ኮቪድ 19 በዓለማችን ላይ ከተከሰተ ጀምሮ የሁሉም የዓለማችን አገራት ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል። በኢትዮጵያም ኮቪድ መከሰቱ ከተገለጸበት እለት አንስቶ አንድ ኹለት እያለ አሁን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር አራት ሺሕ የሚጠጋ ሆኗል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኮቪድን ለመከላከል ባወጣው መመሪያ፣ ማለትም 30/2013ን መሠረት በማድረግ የአዲስ አበባ ትራንፖርት ቢሮ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን መወሰን የሚያስችል አዲስ መመሪያ ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ይፋ አድርጓል።
ከሚያዝያ 26 ቀን 2013 ጀምሮ ተፈፃሚ ይሆናል የተባለውና ከትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥና አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ኮሮናን ለመከላከል መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በተመለከተ በተሻሻለው መመሪያ ዙሪያ ባሳለፍነው ሳምንት ቢሮው መግለጫ ሰጥቷል።
መመሪያው በመዲናዋ በሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እና ሌሎች የሕዝብ ማመላለሻና መንቀሳቀሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተፈፃሚ እንደሚሆን የቢሮው ኃላፊ ኢንጂነር ስጦታው አካለ አስታውቀዋል።
በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ማንኛውም ዓይነት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ያልሆኑ ተሽከርካሪዎች የተሳፋሪ ቁጥር ወይም የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ መሆኑ ኢንጂነር ስጦታው ተናግረዋል። በዚሁም መሰረት የሚኒባስ ታክሲ የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ ሲሆን በልዩ ሁኔታ ከኋላ ወንበር ሦስት ሰው ብቻ እንዲጭኑ ተደርጓል።
የሀይገር እና ቅጥቅጥ አውቶቡስ ደግሞ የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ እና በተጨማሪ አምስት ሰው እንደሆነ ገልጸዋል።
የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የሸገር የብዙኀን ትራንስፖርት እና የመንግሥት ሠራተኞች ሰርቪስ አውቶቡሶች የተፈቀደ የትራንስፖርት ተሳፋሪ ቁጥር ወይም የመጫን አቅም በተሽከርካሪ ወንበር ልክ እና በቁም ለመጫን ከተፈቀደው 50 በመቶ ሰው መሆኑም አስታውቀዋል።
ማንኛውም ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) የጭነት ልክ አሽከርካሪውን ጨምሮ ሦስት ሰው ሲሆን፣ ባለ አራት እግር (ባጃጅ) ተሽከርካሪ የመጫን አቅም በወንበር ልክ መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።
ታክሲ እና ሌሎች መሰል የሜትር ታክሲ ተሽከርካሪዎች ደግሞ የተሳፋሪ የጭነት ልክ በተሽከርካሪው ወንበር ልክ ነው።
የትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ መጠን በተመለከተ ቀደም ሲል በአገራዊ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት በተደረገው አዲስ የታሪፍ ጥናት ጭማሪ መሠረት የሚቀጥል ነው ብለዋል። የብዙሃን ትራንስፖርት ታሪፍን በተመለከተ አሁንም መንግሥት እያደረገ ባለው ድጎማ የሚቀጥል እንደሆነም ነው የቢሮ ኃላፊ የጠቀሱት።
ማንኛውም የከተማዋ የትራንስፖርት ተሳፋሪ ወይም ተጠቃሚ፣ አሽከርካሪ እና ረዳት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ጭምብል) ማድረግ እንዳለባቸው የቢሮ ኃላፊው አሳስበዋል። ሆኖም ይህን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ወይም ጭምብል ያላደረገ ተሳፋሪ በተሽከርካሪ ላይ ማሳፈር ወይም የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪ ላይ አገልግሎት ማግኘት እንደማይቻል ኢንጂነር ስጦታው አስረድተዋል።
‹‹የከተማችን የሕዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች የተሳፋሪውን ጤንነት ለመጠበቅ የሚረዳ የአየር ዝውውር በተሽከርካሪው መኖሩን ለማረጋገጥ የተሽከርካሪውን መስኮት መክፈት አለባቸው።››ም ተብሏል። ማንኛውም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልገሎት ተጠቃሚ፣ አሽከርካሪ እና ረዳት ወደ ተሽከርካሪው ከመግባታቸው በፊት የእጅ ንፅህና የሚጠብቁ አልኮል ወይም ሳኒታይዘር ወይም ውሃና ሳሙና መጠቀም አለባቸው። ሁሉም በከተማዋ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቢያንስ በቀን ኹለት ጊዜ ዲስ ኢንፌክት (Disinfect) ማድረግ እንዳለባውም ተመላክቷል።
በተያያዘም በከተማዋ የሥራ ሰዓት መውጫ ማለትም ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ድረስ ከቀኑ 10፡00 እስከ ምሽት 2፡00 (ኹለት ሰዓት) ድረስ ማንኛውም ከባድ ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ እንደማይችልም ተገልጧል። በዚህ መሰረት በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን ክልከላዎች በሚጥሱ አካላት ላይ መመሪያው የቅጣት ውሳኔ አስቀምጧል።
ከመጫን ልክ በላይ ማሳፈር ለሚኒባስ 1000 (አንድ ሺሕ) ብር፣ ሀይገር ወይም ቅጥቅጥ 1500 (አንድ ሺሕ አምስት መቶ) ብር፣ አውቶቡስ 1500 (አንድ ሺሕ አምስት መቶ) ብር፣ ታክሲ (ላዳ፣ ሜትር ታክሲ) 500 (አምስት መቶ) ብር፣ ባለሦስት ወይም ባለአራት እግር ባጃጅ ወይም ሞተር ሳይክል 500 (አምስት መቶ) ብር እንደሚያስቀጣቸውም በመመሪያው ተቀምጧል።
በተለይ ደግሞ ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቢያንስ በቀን ኹለት ጊዜ ዲስ ኢንፌክት (Disinfect) ማድረግ እንዴት እንዳለባቸው ሲገልጹ፣ ሁሉም የትራንስፖርት ሰጭ ተሽከርካሪዎች ከመነሻቸው ተሽከርካሪዎቻቸውን በፀረ ተዋህስያን እንዲያፀዱ ይደረጋል። ለዚህም ትራፊክ ፖሊስ እንዲሁም የትራንስፖርት ባለሥልጣን በኩል ቁጥጥር ይደረጋል በማለት አሳውቀዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ መሠረት፣ ይህ ጽሑፍ ለአንባብያን እስከረደሰበት እለት ድረስ በአጠቃላይ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 260 ሺሕ 139 ደርሷል። 203 ሺሕ 408 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል። 3 ሺሕ 795 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አጥተዋል። በድምሩ አንድ ሚሊየን 215 ሺሕ 934 ሰዎች ደግሞ የኮቪድ ክትባት ወስደዋል።
![]() | ![]() |
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013





