በአዲስ አበባ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በኮንትራት ለተቀጠሩ መምህራን የቤት ድጎማ አበል ሊከፈል ነው

0
1294

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ዉስጥ የኮንትራት ቅጥር መምህራን እና ርእሰ መምህራን የቤት ድጎማ አበል ሊከፈላቸዉ እንደሆነ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ዉሳኔውን ያስተላለፈዉ የከተማ አስተዳደሩ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሀብት ቢሮ ሲሆን በውሳኔውም መሰረት በኮንትራት ለተቀጠሩ መምህራን ከየካቲት 1/2013 ጀምሮ የቤት ድጎማ አበሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተወስኗል።

የኮቪድ 19 ወረርሽን ተከትሎ በትምህርት ቢሮ የኮንትራት ቅጥር የተደረገላቸዉን መምህራን የቤት ድጎማ አበል ተጠቃሚ ባለመሆናቸዉ ቅሬታ ፈጥሮባቸው እንደነበር እና ቅሬታቸዉን ለሚመለከታቸዉ አካላት ጥያቄዉን ቀርቦ ሊፀድቅ ችሏል ሲሉ የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር የስርአተ ፆታ ተጠሪ የሆኑት ማህሌት ብርሀኑ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ተናግረዋል።

ውሳኔው ግማሽ ዓመት ላይ እንደ መፅደቁ የበጀት ችግር አላጋጠማችሁም ወይ ብለን ለጠየቅናቸዉ ጥያቄ የከተማው አስተዳደር የበጀት እጥረት እንዳያጋጥም እና መምህራኑም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲባል የታጠፈ ፕሮጀክት መኖሩን ተናግረዋል። በዚህም ማኅበራቸው እና መምህራኑ በጣም ደስተኛ መሆናቸዉን ማህሌት ገልጸዋል። እንደ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መረጃ በኮንትራት የተቀጠሩ ወደ አንድ ሺሕ አራት መቶ የሚጠጉ እና በቋሚነት ደግሞ 25 ሺሕ በላይ መምህራንና ርእሰ መምህራን እንዳሉ ገልጸዋል።

በውሳኔው መሰረት ከየካቲት 1/2013 ጀምሮ ለሁሉም ኮንትራት ቅጥር መምህራን በካቢኔ የተፈቀደዉን ብር ሦስት ሺሕ ብር የቤት ድጎማ አበል እንዲክፈላቸዉ መወሰኑን አዲስ ማለዳ ካገኘችው ከከተማ አስተዳደሩ የሰው ሀብት እና ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ተፈርሞ በወጣ ደብዳቤ ለማወቅ ችላለች።

የቤት አበል ድጎማ አበል የተሰጣቸው የኮንትራት ቅጥር መምህራን ግን የሰርቪስ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ይህም ኮንትራታቸዉን ሲጨርሱ መታወቂያ መሰብሰብና መቆጣጠር ከባድ ስለሚሆን እንደሆነ ተመላክቷል።
አዲስ ማለዳ ከመምህራን ማኅበሩ ባገኘችው መረጃ መሰረት የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት ኮንትራት ቅጥር መምህራን እንዳልነበሩ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ርእሰ መምህራንን በድጎማዉ ላይ ያላቸዉን አስተያየት ጠይቀናቸዉ ድጎማዉ በኮንትራት ተቀጣሪም ሆነ በቋሚ መምህራን ላይ የሥራ መነቃቃትን ከመፈጠሩም በላይ በተወሰነ ሁኔታም ቢሆን ያለባቸዉን የቤት ኪራይ ሊደጉም እንደሚችል ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

የኮሮና ቨይረስ ወረርሽኝ መፍትሄ ቢያገኝ እና የፈረቃ ትምህርት ቢቀር እነዚህ የኮንትራት መምህራን እንደየ ሁኔታው ሊቀጥሉ እና ሊያቆሙ እንደሚችሉ የአዲስአበባ መምህራን ማኅበር ለአዲስ ማለዳ ጠቁሟል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መደበኛ መምህራን ከዚህ ቀደም የሚከፈላቸው የቤት አበል በወር 850 ብር መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ ለመደበኛ መምህራን 850 ብር የነበረውን የቤት ኪራይ አበል ኹለት ሺሕ 200 በመጨመር በወር ሦስት ሺሕ ብር እንድከፈላቸው ማድረጉ ይታወቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 127 ሚያዚያ 2 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here