ከባንኮች ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ የ<ፖስ> ማሽን የክፍያ አገልግሎት ሊጀመር ነው

የሰንፔይ ሶሉሽን አክሲዮን ማኅበር በአገራችን በእድገት ላይ የሚገኘውን የፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት አስተዋፅዖ ለማድረግ ብሎም ተመራጭ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች ማድረስ አላማው ያደረገ የዲጂታል የክፍያ ስርዓት በ100 ሚሊዮን ብር ካፒታል መነሻ አክሲዮን ማኅበሩን በመመስረት ላይ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባወጣው አዲሱ መመሪያ መሰረት ፍቃድ ጠይቆ በቅርብ ወራት ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ የተገለጸው የሰንፔይ ፖስ ማሽን ወይንም የክፍያ ነቁጥ የዲጅታል የክፍያ ስርዓት በአገራችን ባንኮች ከሚሰጡት የክፍያ አገልግሎት ውጭ በግል ተቋም ደረጃ የሚደረግ የመጀመሪያው እንደሆነ እና በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ስድስት ሺሕ ያህል የፖስ ማሽን ወደ አገር ውስጥ እንደሚያስገቡ ገልጸዋል።

ይህ የክፍያ አገልግሎት ሲተገበር ከባንኮች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ተገልጿል። አገልግሎቱን የሚያገኙ ግለሰቦች ባለሀብቶችም ሆነ ተቋማት የባንክ ተቀማጭ ሂሳብ ያላቸው መሆናቸውም ተገልጿል። በአገራችን አሁን ቁጥራቸው ዘጠኝ ሺህ 800 ያህል የፖስ ማሽኖች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ ያገኘቸው መረጃ ያመላክታል።

የሰንፔይ ሶሉሽን አክሲዮን ማኅበር እስከአሁን ድረስ የተሸጠ አክሲዮን 13 ሚሊዮን ብር ያክል ሲሆን ቃል የተገባ ደግሞ 87 ሚሊየን ብር እንደሆነ ተገልጿል። የአክሲዮን ድርሻ ለመግዛት የአንዱ አክሲዮን ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ አንድ ሺሕ ብር እንደሆነ ተገልጿል።

ሰፊ እና መሰረታዊ የፋይናንስ አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ያልተቆጠበ ተሳትፎ እና ኢንቨስትመንት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ እና በዚህ ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ የተነሳው ሰንፔይ ሶሉሽን አክሲዮን ማኅበር በኢትዮጵያውያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ዳያስፖራዎች በመቋቋም ላይ የሚገኝ አክሲዮን ድርጅት ሲሆን በአገራችን በኮንስትራክሽን ዘርፍ ዝነኛ የሆነው የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ እህት ኩባንያዎች መስራች እንዲሁም ባለቤት እና አስተዳዳሪዎችንም በከፊል ባለአክሲዮንነትና መስራችነት ያቀፈ እንደሆነ ተገልጿል።

የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ሐሙስ መጋቢት 16 በማሪዮት ኢንተርናሽናል ሆቴል በተደረገበት ወቅት የሰንፔይ ሶሉሽንስ ተወካይዋ ዕፁብ አለማየሁ እንዳሉት “እኛ እያደገ የመጣውን የክፍያ ቴክኖሎጂ ዘርፍ በመቀላቀል በጣም ደስተኞች ነን። ባለፉት ኹለትና ሦስት ዓመታት አገራችን በበርካታ ዘርፎች አገራዊ ሪፎርሞች በማድረግ ላይ መገኘቷን ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ከእነዚህ አገራዊ የሪፎርም አጀንዳዎች መካከል የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነው የፋይናንስ ዘርፍ አንዱ ነው። ከዚሁ አንፃር ይህንን ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜ እንደሆነ እናምናለን” በማለት ተናግረዋል።

አገሪቱ በአገልግሎት አቅርቦቶች ዲጂታላይዜሽን እና በአገሪቱ የፊንቴክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ዕድገትን በማፋጠን አንድ የአፍሪካ የእድገት መብራት እንድትሆን የበኩላችንን እንሰራለን ብለዋል።
ተወካይዋ አክለውም የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማግኘት ብዙ ተግዳሮቶችን ሊፈቱ የሚችሉበትን ኢንዱስትሪ በመቀላቀላችንም ደስተኞች ነን። የግሉ ዘርፍ እንደ ሰንፔይ የፋይናንስ ቴክኖሎጂዎች ያሉ ድርጅቶችን በመጠቀም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የፊንቴክ ተሞክሮዎችን ወደ አገር ውስጥ የማምጣት ሂደትን በማፋጠን በፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛውን ሚና መጫወት ይችላል ብለዋል።

ሰንፔይ ሶሉሽንስ በአገራችን በግንባታ፣ በሪል እስቴት፣ በሆቴል ልማት ተሰማርተው የሚገኙት የሰንሻይን ኢንቬስትመንት ግሩፕን ጨምሮ ሌሎች ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአክሲዮን ባለቤትነት የተሳተፉበት አክሲዮን ኩባንያ ሲሆን በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ አገልግሎቶችን በተመጣጣኝ ዋጋዎች በማቅረብ በአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ድርጅት የመሆን ራዕይ እንዳለው በአክሲዮን ምስረታ ላይ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here