይቃለች። እርሳቸውም ‹‹ፈጣሪ አለ። እኔ አልከተብም። የግድ እንኳን ቢሆን ልጆቼን አማክሬ ነው የምከተበው›› በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።

ሌላው ዕድሜያቸው 45 የሆኑ አንድ ግለሰብ በበኩላቸው ክትባቱን እንደማይከተብ ነው የገለጹት። ‹‹ምክንያትዎ ምንድን ነው?› ለሚለው ጥያቄም ‹‹በቃ አልፈልግም!›› የሚል ምላሽ በደፈናው ሰጥተዋል።
ሌላኛዋ የ29 ዓመት ወጣት ደግሞ ክትባቱ መሰጠት ከተጀመረ እንደምትወስድ ነው የተናገረችው። የ31 ዓመቱ ወጣት ‹‹ክትባቱ ውጤታማ ይሁን አይሁን ሳላውቅ በቶሎ አልከተብም።ይህንን ለማየት ደግሞ ጊዜ ያስፈልጋል።›› ብሏል።
ክትባቱን የደም መርጋትና ሌሎች የጤና ችግሮችን ያስከትላል በማለት ጀርመንን ጨምሮ 13 የአዉሮፓ ኅብረት አባል አገራት ክትባቱን በጊዜያዊነት ከመስጠት አግደው እንደነበር የተለያዩ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኀን ሲዘግቡ ተሰምቷል። ነገር ግን የአውሮፓ መድኃኒቶች ተቋም ይህን የአገራቱን አቋም በመቃረን፣ ‹አስትራዜኒካ› የተባለዉ ክትባት ጥቅም ላይ ሊዉል የሚችል አስተማማኝነቱም የተረጋገጠ ነው ብሎለታል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የክትባቱን ተጓዳኝ ምልክት እያጠናች መከተቧን እንደምትቀጥልና የተባለው የደም መርጋት እንዳላጋጠመ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የኮቪድ 19 ሕክምና ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ቀናኢ በበኩላቸው፤ ክትባቱ ለሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ከመጋቢት 14/2013 ጀምሮ እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ይህም አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኹለት ጊዜ (በዙር) እንደሚሰጥ ይናገራሉ።

ክትባቱን መውሰድ የሰውነት ኮቪድን የመከላከል አቅም እንዲያመነጭ ከማድረጉ በተጓዳኝ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጽኑ ሕመም ለመከላከል ይረዳል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች የደም መርጋት ገጥሟቸዋል ተብሎ በዓለማቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተነገረው ሳይንሳዊ ሂደትን ያልተከተለ ነው ሲሉ የሚናገሩት ዶክተር ደሳለኝ፤ ችግሩ የገጠማቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን እንዲሁም ከዚህ ቀደምም የደም መርጋት ያጋጠማቸው ሰዎች እንደሆኑ በድጋሚ በተደረገው ጥናት መታወቁን ጠቅሰው፣ ይህንን ተከትሎ አገራቱ ያቋረጡትን ክትባት በድጋሚ መስጠት መጀመራቸውንም ያነሳሉ።

የጎንዮሽ ጉዳቱስ?
የክትባቱን አስተማማኝነት በተደጋጋሚ የሚያነሱት ዶክተር ደሳለኝ፤ ነገር ግን እንደ ማንኛውም ክትባት የጎንዮሽ ጉዳት ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ‹‹ከ20 እስከ 30 በመቶ ባሉ ሰዎች ላይ ክትባቱን ሲወስዱ ትኩሳት ያጋጥማቸዋል። ይህ ደግሞ ማንኛውም ክትባት ሲወሰድ የሚያጋጥም ነው።›› በማለት ጊዜያዊ ትኩሳትና ድካም ሊያጋጥም እንደሚችል ይጠቁማሉ።

የጎንዮሽ ጉዳቱን በሚመለከት በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ያልተጨበጠ መረጃ ሲነገር ይሰማ እንጂ፣ ክትባቱ የሚያደርሰው ከባድ የጎንዩሽ ጉዳት እንደሌለ ነው ባለሙያው የሚገለጹት።

ክትባቱን መውሰደ የሚችሉት እነማን ናቸው?
የጤና ባለሙያች፣ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች፣ ለኮቪድ ተጋላጭ የሆኑ፣ ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ክትባቱን በቅድሚያ ያገኛሉ።
በበኩላቸው ክትባቱን እንደወሰዱ የገለጹት ባለሙያው፤ ክትባቱን ከመስጠት በፊት ግን መደረግ ያለበት ጥንቃቄ እንዳለ አሳስበዋል። ይህም ሰውነታቸው አለርጂ ያለባቸው፣ ሰውነታቸው እየደማ ያለ ሰዎች እንዲሁም ነፍሰጡር ሴቶች ክትባቱ መውሰድ እንደሌለባቸው መክረዋል። የሚያጠቡ ሴቶች ግን መከተብ እንደሚችሉ ዶክተር ደሳለኝ ያስረዳሉ።

አክለውም አሁንም ድረስ በኮቪድ እየተጠቁ ያሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ፣ ክትባቱ የሚሰጠውም ለሁሉም ኅብረተሰብ ባለመሆኑ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። መረጃ ከባለሙያዎች መውሰድ ተገቢ እንደሆነም ዶክተር ደሳለኝ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ በትግራይ ክልል መቀለ ከተማ ተገኝተው ክትባቱን ባስጀመሩ ዕለት፣ በዓለማቀፍ ደረጃ የክትባት ውስንነት መኖሩን በመግለፅ፤ ኅብረተሰቡ ክትባት ተጀመሯል ብሎ መዘናጋት እንደሌለበት አሳስበዋል።


ስለ ኮቪድ ክትባት የማናውቃቸው ጉዳዮች

  • ክትባቱን የወሰደ ሰው ውደ ሌላ ሰው ያስተላልፋል ወይስ
  • ክትባቱ መጀመሩ የቫይረሱን ስርጭት በምን ያክል መጠን ሥርጭቱን ማስቆም ይችላል

ስለኮቪድ ክትባት የምናውቃቸው እውነታዎች

  • አስትራዜኒካ የተባለው ክትባት ውጤታማነት 63 በመቶ መሆኑ
  • ክትባቱ አንደማንኛውም ክትባት የጎንሽ ጉዳት ያለው መሆኑ እና የጡንቻ መገጣጠሚያ ህመም፣ክትባቱን የተወጋንበት ቦታ ላይ የመለብለብ ስሜት ያለው መሆኑ

የኮቪድ ክትባት ሁለት ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ እና አንዱን የክትባት ዓይነት ከጀመሩ ሌላ መውሰድ የማይቻል መሆኑስለ ኮቪድ ክትባት የማናውቃቸው ጉዳዮች

  • ክትባቱን የወሰደ ሰው ውደ ሌላ ሰው ያስተላልፋል ወይስ
  • ክትባቱ መጀመሩ የቫይረሱን ስርጭት በምን ያክል መጠን ሥርጭቱን ማስቆም ይችላል

ስለኮቪድ ክትባት የምናውቃቸው እውነታዎች

  • አስትራዜኒካ የተባለው ክትባት ውጤታማነት 63 በመቶ መሆኑ
  • ክትባቱ አንደማንኛውም ክትባት የጎንሽ ጉዳት ያለው መሆኑ እና የጡንቻ መገጣጠሚያ ህመም፣ ክትባቱን የተወጋንበት ቦታ ላይ የመለብለብ ስሜት ያለው መሆኑ

የኮቪድ ክትባት ሁለት ጊዜ የሚሰጥ መሆኑ እና አንዱን የክትባት ዓይነት ከጀመሩ ሌላ መውሰድ የማይቻል መሆኑ


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here