የኮቪድ 19 ገዳይነቱ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መጥቷል። የሕብረተሰቡ መዘናጋትም እንዲሁ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ ነው። በኮሮና እናቱን አባቱን የቅርብም የሩቅም ቤተሰቡን አልያ ወዳጅ ዘመዱን ያልተነጠቀ ወይንም ታሞ ያገገመ ወገን ዘመድ ጓደኛ የማያውቅ ባይኖርም፣ አሁን እየተደረገ ያለው ግን እኔን ካልነካኝ አላምንም አይነት አካሄድ እና ቸልተኝነት ነው።
የእለት ተእለት ገቢውን ለማግኘት ከቤት ወጥቶ በታክሲ ሰልፍ ከሚጋፋው እና በአውቶብስ እግር ላይ ቆሞ እና ተዛዝሎ ወደ ሥራ ከሚሄደው፣ አልያም ከሥራ ከሚመለሰው አዲስ አበቤ በተጨማሪ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር እና በያዝነው ግንቦት ወር የተደረጉ ሕዝባዊና ሐይማኖታዊ በዓላትን ለመታደም ወደ አደባባይ በገፍ የሚወጣው ሰው ቁጥር ኮሮና አገራችን ውስጥ በየእለቱ ከ20 እና ከ30 በላይ ሰዎችን እየነጠቀን ያለ አላስመሰለውም።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ባለፈው ሚያዝያ 24 የተከበረው የፋሲካ በዓል በርካቶች ከወዳጅ ዘመድ የተገናኙበት ለደስታና ለተዝናኖት ወደ ተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች ተጉዘው የታደሙበት ነው። በሥፍራዎቹ እንኳንስ ርቀት መጠበቅ ቀርቶ የመቀመጫ ቦታ የጠፋበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝብታችን ነው።
ከፋሲካ በዓል አንድ ቀን ቀደም ብሎ በተከበረው የስቅለት በዓልም በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥም ሆነ በቅጥር ግቢያቸው የተገኙ ምእመናን ቁጥር ቀላል የሚባል አልነበረም። ከፋሲካ በዓል ጋር ተያይዞ በነበረው ግብይትም የገበያ ስፍራዎች መጨናነቅ እንደ ማንኛውም ቀን እንጂ ኮሮና እንደተስፋፋባት እና የሕክምና ባለሙያዎቿ ከአገሪቱ የማከም አቅም በላይ መሆኑን በአጽንኦት እንደገለጹባት አገር ነዋሪ አልነበረም።
ሚያዝያ 27 የአርበኞች የድል ቀን ላይም አርበኞችን ለማሰብ ብዙዎቻችን ወደ አደባባይ ወጥተን ነበር። ራሳቸው የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት አባት እና እናት አርበኞችም በስፍራው ተገኝተው ነበር። በርካቶች ከእነኝህ አርበኞች ጋር በመሆን ፎቶ ሲነሱም ተስተውሏል። ይህ ያልተገባ መቀራረብ በተለይ ደግሞ በእድሜ የገፉትን የበለጠ እንደሚፈትን እየተነገረ አለመስማት በቀኑ ላሰብናቸው አርበኞቻችን እንደ አለማሰብ ይቆጠራል።
ሌላኛው ባሳለፍነው ሳምንት “ብልጽግና ፓርቲን” ለመደገፍ መንገድ ተዘግቶ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሲሆን፣ በሰልፉ ላይ በርካቶች ታድመዋል። መንግሥት በአንድ በኩል ኮሮናን ለመከላከል ያስችል ዘንድ ባወጣው መመሪያ ላይ ከ50 በላይ ሆናችሁ እንዳትሰባሰቡ እያለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እኔን ለመደገፍ በገፍ ሰልፍ ውጡ ማለቱ የሚጣረስ ሀሳብና ተግባር ነው።
ኮሮናን ለመከለከል በጤና ሚኒስቴር በኩል የወጣው መመሪያ ቁጥር 30/2112 ተግባራዊ ለማድረግ ጤና ሚኒስቴር ከፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ኮሚቴ አባላት በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የተጀመሩ መልካም ተግባራት ቢኖሩም ከችግሩ አንፃር ገና ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። ስራው የጋራ ርብርብን የሚጠይቅ መሆኑን በመረዳት ባለድርሻ አካላት የየራሳቸውን ተግባር በመከወን የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ ጫናዎችን ማቃለል አለባቸውም ብለዋል።
በተለይ ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ በማተኮርና በቀጣይ የሚከናወኑ የበዓላት ዝግጅቶችን ምክንያት በማድረግ፣ እንዲሁም የተለያዩ የማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀት መመሪያውን በማይተገብሩት ላይ የማስተማርና ሕግ የማስከበሩን ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽነር ጌቱ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ባለማድረግ ከ70 ሺሕ በላይ ሰዎችን በመቆጣጠር የማስተማሪያ እርምጃ መወሰዱን ከኮሚሽኑ ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል።
ግንቦት ወርን ስንመለከት፣ ደግሞ ማክሰኞ ግንቦት ሦስት ቀን በተደረገ የጎዳና ላይ የዒፍጣር ፕሮግራም፣ እንዲሁም የዒድ አልፈጥር በዓል ቀን በስቴዲምና አካባቢው የታደመው ህዝበ ሙስሊም ቁጥር ስፍር አልነበረውም። ይህን መሰል የጎዳና ላይ ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞችም ተደርጓል። ኮቪድ 19 ግን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይገደብ ገዳይነቱን ቀጥሏል። ሐሙስ ግንቦት አምስት የዒድ-አልፈጥርን በዓል አስመልክቶ ለስግደት የተሰባሰበው ሕዝበ ሙስሊም ከዒፍጣሩ ቁጥር በብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነበር።
![]() | ![]() |

ዘሚ የኑስ
ዘሚ የኑስ የኒያ ፋውንዴሽንና የጆይ ኦቲዝም ማዕከል መስራች ነበሩ። “በኮሮና እንዳልሞት ጸልዩልኝ” በማለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረው እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህን ቢሉም የብዙ ኦቲዝም ተጠቂ ህፃናት እናትን ተነጥቀናል።
ዘሚ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 2012 ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጋር አድርጋው ከነበረው ቃለ መጠይቅ የቀነጨብኩት ነው። የዘሚን ሃሳብና ማንነት በትንሹ ታገኙበታላችሁ።
“ዘሚ የተወለደችው አዲስ አበባ ነው። እንደ አብዛኛው የአዲስ አበባ ህጻን ከመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ካሉ ሠርቶ አዳሪዎች የተወለደች ግን በጥሩ ያደገች፣ እናትና አባቷ ለአንድ ልጅ የሚገባውን ሁሉ እየሰጡ ያሳደጓት፣ ካቴድራል ትምህርት ቤት የተማረች፣ ደስተኛ እና ራሷን የሆነች ልጅ ናት።” በማለት ነበር ራሷን የገለጸችው።
“ራሷን የሆነች ልጅ ስል ከልጅነት ጀምሮ ማንንም አልከተልም። አዳዲስ ፈጠራዎች ራሴ እፈጥራለሁ፣ መልበስ የምፈልገውን በራሴ ዲዛይን እለብሳለሁ። በዚህ አባቴ በጣም ነው ይደግፈኝ የነበረው፤ ራስሽን ሁኚ ይለኝ ነበር። እናቴ ግን በዚህ ትንሽ አትስማማም። በጣም ጠንካራ እናት ነበረችኝ። ለምሳሌ ልብስሽ አጠረ ብላ ትጥላለች። ግን ጥሩ ነው ያደኩት፤ ልጅነቴንም ተጠቅሜአለሁ። በዝናብ መደብደቡ፣ ጭቃ እና ጎርፍ ላይ መጫወት፣ ተልኬ ስወጣ ጠፍቼ ጓደኞች ጋር መሔድ፣ ያላሳለፍኩትና የማላውቅበት ከእኩዮቼ ጋር መጣላትና መደባደብን ነው።” በማለትም ልጅነቷን እና እድገቷን አስታውሳ ነበር።
“በኒያ ፋውንዴሽን የምንሠራው ኦቲዝም ላይ ብቻ አይደለም። ከኦቲዝም በፊት ወጣቶች ላይ ብዙ ሠርተናል። በተለይም የተቸገሩ ወጣቶች ላይ፣ ሴተኛ አዳሪ ሆነው የሚተዳደሩ ሴቶች ላይ፣ ችግር ላይ ያሉ ወንዶች፣ ምክር፣ ሥራ… ብቻ ሰው የሚፈልጉ ወጣቶች ላይ ብዙ ሠርተናል። ከዛ ነው ወደ ኦቲዝም የገባነው።” በማለትም የበጎ አድራጎት ሥራ ጅማሮዋን ገልጻ ነበር።
ለሳምንታት ያህል በህክምና ሲረዱ ቆይተው ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 በጳውሎስ ሆስፒታል ማረፋቸውን በተለያዩ ማኅበራዊ ገጾች፣ የመንግስት እና የግል መገናኛ ብዙኀን ደረ ገጾች ላይ ተገልጿል። ዘሚ የኑስ ሚያዝያ 4 ቀን 2013 የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ሲያደርጉ የኮሮና ቫይረስ ስለተገኘባቸው እና ከቀናት በኋላም ለመተንፈስ ተቸግረው ኦክስጅን በማስፈለጉ ሚሊኒየም ሆስፒታል ገብተው ሲታከሙ ነበር። ወደ መጨረሻም ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተዛውረው በጽኑ ህክምና ማዕከል ውስጥ ሲረዱ መቆየታቸውን ተገልጿል።
በጆይ ኦቲዝም ማዕከል የስንብት ሥነ ስርዓት የተከናወነላቸው ሲሆን፣ ግንቦት 3 ቀን 2013 የቀብራቸው ሥነ ስርዓት ተፈጽሟል። ወይዘሮ ዘሚ የኑስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነበሩ።
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013





