የጤና አገልግሎትን የተመለከተ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

0
1094

የጤና አገልግሎቶችን በአጠቃላይ የሚያስተዳድር የጤና አገልግሎት አዋጅ የተሰኘ አዋጅ በረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ በጤና ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክትር አብዱልዓዚዝ ሱዉዲ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የጤና አገልግሎት ረቂቅ አዋጁ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር ያወጣውን የ10 ዓመት መሪ እቅድ ለማሳካት፣ በጤና ተቋማት ላይ የሚደረግን ቁጥጥር ለማጠናከር እየተዘጋጀ ያለ ረቂቅ እንደሆነ ሰምተናል፡፡ ዓመታትን ከወሰደ ጥናት በኋላ በሙያው ልምድ ያላቸው የሕክምና እና የሕግ ባለሙያዎች እንዳዘጋጁት እንዲሁም የሚመለከታቸው የጤና ማኀበራት እና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እስከ ክልል ድረስ አስተያየት እንደሰጡበት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዚህ በፈት የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥጥር ይደረግባቸው የነበረው በኢትዮጵያ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን በኩል በ2002 በወጣ አገራዊ አዋጅ ቁጥር 661 መሰረት እንደነበረ አብዱልዓዚዝ አስታውሰዋል። አዲስ እየተረቀቀ የሚገኘው አዋጅ ከዚህ በፊት ያልነበሩ እንደ ንቅለ-ተከላ የመሳሰሉ አዳዲስ ሕክምናዎችን በሕግ ማዐቀፍ ለመቆጣጠር ስለሚያስፈልግ፣ ተጠያቂነትን እና ጥራትን ለመቆጣጠር የተዘጋጀ ነው ብለዋል። የጤና አገልግሎት አስተዳደር አዋጁ ሁሉንም የመንግሥትም ሆነ የግል የጤና ተቋማት የሚያስተዳድር እንደሆነ ተገልጿል።

ረቂቅ አዋጁ 12 ክፍሎች እና 68 አንቀጾች ያሉት ሲሆን፣ በረቂቁ ከተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የተገልጋይ መብቶች እና ግዴታዎች፣ የጤና ተቋማት መብቶች እና ግዴታዎች፣ ስለ ክትባቶች፣ የተገልጋይ ፈቃደኝነት፣ የድንገተኛ ሕክምና እና የሪፈራል ቅብብሎሽ አገልግሎት፣ እንዲሁም በማገገሚያ ስፍራዎች ያሉ አገልግሎቶች እና ሌሎችም ጉዳዮች ናቸው፡፡ ስለ አንጎል ሞት ወይንም ሰውን በኦክስጂን በመታገዝ በህይዎተ ስለማቆየት በመጀመሪያው የአዋጁ ክፍል እንደተካተተ አስረድተዋል። በረቂቁ ስለ ልዩልዩ የጤና አገልግሎቶች የተደነገገ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል የአዕምሮ ጤና ተካቷል፡፡ በእኛ አገር የአዕምሮ ሕመም እንደ ሌሎች ሕመሞች ትኩረት ይሰጠው ዘንድ በረቂቁ በመጀመሪያው ክፍል ላይ መካተቱን አብዱለዓዚዝ አያይዘው ገልጸዋል።

በክፍል ኹለት ደግሞ ስለ ሕዋስና ሕብረ ሕዋስ የአካል ክፍሎች ልገሳ እና ንቅለ ተከላ ማለትም በብዛት ከሚታወቀው የኩላሊት ንቅለ ተከላ በተጨማሪ ስለሚለገሱ የሕዋስ እና የሕብረ ሕዋስ ክፍሎች፣ እንዲሁም የዓይን ብሌን ልገሳ ጋር የተያያዘ ልገሳ ጭምር የሚሠራበት የሕግ ማዐቀፍ ያልነበረ በመሆኑ የደም ልገሳንም ጨምሮ በዚህ ክፍል መካተቱን አሳውቀዋል። በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎትም በዚህ ክፍል የተካተተ ሲሆን፣ ይህን የሕክምና አገልግሎት የሚወስዱ ሰዎች በሕጋዊ ጋብቻ የተጣመሩ እንዲሆኑ በረቂቅ አዋጁ ተቀምጧል። ስለ ባህል እና ተደጋጋፊ እና አማራጭ ሕክምና በዚሁ ረቂቅ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ በጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆን በባህል የሕክምና መስጫ ተቋማት ስለሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች በረቂቁ ክፍል አራት ላይ ተብራርቷል።

የሰው ሀብት ልማት እና አስተዳደር፣ ስለ ሕክምና ሙያ ፍቃድ፣ ስለ ብቃት ማረጋገጫ እና ምዘና፣ ስለ ጤና ባለሙያዎች ሙያዊ ስነ ምግባር፣ ስለ ጤና ባለሙያዎች የመማክርት ጉባዔ በክፍል አምስት የተቀመጠ ሲሆን፣ በክፍል ስድስት ደግሞ ስለ ጤና እና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር እንደተካተተ፣ በአጠቃላይም 12 ክፍሎች እንዳሉት ከአብዱለዓዚዝ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል። የጤና አገልግሎት ረቂቅ አዋጁ ወደ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተልኮ አስተያየት ተሰጥቶበት ወደ ጤና ሚኒስቴር የተመለሰ ሲሆን፣ የተሰጡ አስተያየቶች ተሟልተው ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እንደሚላክ ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here