መነሻ ገጽአምዶችዓውደ-ሐሳብአጥር - አልባ የዐቢይ ጥንስሶች በአዲስ አበባ

አጥር – አልባ የዐቢይ ጥንስሶች በአዲስ አበባ

ሰዎች ቤታቸውን አጽድተው፣ ግቢያቸውን ጠርገው ቆሻሻን ከግቢ ውጪ ይጥላሉ። ውጪው መንገዱ የማን ነው? ከተማው የማን ነው? አገሩ የማን ነው? አዲስ አበባም ብዙ ቆሻሻዎች ከሥሟ ያፋቷት ከተማ ሆኖ ይህ ነገሯ ሲነቀፍባት ኖራለች። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የተለያዩ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት እየተባሉ የሚጠሩ ሥራዎች ቢያንስ ብዙ እንቅስቃሴ አለባቸው በሚባሉ የመሃል ከተማዋ አካባቢዎች የዕይታ ለውጥን እያሳዩ፣ እየተዋቡ ይገኛሉ። ሽመልስ አረአያ (ፒ.ኤች.ዲ) ይህን ሐሳብ በማንሳት የሚሠራውን አድንቀው በተያያዘም የብዙዎችን ‹አጥር አፍቃሪነት›ም በመጥቀስ ይህን አሰናድተዋል።

ይህን ጽሑፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ እኩለ ሌሊት ከእንቅልፌ እንደነቃሁ ምንም ከማድረጌ በፊት አመል ሆኖብኝ በዳበሳ የምፈልገው የእጅ ስልኬን እንዳነሳሁ ዩቲዩብ ስከፍት የመጀመሪያ ያገኘሁት ቪድዮ ነው። በቪድዮው በአንዱ የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያ ገጽ ላይ ከተጫነ ጥቂት ሰዓታት ያስቆጠረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጻ የሚያደርጉበት ‹ቃል በተግባር› የተሰኘ የአንድ ሰዓት ተኩል ዘጋቢ ፊልም ነው።

ከዚህ ዘጋቢ ፊልም መረዳት እንደቻልኩት የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወጠነው ሰፊ ሥራ ከእንጦጦ ተነስቶ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ የሚዘልቅ ድምር ፕሮጀክቶች ውጤት ሲሆን፣ በተናጥል የሚሠሩ ቢመስልም ሲጠናቀቁ ከተማዋን እንደሥሟ አዲስ ለማድረግ ያለሙ ናቸው። እነኚህ በተለያየ የፕሮጀክት ሥም እየተተገበሩ የሚገኙ ሥራዎች ዛሬን ከትላንት እንዲሁም ከነገ ጋር የሚያስተሳስሩ ዘመን ተሻጋሪ አሻራዎች ናቸው።

በእንጦጦ ወይም በወዳጅነት አደባባይ ጊዜውን ያሳለፈ መንፈሱን አድሶና ተዝናንቶ ይመለሳል። ወደሳይንስ ሙዚየም ጎራ ካለም ትላንትን ወደዛሬ በማቅረብ አጉልቶ ይመለከትበታል። ወደ ቤተ-መጻሕፍት ጎራ ቢል እውቀትን በመቅሰም የነገ እሳቤውንና ዕይታውን ያስተካክልበታል።

በአጠቃላይ ለዕይታ እንኳን በማይስብ አኳኋን በየቦታው ታጥረው ለዘመናት የተቀመጡ ክፍትና ያልለሙ አካባቢዎች አሳቢ የሆነ ጭንቅላትና የሚሠሩ እጆች እየጎበኗቸው እንደሆነ ከሚሠራው ሥራ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል። ሁሉም ሥራ ከሐሳብ (idea identification) ሲጀምር፣ ይህም በወረቀት ላይ ይሰፍራል፤ ለትግበራው (Implementation) በዕቅድ መልክ ይዘረዘራል። በዕቅዱ መሠረት ተጠናቅቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት የተደረጉ ፕሮጀክቶች ያሉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በትግበራ ላይ ይገኛሉ። ይህ እንደ ኢትዮጵያዊ እጅግ ደስ ያሰኛል።

አዲስ አበባ ከጎበኟት የውጭ እንግዶች የሚሰማው ትችት ከዚህም የበለጠ ስለጽዳቷ ትኩረት ተሰጥቶ በመሥራት ገጽታዋ መቀየር እንደሚገባ ነው። ለትምህርት አውሮፓ በተገኘሁ ጥቂት ሳምንታት ለምርምር ሥራዬ አጋዥ ይሆነኛል ብዬ ለመማር የተመዘገብኩትን ኮርስ የሚያስተምረን የዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር የአንድ ኢትዮጵያዊ ተማሪ የምርምር ሥራ አማካሪ ነበር። ይህ ሰው የተማሪውን የመስክ መረጃ አሰባሰብ አፈጻጸም ግምገማ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ኖሯል። ከኢትዮጵያ ጉዞ እንደተመለሰ ስለኮርሱ ገለጻ ለመስጠት በክፍል ውስጥ ተገናኘን። ለዚህ ኮርስ በክፍሉ ውስጥ የተገኘን ተማሪዎች ሁላችንም አዲስ ገቢ ስለነበርን ስለራሳችንና ከየት አገር እንደመጣን በየተራ እንድናስተዋውቅ እድል ተሰጠን።

እኔም ተራዬ ሲደርስ በኩራት ከኢትዮጵያ መምጣቴን በመግለጽ እራሴን አስተዋወቅሁ። በወቅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገሬ ወጥቼ በአውሮፓ ምድር የተገኘሁ ሲሆን ስለአገሬ ሳስተዋውቅ የነበረኝ ግምት በክፍል ውስጥ ያሉት ከተለያየ አህጉራት የተሰባሰቡት ተማሪዎች ስለጀግንነታችንና አይበገሬነታችን (ያውቁናል ብዬ ስለደመደምኩ) ከገለጻው መጠናቀቅ በኋላ ማብራሪያ መጠየቃቸው አይቀርም የሚል ነበር።

ነገር ግን ‹‹ከኢትዮጵያ…›› የሚል ቃል ከአንደበቴ ከመውጣቱ ከፕሮፌሰሩ እና ከተማሪዎቹ በኩል የገጠመኝ ምላሽ ግምቴን ስህተት አደረገው፤ ቆሌዬንም የሚገፍ ነበር። የተማሪዎቹ እርስ በእርስ መተያየት ከማስተናገዴ የፕሮፌሰሩ ምላሽ ደግሞ የባሰ አሸማቃቂ ሆነ። ከሳምንት በፊት ኢትዮጵያ እንደነበረ፣ ከወዳጆቹ የአዲስ አበባ የሥሟ ትርጉም (በእንግሊዝኛ ለተማሪዎቹ በመናገር) መረዳቱን፣ ሆኖም ግን ከተማዋ እንደሥሟ ሳትሆን ከሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ሲነጻጸር በባሰ ሁኔታ የቆሻሻ ክምር የተጫናት ናት ብሎ ሲናገር፤ ሁሉም ተማሪ በሳቅ ክፍሉን አናጋው።

የአዲስ አበባ ጽዳት ጉዳይ አሳሳቢነት ምንም ጥርጥር ባይኖረውም አንዳንድ የምዕራባውያን ‹ወዳጆቻችን› ስለኢትዮጵያ በብዛት የሚነገሩ በጎና አስደማሚ ነገሮች ባሉበት አሉታዊ ጎኖች ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ሳስበው በጣም ይገርሙኛል። በተደጋጋሚ እንደታዘብኩትም ይህም ፕሮፌሰር የዚህ አስተሳሰብ ተጠቂ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

በዚህ አግባብ ኢትዮጵያን ለመግለጽ የተፈለገበት ምክንያት ለማብራራት መሞከር አንባቢን ማድከም ነው። በተለይ በዚህ ወቅት የገጠመንን የውጭ ጫና ለተገነዘበ ኢትዮጵያ የሚለውን ሥም በዓለም መድረክ ሁሉ ማጠልሸት የሙሉ ጊዜ ሥራ የሆነ ይመስላል። ለዚህ በአገራችን አንድ አባባል አለ፦ ‹‹ምቀኛህን መተባበር ከፈለግህ ጠንክረህ ሥራ›› የሚል ነው።

ወደታሪኩ ስመለስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት በሰማሁ ጊዜ በዚያ ክፍል ውስጥ የተፈጠረውን ክስተት ሁሌም በምናቤ ተመልሼ እንዳስታውሰው እገደዳለሁ።
አዲስ አበባን እንደሥሟ ውበት ለማልበስ የተጀመረው የቃል ተግባር በትልቁ ስዕል ስንመለከተው ከተሞች ለነዋሪዎቿ ምቹና ጽዱ መሆን እንዳለባቸው በ2030 እንዲሳኩ የተባበሩት መንግሥታት ካስቀመጣቸው 17 ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች (Sustainable Development Goals – SDGs) መካከል አንዱ ነው። በተጨማሪም መንግሥት የሥራ እድል ፈጠራ፣ ድህነት ቅነሳ፣ እንደዚሁም የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ለሚያደርገው ጥረት ቁልፍ መፍትሄ ነው።

የአሁኖቹ የአዲስ አበባ ገጽታን ለመቀየር ያስችላሉ የተባለላቸው ፕሮጀክቶች የሚያስገኙት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም አካባቢያዊ ጥቅሞች በሚመለከት ‹የእንጦጦው ፕሮጀክት› በሚል ርዕስ በዚህ ጋዜጣ ላይ ከወራት በፊት አንድ ጽሑፍ የጻፍኩኝ ሲሆን፣ አንባቢ ከዚያ መለስ ብሎ እንዲያነብልኝ በአክብሮት እጋብዛለሁ።

በርቀት ሆኜ በሚድያ ስሰማቸው የነበሩና እስክጎበኛቸው ከጓጓሁላቸው የሸገር ፓርኮች መካከል የተጠናቀቁት የወዳጅነት አደባባይ እና አንድነት ፓርክ በመጎብኘቴ የተሰማኝ ስሜት ልዩ ነው። በተለይ የአንድነት ፓርክ ከመካነ-እንስሳት (Zoo) በተጨማሪ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ባህልና ሥልጣኔ ከማሳየቱም በላይ የኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ ያልተወከለ ማግኘት ይከብዳል።

በትላልቅ የአውሮፓ ከተሞች መካነ-እንስሳት መመስረት የተለመደ ነው። በመሆኑም በእነኚህ ከተሞች እግር ጥሎት የተገኘ ስፍር ቁጥር የሌለው ጎብኚ በግፊያ የተጠየቀውን በመክፈል ይጎበኛቸዋል። ለምሳሌ በ1858 እንደተመሠረተ የሚነገርለት በመሃል ፍራንክፈርት ከተማ በ11 ሺሕ ሄክታር መሬት ላይ የተንጣለለው የፍራንክፈርት መካነ-እንስሳት (Zoo Frankfurt) ከ5000 በላይ እንስሳት መኖሪያ ሲሆን ከበርሊን Zoo በመቀጠል እጅግ ጥንታዊው ነው ይባልለታል።

ይህን ፓርክ ለመጎብኘት ከ18 ዓመት በላይ የሆነ አዋቂ 12 ዩሮ የሚጠየቅ ሲሆን ከዚያ በታች የእድሜ ክልል ላይ ያሉ ደግሞ የአዋቂዎቹን ግማሽ ብቻ እንዲከፍሉ ይደረጋሉ። በቤተሰብ ለሚጎበኙም እንዲሁ የሂሳብ ማሻሻያ ተደርጎ ከ30 ዩሮ በላይ አይከፍሉም። ይህንን የመሰለ የአከፋፈል ስርዓት በአንድነት ፓርክ ላይ ተግባራዊ መደረግ ይኖርበታል። አለበለዚያ ከ10 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ሳይቀሩ በአዋቂ ልክ ሒሳብ ማስከፈል በምንም መልኩ ትርጉም አይሰጥም።

ይህ እንዳለ ሆኖ አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ሳያመነታ ሊጎበኛቸው የሚገቡ ድንቅና ውብ ፓርኮች አዲስ አበባ ውስጥ ተገንብተዋል ማለት ይቻላል። እንደዜጋ ከእኛ የሚጠበቀው ቅድሚያ በተግባር ተጠናቅቀው አገልግሎት የሚሰጡ ፓርኮችን መጎብኘት ነው። ከዚያ በኋላ ትችትም ቢቀርብ ያማረ ይሆናል።

- ይከተሉን -Social Media

አጥር የማጠር ፍቅር
ብዙዎቻችን ለአጥር ያለን ፍቅር እጅግ የተለየ ነው። ለአንድ መጽሐፍ ወደዋናው ፍሬ ሐሳብ ከመግባታችን በፊት መግቢያ መጻፍ ግድ እንደሆነ ሁሉ፣ ለአንድ ቤትም አጥር ተበጅቶለት መግቢያ መውጫ ሊኖረው የግድ ያስፈልጋል የሚሉ ብዙዎች አሉ። ሆኖም የአጥር አፍቃሪዎች ስለአጥር አስፈላጊነት የተለያየ ምክንያት እንደሚኖራቸው መገመት ይቻላል። አንዳንዱ በፍርሃት የተነሳ አጥር ከማጠር አልፎ ከአናቱም አደገኛ የኤሌክትሪክ አጥር የሚል መልዕክት ያስቀምጥበታል።

ይህ የደኅንነት ስጋት መኖሩን አመላካች ነው። አንዳንዱ የሚሠራው ነገር ከጎረቤት እንዳይታይበት የሚሸሽገው ስለሚኖረው አጥር ያጥራል። ይህ የደኅንነት ስጋት ሳይሆን የግለኝነት ማሳያ (privacy) ነው። ነገር ግን ከሌላው በተለየ ኢትዮጵያዊያን ማኅበራዊ ግንኙነታችን ሰፊ እንደሆነ እና አብረንም የምንበላ የምንጠጣ መሆናችንን የምንናገር ሰዎች ነን።

ለምሳሌ የምዕራብ አውሮፓ አገራት የተወሰኑ ከተሞቻቸው የመጎብኘት እድሉ የነበረኝ ሲሆን፣ መለስ ብዬ ሳስበው ከሚመጡልኝ ነገሮች አንድም አጥር አለማየቴን ነው። ወይም ምንም እንዳያሳይ ተደርጎ የታጠረ አጥር ማየቴን አላስታውስም። እንዲያውም ትምህርቴን የተከታተልኩበት ዩኒቨርስቲ በተለያየ ቦታ የሚገኙ ካምፓሶች አጥር አልባ ናቸው።

አስገራሚው ደግሞ የእኛ ዩኒቨርስቲዎች ያን ሁሉ በጀት መድበው አጥር የሚያጥሩት ለምን ብለው ይሆን? ዓለምን ‹‹በቀላሉ በመመልከት ተመራማሪ ትውልድ›› ለማፍራት የተቋቋሙት እነዚህ ዩኒቨርስቲዎቻችን ሁሉንም ካምፓሶቻቸው በአጥር ለመከለል የሚጣደፉት ለምንድን ነው? የሁሉም አጥር አጣሪ ዋናው ጉዳይ በአጥር በመከለል ውስን የሆነው መሬት አስፋፍቶ የመያዝ እሽቅድምድም ይመስላል።

ግለሰቦች ከስግብግብነት ባህርያቸው የተነሳ ነው ቢባል እንኳ፣ የመንግሥት ተቋማት ሳይቀሩ ለአጥር ያላቸው ፍቅር አይጣል ነው። ውስን የሆነው የመሬት ሀብት በእንዲህ አይነት ስግብግብነት በአጥር ሲያዝ እያደገ ከሚመጣው የሕዝባችን ቁጥር አንጻር ተጎጂ የሚሆነው የአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍ ሲልም አገር ነው።

ይህ የሚያመላክተው ሁሉም የአጥር አፍቃሪ ምክንያቱ የደኅንነት ስጋት አይደለም ማለት ነው። በአጥር መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ለኢንቨስትመንት የሚውል ሀብት ብክነት ያስከትላል። መጠኑ አነስተኛ የማይባል የአገሪቱ መሬትም እንዲሁ አጥር ተሸክሞ ዓመታት ያስቆጥራል። አገሪቱ ውስጥ በአጥር ተከልለው ምንም የልማት ሥራ ያልተከናወነባቸው ቦታዎች ኦዲት ቢደረጉ እጅ በአፍ የሚያስጭን ማስረጃ እንደሚገኝ ጥርጥር የለውም።

ሲጠቃለል አጥር ማጠር ትርጉሙ ‹ከክልሌ ውስጥ ላይህ አልፈልግምና አትድረስብኝ› እንደማለት ነው። በተከለለው ግዛቴ ማንንም አላስገባም፤ አላስነካም እንደማለትም ነው። ግቢያችን አጥረን ስናበቃ በመንደሩ ዐይተነው ያላወቅነው ሰው አለፍ ሲል ‹‹እንዴት እዚህ ተገኘ?›› ከማለት አልፈን የምንሠራባቸውን መሥሪያ ቤቶች ሳይቀር የአጥር ልክፍታችን ሰለባ እንዲሆኑ እናደርጋቸዋለን። አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎቻችን የዚህ በሽታ ተጠቂዎች ሆነዋል። ሰው ሠራሽ አጥሮቹ ይፍረሱና በሰፊዋ አገራችን በአንድነት በመተሳሰብ እንኑር!
የአንዳንዱ የአጥር ልክፍት ደግሞ አይጣል ነው። ተቀጥረው በሚሠሩበት መሥሪያ ቤት መረጃ ለሌሎች እንዳይደርስ በአጥር መከለል የሚፈልጉ ብዙ አሉ። እነኚህ ‹እኔ ሳላውቀው ለማንም ቢሆን መረጃው አይድረሰው!› የሚሉ አጥር አጣሪዎች ናቸው። መረጃን እንደደላላ አፍኖ በመያዝ ከዚህ ማትረፍ ይፈልጋሉ። ይህ በራስ ካለመተማመን የተነሳ በፍርሃት ቆፈን መያዝን ከማመልከት ውጭ ሌላ ትርጉም የለውም።

ደላላ ገዥና ሻጭ በመረጃ እንዳይገናኙ አራርቆ በማኖር የኹለቱን ሐሳብ ተራ በተራ እየተቀበለ በመረጃ እቀባ ብቻ የሚተዳደር ኪራይ ሰብሳቢ (rent seeker) ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት ቃሉ የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሐሳብ ሲሆን ትርጉሙም አንድ አካል ምንም ዓይነት የምርታማነት አስተዋጽዖ ሳያደርግ ወይም እሴት ሳይጨምር ሀብት ወይም ትርፍ የማግኘት ተግባር ነው።

- ይከተሉን -Social Media

መረጃው በመውጣቱ በተቋማትና በሰዎች ደኅንነት ላይ አደጋ እንዳያስከትል መጠንቀቅ ተገቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በፍጥነት የሚተላለፍ መረጃ ሥራን ያቀላጥፋል፤ ወጪም ይቀንሳል። ለዚህም ሚናው የመረጃ ቴክኖሎጂ እየተራቀቀ ይገኛል። ከዚህ በተጻራሪ መረጃ ለማፈን አጥር ማበጀት በራስ አለመተማመንን ከማመላከቱም በላይ በሌሎች ልፋት ለማትረፍ መሞከርና መከጀልን ያመለክታል።

ከዚህ ጋር የሚዛመድ የመረጃ አለመመጣጠን (Information Asymmetry) የሚባል የኢኮኖሚክስ ጽንሰ-ሐሳብም አለ። የመረጃ አለመመጣጠን ማለት በገዢና በሻጭ መካከል አንዱ (በዋናነት ሻጩ) የበለጠ መረጃ የሚኖረው መሆኑን ለማመላከት ነው። መረጃ ማፈን የግብይት ሚዛን መዛባት ከማስከተሉ አልፎ ብዝበዛን ያስከትላል። ኹለቱ ተገበያዮች እኩል የመረጃ ባለቤት ባለመሆናቸው ውስን መረጃ ያለው አካል ተጎጂ ይሆናል፤ የበዛ መረጃ የተቆጣጠረው ተጠቃሚ በመሆን እቃው በማይገባው ዋጋ ይገዛል ወይም ይሸጣል። ከዚህ እንደምንረዳው እንግዲህ መረጃን አጥሮ መያዝ ከግል ጥቅም ማግበስበስ የሚመነጭ ስግብግብነት ማሳያ ነው።

ማጠቃለያ
በዚህ ወቅት ስለአገራችን ሁኔታ በዓለም መድረኮች የሚንጸባረቀው ሀሳብ ለጆሮ አይመችም። በሌላ በኩል ለዘመናት በውጥን ደረጃ ሲንከባለል ቆይቶ በዚህ እድለኛ ትውልድ እየተገነባ የሚገኘው የሕዳሴ ግድብ ተጠባቂው ኹለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ሊከናወን ቀናት ቀርተውታል። እንደዚሁም በአገር ዐቀፍ ደረጃ ‹ስድስተኛው› ብሔራዊ ምርጫ ተካሂዷል።

በሌላ በኩል ደግሞ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የሚሰማው ጥሩ ያልሆነ ዜና የአገሩን ሉዓላዊነት እንዲከበር እና አንድነት እንዲጠበቅ ለሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ምቾት አይሰጥም። ይህንን የውስጥ መቆራቆሳችን እንደመነሻ በመጠቀም ልብ ብሎ ላስተዋለ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚወያዩና የሚጽፉ ምዕራባውያን ‹ወዳጆቻችን› አጀማመራቸው የትግራይ ሰብዓዊ ቀውስ ይሆንና መዳረሻቸው ግን የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። መጀመሪያ በጉድለታችን ካሸማቀቁንና እጅ ወደላይ ካሰኙን በኋላ የሚፈልጉት ዋነኛው አጀንዳቸው ላይ ፊጥ ሲሉ እየታዩ ነው።

ስለሆነም ዋናው ጉዳይ ምዕራባውያን ‹ወዳጆቻችን› ከማገዝ ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና በማሳደር የጉዞ ማዕቀብ እርምጃ እስከመውሰድ ለምን ፈለጉ የሚለው ነው። ዋናው ዓላማቸው እንደሚሉት ስለትግራይ ወይም ስለሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ሳይሆን ስለሕዳሴው ግድብ ፖለቲካ ነው ለማለት ያስደፍራል። ለምዕራባውያን መንግሥታት ከግብጽ አምባገነን መንግሥት በላይ የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚያደርግ የለም፤ ነገር ግን እንደሁነኛ አጋር ስለቆጠሩት ትንፍሽ አይሉም።

በኢትዮጵያ ላይ የሚጎነጎነው ሴራ ምንጭ አፍሪካ ቀና እንዳትል ድብቅ ፍላጎት ያላቸው አካላት የዓለም ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌትና የአፍሪካ ኩራት በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የሃያ አራት ሰዓት ዘመቻ ለማድረግ እረፍት አልባ ሆነው እናገኛቸዋለን።
በዚህ ዙሪያ ‹የምዕራባውያን ስጋትና የኢትዮጵያ ዳግም የአፍሪካ ተስፋ› በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ ከወራት በፊት የጻፍኳት አንዲት ጽሑፍ አለችኝ። እነዚህ ድብቅ ፍላጎት ያላቸው አካላት ከተከናወነው አገራዊ ምርጫ አኩራፊ ለማግኘት አሰፍስፈው እየጠበቁ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። በውድድር አሸናፊ ተሸናፊ እንደሚኖር ቢገመትም ምርጫው ያለምንም ኮሽታ በሰላም እንዲጠናቀቅ በማድረግ አሰፍስፈው ለሚጠብቁን ታሪካዊ ባላንጣዎቻችን ምኞታቸው መና በማስቀረት ኢትዮጵያ ዳግም እንድታሸንፍ ማድረግ የኹሉም ኃላፊነት ነው።

በዚህም ከተደቀነብን የውስጥና የውጭ ፕሮፓጋንዳ ጫና ሳንንበረከክ አገራችን በክፍለ-አህጉሩ ያላትን ተሰሚነት አስጠብቃ የበለጠ ሚናዋን እንድትጫወትና በዓለም መድረክ በአጋርነትና በወዳጅነት የምትነሳ ለማድረግ ኹሉም ዜጋ አንድነቱን በማጠናከር ለአገራችን ዘብ መቆም ያለበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ምክንያቱም በኢትዮጵያ የመንግሥት ስርዓት መፍረስ ተከስቶ አለመረጋጋት ቢሰፍን ደስታቸው ወደር የማይገኝለት ታሪካዊ ጠላቶች አሉብን።

ከታሪክ እንደተማርነው እነዚህ የቀን ሕልመኞች ድሮውንም አንድነታችን በማጠናከር ብቻ በራሳችን አቅም አሸንፈናቸዋል፤ አሁንም ቀድሞ እንደነበረው አንድነታችን በማጠንከር በፈጣሪን ታግዘን ማንኛውንም የምድር ኃይል የማሸነፍ ልምዱም አቅሙም አለን።
ሽመልስ አርአያ (ፒ.ኤች.ዲ.) በጀርመን ዓለማቀፍ ትብብር (GIZ) ውስጥ በአማካሪነት እየሠሩ ይገኛሉ።

- ይከተሉን -Social Media

በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተገለጹት አመለካከቶች የግላቸው ሐሳብ ብቻ እንጂ የሚሠሩበት ድርጅት አቋም የሚያንፀባርቅ እንዳልሆነ እወቁልኝ ብለዋል። ጸሐፊውን ለማግኘት araya.gedam@gmail.com አድራሻ መጠቀም ይቻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 138 ሠኔ 19 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች