ሽልማቱ እና የተነሳው ቅሬታ

0
989

እለተ ሐሙስ፤ መጋቢት 30 ቀን 2013 ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከ‹አንጋፋ› የሕይወት ዘመን ሽልማት ቦርድ ጋር በመተባበር ያዘጋጁትና በጥበብ ዘርፍ አንጋፎችን ያሰባሰበ አንድ መድረክ በእንጦጦ ፓርክ ተካሂዶ ነበር። ይህም ‹‹ኢትዮጵያን ስላገለገላችሁ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች›› በሚል ርዕስ ለአንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎች ሽልማት የቀረበበት ነው።

በመንግሥት ደረጃ የሚደረግ እንዲህ ያለ የምስጋና እና የእውቅና መሰናዶ ለጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎች መነቃቃትን ይፈጥራል። ከዛም በላይ ለተተኪ ወጣቶች ተነሳሽነትን እንደሚያሳድር ይታመናል።
በ2012 ሊካሄድ ታስቦለት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 2013 በተራዘመው በዚህ ሽልማት ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሽልማቱን ዓላማ በሚመለከት ንግግር አድርገዋል። በዚህም ተከታዩን አሉ፤
‹‹ኢትዮጵያ ስትመሠረት ምሰሶ ያቀረቡት እነማን ናቸዉ? የሚል ጥያቄ በአእምሮዬ ዉስጥ እንዲነሳ የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። ያንንም ጥያቄ ለመመለስ ባደረግኩት ጥረት እዚህ የተሰበሰባችሁና ያልመጣችሁ በጥበቡ በሁሉም መስክ የምትሠሩ፤ የምታነቡ፤ ሰዎች፤ በእያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ ኢትዮጵያን የሳላችሁና የፈጠራችሁ ሰዎች፤ የኢትዮጵያ ምሰሶ እናንተ ናችሁ የሚል እምነት በውስጤ ተፈጠረ። በዚህ ምክንያት ነው የዛሬው ፕሮግራም ያከናወንነው፣ ምንም እንኳን ለአንድ ዓመት የዘገየ ቢሆንም።››
የጥበብ ዘርፍ ሽልማት በኢትዮጵያ

ዛሬ ላይ በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በመጽሐፍ ወዘተ በየዘርፉ የተለያዩ ሽልማቶች ይዘጋጃሉ። የበጎ ሰው ሽልማት፣ ጉማ ሽልማት፣ ለዛ ሽልማት፣ አዲስ ሚዩዚክ ሽልማት፣ ሆሄ ሽልማት እና መሰል ተጠቃሽ ናቸው። ሆኖም ግን በመንግሥት ደረጃ የሚዘጋጁ ሽልማቶች ከቀሩና ከተዘነጉ ቆይተዋል።

በቀደመው ጊዜ ግን በአገር ደረጃ በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ከፍተኛ ሽልማቶችና የእውቅና መሰናዶዎች ይካሄዱ ነበር። በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የአስተዳደር ዘመን ወቅት የሽልማት ድርጅት ተቋቁሞ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያስረዳል። ይህም በአፍሪካ ደረጃ ሲሸልም የነበረ ነው። እንደውም ከመሸለም አልፎ ተሸላሚዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማቅናት ሙያቸውን እንዲያሳድጉ የሚስያስችል የትምህርት እድልም እንዲያገኙም የሚያደርግ ነበር።

ቅብብል እንደሌለውና አንዱ ሌላውን ጥሎ እንደሚራመድበት የፖለቲካ ሜዳ፣ ቢዘልቁ ለኢትዮጵያ ይጠቅሙ የነበሩ ብዙ ክዋኔዎች በየመንገዱ ቀርተዋል። ታድያ እንደዛው ሁሉ ደርግ በኃይለሥላሴ የተጀመረውን ሽልማት ሳያስቀጥለው ቀረ።
በአንጻሩ በደርግ ዘመነ መንግሥት ለኪነጥበብ እድገት ጥሩ የሚባል አስተዋጽኦ ተደርጓል፤ የሳንሱር መቀስ በአያሌው የበረታበት ጊዜ መሆኑን እንዳለ ሆኖ። የሕዝብ ለሕዝብ ትዕይንትም በጊዜው ከነበሩ ጥበብን የተመለከቱ በጎ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል። በመንግሥት ደረጃ የተደረጉ የሽልማት መሰናዶዎች ግን አሉ ተብሎ ሲጠቀስ አይስተዋልም።

ቀጥሎ በመጣው የኢሕአዴግ የአስተዳደር ዘመን በመንግሥት ደረጃ የተካሄደ ሽልማት ነበር። ይህም ለኹለት ተከታታይ ጊዜ የተከናወነ ነው። ከዛ በኋላ በዚህ ንዑስ ርዕስ መግቢያ ላይ እንዳነሳነው፣ በተለያዩ ግለሰቦች ይልቁንም ፊልም፣ ሙዚቃ እንዲሁም መጻሕፍትን በተመለከተ አንጋፎችን እናክብር፣ የሠሩትን እናመስግን ባሉ ሰዎች፤ እንዲሁም በጎዎችን በመሸለም በጎ እናፍራ ባሉ ፈቃደኞች ምክንያት የተለያዩ የሽልማት ዝግጅቶች በየዓመቱ ሲካሄዱ ይስተዋላል።

ሽልማቱና መስፈርቶቹ
ሽልማቱን በሚመለከት የተንቀሳቀሰው ‹አንጋፋ› የሕይወት ዘመን ሽልማት ቦርድ፣ ለዚህ ሽልማት መስፈርት ብሎ ያስቀመጣቸው ነጥቦች አሉ። እነዚህንም በሽልማቱ ሂደት ውስጥ በሙያዊ አስተዋጽኦ ሱታፌ የነበረው ሰርጸ ፍሬስብሐት በፌስቡክ ገፁ ላይ መስፈርቶቹን እንደሚከተለው በዝርዝር አጋርቷል፤ መስፈርቶቹ ስምንት ናቸው ይላል። እነዚህም በኢትዮጵያ ሥነ ጥበባዊ ልምምድ ውስጥ አዲስ ፈለግ ያስተዋወቁ፤ ሦስት አራተኛ የሕይወት ዘመን እድሜያቸውን በሙያው ውስጥ ያሳለፉ፤ ለሥነ ጥበብ እንቅስቃሴ በማይመች ኹኔታ ውስጥ ሆነውና ፈተናውን ተጋፍጠው ጥበባዊ አስተዋፅኦ ያበረከቱ፤ (እንደየ አግባቡ) በባለሞያዎችና በሕዝብ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ፤ ለአዲስ ትውልድ እውቀትና ልምዳቸውን ያካፈሉ ወይም ውጣ ውረዱን ያቀለሉ ይገኙበታል።
እንዲሁም ደግሞ ለማኅበረሰብ ሕይወት መሻሻል፣ ለማኅበራዊ ሕይወት መዳበር፣ ለአገር ሉዓላዊነትና ተዛማጅ ለሆኑ ጉዳዮች ጉልህ አስተዋጽዖ ያበረከቱ፣ እድሜያቸው ስድሳና ከዛ በላይ የሆነ በመጨረሻ በሕይወት ያሉ የሚሉ ናቸው።

የቅሬታው ከምን ተነሳ?
አንጋፎችና በኪነጥበብ ዘርፍ የአገር ባለውለታ የተባሉ ሰዎች መሸለማቸውና ክብርን ማግኘታቸው ማንንም ቅር የሚያሰኝ እንዳልሆነ እሙን ነው። ነገር ግን ከቅሬታዎች የጸዳ አልነበረም፣ እንከን የለሽም ሆኖ አልተገኘም።
ሽልማቱን ተከትሎ በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ተነስቶ ከታየቅ ቅሬታ መካከል ያልተካተቱ ባለሞያዎችና ጥበብ ዘርፎች ነገር ይገኝበታል። ይህን በሚመለከት አዲስ ማለዳ ሐሳቡን ለመካፈል ከደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርጋለች።
ቴዎድሮስ ለአዲስ ማለዳ ሲናገር በቅድሚያ በጥበቡ ዘርፍ ያሉ ሰዎች መሸለማቸው ተገቢና፣ ሊመሰገን የሚገባ ተግባር ነው ብሏል። እንደአገር ባለውለታን ማመስገን አለማክበር እንደ አገር ሲያስወቅስ የነበረው ጉዳይ ነው አለ።

ነገር ግን በጥቂት ሰዎች ውስጥ መውደቁ፣ በቂ ዝግጅት አለመደረጉ ትልቅ ድክመት ነው ብሏል። በዚህኛው ሽልማትም ያልተካተቱ ዘርፎችና የተረሱ አንጋፋ ባለሞያዎች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ እንደውም ሽልማቱ አንድ ዓመት መራዘሙ (ከ2012 ወደ 2013) ለአዘጋጆቹ በቂ ዝግጅት ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ ነበር ብሏል።

‹‹ነገር ግን አስተባባሪዎቹ በደንብ በጥናት የታገዘና ከየሙያ ማኅበራቱ ጋር በመነጋገር አልሠሩም። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላልተካተቱት ይቅርታ ቢጠይቁም፤ ይህንንም አዘጋጆቹ በቅንጅት ቢሠሩ ኖሮ፣ የሽልማቱን ዋጋ ከፍ ከማድረግ አልፎ መሸለምና መታወስ የሚገባቸውን አንጋፋ የጥበብ ሰዎች ባልተዘነጉ ነበር።›› ሲልም በሐሳቡ ጨምሯል።

በሽልማቱ ካልተካተቱ የጥበብ ዘርፍ ባለሙያዎች መካከል ብሎ ቴዎድሮስ ከጠቀሳቸው ውስጥ … ይገኙበታል ብሏል። በቀረውም ምንም እንኳ የቀረበውን መስፈርት በሙሉ ባያሟሉ እንኳ በየዘርፉ ትልቅ ሥራ የሠሩ ባለሞያዎች ቢያንስ በክዋኔው በእንግድነት እንዲታደሙ መጋበዝ ነበረባቸው ሲልም በበኩሉ ስላተካተቱ አንጋፎች የተሰማውን ቅሬታ አካፍሏል።

ነገሩ ይህ ብቻ አይደለም። ከዚህ በተጓዳኝ ሽልማቱ በመንግሥት የተሰጠ ‹የመጀመሪያው› ተብሎ መጠቀሱን ብዙዎችን ቅር አሰኝቶና አነጋጋሪም ሆኖ ነበር። ይልቁንም በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን ዜናዎች ላይ የጥበብ ዘርፍ ባለሞያዎች ‹ለመጀመሪያ ጊዜ› በመንግሥት ተሸለሙ ተብሎ መቅረቡ እዚህ ጋር ይገናኛል።

በዚህ ዙሪያ ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው፤ ይህ የሚዲያዎቹ ልወደድ ባይነት መገለጫ ነው። መንግሥትን ላለማስቀየም ብለው ሕዝብን ግን አስከፍተዋልም ብሏል።

እንደማጠቃለያ
በዚህ የሽልማት የተዘነጉና ያልተካተቱ እንዳሉ ሁሉ፣ ምስጋና እንዲሁም እውቅና በትክክል የሚገባቸውም ተካትተዋል። በማኅበራዊ ገጽ በተሰጡ አስተያየቶችና በነበሩ ምልልሶች ውስጥ እንዲህ ያሉ መሰናዶዎች ጊዜና ጥንቃቄን የሚፈልጉ መሆናቸውን የሚያመላክቱ ናቸው። በተጓዳኝ ግን ፍጹም የሆነ ሥራ ሊሠራ አይቻልምና ምን ጥንቃቄ ቢደረግ አንዳች እንከን እንደማይጠፋ እሙን ነው።

ቴዎድሮስ ተክለአረጋይ በበኩሉ እንደዚህ ያሉ አገራዊ ዝግጅቶች ሲታሰቡ፣ ተመሳሳይ ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ወይም ስህተቶችን ለመቀነስ እንዲቻል ቅድመ ዝግጅት ላይ በደንብ መሠራት አለበት ብሏል። ይልቁንም ከሙያ ማኅበራት፤ ከመንግሥትና የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ መገናኛ ብዙኀን አልፎም የሚመለከታቸውን ሁሉ በማካተት በተለያየ አንጻር መጣመር ያሻል።

እነዚህንም ሁሉ የሚያሳትፍና በአባልነት ያካተተ በመንግሥት የሚዘጋጅ አገራዊና ሁሉን ዐቀፍ፣ ሰፊና የራሱ በጀት ያለው ሽልማት ድርጅት ወይም ማኅበር መመሥረት እንደሚያስፈልግም ተናግሯል። ይህንን እውን ለማድረግ የገንዘብ ችግር የሚኖር ከሆነም፣ አባላቱ መዋጮና ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተጣምሮ ሽልማቱ እንዲቀጥል በማገዝ የገንዘብ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ባይ ነው።

በሽልማት ዝግጅቱ ሂደት ተሳትፎ የነበረው የሙዚቃ ባለሞያው ሰርጸ ፍሬስብሐት በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዲህ የሚል መልዕክት አስተላፏል፤ ‹‹ለወደፊቱ ልክ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን እንደነበረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሽልማት ድርጅት ተቋማዊ ቅርጽ ያለው፣ በሳይንሱ፣ በምርምሩ፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ፈጠራው፣ በሥነጥበባዊ ሥራዎች ወዘተ እውቂያ እየሰጠ የሚሸልም ብሔራዊ ተቋም በመንግሥት ደረጃ እንዲቋቋም ይደረጋል የሚል ተስፋ አለኝ።››


ቅጽ 3 ቁጥር 128 ሚያዚያ 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here